Sunday, April 14, 2024

ለሦስተኛ ጊዜ ባገረሸው ጦርነት በሰሜን ወሎ ዞን የተፈናቃዮች ቁጥር 150 ሺሕ መድረሱ ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ ባገረሸው ጦርነት ከአማራ ክልል ከሰሜን ወሎ የተለያዩ የወረዳና የቀበሌ ከተሞች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ወደ 150 ሺሕ መድረሱ ተገለጸ፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ መስፍን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ እየተካሄደ ባለው ሦስተኛ ዙር ጦርነት ክልሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮችን በተለያዩ ቦታዎች በመጠለያ እንዲሰፍሩ አድርጓል፡፡

በሰሜን ወሎ ከተሞች ቆቦ፣ ወርቄ፣ ጎብዬና በሌሎች የራያ አካባቢዎች የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥራቸው 150 ሺሕ ይገመታል ብለዋል፡፡ ጦርነቱ በተከፈተባቸው ሌሎች የአማራና የትግራይ ክልል ድንበር አዋሳኞች በተለይም በዋግህምራና በወልቃይት አካባቢዎች በጦርነት ሥጋት የሚፈቀናቀሉትን ዜጎች በተመለከተ አኃዛዊ መረጃ ለጊዜው ማጠናቀር እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የፍልሰቱን መጠን የሚያጣራ ቡድን ወደ ዋግህምራና ወልቃይት አካባቢዎች መላኩን የገለጹት ኃላፊው፣ የተጣራው ቁጥሩ ሲደርስ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው መፈናቀሉ አሁንም መቀጠሉንና ለተፈናቃዮች የምግብና የዕለት ደራሽ ዕርዳታ አቅርቦቱ በጣም ውስን መሆኑን በመግለጽ፣ በጦርነቱ የሕዝቡ ሰቆቃና ስደት እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጠባቂ ከሆኑ አጠቃላይ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ውስጥ አንድ ሚሊዮን ያህሉ ተፈናቃዮች መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በቀደመው ጦርነት ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች፣ ለወራት ከኖሩበት የካምፕ ሕይወት ወደ ቤታቸው ቢመለሱም፣ እንደገና ጦርነት በመጀመሩ አርሰው ራሳቸውን መመገብ ካለመቻላቸውም በላይ፣ አንዳንዶቹ በድጋሚ ተፈናቃይ መሆናቸው የችግሩን ሁኔታ አባብሶታል ብለዋል፡፡

በሰሜን ወሎ መርሳ ከተማ ከ50 ሺሕ በላይ፣ ጃራ በሚባል ቦታ ከ35 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ኢያሱ፣ በተመሳሳይ በሌሎች ካምፓች ተፈናቃዮች እየገቡ መሆኑንና ቀሪዎቹ ደግሞ በወዳጅ ዘመድ፣ እንዲሁም በአካባቢው ማኅበረሰብ ውስጥ ተጠግተው እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ ሥጋትና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ  ዓለሙ ይመር ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ተፈናቃዮችን በመንግሥት ድጋፍ ብቻ ለመርዳት እየተሄደበት ያለው ጥረት ሁለት በመቶ ብቻ ነው፡፡ ለእነዚህ ዜጎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊደርስላቸው ይገባል ብለው፣ ከቆቦ ከተማና ከራያ አቅራቢያ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡት ዜጎች በሕወሓት ታጣቂዎች ንብረታቸው ተጭኖ እየሄደ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከገቡ ነፍሰ ጡር እናቶች መካከል ባለፉት ጥቂት ቀናት 22 እናቶች መውለዳቸውን አቶ ዓለሙ ጠቁመዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋው ባታብል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጦርነቱ በቀጠለባቸው የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች አሁንም ግድያ፣ ዝርፊያና የዜጎች እንግልት ተበራክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -