Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአዲስ አበባ ቴአትርና የባህል አዳራሽ ወዴት እያመራ ነው?

የአዲስ አበባ ቴአትርና የባህል አዳራሽ ወዴት እያመራ ነው?

ቀን:

‹‹ሁላችንም እንደምናውቀው የአዲስ አበባ አስተዳደር ዕድሜ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ አምሮና አሸብርቆ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተውቦ ተመርቋል ሲሉ ሰምቼ ደስ አለኝ፣ በቴሌቪዥንም የባህል አዳራሹን ሳይ ከልብ ተደሰትኩ። ቆየሁ፣ ጠበቅሁ፣ አቤቱታ ሲደረግም እኔም አማረርኩ። ያ የተዋበ የጥበብ አዳራሽ ለባለቤቶቹ የጥበብ ሰዎች አልተሰጠም፣ እነሱም የሚጠበቡበት ቦታ የላቸውምና ከዛሬ ከነገ በሚል ተስፋ እስካሁን አሉ። ስለዚህም እነዚህ የጥበብ አጋሮቼ አዳራሹን በክብርት ከንቲባችን መልካም ፈቃድ እንዲጠበቡበትና የሙያ ቤታችን ማለት እስኪችሉ ድረስ ከዛሬ ጀምሮ ራሴን ከጥበቡ መንደር ማግለሌን….[አስታውቃለሁ]››፡፡

ይህን ኃይለ ቃል ያስተጋባው አንጋፋው የጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ ዓምና ሙሉ ዕድሳቱ የተጠናቀቀው የማዘጋጃ ቤት ሕንፃ አካል የሆነውን የቴአትርና ባህል አዳራሽን ባለሙያዎች ከያንያን ባለመረከባቸው የተሰማውን ሐዘኔታ በአንድ መድረክ ላይ የገለጸበት ነበር፡፡ የርሱና የጥበቡ ቤተሰቦች የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጥረት ታክሎበት ከወራት ቆይታ በኋላ የአዳራሹን ቁልፍ ክፍሉ መረከቡም ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ቴአትርና የባህል አዳራሽ ወዴት እያመራ ነው? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
አንጋፋው ከያኒ ደበበ እሸቱን ጨምሮ የኪነጥበቡ ኃላፊዎች በተገኙበት የቴአትር ቤቱ የማኔጅመንት አባላት አዳራሹን በተረከቡበት ዕለት

 የባህል አዳራሹ ከያንያን ኅዳር 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ለእድሳት ተብሎ ከቦታው መውጣታቸው፣ ዕድሳቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በጥበብ አፍቃሪያንና በባለሙያዎች ውትወታ ምክንያት ደግሞ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. እድሳት ወደ ተደረገለት አዳራሽ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት አንድ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከነበርንበት ወደ ታደሰው ገብተዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ልብ እየሠሩበት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ልምምድ ማድረግ እንደማይችሉ፣ የልምምዳቸው ቀን ስብሰባ ስለሚኖር እንዳትመጡ እንደሚባሉ ያስረዳሉ፡፡ ቴአትር ቤቱ ሙሉ በሙሉ እንዳልተጠናቀቀ፣ የመድረክ መብራትና የተለያዩ የመለማመጃ ቦታዎች እንደሌሉት ያወሱት ባለሙያው፣ ትልቁ ችግር ያሉት በልምምድ ላይ እያሉ ስብሰባ አለ ሲባሉ አቋርጠው መበተናቸው ነው፡፡ አዳራሹ የቴአትር ቤቱ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ ነገር ግን የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ባይተዋር መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌነትም ያነሱት በአዳራሹ ማዘዝና ፈቃድ መጠየቅ የነበረበት የቴአትርና ባህል አዳራሹ ቢሆንም፣ ነገር ግን ነገ ስብሰባ ስላለ እንዳትመጡ እንደሚባሉ አስረድተዋል፡፡ ለተመልካች የተለያዩ የቴአትርና የሙዚቃ ዝግጅቶችን ለማቅረብ መቸገራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሐምሌ ወር ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ክፍሉ መነጋገሩን የገለጹት ባለሙያው፣ ነገር ግን የመድረክ መብራት ከውጭ እየገባ መሆኑን እንደተነገራቸው አስረድተዋል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ አሁንም ለሙያተኞቹ አልተመለሰም። ምንም የማይከፍቱበትና እንደቤታቸው የማያዙበት ቁልፍ ብቻ እንደተሰጣቸው አዳራሹ አሁንም እንደነበረው መሰብሰቢያነቱን ቀጥሏል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ሃያና ሠላሳ  የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ከየክፍለ ከተማው ከሚመጡት ጋር በተሰበሰቡ ቁጥር ሙያተኞቹ ወደ አዳራሹ  እንዳይገቡ እንከለከላለን ያሉት ሌላው ባለሙያ፣ የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ እጁ ላይ የአዳራሹ ቁልፍ ቢኖረውም፣  አሁንም በአዳራሹ የሚያዘው የከንቲባዋ ጽሕፈት ቤት መሆኑን ገልጸዋል። አርቲስቶቹ ቀድሞ እንደመለማመጃ ይጠቀሙበት የነበረው ኮክቴል አዳራሽ  በወንበር ተሞልቶ እንደ ቀድሞው ለቴአትርና ሙዚቃ መለማመጃ ማዋል እንዳልተቻለ ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ለቴአትርና ሙዚቃ አቅርቦት የሚሆኑ መብራቶች እንዳልተገጠሙለት፣ መልበሻ ክፍል ጭምር እንደሌላቸው የቴአትር ቤቱ ሙያተኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል። ‹‹አሁንም ገብታችኋል ከመባል ውጪ፣ እግራችን ገብቶ እጃችን ታስሮ ነው ያለው፤›› ብለዋል።

ጥበብ በባህሪዋ ነፃነትን እንደምትሻ የተናገሩት ከያኒያኑ፣ የልምምድ ቦታ መሠረታዊ ጥያቄ ደግሞ የአዳራሹ ባለቤትነት ጉዳይ ባለመረጋገጡ ነፃነታቸውን እንዳጡ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች ከሙያቸው የተገለሉ ባለሙያዎች ሆነናል›› ሲሉ አክለዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ቴአትር ባህል አዳራሽ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ጋዲሳ፣ አዳራሹ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቢጠናቀቅም የመድረክ መብራት እንደሌለው፣ ግብዓቶቹም ከውጭ እየመጡ መሆኑን እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡ የቴአትር ቤቱ አዳራሽ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ቢታደስም መሠረታዊው ግብዓት የመድረክ መብራት ባለመኖሩ ሥራዎችን መሥራት እንዴት ይቻላል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

‹‹ከውጭ ቴአትር ቤቱን ሲያዩት ግንባታው የተጠናቀቀ እንደሚመስል፣ ነገር ግን ውስጥ ሲገቡ ያልተጠናቀቁ ነገሮች እንዳሉት አይተናል፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው የተነገራቸው ቤቱን የሚያድሰው ተቋራጭ ሥራውን አጠናቆ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት አለማስረከቡን ነው፡፡ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ካላስረከባቸው የባለቤትነት መብት እንደሌላቸው ወይም እንዳልተረጋገጠ የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ሌላኛው የቴአትር ቤቱ ችግር ሥራ አስኪያጁም ሆነ፣ የቡድን መሪዎች የየራሳቸው ቢሮዎች ስለሌላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡

በጊዜው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የነበረውን የኅብረተሰቡን ጥያቄዎችን ያስታወሱት አቶ ኤፍሬም፣ በተፈጠረው ጫና እንደ መፍትሔ በጊዜያዊነት እንደገቡ ገልጸዋል፡፡ ቴአትር ቤቱ ከዚህ ቀደም የነበሩት ዶክመንቶች የሚቀመጡበት የቢሮ አደረጃጀቶች ሁሉ እስካሁን ድረስ እንዳልተስተካከለ ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ቁልፍ ሲረከቡ በቴአትርና ባህል አዳራሹ ሙሉ ሥልጣን ያላቸው እንደመሰላቸው፣ ነገር ግን እድሳቱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ የቴአትር ባለሙያዎች የሚለማመዱበትን ክፍለ ጊዜ ለማውጣት እንኳ መቸገራቸውን አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል፡፡ አሁንም ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት አጠናቀው ይሰጡናል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ የቴአትርና ባህል አዳራሹን ባለመረከባቸው የገጠማቸው ችግሮች የቴአትርና የሙዚቃ ልምምድ ማድረግ እንደማይችሉ የገለጹት፣ በማንኛውም ጊዜ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ሲኖረው ልምምድ ማድረግ እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡ አንዳንዴ ሳምንቱን ሙሉ ስብሰባ ስለሚኖር፣ በዚህ ምክንያት ልምምድ ማድረግ እንዳልቻሉ፣ አሥር ሃያም ሰው ስብሰባ ሲያደርግ ቴአትር ቤቱ ሥራውን መሥራት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡

የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች በየቀኑ ቅሬታ እንደሚያቀርቡ የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ከአቅማችን በላይ መሆኑን ነግረናቸዋል ብለዋል፡፡ አራት የተለያዩ ክፍሎች ማለትም የቴአትር፣ የባህል ሙዚቃ፣ የዘመናዊ ሙዚቃ ልምምድ ማድረግ እንደማይችሉ፣ የቦታ እጥረት መኖሩን፣ ከእድሳቱ በፊት ለተለያዩ ክፍሎች በተለያዩ ክፍሎች ይለማመዱ እንደነበር፣ አሁን ላይ ይህን ለማድረግ እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡

በ1939 ዓ.ም. ግንቦት ቀን እንደተከፈተ የሚነገርለት የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በተለያዩ ጊዜያት በሚያቀርባቸው ተውኔቶች፣ ሙዚቃዊ ድራማዎች፣ የባህልና ዘመናዊ ሙዚቃዎች፣ ዳንስና ውዝዋዜዎች የጥበብ አፍቃሪያን ያስፈነድቁ እንደነበር በታሪክ ይታወሳል፡፡ እንደ አሁኑ ጊዜ በቴክኖሎጂ የተከታታይ ፊልምና ድራማ ሳይጥለቀለቅ በፊት፣ እያዋዙ ትምህርት አዘል የኪነ ጥበብ ሥራዎችን የሚቀርቡበትም መድረክ ነበር፡፡

ዘንድሮ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩን ለማክበር ይበቃል ተብሎ የሚጠበቀው የአዲስ አበባ የቴአትርና ባህል አዳራሽ በስምንት አሠርታት ግድም ጥበባዊ ጉዞው የተለያዩ አደረጃጀቶችን ሲያሳልፍ በርካታ ታላላቅ ከያንያንን ከኪናዊ ሥራዎቻቸው ጋር አፍርቷል፡፡

ቴአትር ቤቱ ካቀረባቸው ተውኔቶች መካከል ቴዎድሮስ፣ ኦቴሎ፣ ጣይቱ፣ አቡጊዳ፣ መልዕክተ ወዛደር፣ የሲስትሮ ኦፔራ፣ እሳት ሲነድ፣ የመንታ እናት፣ መቅድም፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ጁሊየስ ቄሳር፣ ስመኝ ስንታየሁ ወዘተ ይገኙበታል፡፡

የተለያዩ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ያካተተው ዕዝለ ጥበባትም በተወዳጅነቱ ይጠቀሳል፡፡

የቴአትርና የባህል ማዕከሉ ካሉት 140 ሠራተኞች ውስጥ 15 የቴአትር፣ 30 የባህል ሙዚቃ፣ 30 የዘመናዊ ሙዚቃ ባለሙያዎቹ የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...