Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየንግሥቲቱን ኅልፈት ተከትሎ ‹‹እንግሊዝ ይቅርታ ትጠይቅ›› የሚለው የአፍሪካውያን ጥሪ

የንግሥቲቱን ኅልፈት ተከትሎ ‹‹እንግሊዝ ይቅርታ ትጠይቅ›› የሚለው የአፍሪካውያን ጥሪ

ቀን:

የእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ሥርዓተ ቀብር ዘውዳዊው ቤተሰባቸው የቅርብ ዘመዶቻቸውና የተለያዩ አገሮች መሪዎች በተገኙበት መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በለንደን ከተማ በሚገኘው የዌስት ሚኒስትር አቤይ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡ አስቀድሞ በካቴድራሉ በተካሄደው ሥርዓተ ጸሎት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ርዕሳነ ብሔራትና የመንግሥታት መሪዎች የቀድሞ ፕሬዚዳንቶችና እንደራሴዎች መገኘታቸው የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ለንደን እንደደረሱ በሐዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ሐዘናቸውን መግለጻቸው በዚያው የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል፡፡

ቢቢሲ በዘገባው እንዳመለከተው የትናንት በስቲያው ሥርዓተ ቀብር ዊንስተን ቸርችል ከስድሳ ዓመት በፊት ሲሸኙ ከታየው ወዲህ የመጀመርያው ነው፡፡

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ከተገኙ የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች መካከል የታንዛኒያዋ ሱሉህ ሳሚያ ሐሰን፣ የኬንያው ዊልያም ሩቶ፣ የጋናው ናና አኩፎ አዶ፣ የደቡብ አፍሪካው ሲሪል ራማፎስና የሴኔጋሉ ማኪ ላል እንደሚገኙበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

- Advertisement -

በማኅበራዊ ሚዲያ ሲተላለፍ በቆየ አንድ ፎቶ እንደሚታየው ከአፍሪካ የተጓዙ ፕሬዚዳንቶች በሚኒባስ ተሽከርካሪ ተጭነው ወደ ሥርዓተ ቀብሩ አምርተዋል፡፡ ይህም ክስተት ምነው ማሰኘቱ፣ ልዩ ልዩ ትችቶችም በማኅበራዊው ሚዲያ ሲሠራጭ ታይቷል፡፡

የንግሥቲቱን ኅልፈት ተከትሎ ‹‹እንግሊዝ ይቅርታ ትጠይቅ›› የሚለው የአፍሪካውያን ጥሪ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የንግሥቲቱን አስክሬን የጫነው ሠረገላ
ፎቶ፡ ቢቢሲ

የንግሥቲቱ ኅልፈት ያስከተለው የይቅርታ ጥሪ

በደቡብ አፍሪካ ጆሐንስበርግ የሚገኝ አንድ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ የዳግማዊት ኤልሳቤጥን ዕረፍት ተከትሎ አድማጮቹን በስልክ አስተያየት እንዲሰጡ አቅራቢው ኤምጄ ሞጃሌፋ ጋብዟል፡፡

የ22 ዓመቱ ዲጄ ስለንግሥቲቱና ስለእንግሊዝ ኢምፓየር ትሩፋት ወጣቶች ሐሳባቸውን እንዲያጋሩ በጠየቀው መሠረት የመጀመርያው ደዋይ፣ ‹‹በእንግሊዞችና [በንግሥቲቱ] ቅኝ ተገዛን፡፡ የዚያን ግንኙነት ባህሪ በፍጹም አልለወጡም›› ሲል ይናገራል፡፡ ሌላው ደዋይ ደግሞ ‹‹ሰዎቹ ሄደዋል፣ ያለፈው ደግሞ ያለፈ ነው፤›› ሲል አስተጋብቷል፡፡

የፕሮግራሙ አጋፋሪ ኤምጄ ሞጃሌፋ አዲሱ ንጉሥ ቻርልስ ሣልሳዊ ይቅርታ እንዲጠይቁ ፍላጎቱ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

‹‹ብዙ ሰዎች ንግሥቱቱ ይቅርታ አልጠየቁም እያሉ ነው፣ ያኔ ከእሳቸው የፈለጉት ይቅርታ እንዲጠይቁ ነበር፤›› ሲልም አክሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1961 ሪፐብሊክ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ፣ በዚያን ጊዜ ተፈጻሚ የሆነው የአፓርታይድ የዘር መለያየት ፖሊሲ ለዓመታት ሲተገበር አብዛኛውን ዓመት በመንበራቸው የነበሩት ንግሥት ኤልሳቤጥ ናቸው፡፡ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ወጣቶች ያ ታሪክ ዘመን የማይሽረው ጠባሳ እንደተወ ያምናሉ፡፡ አሳማሚውን ነገር ከአሁኑ ጋር እንዴት ማስታረቅ እንዳለባቸው እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል፡፡

ይህንኑ መሪር ስሜት ከአርቲስቶች መካከል ዞሎ ማዮንጎና አዲልሰን ዴ ኦሊቬራ ይጋሩታል፡፡ ‹‹የደቡብ አፍሪካን ታሪክ ስንመለከት ነገሩን ነጥለን ብቻ አንመለከትም፤›› የሚለው ዴ ኦሊቬራ፣ ‹‹አንዱ ነገር ወደ ሌላ ይመራልና›› ሲል ያክላል፡፡

‹‹ጠባሳዎቹን ማስወገድ አይቻልም፤ ጥያቄ የሚሆነው ግን እነዚህ ቁስሎች ፈውስ የሚያገኙት እንዴት ነው?›› ብሎ የተናገረው ማዮንጎ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱም አርቲስቶች አሁን የተፈጠረው አጋጣሚ ንጉሡ ቻርልስ ሣልሳዊ ከአፍሪካ ጋር አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር ዕድል ይሰጣቸዋል ይላሉ፡፡

‹‹ሁላችንም ፀለምተኞች አይደለንም›› የሚለው ዴ ኦሊቬራ፣ ዘውዳዊው ሥርዓትና ንጉሡ ለወደፊቱ ከአፍሪካ ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን ግንኙነት በተመለከተ ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባቸው፣ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ውይይት ማድረግ በጠረጴዛ ዙሪያ መመካከር እንደሚገባቸው እናስባለን ብሏል፡፡

ምን እንደሚጠይቁም አስከትለዋል፡፡ የተዘረፉት የአፍሪካ ቅርሶች የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ የማዕድን ሀብቶች በምሳሌነትም ትልቁ አልማዝ – የአፍሪካ ኮከብ በእንግሊዝ ንጉሣዊ ቤተሰብ እጅ የሚገኘውና የዘውዱ የጌጣጌጥ አካል የሆነው ወደ ነበረበት አገር እንዲመለስ መነጋገር ይገባል ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1963 ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ተላቅቃ ነፃነቷን ባወጀችው ኬንያም ተመሳሳይ አስተያየት መንፀባረቁን የቢቢስ ዘገባ ያሳያል፡፡

የንግሥቲቱ ዜና ዕረፍት በኬንያ ጋዜጦች የፊት ገጽ ሽፋን ቢሰጣቸውም፣ አገሪቱ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ጋር ስላላት ግንኙነት እንደገና ክርክር አስከትሏል፡፡

‹‹እንግሊዞች በአፍሪካ አገሮች፣ በአፍሪካ ባህል፣ በሀብታችንና በኅብረተሰባችን አደረጃጀት ላይ ለፈጸሙት ነገር በእርግጥ ወጥተው በአደባባይ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል፤›› ያለው የ30 ዓመት ዕድሜ ያለው ኔልሰን ንጃው ነው፡፡

የንጃውን አስተያየት እንደሚደግፍ ራሱን በመነቅነቅ የገለጸው የ29 ዓመቱ ሳሚ ሙስዮካ ‹‹አሁንም እንደተገዢዎች እንጂ እኩል እንዳልሆንን ይሰማናል፤›› ብሏል፡፡

ይህ የስሜት ነፀብራቅ ከአንድ ታሪካዊ ጉዳት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ንግሥት ኤልሳቤጥ በነገሡ ከጥቂት ወራት በኋላ የኬንያ የማኦ ማኦ የነፃነት እንቅስቃሴ በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ላይ ባነሳው አመፅ ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

የኬንያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው አኀዝ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የተገደሉት፣ የተሰቃዩት ወይም የተጎዱት 90 ሺሕ ሰዎች ናቸው ብሏል፡፡

ግፉን የተገነዘበው የእንግሊዝ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2013 ለአምስት ሺሕ አረጋውያን ኬንያውያን በቅኝ ግዛት አስተዳደር ጊዜ ለደረሰባቸው በደል 22.6 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል መስማማቱን ዘገባው ገልጿል፡፡  

ከወጣቶቹ በተቃራኒም የቀድሞ ቅኝ ገዢዋን እንግሊዝ በደስታ የሚያስቡ አረጋውያን አልጠፉም፡፡ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ መሆኑን የሚናገሩት ካሮሊን ሙሪጎ የንግሥቲቱ ሞት አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በሕይወቴ ሙሉ የማውቃቸው ናቸው፡፡ ጊዜያቸው ደርሶ ነው እንጂ ማረፋቸው በጣም ያሳዝናል፡፡ ለአዲሱ ንጉሥ ቻርለስ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...