Tuesday, April 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ወጣቶችን ጥራት ባለው ትምህርት በመቀየር ሰብዓዊነት የተላበሳቸው እናድርጋቸው

ክፍል ፪

በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)

የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ

የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋም (ቲቬት) ለአንድ አገር ዕድገትም ሆነ የሥራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ ቁልፍ ስለሆነ፣ በየክፍለ አገሩ ብዛት ያላቸው የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት ጥራታቸውን በጠበቁ ሁኔታ ማቋቋም አለብን፡፡ እነዚህም  ተቋማት፣ የሥልጠና ሥርዓተ ትምህርታቸውም ሆነ፣ የሚያሠለጥኑበት መሣሪያ፣ ከዓለም አቀፍ ጋራ ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ መደረግ ያለበት፣ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጉት የሥልጠና ዓይነቶቹ ተዘርዝረው መታወቅ አለባቸው፡፡

ለእነዚህ የማሠልጠኛ ተቋማት፣ ሥርዓተ ትምህርቱንም ሆነ መሣሪያውን ለመምረጥ ብዙ ኢትዮጵያውያን ስለሌሉ ሞዴል የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቲቬት፣ የሚባለውን እንድናቋቁም እንዲረዱን የግድ የውጭ አገርን ዕርዳታ መጠየቅ አለብን፡፡ ከነዚህ አገሮች ውስጥ ለምሳሌ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስዊድን፣ ቻይና፣ ሩሲያ ወዘተ. ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህንም አገሮች በቀጥታ ጠይቀን ፈቃደኛ ከሆኑ፣ አንድ ሞዴል የተለያዩ የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ  ተቋማት፣ ሥርዓተ ትምህርታቸውን በመቅረፅ፣ ለዚያም የሚሆን መሣሪያ በማቅረብ ለተቋማቱ መምህራን ሊሆኑ የሚችሉትን በማሠልጠን፣ ወዘተ. በመገንባትና በማደራጀት ሊያስረክቡን ይችላሉ፡፡ እኛ ደግሞ እነዚህን ሞዴል ተቋማት እንደ እርሾ ይዘን ብዛት ያላቸው ተቋማት በራሳችን ወጪና ባለሙያ በመገንባት ልናስፋፋ እንችላለን፡፡ እንደ ምሳሌ ብቃት ያላቸው ተቋም የገነቡትን ጣሊያን (የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ማሠልጠኛ ተቋም)፣ ጀርመን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋራ በመተባበር ብዙ ማሠልጠኛ ተቋማትን የገነባውን፣ ሩሲያ የቀድሞውን ባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩን፣ ወዘተ. መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሥልጠና ተቋማትን በምንመርጥበት ጊዜ በዘመናዊ አሠራር፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሆኖ፣ ከአገሪቷ ነባራዊ ሀብት በመነሳት ወደ ውጭ ምርቶቻችንን ለመሸጥ የሚያስችሉን መሆን አለባቸው፡፡

ከነዚህም ውስጥ እንደ የግብርና (እህል፣ ምግብ፣ ዓሳ፣ ወተትና የወተት አስተዋጽኦ፣ ሥጋ፣ ፍራፍሬ፣ ወዘተ.) የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች (የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የኬሚካል ወዘተ.) የባህላዊ ኢንዱስትሪዎች (ሸክላ፣ ሽመና፣ የእንጨት ሥራ) የጤና የግንባታ ኢንዱስትሪዎች ወዘተ ትኩረት መስጠት አለብን፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ለወጣቱ ሥራ ሊፈጥር የሚችለው የግብርናው ሴክተር ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ እንደሚታወቀው የአገራችን ግብርና በባህላዊ መንገድ ነው የሚካሄደው፡፡ በዚህም ለግብርና የሚመች በቂ መሬት፣ ውኃ ወዘተ. እያለን ራሳችንን በምግብ ለመቻል አልቻልንም፡፡ አሁን ያለውን የግብርና አሠራር ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ አሠራር መለወጥ አለብን፡፡

ገበሬው የተማረ በመሆን፣ ከበሬና ከሰው ጉልበት ተላቅቆ በዘመናዊ መሣሪያ የሚያርስ መሆን አለበት፡፡ የሚማረው ግብርናውን ብቻ ሳይሆን፣ በተጓዳኝ ኢኮኖሚውን በማወቅ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን እንዲያመርት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ በዚህና በሌሎቹም ምክንያቶች በየክልሉ በብዛት ጥራቱን የጠበቀ የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ በግብርና አቋቋመን፣ በብዛት ሥራ አጡን ወጣት መሬት፣ የግብርና መሣሪያ፣ የሥራ ማስኬጂያ ገንዘብ ወዘተ. በብድር ሰጥተን ብናስጀምር ወጣቱም ሥራ አግኝቶ አሁን ያለውን ኋላ ቀር የግብርና አሠራር በመለወጥ ከእኛ አልፈን ‹‹የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫትና የግብርና ውጤቶች አቅራቢ›› ልንሆን እንችላለን፡፡ በተጨማሪም፣ በዚህ ዓይነት ተምረው በግብርና ላይ የተሰማሩ ወጣቶች፣ የነገው ዘመናዊ ገበሬዎች በመሆን፣ ሽግግሩን ከኋላ ቀርነት ወደ ዘመናዊ የግብርና ሥራ የሚያሸጋግሩ ከመሆናቸውም በላይ የምርት ግንኙነታቸው ከዓለም ገበሬ ጋራ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ከሠራንበት በጥቂት ዓመታት ዕድገታችን የላቀ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም (ዩኒቨርሲቲዎችን ይጨምራል) በሥርዓተ ትምህርቱ የተግባር ትምህርት በኢንዱስትሪ ቢያስገድድም ለማስፈጸም ትልቅ ችግር አለ፡፡ በዋናነት ኢንዱስትሪዎች አለመተባበራቸው ነው፡፡ በመጀመሪያ ኢንዱስትሪዎቹ፣ ግንዛቤያቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡ ሠራተኛ የሚያገኙት በኢትዮጵያ በቀረጥ ከፋይ ገንዘብ መንግሥት አስተምሮ ነው፡፡ በዚህም ለትምህርት ጥራት አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በኢንዱስትሪና በትምህርት ሚኒስቴር አሳሪ ሕግ ባለመኖሩ ሊተገበር አልተቻለም፡፡ የሌሎች አገሮችን ልምድ በመውሰድ፣ ሁሉንም በሚጠቅም መንገድ ሕግ መዘጋጀት አለበት፡፡ በዚህም ሕግ ላይ ኢንዱስትሪዎች፣ ሠልጣኞችን (ተማሪዎች) በሥራ ቦታቸው የተግባር ሥራ ማሠራት እንዳለባቸው፣ ከተወሰኑ በላይ ለሚያሠሩዋቸው ሠልጣኞች (ተማሪዎች) የቀረጥ ቅነሳ እንደሚያገኙ ወዘተ. ሊካተቱ ይችላል፡፡      

ይህ ሁሉ ዝግጅት ቢደረግም በቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ የሚሠለጥኑ ሠልጣኞች በሙያው ፍላጎት ከሌላቸው፣ “ዘሎ እምቦጭ” ነው የሚሆነው፡፡ ሠልጣኞች የቴክኒክና የሙያ ማሠልጠኛ ተቋማትን የሚቀላቀሉት መሄጃ በማጣት ሳይሆን፣ ፈልገውት እንዲሆን ማበረታቻ መንግሥት ከመዘርጋቱም በላይ የአገሪቱ የማሠልጠኛ ተቋማት ባለቤት የሆነው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ሠልጣኞች የሚመለመሉት ከዩኒቨርሲቲ መሰናዶ በፊት መሆኑን አረጋግጦ፣ አንድ በቴክኒክና ሙያ የሠለጠነ መማር ከፈለገ በዚያው ሙያ ሥር በተቋቋሙት ከፍተኛ ማሠልጠኛ ተቋማት እንጂ በዩኒቨርሲቲው በኩል አይደለም ብሎ መርሐ ግብር መደንገግ አለበት፡፡

አውቃለሁ ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነቱን የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ በቴክኒክና ሙያ የሠለጠኑት፣ ሰላማዊ ሠልፍ በመውጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ በር እንዲከፍት እንዳሳዘዙ፡፡ ይህ መታረም አለበት፡፡ የማሠልጠኛ ተቋሙ የትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ በቴክኒክና ሙያ በሕዝብ ገንዘብ ሠልጥኖ፣ ለአገሪቱ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል የተባለ ወጣት፣ ሥራውን ባጣ ቆየኝ በማድረግ፣ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በር እያንኳኳ የወጣበትን የአገር ሀብት ሲደፋ፣ ሚኒስቴሩ መፍቀድ የለበትም፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ ግለሰቦች የመብት ጉዳይ ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ እኔም አከብራለሁ፡፡ ሠልጣኙ ሞቼ እገኛለሁ ወደ ሌላ ሥራ አማትራለሁ ካለ ቢያንስ ለሥልጠና መንግሥት ያወጣበትን ወጪ መመለሱ መረጋገጥ አለበት፡፡

ሌላው ሠልጣኞቹ በሙያው እንዲበረታቱ፣ የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ደረጃ ከዲግሪ መለስ ያለ ድረስ ማዘጋጀት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ መካከለኛ አውሮፓን እንደ ጀርመን ያሉትን ተሞክሮ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ በጀርመን ሁለት ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት አሰጣጥ አለ፡፡ አንደኛው በቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ የሚሰጥ ሲሆን፣ እንደማንኛውም ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ መሠረቱን አድርጎ ዕቅድ የያዘና በዲዛይን አማካይነት ምርትን ለማልማት (ፕሮጀክትስ ዴቬሎፕሜንት) ወይም የምርቱን ቴክኖሎጂ ለማሻሻል የሚረዳ የትምህርት ዓይነት ነው፡፡ በእነዚህ ላይ ትምህርት ሲጨረስ ዲፕሎም ኢንጂነር (Dipl. Ing.) ከፍ ሲል ደግሞ ዶክተር ኢንጂነር (Dr.-Ing.) ዲግሪ ይሰጣል፡፡ ሁለተኛው ከፍተኛ የቴክኒክ ሙ›ያ ትምህርት በተለያዩ ደረጃ የሚሰጥበት የቲቬት ዓይነት ሲሆን፣ ትምህርቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ መሠረቱን አድርጎ፣ ወጣቱን በከፍተኛ ደረጃ በተለያየ ሙያ (ክህሎት) ሥልጠና በመስጠትና ልምምድ በማድረግ ምርትንና ቴክኖሎጂን ለማዳበር የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡

በቀላሉ ትምህርቱ ሙያ ለሥራና ለኑሮ (‘Skills for work and life’) መሠረት አድርጎ የሚሰጥ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት በከፍተኛ ደረጃ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በየሥልጠና ዓይነት መገንባት አለብን፡፡ እዚህ ላይ በአንዳንድ ቦታ ካለብዙ ጥናት የተቋቋሙትን ዩኒቨርሲቲዎች ወደ የቴክኒክና ሙያ በመቀየር፣ ሚኒስቴሩ ቆራጥ ዓመት እንዲኖረው ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ የሰው ሀብት አስተዳደር በአጠቃላይ የደመወዝ ደረጃና ዕርከን፣ ሥራው በሚሰጠው ውጤት ተምኖ በአዲስ መደንገግ አለበት፡፡ ዲገሪ ስለያዘ ብቻ ደመወዙን ቆልሎ፣ ውጤት እየሰጠ ያለው የሙያ ተመራቂ፣ በአነስተኛ ደመወዝ እንዲሠራ ማስቀመጥ የለበትም፡፡ ሙያተኞች በሠሩት ውጤት በቂ ሲከፈላቸውና ሲከበሩ፣ ሙያቸውን አይለቁትም፡፡ ኅብረተሰቡም በቴክኒክና ሙያ የሠለጠነ፣ ለአገሪቱ ዕድገት ዋና ምሰሶ መሆኑን አውቆ፣ ተገቢውን የአክብሮት ቦታ መስጠት አለበት፡፡ ይህም ሲሆን፣ በቴክኒክና ሙያ የሠለጠኑ፣ ዲግሪ ሸመታ ከመሯሯጥ፣ ተዝናንተው በሙያቸው ይረጋሉ፡፡ በመጨረሻም የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም መገንባት በጣም ውድ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሠልጣኝ፣ ሊሠለጥንበት የሚያስችለው መሣሪያ በነፍስ ወከፍ ይፈልጋል፡፡ አሠልጣኞቹም ንድፈ ሐሳብ ትዮሪ እና ተግባር አጣምረው መያዝ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍላጎትና የተግባር ሥራ መሠረት ያላቸውን የመምህራን እርሾ ለማድረግ በየሙያው ዘርፉ ወደ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኮሪያ ወዘተ. ልከን በከፍተኛ የቴክኒክ ሙ›ያ ትምህርት ቤት እንዲሠለጥኑ ማድረግ አለብን፡፡

 

ዩኒቨርሲቲዎች

በዩኒቨርሲቲዎች ያሉትን የትምህርት ጥራት ክፍተትና የሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩት ትምህርት፣ ወቅቱን የጠበቀ መሆኑንና ካለው የሥራ ዕድል ጋራ መሳ ለመሳ መሆን አለበት፡፡ እዚህ ላይ በተሳሳተ ግንዛቤ፣ ዩኒቨርሲቲዎች ማስመረቅ ያለባቸው ሥራ ፈጣሪዎችን ነው የሚለው አባባል መታረም አለበት፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩት የሳይንስን ዕውቀት ነው እንጂ፣ ሥራን ለመፍጠር ብቃት ያላቸውን አይደለም፡፡ አብዛኞቹ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ሲከፈቱ እንዳለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሥርዓተ ትምህርት ገልብጠው ነው የጀመሩት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀድሞ ትምህርት ክፍሉን ሲከፍት የአገሪቱን የሥራ መቅጠር አቅም አጢኖ ነበር፡፡  አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ግን የገለበጡትን የትምህርት ዓይነቶች ወቅቱን የጠበቁ ናቸው ወይ? በዚሁ ልክ አገሪቱ የሥራ ዕድል ልትፈጥር ትችላለች ወይ? ወዘተ. ብለው አላጤኑም፡፡ ስለዚህ አሁን የሥራ አጥን ችግር ለመፍታት፣ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ቆም ብለው የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ በማድረግ አገሪቷ በወቅቱ ከምትፈልጋቸው የሙያ ዓይነቶች ጋራ የሚያስመርቁትን ማዛመድ አለባቸው፡፡

መንግሥትም በምን የሥራ ዘርፍ (የትምህርት ዓይነት) አገሪቱ የሥራ ዕድል ልትፈጥር ትችላለች የሚለውን አስጠንቶ፣ ለዩኒቨርሲቲዎች መስጠት አለበት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹም በተሰጣቸው ቁጥር ማስመረቅ እንዳለባቸውና ከዚያ በላይ ከአስመረቁ ተጠያቂነትን እንደሚኖር ማወቅ አለባቸው፡፡ እዚሁ ላይ መጠቀስ ያለበት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዎች በተለይ በየኮሌጆቹ ውስጥ አንድን ሙያ በተለያየ ስም በመጥራት፣  የሥራ አጡን ቁጥር እንዲያድግ ማድረጋቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በአካባቢ ጥበቃ (ኢንቫይሮንሜንት)፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በምህንድስና፣ በኅብረተሰብ ሳይንሰ፣ ወዘተ. በምግብና በውኃ ወጣቶችን ያስመርቃሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ምሩቃን፣ ተመሳሳይ ግን በልዩ ልዩ ስሞችና መመረቃቸው፣ የሥራ ገበያውን ያጥለቀልቁታል፡፡ ይህም፣ የሥራ አጡን ቁጥር ያበዙታል፡፡ ስለዚህ እነዚህን በተለያየ የትምህርት ክፍሎች ያሉትን ሁሉ አጣምሮ በአንድ ማዕከል መምራት አላስፈላጊ መምህራንን፣ ቤተ ሙከራን ወዘተ. በመቀነስና በማዕከላዊ የምሩቃንን ቁጥር ለመቆጣጠር ይቻላል፡፡  እነዚህ ነገሮች በደንብ ከተሠሩ፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለውን ተመሳሳይ የትምህርት ዓይነቶች ለማሸጋሸግና እስከነ ጭራሹም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችን እስከ መዝጋት ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ በአገራችን አስከሬን የሚመረምሩ ባለሙያዎች እጥረት አለ ብሎ፣ ከዚህ በፊት የትምህርት ክፍል ከፈተ፡፡ ተማሪዎቹ ሲመረቁ በዚህ ሥራ የተሰማራው የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ብቻ ሆኖ ተገኘ፡፡ እሱም ቢበዛ የሚፈልገው አንድ ወይም ሁለት ምሩቃንን ነው፡፡

በሁለት ሦስት ደርዘን የተመረቁ ምሩቃን ዕድላቸው፣ በየሠፈሩ በአገሪቱ ሥራ የለም ብሎ መንገላወድ ስለሚሆን፣ እንደነዚህ ያሉ የትምህርት ተቋሞች ተፈትሸው መዘጋት አለባቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ዓለም የትምህርት ተቋሞችን መዝጋት፣ መክፈት የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በምህንድስና የትምህርት ተቋም፣ በአንድ ወቅት ተፈላጊ የሥራ መደብ ተለውጦ በሌላ የሥራ መደብ ሊመጣ ይችላል፣ ወይም ብዙ ተመራቂዎች ተፈርቶ የሥራ መደቡ ሊቀንስ ይችላል፣ በዚህን ጊዜ የትምህርት ተቋሙ ወይም ጊዜው በሚፈልገው ዓይነት መስተካከል ወይም አያስፈልግም ተብሎ ሊዘጋ ይችላል፡፡

ሌላው በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋለው፣ በቅጡ የመጀመሪያ ዲግሪን ለማስተማሩ ያልቻሉ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ አስተምረን እናስመርቃለን ብለው የተለያዩ ፕሮግራሞች መክፈታቸው ነው፡፡ የእነሱ ምክንያት ያለብንን የመምህራን ችግር እንቀርፋለን፣ እነዚህን ፕሮግራሞች በመክፈታችን በውጭ ያለንን ስም እናሳድጋለን፡፡ ወዘተ. የሚሉ ናቸው፡፡ ትልቁ አደጋ ምንም በሌለበት ተምሯል ተብሎ ዲግሪ ሰጥቶ አስተማሪ ማድረግ፣ የዩኒቨርሲቲው ትምህርት ጥራቱ እንዳያድግ ነው የሚያደርገው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለማስጀመር ከ50 ዓመት በላይ ፈጅቶበት፣ በኢሕአዴግ ግፊት ነው የከፈተው፡፡

እንደ ማስታወሻ ደርግ፣ የተማሩ ሰዎች ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ ሄደው አልመለስ ስላሉ፣ ይህንን ለመቅረፍ ያየ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ በሲቪልና በኤሌክትሪካል ምህንድስና የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር እንዲከፍት ጠየቀ፡፡ በዚያን ጊዜ ይህንን ደርግ ሊጠይቅ የቻለው፣ በሁለቱም የትምህርት ክፍሎች በእያንዳንዳቸው ከአምስት የበለጡ አንቱ የተባሉ በሦስተኛ ዲግሪ ተመርቀው፣ በዓለም አቀፍ ታዋቂ የሆኑ፣ በቂ ልምድ ያላቸው መምህራን መኖራቸውን በማረጋገጡ ነበር፡፡

 የትምህርት ክፍሎቹ ግን፣ በቂ ቤተ ሙከራ፣ ምርምር ስለሌለ ዝግጁ አይደለንም ነበር መልሳቸው፡፡ ደርግ ሊያስፈራራ ሞከረ፡፡ ትምህርት ክፍሎቹ ግን፣ አንከፍትም ብለው ፀኑ፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ችግር የዶክተሮች ቁጥር ማብዛት ሳይሆን ጥራቱን የጠበቀ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን ማፍራት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት በሙሉ በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጡ ያሉትን የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብሮችን ማስቆም አለበት፡፡ በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች እየተማሩ ያሉትን ወደ አዲስ አበባ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ማዛወር አለበት፡፡ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎቸ ብቻ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር እንዲቀጥሉ ማጠናከር አለበት፡፡   

በአዲስ አበባ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች አንዳንድ ኮሌጆች ለጥራት መውደቅ ምክንያቶቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ ይህም ወጣት አመራሮች፣ በብዛት የሚገኙትን ረዳት፣ ተባባሪና ሙሉ ፕሮፌሰሮችን በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲያስተምሩ አለመጠቀም ነው፡፡ ይህ ካለምንም ማመንታት መታረም አለበት፡፡ የዩኒቨርሲቲም ሆነ የሚመለከታችሁ የመንግሥት አካላት ይህንን በአስቸኳይ ማረም አለባችሁ፡፡ ልምድ ያላቸው መምህራን እያሉ፣ በተሳሳተ አመራር የአገሪቱ ትምህርት ጥራት፣ በዚህም የተነሳ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሚቀጥሯቸው አጥተው ለእኩይ ተግባር እንዲሠለፉ ማድረግ የለብንም፡፡

የመምህራንን እጥረት ለመቅረፍ፣ በአንድ ትልቅ አዳራሽ ፕሮፌሰሮች ትምህርት (ሌክቸር) እንዲሰጡ በማድረግ መልመጃዎቹን (Exercises)፣ አጋዥ ሥልጠና (ቲቶራል) ቤተ ሙከራ ወዘተ. ወጣቶቹን በማሰማራት ትምህርቱን በማሳለጥ ጥራቱን ማስጠበቅ ይቻላል፡፡ እዚሁ ላይ መጠቀስ ያለበት በአሁኑ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው፣ ወጣት መምህራን በደንብ ላልሠሩ ተማሪዎች፣ የተጋነነ ማርክ የመስጠት ጉዳይ ዩኒቨርሲቲው ክትትል አድርጎ ማረም አለበት፡፡ በቀድሞው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ይደረግ የነበረውን የፈተና የማርክ አሰጣጥ ሒደት ብንከተል የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ በዚያን ጊዜ ፈተናው ከመጀመሩ ቀናት በፊት፣ አንድ ኮሚቴ ይቋቋም ነበር፡፡

የዚህ ኮሚቴ ዓላማ ፈተናው ከመሰጠቱ በፊት፣ የተዘጋጀውን ፈተና ከእነ መልሱ ሥርዓተ ትምህርቱን ያረጋገጠ መሆኑን፣ ለጥያቄዎቹ የተቀመጠው ማርክ ወዘተ. በአግባብ ይፈትሻል፡፡ በዚህ ዓይነት የተመረመረው ፈተና ለተማሪዎቹ እንዲፈተኑ ይወሰናል፡፡ ከታረመ በኋላ ለተማሪዎች ውጤቱ ከመሰጠቱ በፊት፣ በትክክል መታረሙና ለሥራውም ማርክ መሰጠቱን ኮሚቴው ያጣራል፡፡ በዚህም ሁሉም እንደ ሥራው ማርክ ያገኛል፡፡  በዩኒቨርሲቲዎች የተጋነነ ማርክ መስጠት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ አሉታዊ ገጽ ፈጥሯል፡፡ ይህም በሥራው ዓለም ይዘውት የመጡት ማርክና፣ የሚሰጡት አልጣጣም በማለቱ ነው፡፡ መንግሥት ኅብረተሰቡ በምሩቃን ላይ ያለውን አለመተማመን ለመቅረፍ የመውጪያ ፈተና ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ አውጇል፡፡

እኔ በመሠረተ ሐሳቡ ባልስማማም የተመራቂው ብቃት ስለሚያሳስበኝ፣ የሚፈታው ከሆነ በጥንቃቄና በዕውቀት ላይ የተዘጋጀ ፈተና መደገፍ ግድ ይለኛል፡፡ ጥንቃቄ ስልም አንድ ተምሬያለሁ የሚል ምሩቅን፣ ምንድነው የሚፈተነው የሚለውን በጥንቃቄ መመለስ አለበት፡፡ የትምህርት ሊቃውንት፣ ‹‹አንድ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ፣ ከተማረው ትምህርት ውስጥ ተመርቆ ሲወጣ፣ ሊያስታውሰው የሚችለው ከ20 በመቶ አይበልጥም›› ነው የሚሉት፡፡ እንግዲህ ፈተናው መሆን ያለበት ሊያስታውሰው በሚችለው ነው፡፡ ይህንንም ለማወቅ ለፈታኙ ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ልምድና የትምህርት ዓይነቱን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ለግንዛቤ እንዲረዳ ‹‹ታዲያ ምኑ ላይ ነው 1/5ኛ የሚያውቅ ምሩቅ፣ ዲግሪ የሰጣችሁት?›› የሚል ሊጠየቅ ይችላል፡፡  ለማለት የተፈለገው በአዕምሮው 1/5ኛውን ያሰታውሳል የተቀሩትን መጻሕፍትን በማገላበጥ ያስታውሳቸዋል ለማለት ነው፡፡ ይህም ሲተነተን በተማረበት ትምህርት ምሩቁ አንድ ቀመር የበዛበት በንድፍ (ዲዛይን) የተደገፈ መፍትሔ አንዲያቀርብ ቢፈለግ፣ ወዲያው መልስ መስጠት ላይጠበቅበት ይችላል ምሩቁ የሚጠበቅበት፣ ትክክለኛ መፍትሔውን መጽሐፍ በማገላበጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መስጠት ነው፡፡ የተማረ የሚባለው፣ በተወሰነለት አጭር ጊዜ ትክክለኛ መልስ መስጠቱ ነው፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ መልሱን እንኳ ቢሰጥ የተማረውን ትምህርት ጥያቄ ያስነሳበታል፡፡

እኩይ ባህሪ እንዴት ይቀረፍ?    

በመጨረሻም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ይዘውት የሚመጡት እኩይ ባህሪ እንዴት ሊቀረፍ ይችላል የሚለውን ማየት አለብን፡፡ ይህንን እኩይ ተግባር ተማሪዎቹ የያዛቸው ከራሳቸው አስተዳደግና ከኅብረተሰቡ ነው፡፡ ይህንን ለማጥፋት በተማሪውና በኅብረተሰቡ የተጠናወተውን እኩይ ተግባር ማየት አለብን፡፡ ለሁለቱም ግን መንግሥት አንድ ተቋም ፈጥሮ ትልቅ ዘመቻ ማድረግ አለበት፡፡ ወደ ወጣቱ ስንመጣ በማንኛውም የትምህርት ዘርፍ ወጣቱ ተመርቆ ወደ ሥራ ከመሰማራቱ በፊት፣ ለአሥር ወራት ብሔራዊ አገልግሎት የሚሠለጥንበት መርሐ ግብር መዘርጋት አለበት፡፡ ይህም መርሐ ግብር በደንብ ተጠንቶ ወጣቱ እኩይ አስተሳሰብን ከአዕምሮው በመፋቅ፣ ብቁ ሰብዕና የተላበሰው በሥራ  ብቻ መክበር እንደሚችል፣ በወሬ ሳይሆን በሥራ አንዲተጋ፣ አገሩ ኢትዮጵያን የሚያሳድግ እንዲሆን፣ ወዘተ. ሆኖ መቀረፅ አለበት፡፡ አነዚህን በአምስት ወሮች ወጣቱን ለማዘጋጀት ቢሞከር የተቀሩትን አምስት ወሮች በብሔራዊ ውትድርና በሚፈለጉበት ጊዜ ተጠባባቂ ወታደር በመሆን፣ ለአገሪቱ ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁበት የሥልጠና መርሐ ግብር፣ ቢፈጠር ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ በዓለም ላይ የተለመደው ብሔራዊ ውትድርና ሥልጠና የሚሰጠው የጦር ትምህርት ብቻ ሳይሆን፣ ዜጋው ኃላፊነት የሚሰማው የሚፈጠርበት ነው፡፡ እዚህ ላይ አደራ የምለው ይህ መርሐ ግብር፣ ከክልሎች ጥያቄ ወይም የእኔ የሚል አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ናት ከፍ ብላ የምትነግሥበት፡፡ ከዚህ ጋራ አብሮ የሚሄደው በአሁኑ ጊዜ በወጣቱ ዘንድ ‹‹ኅብረተሰቡ ወንጀል ሲሠራ፣ ቅጣቱ ብዙ አይደለም፤›› ብሎ እንዲያምን ያደረገውን እንዳልሆነ፣ ማስተማር አለብን፡፡

ኅብረተሰቡን በምናይበት ጊዜ እኩይ ተግባራት፣ በአገራችን ከ30 ዓመት ወዲህ በወረርሺኝ መልክ እየተስፋፋ የመጣ መሆኑን እናገኛለን፡፡ ኅብረተሰቡ ከአሁን በኋላ፣ ደመወዙ ለዕለት ኑሮ የማይበቃው ግለሰብ፣ ቅንጡ ቤትና መኪና ይዞ የሚንቀሳቀሰው፣ ሰርቆ ብቻ እንደሆነ ማጋለጥ አለበት፡፡ ለእንደዚህ ያለ ሰው ማክበር ሳይሆን፣ እንደ ሌባ እንዲቆጥረው ኅብረተሰቡ መቀስቀስ አለበት፡፡ ማንኛውም ወንጀል የሥራ ሰብዕናውን የሚነካ ከባድ ቅጣት መቀጣት አለበት፡፡ በድርጊቱም ቤተሰቡ እንዲያፍር መደረግ አለበት፡፡ ይህንን ያየህ ተቀጣ!!!፡፡ ለዚህም መንግሥት በወንጀለኞችና በሌቦች (ሙስና) ላይ መቀጣጫ የሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ካስፈለገም ሕጉን በጠንካራ ቅጣት አሻሸሎ ማውጣት አለበት፡፡ ሰው የገደለ 12 ዓመት ሌላው እንዲገድል ከማበረታታት ውጪ፣ ሌላ እንዳይገደል አስተማሪ አይደለም፡፡ ከዚህች ደሃ አገር ብዙ የልማት ቀዳዳዎችን የሚሸፍን፣  ሚሊዮኖች ብር ሰርቆ አሥር ዓመት መፍረድ ዕረፍት ሄደህ ስትመለስ ትበላዋለህ ማለት ነው፡፡ ይህንን ያየ ወጣትም ከመማር ይልቅ፣ ሌባ ብሆን ትንሽ ቀን ተቀጥቼ ኑሮዬ የተደላደለ ይሆናል ብሎ እንዲመርጥ ያስገድደዋል፡፡

እዚህ ላይ ከአሥር ዓመት በፊት በአንድ ባንክ የቦርድ አባል ሆኜ ስሠራ፣ የተከሰተው ዘወትር ትዝ እያለ ይገርመኛል፡፡ ባንኩ አንድ ገንዘብ ከፋይ ቀጠረ፡፡ ይህ ሠራተኛ አንድ ዓመት ሳይሞላው፣ በእጁ ያለውን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ሰርቆ ጠፋ፡፡ ይህ ጉዳይ ለእኛ ቀረበልን፡፡ የገረመኝ እንግዲህ ገንዘቡ መጥፋቱ ሳይሆን፣ ሌባው ትምህርቱን ጨርሶ ወዲያውኑ ነው ወደ ባንኩ የገባው፡፡ ይህ ልጅ ታዲያ ትምህርት ቤት እያለ፣ እነ ሒሳብን ሲማር፣ ባንክ ገብቼ ገንዘብ ሰርቄ እጠፋለሁ ብሎ ነው እያሰበ የተማረው፡፡ ይገርመኛል፡፡ በሌቦች ላይ ከባድ ቅጣት መጣል ሌላው እንዲፈራ ያደርጋል፡፡ አለበለዚያ ወንጀለኞቹ “ቢበዛ አዶላ ነው፣ ምን ይመጣል” እያሉ እየዘፈኑብን ሌላውን ያበረታታሉ፡፡

የወንጀል ቅጣት እንደ ኅብረተሰቡ ንቃትና አኗኗር ይፈጸማል፡፡ ኅብረተሰቡ በአስተሳሰብ ባላደገበት ሰዓት ዓይን ላጠፋ፣ ቅጣቱ ዓይኑን ማውጣት ነው፡፡ ቻይና፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ከባድ ወንጀል ለሠሩ እስከ ሞት ይቀጣሉ፡፡ ቻይና ባለሥልጣንም ሆነ ተራ፣ የአገርን ሀብት ከሰረቀ በሞት ትቀጣለች፡፡ በነዚህም ሆነ በሌሎች አገሮች የሞት ቅጣት በከባድ ወንጀልና ስርቆት ለፈጸሙ ሰለሚፈጸም፣ ወንጀል ለመሥራት የፈለገ ሕይወቱ ስለምታሳዝነው፣ የአዕምሮ ችግር ከሌለበት ወንጀል ሊሠራ አይገፋፋም፡፡ በንጉሡ ጊዜ በአንድ ወቅት ስድስት ሰዎች በተለያዩ የከተማው ሠፈሮች ማታ ማጅራታቸውን ተመትተው ተገደሉ፡፡ ፖሊስ ተከታትሎ ይዞ ፍርድ ቤት አቅርቧቸው ፍርድ ቤቱም ሕዝብ በተሰበሰበበት በስቅላት እንዲቀጡ ፈረደ፡፡

ሕዝቡም እኔም ጭምር ወጥተን ሲሰቀሉ በዓይናችን አየን፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ በንጉሡ ዘመን አንድም ማጅራት መቺ አላጋጠመም፡፡ ሰሞኑን አንዲት ወጣት፣ ሥራ ለመሄድ ሰርቪሷ ስላመለጣት በባጃጅ ለመድረስ ባጃጅ ውስጥ ገባች ሦስት ሆነው፣ ለጆሮ በሚቀፍ አኳኋን ገደሏት፡፡ ለነፍስ ገዳዮች ፍርድ እስከ 12 ዓመት እስራት!!! እንደነዚህ ዓይነቶቹ ፍርዶች ናቸው ወንጀል እንዲበዛ ያደረገው፡፡ ኅብረተሰቡ በዳኞችም፣ በመንግሥትም ደንግጧል፡፡ ወንጀሉ ከመቀነስ ይልቅ በወጣቶችም ሳይቀር ተስፋፍቷል፡፡ ሌብነቱ እንደ ወረርሽኝ ሁሉም ቦታ እየተዳረሰ ነው፡፡ ወጣቶችም፣ ወንጀል ብንሠራ ምንም አንሆንም እያሉ እየገቡበት ነው፡፡ መንግሥት እባክህን አገሪቷ በወንጀለኞችና በሌቦች ሳትጥለቀለቅ ወጣቱም፣ ሠራተኛውም፣ ፖለቲከኛውም፣ ነጋዴውም፣ ሌላውም ወዘተ. ወንጀል ከሠሩ፣ ከባድ ቅጣት ለማስፈጸም ሕግህን ፈትሽ፡፡ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በማሳወቅ፣ ዜጎችን ከእኩይ ተግባርና ከስርቆት እንዲርቁ አድርግልን፡፡ መንግሥት በሕግ አምላክ!!!!!! ይብቃ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በላይ ወልደየስ (ዶ/ር-ኢንጂነር) የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ደግሞ በፔትሮኬሚካል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2015/16 የአስተማሪነት ልዕልና ሽልማትን (Distinguished Teaching Award) ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ መሥራች አባልም ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles