Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህር ትራንስፖርት ድርጅት ከአጋሮች ጋር በጭነት ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት የመሰማራት ፍላጎቱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ዘጠኝ ሚሊዮን ቶን ገቢና ወጪ ጭነት ለማስተናገድ ዕቅድ ይዟል

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ ከየብስ ትራንስፖርት ዘርፎች አንዱ በሆነው የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የኢትዮጵያ ጭነት እያደገ ቢሆንም የተሽከርካሪ አቅርቦቱ እየቀነሰ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከተሽከርካሪ ምልልስ ጋር በተገናኘ የሚያጋጥመው ተግዳሮት ከመሠረተ ልማት ጋር የሚያያዝ መሆኑን፣ በዚህ ወቅት ፀጥታ ራሱን የቻለ ችግር ከመሆኑ ውጪ የተሽከርካሪ አቅርቦቱና ዋጋው ሌላው የሚነሳ ጉዳይ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ በተለይ ለየብስ ትራንስፖርት ኢንቨስትመንት ያለው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑን፣ ኢንቨስትመንቱን እንዲስብ በማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ከሠሩና የግሉ ዘርፍ ደግሞ ከተሰማራበት አዋጭ ሥራ እንደሆነ፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አጋር ድርጅቶች ይዞ በዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አቶ ሮባ አብራርተዋል፡፡

ድርጅቱ ባለፈው የበጀት ዓመት የገዛውን ያህል ተሽከርካሪዎች እኩሌታ ከተቻለም ከዚያም በላይ ለመግዛት ማቀዱን፣ ተቋሙ ግዥ በኤልሲ የሚያከናውን በመሆኑ መንግሥት የሚያመቻቸው የተለየ የኤልሲ ተጠቃሚነት ዕድል ካለ የሚጠቀም መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 185 የጭነት ተሽከርካሪዎችን በ14.5 ሚሊዮን ዶላር (760.5 ሚሊዮን ብር) ግዥ ለመፈጸም የምካብ ጄኔራል ኢምፖርት ኤክስፖርት (YEMKAB General Import Export PLC) እና ከቻይናው ሲኖትራክ ኢንተርናሽል (SINOTRUK INTERNATIONAL CO., LTD) መስማማቱ ይታወሳል፡፡

ሁለቱ ድርጅቶች ከ350 እስከ 400 ኩንታል የመጫን አቅም ያለው አንድ ተሽከርካሪ በ78,755 ዶላር ለማቅረብ መስማማታቸውን ከዚህ ቀደም መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በአራት ወራት ውስጥ 185 የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለድርጅቱ እንደሚያስረክቡ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ደንቡ ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡

የጭነት ተሽከርካሪዎች ኢኮኖሚውን የሚሸከሙ፣ ታክስና ቀረጥ የሚቀረጥባቸውን ዕቃዎች ስለሚያጓጉዙ ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር መግባት አለባቸው የሚል ሐሳብ እንዳለቸው አቶ ሮባ አስረድተዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ይህ ብቻም ሳይሆን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ልክ በመጋዘን ላይ ኢንቨስት አልተደረገም፡፡ በተለይም ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች የሚቀመጡበት ዘመናዊ መጋዘን ሊኖር እንደሚገባና ዘርፉ በቢዝነስ ዕይታ ቢወሰድ አዋጭ ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ ሮባ፣ ልዩ የሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች በሚፈለገው ልክ ተገዝተው ወደ ሥራ ቢገቡ የሚያሠራ ዘርፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ድርጅቱ በተያዘው የበጀት ዓመት ከዓምና ገቢና ወጪ ጭነቶች አገልግሎት አፈጻጸሙ የአምስት በመቶ ጭማሪ ያለው አገልግሎት ለማስተናገድ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የአገሪቱ ወጪና ገቢ ጭነት በተያዘው ዓመት ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ እያደገ ከመጣው ከሆልቲካልቸር ምርቶች ኤክስፖርት በተጨማሪ አገሪቱ የስንዴ ምርት ኤክስፖርት ታደርጋለች የሚለውም በዚህ ዓመት ዕቅድ ውስጥ ታሳቢ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ጭነት ከሚገመተውም በላይ ሊጨምር እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ ያንን ታሳቢ በማድረግ ድርጅቱ ካለፈው ዓመት በትንሹ የአምስት በመቶ ተጨማሪ ዕቅድ ይዞ መቅረቡ ተመላክቷል፡፡ ይህም  ዘጠኝ ሚሊዮን ቶን የሚሆን ገቢና ወጪ ጭነት በሁሉም የድርጅቱ አገልግሎት ዓይነቶች እንደሚቀርብ አቶ ሮባ ተናግረዋል፡፡

በ2014 የበጀት ዓመት ከ7.2 ሚሊዮን ቶን በላይ ገቢና ወጪ ጭነት በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መጓጓዙ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ከገቢ አኳያ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 5.6 ቢሊዮን ብር ማግኘቱ መነገሩ አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች