Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዕጩዎቹን ከሕዝብ ደብቆ ለምርጫ የተዘጋጀው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል ከ75 ዓመታት በላይ የቆየው አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሌሎች ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በተለየ የሚታይ ነው፡፡ ወደ 15 ሺሕ አባላት ያሉትና በጥንካሬው የሚጠቀስም ነው፡፡ ይሁንና ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ ከምርጫ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ውዝግቦችን በማስተናገድ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ከምርጫ ሒደት ጋር የተያያዙ ውዝግቦች አባላቱን ፍርድ ቤት ድረስ ያስኬደ ሲሆን፣ ንግድ ምክር ቤቱ ዕግድ ተጥሎበት እንደነበርም ይታወሳል፡፡ 

በንግድ ምክር ቤቱ የምርጫ ሒደት ውስጥ ጽሕፈት ቤት መግባት የለበትም እየተባለ ጽሕፈት ቤቱ የምርጫውን ሲጠቀምበት ነበር የሚል ክስም ሲቀርብ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የተከሰቱ እንዲህ ያሉ ችግሮች ጠንካራ አመራሮች ወደፊት እንዳይመጡ ከማድረጉም በላይ አባላት እንዲሸሹ እያደረገ ነው በሚል ትችት ሲሰነዘርበትም ቆይቷል፡፡ 

ምርጫ በሚደረግባቸው ዓመታት ሁሌም ውጥረት የሚነግሥበት ሲሆን፣ ዘንድሮም ከንግድ ምክር ቤቱ ሕገ ደንብ ውጪ ዘግይቶ በሚካሄደው ምርጫም አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮች አላጡትም፡፡ አሁን በኃላፊነት ላይ የሚገኘው የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ለሁለት ዓመታት ብቻ የተመረጠ ቢሆንም፣ ሥልጣኑን እንደያዘ ከሦስት ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ ምርጫ በማድረግ ኃላፊነቱን ማስረከብ የነበረበት ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ነበር፡፡ ነገር ግን ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታዎችንና ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ ምርጫውን ሳያካሂድ ቆይቷል፡፡ ከምርጫው ሌላ በየዓመቱ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ ዓመታዊ ሪፖርቱን ለአባላት ማሳወቅ ቢኖርበትም፣ ይህንንም ባለመደረጉ በአባላቱ እየተተቸ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን ከብዙ ውትወታ በኋላ መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔንና ምርጫ ለማካሄድ ወስኖ ለዚሁ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ 

የጠቅላላ ጉባዔው ቀን ከተቆረጠ በኋላ ቀድሞ እንደሚደረገው የምርጫ አመቻች ኮሚቴው ተቋቁሞ ይህ አመቻች ኮሚቴ ለፕሬዚዳንትነትና ለቦርድ አባልነት ዕጩዎችን ሲቀበል ቆይቷል፡፡ ለአንድ ወር የዘለቀው የዕጩዎች ጥቆማ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ብዙዎች የመጨረሻዎቹን ዕጩ ከአንድ ሳምንት ቀድሞ ያሳውቃል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ እስካለፈው ሳምንት ዓርብ ድረስ ሊያሳውቅ አለመቻሉ እያነጋገረ ነው፡፡ ሪፖርተር የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች ለማወቅ እስከ ዓርብ አመሻሽ ድረስ ሙከራ ቢያደርግም የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ዕጩዎቹን ሊያሳውቅ አልቻለም።

‹‹አባላት ንግድ ምክር ቤቱን ለመምራት የታጩትን ዕጩዎች ቀድሞ በማወቅ እንዳይዘጋጅ ያደረገ ነው፤›› የሚሉ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት፣ ምርጫው ጊዜ መዘግየቱና ከመተዳደሪያ ደንብ ውጪ ጠቅላላ ጉባዔ ሳይጠራ ሦስት ዓመታት ፈጅቶ፣ አሁንም እንደቀድሞ ተመሳሳይ ስህተት እየተሠራ ነው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡ በተለይ ምርጫው ሊካሄድ አምስት ቀናት እየቀሩት የተወዳዳሪ ዕጩዎች ማንነት ሊገለጽ አለመቻሉ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል። 

ሪፖርተር ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫ አመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አፈወርቅ ዮሐንስ የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች ዓርብ መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚያሳውቁ ገልጸው ነበር። ዕጩዎቹን የማስተዋወቅ ሥራ የዘገየበት ምክንያት ተጠቋሚዎቹ ለዕጩነት የሚያበቃቸውን መሥፈርት በትክክል ስለማሟላታቸው መረጋገጥ ስላለበት ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የማረጋገጥ ሥራው በንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት የአባላት ጉዳዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲያጣሩ የሚደረግ መሆኑን፣ እነዚህ አካላት የማጣራት ሥራውን ካጠናቅቁ በኋላ የዕጩዎቹ ዝርዝር ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል። የማጣራት ሥራው ሳይጠናቀቅ ግን የዕጩዎቹ ዝርዝር ሊገለጽ እንደማይችል ተናግረዋል።  

ዕጩዎቹን የማጣራት ሥራን በተመለከተ ላቀረብንላቸው ጥያቄም በሰጡት ማብራሪያ ከ30 ቀናት  በፊት የምርጫ ሳጥኑ ይዘጋና ተጠቋሚዎች ይለያሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ዕጩ መሆን የሚችለው ምን ዓይነት ሰው ነው? የሚለውን ደግሞ በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት የአባላት ጉዳዮችን የሚመለከተው የንግድ ምክር ቤቱ ክፍል እንዲለይ ይደረጋል ብለዋል፡፡ የተጠቆመው ዕጩ የንግድ ምክር ቤቱ ትክክለኛ አባል ስለመሆኑ፣ የአባልነት ክፍያ በትክክል ስለመፈጸሙ፣ ለውድድር የተቆመው ዕጩ የኩባንያ ባለቤት ወይም ሥራ አስኪያጅ ስለመሆኑና ሌሎች መሥፈርቶችን ስለማሟላቱ እንደሚጣራ ገልጸዋል። በተጨማሪም የሚጠቆመውን ዕጩ በማነጋገር ለመወዳደር ፍላጎትና ፈቃደኛ መሆኑ እንደሚረጋገጥ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የተረጋገጡ ዕጩዎችን ዝርዝር የማሳወቁ ሒደት ጊዜ እንደወሰደ ተናግረዋል።

የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ከንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ሳያካሂድ የቆየው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ቀጣዩን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫውን የሚያካሂደው መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ከመሆኑ አንፃር አባላት ዕጩዎችን ቀድመው አለማወቃቸው ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ 

በዚህ ምርጫ ሒደት ላይ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ግን የሒደቱን መጓተት ተችተዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ አባላት ያሉት እንደሆነ ቢታወቅም፣ ወደ ኃላፊነት ቦታ ለመምጣት ያላቸው ፍላጎት ውስን መሆኑ አዳዲስ አመራሮች እንዳይወጡ ያደርጋል የሚል ሥጋት ያላቸው ከመሆኑም በላይ እንዲህ ያለው አካሄድ ተቋሙን የሚጎዳ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት በተከታታይ ሲያደርጋቸው በነበሩ ምርጫዎች በውዝግቦች የታጀበ እንደነበር በማስታወስም፣ ቀጣዩንና በዘገየው ምርጫ ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የሚሠጉ አባላትም አሉ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላ የምክር ቤቱ አባል የዘንድሮ ምርጫ አመቻች ኮሚቴው ቢያንስ ምርጫው ከመደረጉ ሁለት ሳምንታት በፊት ዕጩዎችን አለማሳወቁ ብዥታ እንደፈጠረባቸው አመልክተዋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በነበሩ የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫዎች የምርጫ አመቻች ኮሚቴው ለፕሬዚዳንትነትም ሆነ ለቦርድ አባልነት ዕጩ የሆኑት ተወዳዳሪዎች ለውድድር ብቁ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ ዕጩዎቹ ራሳቸውን በማስተዋወቅ የምረጡኝ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር። በመጪው ሳምንት ለሚካሄደው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫ ግን እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ በይፋ ራሱን ያስታዋወቀ ዕጩ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአሁኑ ወቅት ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዝዳንትነት በመምራት ላይ የሚገኙት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል፡፡ ሌሎች ነባር አባላትም በተመሳሳይ ውድድር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን ምርጫ የሚያደርገው በአዋጅ ቁጥር 341/95 ነው፡፡ ይህ አዋጅ ይሻሻላል ተብሎ ለዓመታት በረቂቅ ዝግጅት ላይ የቆየ በመሆኑ፣ አሁን ባለው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት በሚካሄደው ምርጫ አዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚወከሉ አራት ተመራጮች በቀጥታ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ይሆናል፡፡ ከእነዚህ አራት የዘርፍ ማኅበራት ተወካዮች ውስጥ ደግሞ አንዱ በቀጥታ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ይሆናል፡፡ ለዚህም የዘርፉ ምክር ቤት ከመስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በፊት ጠቅላላ ጉባዔ አካሄዱ ተወካዮቹን ያሳውቃል፡፡

አሁን በአመራር ላይ ያለው አዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አበባው መኮንን ለሪፖተር እንደገለጹት፣ መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሚካሄደው ምርጫ የአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ የራሱን ቦርድ ከመረጠ በኋላ ከእነዚህ ውስጥ ለአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቀጥታ የሚወከሉ አራት የቦርድ አባላትን ይልካል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት የቦርድ አባላት ቁጥር አሥራ አንድ ሲሆን፣ ከዘርፉ ምክር ቤቱ ከሚወከሉት አራት የቦርድ አባላት ውጪ ያሉ ሰባቱ የቦርድ አባት የሚወከሉት ከንግድ ዘርፉ ሲሆን፣ እነዚህ አባላትም ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሰባቱ የቦርድ አባላት መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም አመቻች ኮሚቴው ከሚያቀርባቸው ዕጩዎች መካከል በሚደረገው ምርጫ የሚለዩ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በምርጫው ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባው፣ የዕጩዎች ጥቆማ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ አሁን ባለው ደረጃ ግን ዕጨዎችን ለማወቅ የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን በዘንድሮው ምርጫ አዳዲስና ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ሊቀርቡ ይችላሉ የሚል ግምት አላቸው፡፡ 

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች በጠንካራነቱ የሚታወቀው የአዲስ አባባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲመሠረት የመጀመርያዎቹ ሁለት ፕሬዚዳንቶች የውጭ ዜጎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ ታሪካዊ ዳራን የተመለከቱ መረጃዎቸ የሚያሳዩ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ሚስተር ቢ. ባባያ ናቸው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን ከ1939 እስከ 1953 ዓ.ም. ከ14 ዓመታት በላይ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በምክር ቤቱ ታሪክ ለረዥም ዓመታት በማገልገል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከእሳቸው ቀጥሎ ሁለተኛው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉ ቢስተር ኤል ዊርትዝ ናቸው፡፡ እሳቸውም ከመጋቢት 1953 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 1954 ዓ.ም. አገልግለዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የመጀመርያውን ኢትዮጵያዊ ፕሬዚዳንት የመረጠው በ1954 ዓ.ም. ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የመጀመርው ኢትዮጵያዊ የሆኑት በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ በቀለ በሻህ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ ምሥረታ ጀምሮ 18 ፕሬዚዳንቶች ንግድ ምክር ቤቱን መርተዋል፡፡ ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ውብ እሸት ወርቅ ዓለማየሁ፣ አቶ ክቡር ገና፣ አቶ ብርሃነ መዋ፣ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ አቶ ኤልያስ ገነቴ፣ አቶ አያሌው ዘገየና አሁን ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች