በሰይፈ ታደለ ኪዳኔ (ዶ/ር)
ከልጅነቴ ነፍስ ካወቅኩበት ከ1970ዎቹ ጊዜ ጀምሮ ስሰማ ያደግኩት እስካሁንም የሚሰማው በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በሱዳን የአንድ አኅጉር ልጆች ብሎም ከአንድ አብራክ የተገኙ ወንድማማቾችና እህትአማማቾች በትርጉም የለሽና በአረመኔያዊ የእርስ በርስ ግጭት እንደ ጠላት በመፈራረጅ ለዕልቂት ተዳርገዋል።
በተመሳሳይ ጊዜ በአፍሪካ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ በሴራሊዮን፣ በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በአንጎላና በማሊ የእርስ በርስ ጦርነት ይካሄድ ነበር። በተጨማሪም በፍልስጤም፣ በኢራቅ፣ በኢራን፣ በእስራኤል፣ በፓኪስታን፣ በአፍጋኒስታንና በካሽሚር የተደረጉ የጦርነት ድራማዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በዜናዎች ላይ አዕምሯችንን የያዙ ነበሩ። አሁንም አንዳንዶቹ ሰላም ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ ከጦርነት ክፉ አባዜ ወይም አዙሪት ለመውጣት ጥረት ያደርጋሉ፣ ወይም አልቻሉም።
በእኔ እምነት በየትኛውም መመዘኛ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ምክንያታዊነት የጎደለው የእርስ በርስ ግጭት ወይም ፍጥጫ የትኛውም ወገን እንደ ጀግንነት ሊወስደው አይችልም። ይልቁንም ጦርነት የኋላቀርነትና የአስተሳሰብ መቀንጨር ማሳያ ነው።
ለዚህም ሁሌም እኔን የሚያሳስበኝ ነገር ቢኖር አንዳንድ ወገኖች በ12ኛው ክፍለ ዘመን ወይም ከዚያ በፊት የነበሩትን ሥልጣኔና የባህል ትውፊት የግል አድርገው ሲከራከሩ እሰማለሁ። መከራከራቸው ባልከፋ ሆኖም እኔ የሚገባኝ ሥልጣኔና ባህል በሰብዓዊነት ማማ ላይ የሚያስቀምጥ እንጂ እንደ አውሬ የሚያናክስ አይደለም። በቂም ትርክት በሌላ ወገን ላይ የሚያነሳሳ መሆንም የለበትም።
ለዚህም ነው በማለዳ ስለአክሱምና ስለላሊበላ ሥልጣኔ እየፎከርክ ስትኩራራ፣ ቆይተህ ረፋዱ ላይ ጠብመንጃ ይዘህ የገዛ ወንድሞችህንና እህቶችህን ገድለህ መፎከር፡፡ የቱ ላይ ነው ሥልጣኔው? መግደልና መፎከር የከንቱ ከንቱነትና የኋላቀርነት መገለጫነቱን መረዳት እንዴት ያዳግታል?
ለማንኛውም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቅሬታ ሊፈታ የሚችለው በውይይትና በውይይት ብቻ ነው። እንደዚያ ማድረግ ካልተቻለም በአገር ውስጥ፣ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰፊው ተደራሽ በሆነው የሕግ የበላይነት መከራከር ወይም መደራደር ይቻላል። ሆኖም እርግጥ ነው እንደዚህ ያለ ባህል እንዳይዳብር ያለፉት አርባ ዓመታት አገዛዞች ሁሉን በር ዝግ በማድረጋቸው፣ በጠብመንጃ ብቻ እንድናስብ መሆናችን እጅግ የሚያሳዝን ነው። ለዚህ ተጠያቂ አንድ አካል ብቻ ስለማይሆን ጣት ከመቀሰር መቆጠብ አስፈላጊ ነው።
በአፍሪካ ውስጥ አብዛኛው ግጭቶች የሚደገፉት በክፉ ዓላማ ጠንሳሾች የውጭ ኃይሎችና በልሂቃን ጥምር ዝግጅት ነው። ይህም አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኃይሎች ከእንዲህ ዓይነት አረመኔያዊ ጦርነቶች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ለማግኘት በሚፈልጉ ቡድኖች እንደሆነ የታወቀ ነው።
ይሁን እንጂ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ያላቸው ልሂቃን የእነዚህን ግጭቶች እሳት በማባባስ የሚጫወቱት ሚና በእጅጉ ከፍተኛ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ከአገር ውስጥ ልሂቃን ድጋፍና ጥቅም ውጪ የሆኑ የውጭ ኃይሎች፣ ለጥቅማቸው ሲሉ የአገር ውስጥ ፖለቲካን መበዝበዝና ማቀጣጠል የሚችሉበት ዕድል ውስን ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በሱዳን በተደረጉ ጦርነቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በስደታት ከቀዬአቸው አፈናቅለዋል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ተገድለዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ በሥነ ልቦና ተጎድተዋል። እነዚህ በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የተካሄዱ ዘግናኝ ጦርነቶች ሁለት አዳዲስ አገሮች ማለትም ኤርትራና ደቡብ ሱዳን እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነዋል፡፡ እንዲሁም ሶማሊያ ወደ ትንንሽ የመንደር መንግሥታት እንድትከፋፈል አድርገዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ያለውን ውስብስብ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት ተጨባጭ ዕውቀትና ልምድ መሠረት ያደረገ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚቆራኝ እምነቴ ነው። እነዚህም የዓድዋ ድል መዘዝ፣ በውኃ ፖለቲካ፣ በተሳሳተ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምና በጂኦፖለቲካዊ ምክንያቶች ናቸው። ያለምንም ፍርኃትና ወገንተኝነት በምክንያታዊነት ምክንያቶቹን መተንተን አስፈላጊ ቢሆንም፣ ነገር ግን ካለው የጋዜጣው ውስን ቦታ የተነሳ ወሳኝ የሆኑትን የፖለቲካና የአስተዳደር ጉዳዮችን በመመርመር ላይ አተኩራለሁ።
በመጀመርያ ከብዙዎቹ አንደኛው ምክንያት የኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ጡዘት የሚጀምረው “እኛ” እና “እነሱ” የሚል ግልብ አመለካከትና የመንጋ አስተሳሰብ ነው። ይህን መሠረት አድርገን በሰሜኑ አገራችን አሁን ያለው ጦርነት ለምን እንደቀጠለ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ሴቶችና ሕፃናትን በጦርነት ቀጣና እያፈናቀለ እስከ መቼ እንደሚቀጥል መጠየቅ አስፈላጊ ነው። ጥያቄው ሰላምን ፈላጊነታችንን መግለጽና ማስረፅ የምንችለው እንዴት ነው? የአፍሪካ ቀንድ በውስጥ ግጭቶች በተለያዩ ዓይነት ሁሉን አቀፍ ጦርነቶች እየተናጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ሥልታዊ የሆነ አድሎአዊነትና ከታሪካዊ ጠላቶች የሚሰጠው ድጋፍ ተባብሶ ቀጥሏል። ይህንንም ሁኔታ ጣት ከመቀሰር ባለፈ እንዴት ሰላምን ማስፈን እንችላለን የሚለውን ለመመለስ፣ ብሎም ግንዛቤያችንን ለማስፋት የሚደረግ ጥረት አንዱ አካል ነው።
ሰላምን መፈለግ የጋራ ውድቀትን በጥልቀት መመርመርና የተሳሳተውን አመለካከት፣ ዕብሪተኝነት፣ ጎጠኝነት መመርመር አስፈላጊ ነው። ስለዚህም አንዱ ወይም ሁለቱም ወገኖች የሚዋጉት ረብ የሌለው ጦርነት መሆኑን ተገንዝበው ራሳቸውን እንዲገመግሙ፣ ሰብዓዊነት እንዲኖራቸውና ራሳቸውን እንዲጠይቁ በማሰብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ከወገንተኝነት በነፃ መንገድ ማንሳት እፈልጋለሁ። የጥያቄው ቅድመ ተከተል ምንም ዓይነት ምክንያት የለውም።
ለሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)
ከ1935 ዓ.ም. የመጀመርያው ቀዳማይ ወያነ እንቅስቃሴ ጀምሮ በሕወሓት የቀጠለው በኢትዮጵያ ውስጥ ጉልህ የሆነ የአመፅና የብጥብጥ ምንጭ ሆኖ፣ ከሁለቱም ወገኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። በዚህም የተነሳ ንፁኃን የትግራይ ወጣቶች ጥቂት የልሂቃን ቡድን አባላት በሥልጣን ላይ እንዲቆይ ለማድረግ፣ ኢፍትሐዊ በሆነ የበላይነት ስካር ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሆነው ቆይተዋል።
የሕወሓትን መሪዎች መጠየቅ የምፈልገው መቼና ምን ያህል ሰው ሲሞት ነው የሕዝብ በገፍ ማለቅና የእርስ በርስ ዕልቂት አሳዝኗችሁ ወደ ልቦናችሁ የምትመለሱት? መቼ ነው የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በውይይትና በሠለጠነ አግባብ መፍታት የምትለምዱት?
ከ1983 እስከ 2010 ዓ.ም. እንደ ገዥ ፓርቲና መንግሥት በቆያችሁበት ጊዜ፣ ትሰብኩ የነበረው የተጨቆኑና የተገለሉ ድምፆችን የጎሳና የአናሳ የጎሳዎች (Ethnic and Tribal Minorities) ተቆርቋሪ ወይም ሻምፒዮን እንደሆናችሁ ነበር። ይሁንና በአንፃሩ ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ የጎሳ አወቃቀር የነበራቸውን እንደ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ)፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል የመሳሰሉት የተቃዋሚ ቡድኖችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ተቃዋሚዎች ለማጥፋት ትንቀሳቀሱ ነበር። በተጨማሪም ከፀበኝነት ባህሪያችሁ የመነጨ ከኤርትራ ጋር የድንበር ግጭት ውስጥ አገሪቱን አስገባችሁ፣ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት አገሪቱን በጠላትነት አስፈረጃችሁ፣ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮችን አፈናቅላችኋል፣ በተጨማሪም በአጠቃላይ ተቃዋሚዎችን ማሳደድና ማጥፋት ተግባራችሁ ነበር።
ለምን ይሆን በሥልጣን ዘመናችሁ ለጦርነት ትዘጋጁ የነበረው? ይህንን ያህል መሣሪያ በኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብት ገዝታችሁ እንደ ጃርት እየቆፈራችሁ የቀረባችሁት ለምንድነው? ይህ ለኢትዮጵያ ሰላም እንደማይሆን ዕሙን ነው። አሊያም ለዘለዓለማዊ ሥልጣን ወይስ ለቅዠት ሪፐብሊክ? እኔ እንደ አንድ አፍቃሪ አፍሪካዊ (Pan Africanist) አመለካከት፣ የትግራይ ክፍለ ሀገር ሆነች ኢትዮጵያም ብሔር የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በአንፃራዊነት አታሟላም።
የመርሳት አባዜ ከሌለባችሁ በስተቀር ከ27 ዓመታት ጨቋኝ አገዛዝ በኋላ ከማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን የተባረራችሁት በገዛ ጓዶቻችሁ መሆኑን የምታውቁ ይመስለኛል። ታዲያ ለምን መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠላትነት ፈረጃችሁ የዕልቂት ድግሥ የደገሳችሁለት? ይህ ምን ዓይነት ዕብደት ነው?
ለገዥው ብልፅግና ፓርቲና ለኢትዮጵያ መንግሥት
የሕወሓትን ሕገ መንግሥት ተቀብሎ እያስፈጸሙና እየተከላከሉ የሕወሓትን መዋቅር መታገል ተቃርኖ አይደለምን? መንግሥት በስታሊናዊ የብሔርና ብሔረሰቦች ጥያቄ ላይ የተመሠረተውን ሕገ መንግሥት ለማስተካከል ዝግጁ የሚሆነው መቼ ነው? መንግሥት አገሪቱን በቋንቋና በጎሳ ላይ የተመሠረተውን የአስተዳደር መዋቅር የሚያርመው መቼና እንዴት ነው?
መንግሥት የጨቋኝና ተጨቋኝ የሚለውን የተሳሳቱ ትርክቶችን በማስተካከል፣ በመንግሥት ደረጃ ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚጀምረው መቼና እንዴት ነው? ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሕዝብ የጥቁር (Negroid) ዘር ሆኖ ሳለ የጎሳዎችንና የቋንቋን ልዩነት የዘር እንደሆነ ተደርጎ የሚቀርበውን መቼ ነው ለማቆም ጥረት የሚደረገው?
የትግራይን ሕዝብና ሕወሓትን አንድ አድርጎ ማቅረብ በእጅጉ ስህተት ነው። አንድ ሊሆኑ ስለማይችሉ፡፡ ሆኖም ከሕወሓት ጨቋኝ ባህሪ በመነሳት ሕዝቡን አስገድዶ በማሳመን ከጎኑ ሊያሠልፍ እንደሚችል ዕሙን ነው። ሆኖም መንግሥት እንደ መንግሥትነት ይህንን እውነታ ለመለወጥ ምን ዓይነት የሰላም አማራጮች አሉት?
የሰላሙ ሐሳቦችም ወጥነት ባለው መንገድ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መግለጽ የለባችሁም ወይ? መንግሥት ለትግራይ ክልል ሁሉንም አስፈላጊ አገልግሎቶች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የመስጠት ግዴታ አለበት። ለዚህ ምን ዓይነት ጥረቶችን ነው የሚያደርገው? ይህም የመንግሥት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕዝብም ጥያቄ መሆን አለበት።
ለትግራይ ክልል ሕዝብ
መቼ ነው የትግራይ ተወላጆች ሕወሓት በሌላው ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ የሚያደርሰውን ግፍ በቃ ብለው ስለሰላም የሚጠይቁት? መቼ ነው የትግራይ ተወላጆች የሰላም አየር እንዲተነፍስ ከሌሎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በሰላም ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ሕወሓትንም ሆነ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚጠይቁት? የትግራይ ክልል ሕዝብ የኢትዮጵያን ባህልና ወግ በሚመጥንና በሠለጠነ አግባብ ያለውን ሥጋት እንዲያሰማ ጫና እንዲያሳድር እማፀናለሁ።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ
ኢትዮጵያ “የሰው ልጅ መገኛ” እንዲሁም ከጥቂቶች አንደኛዋ የጥንት ሥልጣኔ ማዕከል ተብላ ትታወቃለች። ለአፍሪካና ለዓለም ብዙ የፍልስፍና ጥበብ ምንጭ በመሆን አስተዋጽኦ አድርጋለች። ኃያላን ቅኝ ገዥዎችን በማሸነፍ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ብሎም ለአፍሪካውያን ኩራት ነው። በእነዚህ ገድሎች ውስጥ የትግራይ ክልል ሕዝብ ያደረገው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ተገቢ ክብርና ዕውቅና ያሻዋል።
ስለሆነም የተቀረው የኢትዮጵያ ዜጎች የትግራይን ሕዝብ ከማግለል እንዲቆጠቡ ብሎም “እኛ” እና “እነሱ” ከሚል ዕኩይ አመለካከት እንዲወጡ አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ሁሉን ኢትዮጵያዊ አይወክልም። እኛ “እነሱን” ነን፣ “እነሱ” በውስጣችን ነው የሚኖሩት፡፡ ስለዚህ “እኛ” እና “እነሱ” የሚባል ነገር ሊኖር አይገባም። ስለዚህ መቼ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትግራይ ክልል ባሉት ወንድሞቹና እህቶቹ ላይ የሚያደርሰውን ግፍ በቃ ብሎ ከጦርነት አማራጭ ውጪ በሰላም የሚፈታበትን አግባብ መንግሥትን የሚጠይቀው?
ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቦች
እንደ አንድ አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ፣ ከእውነተኛ ተቆርቋሪነት የተነሳ እጃቸውን የዘረጉትን አደንቃለሁ። ይሁን እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ውስጥ የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ኢትዮጵያዊ መፍትሔን እንዲያበረታቱ ይመረጣል።
ለአፍሪካ ኅብረት
የአፍሪካ ኅብረት ሁለቱም ወገኖች ላይ ያለ አድልኦ እንዲሳተፉና አስፈላጊውን የሰላም አማራጮች የማቅረብና የማደራደር ሙሉ ሕጋዊና ሞራላዊ መብት አለው። ሆኖም የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት መቃወም ይጠበቅበታልና የሰላም መፍትሔው አፍሪካዊ መሆን አለበት። አለበለዚያ ታሪክ ይፈርዳል።
ለአፍሪካ ምሁራን
በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት ታጣቂዎች መካከል ያለውን ትግል የሚመለከቱ በርካታ ኅትመቶችን ለማየትና ለማጥናት ዕድሉን አግኝቻለሁ። አንዳንዶቹ በእኔ እምነት የፕሮፓጋንዳ ሰለባዎች ናቸው። አንዳንድ የሁኔታው መሠረታዊ ዕውቀት የሌላቸው ምሁራን በፍልስጤምና በእስራኤል ወይም በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ያለውን ዓይነት ግጭት አስመስለው አቅርበዋል። ስለሆነም ነባራዊውን ሁኔታ ለመረዳት ጥልቅ ጥናትና ምርምር ማካሄድ የትኛውንም ወገን ሳይደግፉ ገለልተኛ አመለካከት እንዲይዙ እመክራለሁ፣ ተመራጭም ነው።
ምክንያቱም ዛሬ በውሸት መነሻነት የምንጽፈው ማንኛውም አስተያየት ለአፍሪካ አንድነት፣ ሰላምና ልማት በረዥም ጊዜ ውስጥ መጥፎ አርዓያ በመሆን እኛኑ ይጎዳናልና።
የመፍትሔ ሐሳብ
ይህ የእርስ በርስ ግጭት በጦርነትም ሆነ በሰላማዊ ድርድር ቢፈታም ዘላቂያዊ ዋስትና ሊሆን አይችልም። ዘላቂያዊ ሰላማዊ ዋስትና በሕዝቦች መካከል የሚደረግ መተማመን፣ መግባባትና ለላቀ ዓላማ በጋራ መቆም ይጠይቃል። ስለሆነም ከዚህ በታች ያሉት ሁለት ዋና ዋና ሐሳቦች መንግሥትም ሆነ አማፂያኑ ቢገነዘቡት መልካም የሰላም አማራጭ ያመጣል ብዬ አምናለሁ።
አንደኛ “የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያውያን” በሚል ጽንሰ ሐሳብ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጣ የአዋቂዎችና የሽማግሌዎች አገር አቀፍ ተግባራዊ ኮሚቴ በማዋቀር፣ በጦርነት የተጎዳውን ብሎም ጦርነት የሚካሄድበትን አካባቢ ያለውን ሕዝብ በማናገር ሰላም የሚሰፍንበት መንገድ መቀየስ ይሆናል።
ሁለተኛ ሰላም እንዲሰፍን አስተዳደራዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በሕዝብ ፈቃድ ይሉኝታ ማግኘት አስፈላጊ ነው። ስለሆነም በሀቀኝነትና ያለ ምንም ወገንተኝነት አስተዳደራዊ ድንበሮችን በሕዝብ ፍላጎትና በሳይንሳዊ ዘዴ በመታገዝ መፍታት አስፈላጊ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ክምችት ከአካባቢው ማስወገድ በሕዝብ የሚሠራ ተግባር ሊሆን ይገባል።
ማስታወሻ ይህ ጽንሰ ሐሳብ አሁን ካለው አገር አቀፍ የዕርቅና የሰላም ኮሚሽን የሚገናኝ ሳይሆን፣ ውስን ኃላፊነት ኖሮት የጦርነት አዝማሚያዎችን የሚቀለብስና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ሆኖ ቢታይ መልካም ነው። ሆኖም ድምር ውጤቱ የአገር አቀፍ የዕርቅና የሰላም ኮሚሽን የሚረዳ ይሆናል።
በመጨረሻም ሁለቱም ወገኖች የተሳሳተውን አመለካከት፣ ዕብሪተኝነት፣ ጎጠኝነት (Ego) ወደ ጎን በመተው የሠለጠነ መፍትሔ እንዲፈልጉ አጥብቄ እማፀናለሁ። በዚህም የኢትዮጵያ የግጭት ዘመን ያበቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲሱ ዓመት የሰላም አየር የምንተነፍስበት እንዲሆን ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እመኛለሁ። ይህንን ትርጉም የለሽና አረመኔያዊ ጦርነት ከኋላችን ትተንና አገራችን ተረጋግታ በሰላምና ብልፅግናን እንደምትቀጥል ተስፋዬ ሙሉ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የፓን አፍሪካዊ አስተሳሰብና ውይይት ተቋም (አይ-ፒ-ኤ-ቲ-ሲ) ከፍተኛ የምርምር ባልደረባና የአፍሪካ ድምፅ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡