በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣ ሁሉም ታክሶች ተነስተው ወደ አገር ውስጥ በአነስተኛ ታክስ እንዲገቡ መወሰኑ ድጋፍ ይቸረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ የታየው ሥርዓተ አልበኝነት የተሞላው የዋጋ ጭማሪ፣ በእንዲህ ዓይነትና በሌሎችም ውሳኔዎች ሥርዓት እንዲይዝ ሲደረግ መንግሥትን ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት በሌሎች ምርቶችና ዘርፎች የሚስተዋለውን አልጠግብ ባይነት በተጠና መንገድ ፈር እንዲያሲዝ፣ በመስኩ የካበተ ልምድ ያላቸውን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምክረ ሐሳብ ማዳመጥም ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ የምርቶችን አቅርቦት ሰንሰለት ከደላሎች ጣልቃ ገብነት ለማላቀቅ፣ በጥቁር ገበያ ዘዋሪዎች አማካይነት ፈር የሳተውን ግብይት ለማስተካከልና የዜጎችን የመግዛት አቅም ከመጠን በላይ እየፈተነ ያለውን የኑሮ ውድነት መልክ ለማስያዝ ባለሙያዎች የሚያቀርቡትን ምክር መንግሥት በአንክሮ ይስማ፡፡ በስመ ነፃ ገበያ መረን የተለቀቀውን የግብይት ሥርዓት መልክ ማስያዝ የሚቻለው፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በሚስተዋለው ሥርዓተ አልበኝነት ምክንያት፣ ኑሮው ከዕለት ወደ ዕለት ቁልቁል እየወረደ ነው፡፡ ምክንያታዊ ባልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች ምክንያት የኑሮ ውድነቱን መቋቋም እያቃተው ነው፡፡ መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን ከማስተካከል ጎን ለጎን እንደ ሰደድ እሳት የሚግለበለበውን የዋጋ ግሽበት ማቃለል፣ ፍትሐዊ የታክስ ሥርዓት በማስፈን የሠራተኛውን ሕዝብ ጫና ማቅለል፣ ግብር የሚሰውሩና የሚያጭበረብሩትን ሕግ ፊት ማቅረብ፣ ምርቶችን የሚደብቁና የሚያከማቹትን በሕግ መፋረድ፣ ምርቶች በብዛት እንዲመረቱና ከደላላ ጣልቃ ገብነት ለሸማቹ እንዲቀርቡ ማድረግ፣ ለወጣቶች ሥራ በብዛት የሚፈጠርባቸውን አማራጮች ማመቻቸትና የመሳሰሉት ዕርምጃዎች በጥናት ላይ ተመሥርተው እንዲወሰዱ ማድረግ ይገባል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ጤናማና ውጤታማ መሆን የሚችለው ተጓዳኝ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል አቅም ሲገነባ ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ የጥቂቶች መፈንጫ የሆነውና ሸማቾች ለአስከፊ የኑሮ ውድነት የተዳረጉት፣ በምርቶች እጥረትና በፍላጎት ማደግ ብቻ ነው የሚለው ክርክር ውኃ አይቋጥርም፡፡ የምርቶች እጥረት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ያሉትን ምርቶች በአግባቡ ሸማቾች ዘንድ ማድረስ አልተቻለም፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብ በነፃነት ሥራውን የማከናወን መብቱ መጠበቅ አለበት፡፡ ይህ ማለት ግን አጋጣሚዎችን ለራስ ጥቅም ለማድረግ ሲባል ብቻ ኢኮኖሚውን የሚያንኮታኩት ድርጊት ውስጥ መገኘት የለበትም፡፡ መንግሥት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የቀረበለትን ምክረ ሐሳብ ቢያዳምጥ ኖሮ፣ የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሆንም ነበር፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ በንግድ ምክር ቤቶቹም ሆነ በዘርፍ ማኅበራቱ አማካይነት ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር፣ ሕገወጥ ተዋንያን ከግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲወጡ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ መንግሥትም ባለሥልጣናቱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በፍፁም ሕገወጥ የንግድ ተዋንያን እንዳይሆኑ ማድረግ አለበት፡፡ ከማናቸውም የምግብና ምግብ ነክ ካልሆኑ ምርቶች ሥርጭትና ችርቻሮዎች ውስጥ እንዳይገኙ ያድርግ፡፡ ተባባሪ ሆነው የግብይት ሥርዓቱን የሚያተራምሱ ደላሎችንም አደብ ያስገዛ፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ጤናማ ፉክክር እያደረገ ሥራውን እንዲያከናውን የትርፍ ህዳግ ደንብ ያውጣ፡፡ ምርት አንቀው የሚይዙትንም ሆነ የሚሰውሩትን በሕግ ያስቀጣ፡፡ ሸማቹ ሕዝብ የመግዛት አቅሙ የሚዳከመው ምርቶችና አገልግሎቶች በሕገወጦች ሲታገቱ ነው፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለት ነፃ ሆኖ ገበያው መረጋጋት የሚችለው ምርቶች በገፍ ሲቀርቡ ነው፡፡
መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን በተጠና መንገድ በባለሙያዎች ድጋፍ በሚገባ መፈተሽ ከቻለ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ነገሮች ይስተካከላሉ፡፡ ለበርካታ ዓመታት የግብይት ሥርዓቱን አንቀው የያዙት ጥቂቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ጥቂቶች ደግሞ ከመንግሥት ሹማምንትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መነገድ ስለለመዱ የሚነካቸው የለም፡፡ እዚህ አካባቢ በሚገባ መፈተሽና ማስተካከል ከተቻለ፣ ሌላው ዕዳው ገብስ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በስንዴ ምርት ከራሷ አልፋ ኤክስፖርት እንደምታደርግ እየተነገረ ነው፡፡ በሌሎች ምርቶችም ወደ አገር ማስገባት ሳይሆን ወደ ውጭ መላክ እንደሚቻል እየተሰማ ነው፡፡ ይህ መልካም ዜና ተግባራዊ እንዲሆን ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግም እየተስተጋባ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ምኞት ተግባራዊ መሆን የሚችለው ግን ተቋማዊ ጥንካሬ ሲኖር ነው፡፡ ተቋማዊ ጥንካሬ እንዲኖር በትምህርት፣ በልምድና በሥነ ምግባር የታነፁ አመራሮችና ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከሌብነትና ከዘራፊነት ጋር ስማቸው የማይነሳ ቅንና አገር ወዳዶች ሞልተዋል፡፡ እነዚህ ደግሞ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን አገር መገንባት የሚችሉ ናቸው፡፡ ለዚህም ሲባል ነው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መፈለግ ያለባቸው፡፡
ብቁና ጠንካራ አመራር ሲኖር ሌብነትና ሕገወጥነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ብዙኃኑ ሠራተኞች ከሚያገኙት ላይ በአግባቡ የገቢ ግብር እየገበሩ፣ ጥቂቶች ግብር በመሰወርና በማጭበርበር አገር የሚያደሙት ቁጥጥሩ ሲላላ ነው፡፡ የቁጥጥር መላላት ምክንያት ደግሞ አንድም ከብቃት አልባነት ሌላም ከጥቅም ተጋሪነት ስለሚመነጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጥቂቶች ያላግባብ እየበለፀጉባት ብዙኃኑ እያደር ቁልቁል የሚወርዱባት፣ ጠንካራና ብቁ አገር ወዳድ አመራሮችና ባለሙያዎች ጠፍተው አይደለም፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ ውስጥ የተሰገሰጉ ሌቦችና ዘራፊዎች ስለማይሰለቻቸው ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ከእነ ቤተሰቦቻቸውና የጥቅም ሸሪኮቻቸው ጋር ዘው ብለው ገብተው እጥረትና የዋጋ ጭማሪ የሚፈጥሩት፣ መንግሥታዊ ተቋማት ብቁና ጠንካራ ሆነው እንዳይገኙ የሚፈልጉ ሴረኞች በመብዛታቸው ነው፡፡ መንግሥት የግብይት ሥርዓቱንም ሆነ መንግሥታዊ መዋቅሮቹን ከእንዲህ ዓይነቶቹ ማፅዳት ፍላጎት ካለው፣ አሁንም ደግመን ደጋግመን እንላለን ለጠንካሮችና ለብቁዎች ዕድሉን ይስጥ፡፡ የመንግሥት ቁርጠኝነት ካለ ኢኮኖሚው በደላላ ከመመራት ነፃ ይወጣል፡፡ ምርቶች ያለ ምንም እንከን ሸማቹ ዘንድ በተመጣጣኝ ዋጋ ይደርሳሉ፡፡ ዜጎች ከሸማችነት አልፈው አምራች ለመሆን ጭምር ይደፋፈራሉ፡፡
በኢትዮጵያ እኩልነት የሰፈነበት ሥርዓት ለመመሥረት የሚያስችሉ በርካታ ሐሳቦች አሉ፡፡ እነዚህ ሐሳቦች ተብላልተው ውጤታማ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅ የሚያስችሉ ጥናቶችን ለማድረግ ይረዳሉ፡፡ ሥራዎች ሁሉ በጥናት ላይ እንዲመሠረቱ ደግሞ ብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ጥቂቶች የግብይት ሥርዓቱን በመቆጣጠር እንዳሻቸው የሚያደርጉት ለአገር የሚጠቅሙ ሰዎች ገለል ሲደረጉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሌላው ቢቀር ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት አሠርታት ከመጠን በላይ ተዘርፋለች፡፡ ጥቂቶች የአገሪቱን መሬት ወረው ተቀራምተዋል፡፡ ጥቂቶች የባንክ ብድሮችን በቁጥጥራቸው ሥር በማድረግ ያሻቸውን አድርገዋል፡፡ ጥቂቶች ከቀረጥ ነፃ ዕድሎችን በመጠቀም ቤተሰቦቻቸውንና የጥቅም ሸሪኮቻቸውን አበልፅገዋል፡፡ ጥቂቶች የግብይት ሥርዓቱን አንቀው በመያዝ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ተቆጣጥረዋል፣ ዋጋ ወስነዋል፣ ምርቶችን ደብቀው አከማችተው ከብረዋል፡፡ በተጨማሪም ጥራታቸው የተጓደለ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት ሀብት አከማችተዋል፡፡ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶችን ገበያው ውስጥ በማሠራጨት ብዙዎችን ለሕልፈተ ሕይወትና ለአካል ጉዳት ዳርገዋል፡፡ አሁን ደግሞ ኢኮኖሚው በጥቁር ገበያ የሚመራ ይመስል የውጭ ምንዛሪ ገበያውን እያጦዙት ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ መሆኑ ያብቃ!