Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ነባር ‹‹ላዳ›› ታክሲዎችን መሸጥና መለወጥን ጨምሮ ለሌላ ማስተላለፍ ተከለከለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ ‹‹ላዳ ታክሲ›› ተብለው የሚታወቁትን ተሽከርካሪዎችን መሸጥ፣ መለወጥ ወይም ለሌላ ማስተላለፍ አገልግሎቶች መስጠት ማቆሙን አስታወቀ፡፡

የከተማዋ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ትናንት ማክሰኞ፣ መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ፣ ከትራንስፖርት ቢሮ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት እነዚህን አገልግሎቶች ለላዳ ታክሲዎች መስጠት ማቆሙን አስታውቋል፡፡ እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ ላዳዎችን መሸጥ፣ መለወጥና ለሌላ ማስተላለፍ የተከለከለው ረዥም የአገልግሎት ዘመን ያላቸው እነዚህ ታክሲዎችን በአዲስ የመተካት ሥራ በመጀመሩ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይርጋዓለም ብርሃኔ፣ ቢሯቸው ይህንን አቅጣጫ ያስተላለፈው ከገንዘብ ሚኒስቴር በመጣ ጥያቄ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት የላዳ ታክሲዎች ከፍተኛ የነዳጅና የመለዋወጫ ወጪዎችን የሚያስከትሉ መሆኑን የጠቀሰው የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ማስታወቂያ አስረድቷል፡፡ ማስታወቂያው አክሎም የገንዘብ ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም. ያወጣው መመርያ፣ የተደራጁ ማኅበራት ከቀረጥ ነፃ የሚያስገባቸው አዳዲስ ተሽከርካሪዎች እነዚህ ታክሲዎችን መተካት እንዲችሉ መፍቀዱን አስታውሷል፡፡

ባለሥልጣኑ በማስታወቂያው፣ ‹‹በአዲስ የሚተኩ ነባር ላዳዎችን መሸጥና መለወጥ ወይም ለሌላ ማስተላለፍ የማይቻል መሆኑን እናሳውቃለን፤›› ብሏል

የገንዘብ ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም. ያወጣው መመርያ ያገለገሉ ላዳ ታክሲዎችን የሚተኩ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በተበታተነ ሁኔታ ወይም በከፊል በተበታተነ ሁኔታ ወደ አገር በገቡ የተሽከርካሪ አካላት የተመረቱ አዲስ ተሽከርካሪዎችን ከማንኛቸውም ቀረጥና ታክስ ነፃ መግዛት እንደሚቻል ደንግጓል፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ውሳኔ ያወጣው ታክሲዎቹ ለዓመታት ያገለገሉ በመሆናቸው ለመለዋወጫና ለነዳጅ የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እያስከተለ በመሆኑን እንደሆነ በመመርያው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ይህንን መብት የሚያገኙት የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ማኅበራት ብቻ ሲሆኑ፣ ተጠቃሚ የሚሆኑትም በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የተገጣጠሙ ተሽከርካሪዎችን ሲገዙ መሆኑን መመርያው አስቀምጧል፡፡

እነዚህን ታክሲዎች ለመተካት የመገጣጠሙን ሥራ የሚሠሩ አምራች ፋብሪካዎች፣ የተሽከርካሪዎቹን አካላት የሚያስገቡት ተገቢውን ቀረጥና ታክስ አስቀድመው ከፍለው ነው፡፡ ይሁንና ተሽከርካሪዎቹን ገጣጥመው ለመብቱ ተጠቃሚዎች ማስተላለፋቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባቀረቡ በ30 ቀናት ውስጥ የከፈሉት ቀረጥና ታክስ ተመላሽ እንደሚደረግ መመርያው አስቀምጧል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲዎች ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ገላው፣ የከተማ አስተዳደሩ ላዳ ታክሲዎችን መሸጥ፣ ለመወጥና ስም ማዘወር ሲከለክል ማኅበራቸው ገለጻ እንዳልተደረገለት ጠቅሰው ቅሬታ አሰምተዋል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ ይህ ትዕዛዝ መተላለፉ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ ታክሲያቸውን ከቀየሩ በኋላ፣ ይህንኑ ታክሲ ለሌላ ግለሰብ ሸጠው ግለሰቡ በድጋሚ ከቀረጥ ነፃ መብት ተጠቃሚ እንዳይሆን ቁጥጥር ለማድረግ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይሁንና ትዕዛዙ ባለንብረቶች ታክሲያቸውን ሸጠው ገንዘብ ማግኘት ቢፈልጉ ይህንኑ መብታቸውን የሚከለክል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ሲያስረዱ፣ ‹‹የታመመ ሰው መኪናውን ሸጦ መታከም ቢፈልግ እንዴት ሊሆን ነው?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ሪፖርተር በክልከላው ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች አልተሳኩም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች