Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከነገ ጀምሮ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከነገ ጀምሮ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል

ቀን:

  • 13 ሚሊዮን ተማሪዎች አልተመዘገቡም

የትምህርት ሚኒስቴር አምስት ዓመታት ሲያዘጋጅ የቆየው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት፣ ከነገ ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መተግበር ይጀምራል፡፡

የዘጠነኛና የአሥረኛ ክፍል ሥርዓተ ትምህርት ደግሞ በኢትዮጵያ በሚገኙ 80 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሙከራ ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችና የትምህርት ደረጃ አደረጃጀት ላይ የተደረጉ ለውጦችን የያዘው የአንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት፣ አገር በቀል ዕውቀቶችን በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ ለማካተት የተሞከረበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ የመጻሕፍት ዝግጅቱ ብቻውን ሦስት ዓመት እንደፈጀም አክለዋል፡፡

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ውስጥ ከተደረጉ ለውጦች መካከል አንዱ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የግብረ ገብ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑ እንደሆነ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ዛፉ አብርሃ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለሰባተኛና ለስምንትተኛ ክፍል ተማሪዎች ራሳቸውን የቻሉ የትምህርት ዓይነቶች ሆነው ይሰጡ የነበሩት ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂና ፊዚክስ ‹‹ጄኔራል ሳይንስ›› በሚል የትምህርት ዓይነት እንደተጠቃለሉ፣ ኃላፊዋ የትምህርት ሥርዓቱን አስመልክቶ ዓርብ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በተሰጠው መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት የሙያ ዕውቀት እንዲኖራቸው በማለትም፣ የሰባተኛና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ‹‹ኬሪየር ኤንድ ቴክኒካል ኤጁኬሽን›› የተባለ የትምህርት ዓይነት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ ወ/ሮ ዛፉ፣ ‹‹[ይህ የትምህርት ዓይነት] መጠነኛ የሆነ የአካውንቲንግ፣ ቢዝነስ፣ እርሻና ሌሎች የሙያ ትምህርቶችን ዕውቀት የሚያስጨብጥ ነው፤›› በማለት የትምህርት ዓይነቱ ምን ዓይነት ጉዳዮችን እንደሚዳስስ አስረድተዋል፡፡

ተማሪዎቹ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ይኼ ትምህርት ራሳቸውን የቻሉ እንደ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ጤና፣ ግብርና፣ ቢዝነስና አካውንቲንግ ባሉ የሙያ ትምህርት መስኮች እንደሚበተን ገልጸዋል፡፡ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከእነዚህ የሙያ ትምህርቶች ውስጥ የመረጡትን እንደሚወስዱም አክለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚችል ዜጋን መፍጠር የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አንዱ ዓላማ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ዛፉ፣ ለዚህም ሲባል የእንግሊዝ ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከሥርዓተ ትምህርት ጥናት እስከ መጻሕፍት ዝግጅት በገምጋሚነት መሳተፉን አስረድተዋል፡፡ መጻሕፍት የይዘት መታጨቅ፣ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የትምህርት ይዘቶችን ያላገናዘበና ከተግባራዊ ሙያ ጋር አለመጣጣም የቀድሞዎቹ መጻሕፍት ላይ የታየ ችግር ሆኖ መለየቱንና ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በአዲሶቹ መጻሕፍት ዝግጅት ውስጥ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ዕገዛ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ለአንደኛ ደረጃ የተዘጋጁት መጻሕፍት በሙሉ በትምህርት ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ እንደሚለቀቁ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት 6፣ 2፣ 2፣ 2 በሚል የአደረጃጀት የተዋቀረ መሆኑን ያስረዱት ወ/ሮ ዛፉ፣ ከአንደኛ ክፍል በፊት አምስትና ስድስት ዓመት ዕድሜ ላላቸው ሕፃናት የሚሰጠውና ለሁለት ዓመታት የሚቆየው ትምህርት ‹‹ቅድመ መደበኛ›› የሚል ምድብ እንደተሰጠው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹አንደኛ ደረጃ›› ትምህርት የሚባለው ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለው ሲሆን፣ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ‹‹መካከለኛ›› ደረጃ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ በሚል ተከፍሎ የነበረው ከዘጠነኛ እስከ 12ተኛ ክፍል ያለው የአራት ዓመት ቆይታ አሁን ሁለተኛ ደረጃ በሚል ተጠቃሏል፡፡

አዲሱ የመጀመሪያ የትምህርት ሥርዓት ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲጀመር አብረው ትምህርት የማይጀምሩ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የትምህርት ፕሮግራሞች ጥራትና ማሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ወጋሶ ገልጸዋል፡፡ በጦርነት ምክንያት የትምህርት ቤቶች መውደም፣ የተማሪዎችና ወላጆች መፈናቀል፣ እንዲሁም ድርቅ ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች አለመጀመር በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንደገለጹት፣ 2014 ዓ.ም. ሳይጠናቀቅ በአጠቃላይ በአገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች 29.3 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ እስከ ጳግሜን 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የተመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት 16.3 ሚሊዮን ነው፡፡ ይህም የዕቅዱን 55.6 የሚሸፍን ነው፡፡

‹‹2014 ዓ.ም. ለትምህርት ዘርፉ ከባድ ዓመት ነበር፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ ነገር ግን የተማሪዎች ምዝገባ አፈጻጸም ከ55 በመቶ አለመዝለሉ ከፍተኛ ሥራ መሠራት እንዳለበት የሚጠቁም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጦርነት ባገረሸባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ ካልተፈጸመባቸው አካባቢዎች መካከል መሆናቸውን የሚኒስትሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አመለወርቅ ሕዝቅኤል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ክልሎች ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት የመመለስ ዘመቻ እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ትምህርት ቤቶች እስከ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ ስለሚሆኑ ምዝገባውን ያከናውናሉ የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...