Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የማሪ ስቶፕስ ኢትዮጵያ የሥነ ተዋልዶ አገልግሎትና የቤተሰብ ዕቅድ

በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተለይም በገጠራማ ቦታዎች በቂ የሆነ ግንዛቤ ባለመኖሩ የተነሳ እናቶች በወሊድ ምክንያት እየሞቱ ይገኛል፡፡ የእናቶችን ሞት ለመግታት፣ የቤተሰብ ዕቅድን ለመስፋፋት፣ መንግሥትም ሆነ የግል ተቋሞች እየሠሩ ቢሆንም ክፍተቱ ግን ሙሉ ለሙሉ ተቃሏል ማለት ይቸግራል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከሦስት አሠርታት በላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አሁንም በቤተሰብ ዕቅድና የሥነ ተዋልዶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አቶ አበበ ሽብሩ የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የድርጅቱ ሥራን አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እንዴት ተመሠረተ?

አቶ አበበ፡- ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከተመሠረተ ከ31 ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በእናቶች ወሊድ ወቅትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይም የእናቶችን ጤና ከመጠበቅ አኳያ እየሠራ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በወሊድ ወቅት የእናቶችንም ሞት ለመታደግ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት ግንዛቤዎችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ድርጅቱም መንግሥታዊ ከሆኑና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ አገልግሎቱንም ለመስጠት 20 የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከሎችን አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከተቋቋሙ የጤና መስጫ ማዕከሎች መካከል አራቱ የማዋለጃ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡ እነዚህም ሆስፒታሎች ላይ ዘመናዊ የሆኑ የማዋለጃ ግብዓቶችን በመጠቀም የእናቶችን ሞት መታደግ ተችሏል፡፡ በቀጣይም በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንደዚሁ ዓይነት የማዋለጃ  ሆስፒታሎችን ለመገንባት ተቋሙ ዕቅድ ወጥኗል፡፡ በቅርቡም 17 ተንቀሳቃሽ የሆኑ የሕክምና ባለሙያ ቡድኖችን በማዋቀር በተለያዩ ቦታዎች አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት አጠናቀናል፡፡ በእነዚህም የሕክምና ባለሙያዎች አማካይነት የሥነ ተዋልዶና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የምናደርግ ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በጤና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ከ150 በላይ የግል ተቋሞች ጋር በመተባበር ለእናቶች የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ የሆኑ ዕድሎችን እየፈጠርን ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡ በሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?

አቶ አበበ፡- እስካሁን በሥራችን ላይ የተለያዩ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ በተለይም ደግሞ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላትና አቅማችንን ለማሳደግ የግብዓት ችግር እያጋጠመን ይገኛል፡፡ በተለይ የለጋሽ ድርጅቶች ለተቋሙ የመለገስ ፍላጎታቸው እየቀነሰ በመጣ ቁጥር የተቋማችን አቅምም እየተዳከመ መምጣቱ ትልቅ ችግር ሆኖብናል፡፡ ነገር ግን ይህንን ችግር ለመፍታት ተቋሙ የራሱ የሆነ ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ ይህም የገቢ ማሰባሰቢያ በመጠቀም ተቋሙ ያሉበትን የግብዓትም ሆነ ሌሎች ችግሮችን በመፍታት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ ከዚህ በፊት የነበሩትን አሠራሮችን በመቀየርና ወጥ የሆነ አሠራሮችን በማምጣት ዘርፉን እያገዘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም የለጋሽ ድርጅቶችን እጅ በየጊዜው ከመጠበቅ እንድንቆጠብ ረድቶናል፡፡ በተለይም ደግሞ ከመንግሥት ጎን በመቆም የጤና ዘርፉ ያሉበትን ተግዳሮቶች ለመግታት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይኼ ከሆነም ዘርፉ ወደ ተሻለ ደረጃ ያድጋል፡፡

ሪፖርተር፡በኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ተቋማቱ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምን እየሠራ ይገኛል?

አቶ አበበ፡- እንዳልከው በኢትዮጵያ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት ተቋሙ በራሱ በኩል ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ተቋሙም ጥራቱን ያማከለ የሥነ ተዋልዶና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎቶችን ከመስጠት ውጪ ሴቶች ልጆች በዕድሜያቸው ልክ የሚመች መረጃ እንዲያገኙ እያመቻቸ ይገኛል፡፡ ከእናቶች ጤና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ የማኅበረሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ በተለይም በማኅበረሰቡ በኩል ያለው ንቃተ ህሊና አናሳና የተገደበ መሆኑ ችግሩን ሊያባብሰው ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋሙ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት በአገር አቀፍ ደረጃ በመንቀሳቀስ ማኅበረሰቡ በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖረው እያደረገ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡ክልሎች ላይ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረጋችሁ መሆኑን ተናግራችኋል፡፡ ምን ዓይነት ለውጥ አምጥታችኋል?

አቶ አበበ፡- እንደ እኔ በዘርፉ ላይ የተለያዩ ለውጦችን አምጥተናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት በጤና ዘርፍ ላይ ያስቀመጣቸውን ፖሊሲዎች በተለያዩ ክልሎች ተፈጻሚ በማድረግ ዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት ችለናል፡፡ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ የክልል ጤና ቢሮዎች ጋር ቅንጅት ፈጥረን እየሠራን ይገኛል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሁሉ ስንሠራ በመንግሥት የጤና ተቋም ላይ የአቅም ውስንነት በመኖሩ ሥራችን ላይ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ በተለይ የፋይናንስና የግብዓቶች ችግር በሚኖርበት ጊዜ በአብዛኛው ሥራችን ሊስተጓጎል ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ ችግሮች በመጋፈጥ ተቋማችን የመንግሥት የጤና ተቋሞችን እየደገፈ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡ከሌሎች ተቋሞች ጋር በቅንጅት እየሠራችሁ ትገኛላችሁ፡፡ ቅንጅት ፈጥራችሁ በመሥራታችሁ ምን ዓይነት ለውጥ አምጥታችኋል?

አቶ አበበ፡- በእርግጥ ድርጅቱ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ በጤና ሴክተሩ ላይም መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተቋሞች በራሳቸው መንገድ ብቻ ሠርተው ለውጥ ያመጣሉ ብሎ ማሰብ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ስለዚህ ተቋሞች ከሌሎች ተቋሞች ጋር ቅንጅት ፈጥረው እየሠሩ ይገኛል፡፡ ወደፊትም ይህንኑ አሠራር በመከተል ተግባራዊ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሴት ልጆች  የወር አበባ ካዩበት የመጀመርያ ጊዜ ጀምሮ እስከሚያቆሙበት ሒደት ውስጥ የሚያስፈልጋቸው የጤና አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት አጠናቀናል፡፡ ከእነዚህም አገልግሎቶች መካከል የጡት ካንሰር፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የመሀንነት ችግሮችን በማውጣት እንደየ ዕድሜያቸው ክልል በመለየት አገልግሎቱን የምንሰጥ ይሆናል፡፡ ይህንንም ሥራ ስንሠራ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር ቅንጅት ፈጥረን ይሆናል፡፡ ይህንንም አገልግሎት የምንሰጠው አብዛኛውን የገጠሪቱ ክፍሎች ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሲሆን አገልግሎትም በነፃ የምናከናውን ይሆናል፡፡ ይህንን አሠራር ከተከተልን በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ከመቀነስ ባለፈ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

አቶ አበበ፡- በቀጣይ ይህንን አገልግሎት በማስፋት በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ላይ ተደራሽ ለመሆኑ ሰፊ ዕቅድ ይዘናል፡፡ በተለይም የሥነ ተዋልዶ ፕሮግራም፣ የቤተሰብ ዕቅድና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች በገጠራማ ቦታዎች ላይ ብዙም አይታይም፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ተቋሙ አቅሙን በማሟጠጥ ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ድርጅቱም ሴቶችም ሆነ ቤተሰቦች የተሟላ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁነኛ የጤና ዋስትና ለመስጠት እንዲሁም ዘርፉ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ቁርጠኛ የሆነ አሠራር  ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ...