Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራና አፋር ክልሎች በተፈጸሙ ወንጀሎች በተጠረጠሩ የሕወሓት አመራሮች ላይ ክስ ሊመሠረት ነው

በአማራና አፋር ክልሎች በተፈጸሙ ወንጀሎች በተጠረጠሩ የሕወሓት አመራሮች ላይ ክስ ሊመሠረት ነው

ቀን:

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአማራና በአፋር ክልሎች ተፈጽመዋል በተባሉ የጦር ወንጀልና በሰብዕና ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠርጣሪ የሆኑ የሕወሓት አመራሮች ላይ፣ በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ክስ እንደሚመሠርት ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሮች ግብረ ኃይል በሥሩ ካሉት አራት ኮሚቴዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የምርመራና ክስ ኮሚቴ ባጠናቀረው የመጀመርያ ምዕራፍ፣ የመጀመርያ የምርመራ ሪፖርት ላይ የሚመሠረተው የክስ ሒደት፣ የማስረጃ ምዘና እየተካሄደበት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ሊመሠርትባቸው ያሰባቸውን ግለሰቦች ብዛትና ስም ዝርዝር ይፋ አላደረገም፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ፣ በክልሎቹ የተፈጸሙት ወንጀሎች “እንደ ድርጅት” እየተመሩ የተፈጸሙ በመሆናቸው፣ ክሱ ትኩረት የሚያደርገው የሕወሓት ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች ላይ እንደሚሆን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሚኒስቴሩ ምርመራው በሒደት ላይ እያለ በተቋረጠውና የ124 ሰዎች ሕይወት ባለፈበት በአክሱም የተፈጸመ ወንጀልን በተመለከተ፣ በታኅሳስ ወር የክስ ሒደት ለመመሥረት ዕቅድ ይዟል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት አባላት ኅዳር 2013 ዓ.ም. እንደፈጸሙት በተገለጸው የአክሱም ግድያ ፍትሕ ሚኒስቴርና የፌዴራል ፖሊስ ለሦስት ወራት ምርመራ ሲያደርጉበት የነበረ ሲሆን፣ በሰኔ 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ ሳይጠናቀቅ መቋረጡ አይዘነጋም፡፡

አሁን የምርመራ ሒደቱ በሚኒስቴሮች ግብረ ኃይል ሥር ባለው የምርመራና የክስ ኮሚቴ የተያዘ ሲሆን፣ ኮሚቴው ሁኔታዎች ተመቻችተው ምርመራው እስከሚጠናቀቅ ባሉት መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ለክስ እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ይፋ ተደረገው የሚኒስቴሮች ግብረ ኃይል ባለ 46 ገጽ የምርመራ ሪፖርት ትኩረት ያደረገው፣ የሕወሓት አመራሮችና ታጣቂዎች በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸሟቸው ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ነው፡፡

በአጠቃላይ 158 አባላትን የያዙ የምርመራ ቡድኖች በአማራና በአፋር ክልሎች ዘጠኝ ያህል አካባቢዎች ተሰማርተው፣ ከአሥር ሺሕ በላይ ምስክሮችን እንዳናገሩ፣ 3‚087 የጽሑፍ ሰነድ፣ 2‚599 የቪዲዮና ፎቶግራፍ ማስረጃዎችን እንደሰነዱ ተገልጿል፡፡ የተሰበሰቡት መረጃዎችም ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች 2‚831 ሰዎች ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን፣ 2‚212 ሰዎች አስገድዶ መድፈርና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች እንደተፈጸመባቸው፣ እንዲሁም 1‚315 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ማካተታቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

አብዛኞቹ ግድያዎች በሕወሓት ኃይሎች መፈጸማቸውን ያመላከተው ሪፖርቱ፣ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በ“ኦነግ ሸኔ” የተፈጸሙ ግድያዎች መኖራቸውን አካቷል፡፡

ግድያዎቹ በእሩምታ ተኩስ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ አካል በመቆራረጥና በሌሎች መንገዶች የተፈጸሙ መሆናቸውን ረቡዕ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ሪፖርቱ ይፋ በተደረገበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት አቶ ፈቃዱ፣ የብልፅግና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም የፋኖ፣ የሚሊሻ፣ የልዩ ኃይል፣ የወረዳና የቀበሌ አመራር ቤተሰቦች ናቸው የተባሉ ሰዎች እየተለዩ መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹በጦርነቱ የተሳተፉ የሕወሓት አባላት በተናጠል የፈጸሙት ሳይሆን አመራሩ የመራው ግድያ እንደነበር መናገር ይቻላል፤›› በማለትም የተደረሰበትን ድምዳሜ አስረድተዋል፡፡ በጦርነት ላይ የተማረኩ የሕወሓት ታጣቂዎች አመራሮቻቸው በሰጧቸው ሥልጠና “ለበቀል” አዘጋጅተው እንዳሰማሯቸው መናገራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በሕወሓት ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ አስገድዶ መድፈርና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶችም፣ ‹‹የማኅበረሰቡ እሴት ለመጉዳት ታስበው የተፈጸሙ›› እንደሆኑ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርቱ ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ግለሰቦች የተደፈሩት ዕድሜና ማኅበራዊ ሁኔታን ባለየ መንገድ እንደሆነ ማሳየቱን ምሳሌ አድርገው አቅርበውታል፡፡

በክልሎቹ የተዘረፉና የወደሙ መሠረተ ልማቶችና ንብረቶችን በተመለከተም፣ ‹‹ለንብረት ማውደምና መዝረፍ የሀብት ማሰባሰብ ግብረ ኃይል (Resources Mobilization Taskforce) ተቋቁሞ በክልሉ ንግድ ቢሮ የሚመራና አፈጻጸሙ የሚገመገም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ደኤታው አክለውም የንብረት ዘረፋው ‹‹በሕወሓት አመራር የሚመራው እስከ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ድረስ ሪፖርት የሚደረግበት ነው፤›› የሚል ክስ አቅርበዋል፡፡

በምርመራው የተገኙ መረጃዎች ተዳምረውም የሕወሓት ኃይሎች በአማራና በአፋር ክልሎች የጦር ወንጀልና ሰብዕና ላይ የተፈጸመ ወንጀል ፈጽመዋል የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚያስችል በቂ ምክንያት መስጠታቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው የምርመራ ኮሚቴው ቀጣይ ዕርምጃው ማስረጃዎቹን አጠናቅሮ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ክሶቹን ማደራጀትና ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሆነ፣ በሪፖርቱ ማጠናቀቂያ ላይ ተመልክቷል፡፡

ኮሚቴው ይህንን ሥራ እያጠናቀቀ መሆኑን የተናገሩት አቶ ፈቃዱ፣ የተፈጸሙት ወንጀሎች በአገሪቱ ሕግና ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ልማዳዊ አሠራሮች፣ የጦር ወንጀልና ሰብዕና ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊባሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ክሱ ሲመሠረት፣ ‹‹ሒደቱን ከሩቅ ሆነው የሥልጠና ካሪኩለማቸው ውስጥ አስገብተው ሲሠሩ የነበሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ በአካል በየቦታው የነበሩና እየተንቀሳቀሱ ሲመሩ የነበሩ ባለሙያዎችና በግምባር የነበሩ አመራሮችን›› እንደሚመለከት ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል፡፡ የእነዚህ አመራሮች ማንነት ከምርኮኞች በተገኙ ምስክርነቶችና ሌሎች መረጃዎች እንደተለየም አክለዋል፡፡

አቶ ፈቃዱ፣ ‹‹ክስ የሚመሠረተው እያንዳንዱ ይህንን ድርጊት ሲፈጽም የነበረ ታጣቂ ላይ ሊሆን አይችልም፡፡ አብዛኛው የተማገደበትና ያልተመለሰበት ሁኔታ ነው ያለው፤›› በማለት ክሱ አመራሮች ላይ እንደሚያተኩር አስረድተዋል፡፡

ይሁንና ክስ ይመሠረትባቸዋል የተባሉ የሕወሓት አመራሮች መያዝና አለመያዝ የሚወሰነው ጦርነቱ የሚጠናቀቅበት መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ዘመቻ ውስጥ የገባው፣ ‹‹ሕግ ለማስከበርና ወንጀለኞችን ለመያዝ›› መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታው፣ ‹‹በየትኛውም መንገድ ጦርነቱ ቢጠናቀቅ ትልልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ሰዎች ከመጠየቅ አይድኑም፤›› ብለዋል፡፡

ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ የመከላከያ ሠራዊት የጦር ፍርድ ቤት 60 ጉዳዮችን ተመልክቶ በ27 ክሶች ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ በ25 ክሶች የተከሰሱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ተብለው እስከ 25 ዓመታት የእስራት ፍርድ እንደተላለፈባቸውና አንድ ግለሰብ ዕድሜ ልክ እንደተፈረደበት ታውቋል፡፡ በሁለቱ ክሶች የቀረቡ ሰዎች ነፃ ሲባሉ 33 ጉዳዮች በሒደት ላይ መሆናቸውን ፍትሕ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...