Saturday, July 13, 2024

ግጭትና ሰብዓዊ ቀውስ በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሰሜን ወሎ ዞን ትንሿ ከተማ መርሳ የጥይት ድምፅ ባትሰማም፣ የዜጎችን ሰቆቃ ለማድመጥ ግን ሩቅ አይደለችም፡፡ መርሳ ጦርነት ከሚካሄድበት ራያ ቆቦ ግንባር በአማካይ በ80 ኪሎ ሜትር ወደ ደቡብ ትርቃለች፡፡ ከተማዪቱ ለጊዜው ከግጭቱ ትራቅ እንጂ የግጭቱን ወላፈን ግን አላመለጠችም፡፡

በራያ ቆቦ ግንባር ግጭት ከሚካሄድባቸው ቀጣናዎች የሚሰደዱ ዜጎች መዳረሻቸው መርሳ ከተማ ሆናለች፡፡ ሕወሓት ከተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚፈናቀሉ ዜጎች በተለያዩ መንገዶች ስቃዩን አምልጠው የሚጠለሉባት መርሳ ከተማ ናት፡፡ በራያ ቆቦ ግንባር በነሐሴ አጋማሽ 2014 ዓ.ም. የተጀመረው ጦርነት ብዙ ዜጎችን ወደ መርሳ እያሰደደ ይገኛል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር እንደሚናገሩት፣ በመርሳ ከተማ እየተጠለሉ ካሉ በግጭት ከተፈናቀሉ ዜጎች ውስጥ በርካቶቹ እናቶች፣ ሕፃናቶችና አቅመ ደካሞች ይገኙበታል፡፡ ‹‹ባለፉት ሦስት ቀናት (ማለትም ማክሰኞ፣ ረቡዕና ሐሙስ) ብቻ 22 ነፍሰ ጡሮች በመርሳ መጠለያ ጣቢያዎች ወልደዋል፤›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ዓለሙ፣ ግጭቱን ሽሽት በየቀኑ በርካታ ዜጎች ወደ መርሳ ከተማ በመፍለስ ላይ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

አቶ ዓለሙ እንደሚናገሩት፣ በመርሳ በስምንት መጠለያ ጣቢያዎችና በየማኅበረሰቡ መኖሪያ  ተፈናቃዮች ተጠልለዋል፡፡ አዲሱ ግጭት ወደ 80 ሺሕ አካባቢ ተጨማሪ ተፈናቃዮችን መፍጠሩን በመጥቀስም፣ በአጠቃላይ ቢሯቸው ከ92 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮችን መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ግጭቱ ካለባቸው አካባቢዎች በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እየመጡ ነው፡፡ ለእነዚህ አሁን ባለን አቅም እንኳን ሕክምናና ሌላ አገልግሎት ቀርቶ መሠረታዊ ሕይወት አድን ምግብ ለማቅረብ እየተቸገርን ነው፤›› ሲሉም አቶ ዓለሙ ያክላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደታየው በርካታ መፈናቀልና ሰብዓዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ የእነዚህ ሰብዓዊ ቀውሶች መሠረታዊ ምንጭ ደግሞ ፖለቲካዊ ችግር መሆኑ ይነገራል፡፡ በዋናነት ፖለቲካ አመጣሽ ግጭቶችና ጦርነቶች በኢትዮጵያ ለተፈጠሩና እየተፈጠሩ ላሉ ሰብዓዊ ቀውሶች ዋና መነሻ ምክንያቶች መሆናቸውን በርካታ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 ብቻ በዓለም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ38 ሚሊዮን ወደ 59 ሚሊዮን አሻቅቧል፡፡ በዚሁ ጊዜ ለአገር ውስጥ መፈናቀል ዋና ምንጭ የሆነው ግጭት ሲሆን፣ ከአጠቃላዩ ከ59 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ውስጥ 53 ሚሊዮኖቹ ግጭትንና ጥቃትን ሽሽት ነው ከቤት ንብረታቸው የሸሹት ተብሏል፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ያፈናቀላቸው ሰዎች ቁጥር ከ5.9 ሚሊዮን በማይበልጥ አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው የ‹‹ኢንተርናሽናል ዲስፕሌስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር›› (IDMC) ጥናት የሚያመለክተው፡፡

ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ከዓለም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር 80 በመቶ ይሸፍናል፡፡ የቀጣናው አገሮች ወደ 11 ሚሊዮን ሕዝብ እንደተፈናቀለባቸው የሚያትተው ጥናቱ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ቀዳሚዋ ናት ሲል ያስቀምጣታል፡፡

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2021 ዓመት ወደ 5.1 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሉ የሚለው ጥናቱ፣ ይህ አኃዝ ከቀደመው ዓመት በሦስት እጥፍ የሚበልጥና በዓለም ታይቶ የማያውቅ ጭማሪ በአንድ ዓመት ውስጥ የተመዘገበበት መሆኑን ይገልጻል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግጭቶችና ጥቃቶች ዋና ምንጭ መሆናቸውን የሚጠቅሰው ጥናቱ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል የቀጠለው ጦርነት የችግሩ ዋና ምንጭ ነው ሲል ያብራራል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) በበኩሉ፣ በዓለማችን 89.3 ሚሊዮን ያህል ሕዝቦች ተገደው ቤት ንብረታቸውን መልቀቃቸውንና መሰደዳቸውን ያስረዳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 ብቻ በኢትዮጵያ 1.5 ሚሊዮን ዜጎች መልሰው መቋቋም ቢችሉም፣ ነገር ግን በተቃራኒው 2.5 ሚሊዮን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ይላል ድርጅቱ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ወደ 4.7 ሚሊዮን ወይም የዓለምን አንድ – አምስተኛ ስደተኞች ማስጠለላቸውን የኮሚሽኑ ጥናት ይገልጻል፡፡ ከኡጋንዳና ከሱዳን ቀጥሎ ኢትዮጵያ 821,300 የጎረቤት አገሮች ስደተኞችን ማስጠለሏንም ተቋሙ ይጠቅሳል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ የውጭ ስደተኛ ይዛ በተጨማሪ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ችግር መፈተኗ የሚቀጥል ከሆነ፣ ችግሩ ከአቅሟ በላይ በመሆን የዓለም የስደተኞች ቀውስ ምንጭ እንደምትሆን ብዙዎች ይገምታሉ፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግጭቶች እየፈጠሩት ያለውን መፈናቀልና የሰብዓዊ ቀውስ ችግር ተረድቻለሁ ይላል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ሊቀመንበር አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ ‹‹ዓለም በጦርነት፣ በረሃብና በኢፍትሐዊነት እየተሰቃየች ትገኛለች፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ግጭትና አለመረጋጋት ዋና የዓለማችን ችግር መሆኑን የጠቀሱት አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ ‹‹ቡድን 20 ተብለው የሚጠሩት የዓለማችን አዳጊ አገሮች 80 በመቶ የምድራችን በካይ ጋዝ ልቀት ምንጭ ቢሆኑም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ስቃዩን እያየ ያለው የደሃ አገሮች ዜጋ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዓለማችን የሚፈጠሩ ግጭቶች እያስከተሉ ያሉትን ቀውስ በተመለከተ ከሰሞኑ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት በብራዚልና በአየርላንድ ጠያቂነት ስብሰባ የጠራ ሲሆን፣ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ሕዝቦች መክሯል፡፡ ከስብሰባው ቀደም ብሎ የወጣ መግለጫም እንደ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ የመንና ደቡብ ሱዳን በመሳሰሉ አገሮች ከ648 ሺሕ በላይ ሕዝብ በግጭት የተነሳ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ጠባቂ ለመሆን መዳረጉን አመልክቶ ነበር፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማርቲን ግሪፍስ፣ 13 ሚሊዮን ሰዎች በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ለፀጥታው ምክር ቤት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በምዕራብ ኦሮሚያና በደቡብ ክልል አካባቢዎችም ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሰብዓዊ ረድዔት ለመላክ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያስረዱት፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢስሊም ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ ይህንኑ ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ለተረጂዎች ድጋፍ ለማቅረብ አስቸኳይ ድጋፍ፣ እንዲሁም ነፃ የመንቀሳቀሻ መንገድ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) በትዊተር ያጋሩት የዴቪድ ቢስሊ መልዕክት፣ የትግራይ ኃይሎች የድርጅቱን ነዳጅ በቅርቡ መዝረፋቸው የድርጅቱን እንቅስቃሴ በትግራይ እንዳስተጓጎለውም ይጠቅሳል፡፡

ይህንኑ የሚደግፍ ሐሳብ የሰነዘሩት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ቫለሪ ጉርኔሪ በበኩላቸው፣ ድርጀቱ በኢትዮጵያ እያቀረበ ያለው ሰብዓዊ ረድዔት 50 በመቶ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከተመድ ጠቅላላ ጉባዔና ከፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጉዳይን በተመለከተ የፓናል ውይይት ላይ ግጭት ባለባቸው አገሮች ሰብዓዊ ረድዔት ለማቅረብ ፈተና መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ የግጭት ቀጣና ላሉ ሰዎች ዕርዳታ ለማቅረብ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቂ ትኩረትና ድጋፍ እያደረገ አይደለም ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ጉዳይ በተለይ የዓለም አቀፍ ለጋሾችና ዕርዳታ አቅራቢዎች ፖለቲካዊ ጫና ለማሳረፊያነት አውለውታል፤›› የሚል ቅሬታም ይቀርባል፡፡ ከሰሞኑ ከተመድ ስብሰባዎች ጎን ለጎን በተጠራው የፓናል ውይይት ላይ ተናጋሪ የነበሩት በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ዮሴፍ ካሳዬ (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት ስም የሚደረግ ጫናን እንደማትቀበል ተናግረዋል፡፡

‹‹የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ለጋሶችና ዕርዳታ አቅራቢዎች በኢትዮጵያ የምታደርጉትን ሰብዓዊ ዕርዳታ በአድናቆት እንቀበላለን፣ ከልብም እንደግፋለን፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሲንቀሳቀሱ ሁሉም ገለልተኝነታቸውን በመጠበቅና የኢትዮጵያንም ሕግ አክብረው መሆን እንዳለበት ማሳሰብ እንፈልጋለን፤›› ሲሉ ነበር ለጋሾች የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያ ለአብዛኛው የአገር ውስጥ ተፈናቃይና ዕርዳታ ፈላጊ በራሷ አቅም ድጋፍ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም ከምታደርገው ጥረት ጎን ለጎን፣ ከ800 ሺሕ በላይ የውጭ ስደተኞችን በግዛቷ ማስጠለሏንም ዮሴፍ (አምባሳደር) ለዓለም ዕርዳታ አቅራቢዎች ነግረዋል፡፡

ከሰሞኑ በተጠሩ የተመድ ስብሰባዎችና ተጓዳኝ የውይይት መድረኮች ግጭትና ሰብዓዊ ቀውሶች ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ችግሮች መሆናቸው ተደጋግሞ ተወስቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በሁለቱም ማለትም በግጭትና በሰብዓዊ ቀውስ የሚሰቃዩ አገሮችም ተደጋግሞ ስማቸው ሲነሳ ከርሟል፡፡ ዓለም ስለዚህ ቀውስ ምን ላድረግ? ብሎ የመከረባቸው እነዚህ ወሳኝ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረኮች ግን የእንግሊዝ ንግሥት የሐዘን ሥነ ሥርዓት ዜና ጥላ ያጠላባቸው ሆነው አልፈዋል ተብሏል፡፡

ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ችግር መፍትሔ ለመስጠትም ሆነ የሰብዓዊ ረድዔት የገንዘብ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ግንባር ቀደም ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ የቡድን 20 አባል አገሮች አብዛኞቹ መሪዎች የተመድ ስብሰባን መካፈል ትተው፣ ለንግሥቲቱ ቀብር ወደ እንግሊዝ ያመራሉ መባሉ ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉተሬስን በንዴት እንዲጦፉ ነበር ያደረጋቸው፡፡ ስለዚሁ የተጠየቁት ጉተሬስ፣ ‹‹እኔ በቀብሩ ላይ አልገኝም፡፡ በተመድ ዋና ጽሕፈት ቤት የምመራው ብዙ ወሳኝ ስብሰባ አለኝ፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

‹‹ዓለም በግጭት የሚፈጠር ሰብዓዊ ቀውስ እያሳሰበኝ ነው፤›› ቢልም፣ ከሰሞኑ እንደታየው እንደ ኢትዮጵያና ሩሲያ ያሉ አገሮች ለተባባሰው ቀውስ ዋና ተጠያቂዎች ናቸው በሚል ጣት ሲቀስር ነው የታየው ይላሉ አንዳንድ ተቺዎች፡፡

ከሰሞኑ በተባባሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ወደ መርሳ ከተማ እየጎረፉ ላሉ ተፈናቃዮች የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ ለማድረግ ዝር አለማለታቸው ተነግሯል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለሙ፣ በአካባቢው ላሉ ተፈናቃዮች ከወርልድ ቪዥን (World Vision) ውጪ ድጋፍ ለማድረግ የመጣ ዕርዳታ አቅራቢ የለም ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በመርሳ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች በግል ሰዎችን በማስተባበር ድጋፍ የሚያቀርበው ወጣት መሐመድ አብዱ፣ ‹‹ለተፈናቃዮቹ እየደረሰ ያለው የአካባቢው ኅብረተሰብ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በመስጊድና በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ዕርዳታ እያዋጣ ነው፡፡ እኛም በየቤቱና በየአካባቢው እየዞርን ዕርዳታ እናሰባስባለን፡፡ ወርልድ ቪዥን የሚባል ድርጅት የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ ዓይቻለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የውጭ ዕርዳታ ድርጅቶች ለተፈናቃዮች ሲረዱ አላየሁም፤›› በማለት በአካባቢው ያለውን የረድዔት አቅርቦት ሁኔታ ተናግሯል፡፡

በሰሜን ወሎ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ በእጅጉ መባባሱን ደግሞ አቶ ዓለሙ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በጃራ አካባቢ ባለው መጠለያ ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ በአጠቃላይ በዞናችን ከ155 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ አሁንም ተጨማሪ ተፈናቃዮች እየመጡ ነው፡፡ ይህ በመንግሥት አቅም ብቻ የረድዔት አቅርቦቱ የሚሸፈን ባለመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይድረስልን፤›› ሲሉ አቶ ዓለሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡   

ይህ የራያ ቆቦ ግንባር ጦርነት የፈጠረው የአንድ አካባቢ የሰብዓዊ ቀውስ እንጂ፣ መላውን የቀውስ ሁኔታ የሚሳይ ነው ተብሎ አይገመትም፡፡ አሁን ጦርነቱ በሦስት አቅጣጫዎች መቀጠሉ ነው የሚነገረው፡፡ በአፋር ክልል በኩል ጦርነቱ እያስከተለ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ከክልሉ አደጋ መከላከል ቢሮ በኩል ለማወቅ በጽሑፍ መልዕክት (ቴክስት) በቴክስት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም አልተሳካም፡፡ ግጭቱ በራያና በአፋር ክልሎች ብቻ ሳይሆን፣ በወልቃይትና በሰቆጣ ግንባሮችም በሰፊው መቀጠሉ ነው የሚነገረው፡፡ በራያ በኩል ካለው ሁኔታ በመነሳት ጦርነቱ በእነዚህ አቅጣጫዎችም የከፋ የሰብዓዊ ቀውሶች ሊያደርስ እንደሚችል ነው የሚገመተው፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ወደ ትግራይ ክልል ይደረግ የነበረው የሰብዓዊ ረድዔት አቅርቦት ግጭቱ ካገረሸ ወዲህ ተቋርጧል፡፡ በዚህ የተነሳ በትግራይ ክልል ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይባባስ እየተሠጋ ይገኛል፡፡ ይህን ለፖለቲካ ጫና ማሳደሪያነት ለማዋል የዓለም ለጋሾች ሲሞክሩ ከመታየታቸው ባለፈ፣ በተጨባጭ የድጋፍ ዕርምጃ ሲሰጡ አለመታየቱ ትዝብት ላይ ሲጥላቸው እየታየ ነው፡፡

ከሰሞኑ ከተመድ ስብሰባ ጎን ለጎን ተካሂዶ በነበረው የፓናል ውይይት ላይ ለአፍሪካ ዕርዳታ ፈላጊ የገንዘብ ድጋፍ ስለሚገኝበት ሁኔታ ይናገራሉ ተብለው የተጠበቁ አንዲት የዓለም ባንክ ተወካይ፣ ‹‹በአፍሪካ የኢንሴክቶ (ነፍሳት) ልማትን ማስፋፋት ለዘላቂ የምግብ ዋስትና አዋጭ ነው፤›› ብለው ሲናገሩ መደመጣቸው አስተዛዛቢ ነበር ተብሏል፡፡

የ‹‹ሴቭ ዘ ችልድረን›› ተወካይ የሆኑት አንዲት ተናጋሪ ግን በንዴትና በእልህ ተሞልተው፣ ‹‹እኛ ወሬ ስናወራ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ግን በየ48 ሰከንዶች አንድ ሕፃን በምግብ እጥረት ይሞታል፤›› ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡ ‹ግጭት የዓለም ሰብዓዊ ቀውስን እያባባሰ ነው› የሚለው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ እንዲህ ያሉ አስተያየቶችን ለመስማት ጆሮ እስካላገኘ ድረስ ደግሞ የዓለም ግጭቶችም ሆነ ግጭት አመጣሽ ሰብዓዊ ቀውሶች እንደማያቆሙ ነው የተገመተው፡፡.

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -