Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት አቅም በየቀኑ እየተመናመነ ሲሆን፣ በምግብም ሆነ ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየባሰበት ነው፡፡ የውጭ የምንዛሪ ተመን በመደበኛው ግብይት በዶላር 53 ብር አካባቢ ቢሆንም፣ በተለምዶ ጥቁር ገበያ በሚባለው ትይዩ ገበያ ውስጥ ከ90 ብር በላይ መመንዘሩ የኢኮኖሚውን ጤና መቃወስ አመላካች እየሆነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ባንክ ውስጥ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በሥጋት ንብረት ግዥ ላይ በመሰማራታቸው፣ በፍራንኮ ቫሉታ ንግድ መፈቀድ ሳቢያ ዶላር የሚያስሱ በመብዛታቸውና ገበያው ውስጥ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የስግብግብነት ግመታ (Speculation) በመናኘቱ፣ ኢኮኖሚውን እንደ አውሎ ንፋስ እያወዛወዙት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመሬት፣ በቤትና በተሽከርካሪ መሸጫ ዋጋ ላይ እየታየ ያለው የዋጋ መናር አንዱ አደገኛ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከላይ የተጠቀሱ ሰበቦች ማቆሚያ ለሌለው የዋጋ ግሽበት መንስዔ ይሆናሉ፡፡

  በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ቀልብ ከኑሮዋቸው በላይ የአገር ሰላምና ህልውና ላይ ቢሆንም፣ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው አደገኛ እንቅስቃሴ ካልተገታ የሰዎች የመግዛት አቅም ቀጥ ሊል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከምግብ ምርቶች መካከል እንደ ዳቦ፣ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉት፣ እንዲሁም ከግንባታ ማቴሪያሎች እንደ ሲሚንቶ ያሉት ሥውር እጆች እያገቷቸው የዋጋ ግሽበቱ ከሚታገሱት በላይ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ የመንግሥት ሹማምንትና ቤተሰቦቻቸው የተሰማሩባቸው የንግድ ዘርፎች፣ ለዋጋ ግሽበት መባባስ ዋነኛ ሰበቦች መሆናቸው በግልጽ እየተሰማ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አደገኛ አካሄድ በፍጥነት ካልቆመ በስተቀር፣ ኢትዮጵያ የዚምባቡዌን የሚያስንቅ የዋጋ ግሽበት እንደሚያጋጥማት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ በተገቢው መንገድ ካልተመራ ውጤቱ ውድቀት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት አያዳግትም፡፡ ገበያው በደላላ ሠራዊት ታንቆ ተይዞ ገንዘብ ያለው ሁሉ በመንገብገብ ሥርዓተ አልበኝነት ሲያነግሥበት፣ መንግሥት የከፋ አደጋ ከመድረሱ በፊት ማረጋጋት ይጠበቅበታል፡፡ ብልሹው የግብይት ሥርዓት ውስጥ የተንሰራፋው ሕገወጥነት በሕግ አደብ ይግዛ፡፡ አደጋው ከመጠን በላይ እየከፋ ነው፡፡

  ጦርነት ውስጥ ያለ መንግሥት ወጪው እያደር መጨመሩ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የዘንድሮ በጀት ዓመት ሲፀድቅ እንደተገለጸው የፕሮጀክት ወጪዎችን በመቀነስ ሰብዓዊ ልማት ላይ ቢተኮር መልካም ነው፡፡ ሥርዓት አልባውን የግብይት ሥርዓት በጥናት ላይ በተመሠረተ የፖሊሲ ማከሚያ ፈር ማስያዝ ይገባል፡፡ ከመደበኛ የንግድ ተዋንያን ውጪ ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ ያሰፈሰፉ ኃይሎችን መግታት ይጠቅማል፡፡ የብር የመግዛት አቅም እንዲመናመን ምክንያት የሆኑ የፖሊሲ ውሳኔዎችን በመቀልበስ፣ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለውን የመስገብገብ እንፋሎት እንዲቆም ማድረግ ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ገበያው ውስጥ ሰርገው የገቡ አላስፈላጊ ተዋንያንን በፍጥነት ማስወጣት አለበት፡፡ እንደ ፍራንኮ ቫሉታ ያሉ አሠራሮች የፈጠሩት ተፅዕኖ ካለም በፍጥነት ተጠንቶ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ ለችግር ደራሽ የተባሉ አሠራሮች የጎንዮሽ ጉዳታቸው ኢኮኖሚውን ማጥ ውስጥ እንዳይከት ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ የምርት አቅርቦቶች መስመር ላይ የቆሙ ደላሎችና ግብረ አበሮቻቸው ገለል ይደረጉ፡፡ ኢኮኖሚው አደጋ ውስጥ ነው፡፡

  የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ራሱን የቻለ ራስ ምታት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በፊት ንዑስ ሳንቲምና ሌሎች ቅንስናሾች የነበራቸው ዋጋ ጠፍቶ አሁን ገበያው ውስጥ የሉም፡፡ አንድ ብር የመግዛት አቅሙ ተመናምኖ ለዝርዝር ማሟያ ከመሆን ያለፈ ሚና አጥቷል፡፡ ዝቅተኛው የአምስት ብር ኖትም ለአጭር ርቀት ታክሲ ታሪፍ ክፍያ ካልሆነ ፈላጊ እያጣ ነው፡፡ አሥር ብር ለእኔ ቢጤ ምፅዋትና ለፓርኪንግ ሠራተኞች ጉርሻ ከመሆን የዘለለ ዋጋ በማጣት ላይ ነው፡፡ ይህ አጭር ምሳሌ የኢኮኖሚውን መክፋትና ምንም ተጨማሪ ገቢ የሌለውን ብዙኃን ሕዝብ ሰቆቃ ቁልጭ አድርጎ እያሳየ ነው፡፡ ኢኮኖሚው እንዲህ እያደር ቁልቁል እየሄደ ባለበት ጊዜ ቆም ብሎ ፈጣን መፍትሔ ካልተፈለገ፣ ምንም ዓይነት የገቢ ጭማሪ ማግኘት የማይችሉ ተቀጣሪ ሠራተኞችና በቀን ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎች ለመገመት የሚከብድ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በሚያጋጥምበትና ገበያው በስግብግነት ግመታ ሲተራመስ፣ መንግሥት እጅጌውን ጠቅልሎ የፖሊሲ ማስተካከያ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሰሞኑን በተሽከርካሪዎች ዋጋ ላይ እየተስተዋለ ያለው ጤነኛ ያልሆነ ጭማሪ ገበያውን የበለጠ ከማተራመስ አልፎ፣ ኢኮኖሚውን በእንብርክኩ ሊያስኬደው እንደሚችል ለመተንበይ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡

  በሌላ በኩል ከውጭ በሃዋላ ወደ አገር ውስጥ መግባት ያለበት የውጭ ምንዛሪ መንገድ ላይ እየተጠለፈ ነው፡፡ በባንኮችና በገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች አማካይነት ወደ አገር ውስጥ መግባት የነበረበት የውጭ ምንዛሪ፣ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ባሉ ሕገወጥ ተዋንያን አማካይነት የጥቁር ገበያ ሰለባ እየሆነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመደበኛውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን ልዩነት ከአርባ ብር በላይ እያሻቀበ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በሕገወጥ መንገድ በዝርፊያ የሚገኝ ገንዘብ የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ምክንያት እየሆነም ነው፡፡ ባንኮች አካባቢ ለውጭ ምንዛሪ እየተከፈለ ነው የሚባለው የኮሚሽን ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ባንኮች በኃላፊነት ስሜት መሥራት ሲገባቸው፣ የበለጠ ችግር ፈጣሪ ሆነው ከተገኙ ራሱን የቻለ መከራ ያስከትላሉ፡፡ በስንት መከራ ከኤክስፖርትም ሆነ ከሌላ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ተሻሚው ብዙ ስለሆነ፣ ይህም ችግር የኢኮኖሚውን ጣር ያበዛዋል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ አያያዝና አጠቃቀም ጋር የሚስተዋሉ የዓመታት ችግሮች መፍትሔ ካልተበጀላቸው መከራው ተባብሶ ይቀጥላል፡፡

  ኢኮኖሚው ውስጥ ከሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ የግብይት ሥርዓቱ የኢኮኖሚ ሕግጋትን መከተል አለመቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሐምሌ ወር ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ሲጨምር፣ የተሽከርካሪ ዋጋ በአንፃራዊነት መቀነስ ሲገባው በየቀኑ ወደ ላይ እየተተኮሰ ነው፡፡ የአቅርቦትና የፍላጎት ጽንሰ ሐሳብ ውሉ እስኪጠፋ ድረስ ገበያው ብልሽትሽቱ የሚወጣው በደላላ ስለሚዘወር ነው፡፡ ደላላ የሚያሾረው ገበያ በስግብግብነት ግምት ስለሚመራ፣ በሒደት ላይ ያለ ምርት ሳይቀር ገበያው የሚወሰነው በደላላ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ ኢኮኖሚውን መምራት የሚገባቸው አካላት ተዓምር የሚጠብቁ ይመስል እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው፣ ደላላ ገበያውን እያተራመሰ አንዴ በውጭ ምንዛሪ ሌላ ጊዜ በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ማነቆ በመፍጠር አገር መጫወቻ እየሆነች ነው፡፡ መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን መቆጣጠርና ማስተካከል ሲገባው በስመ ነፃ ገበያ ሕገወጥነት ሲንሰራፋ፣ ቀጥሎ የሚመጣው የማፍያ ኔትወርክ እንደሚሆን አለመጠርጠር ሞኝነት ነው፡፡ ኢኮኖሚውን በጥናት ላይ በመመሥረት ከገባበት አደገኛ ጎዳና ውስጥ ለማውጣት መነሳት የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ መንግሥት የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን፣ ፈጣንና አስተማማኝ ዕርምጃ በመውሰድ ያንዣበበውን አደጋ ያስወግድ! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  ሴረኝነት የሰላም ጠንቅ ነው!

  በአዲሱ ዓመት የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የሕዝባችንን ፍላጎት...