Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ክልል ሕጋዊ ላልሆኑ ደላሎች ክፍያ የሚፈጽሙ ተገበያዮች ግብር እንዲከፍሉ መመርያ አስተላለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከግብር የሚገኝ ገቢን ለማስፋት ተከታታይ መመርያዎችንና ሰርኩላሮችን እያስተላለፈ የሚገኘው የአማራ ክልል፣ ሕጋዊ ባልሆኑ ደላሎች አገልግሎት አግኝተው ክፍያ የፈጸሙ ሻጭና ገዥ፣ ደላላው ሊከፍል ይገባ የነበረውን ግብር እንዲከፍሉ የሚያዝ መመርያ አስተላለፈ፡፡

ገዥና ሻጭ ከደላሎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ ጥብቅ ትዕዛዞችን በማስተላለፍ፣ ከደላሎች ግብር የሚሰበሰብበትን ሥርዓት የዘረጋው መመርያው፣ ገዥና ሻጭ የስመ ንብረት ዝውውርና የኪራይ ውል ሲፈጽሙ ያገናኛቸውን ደላላ የንግድ ፈቃድና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የምስክር ወረቀት እንዲያቀርቡም ያዛል፡፡

በክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ጸጋ ጥበቡ (ዶ/ር) ሰሞኑን ተፈርሞ ለዞንና ከተማ ገቢዎች መምርያዎች የተላለፈው መመርያ፣ ፈቃድ ያላቸው ደላሎች ከዚህ ቀደም ቁርጥ ግብር ሲከፍሉበት የነበረውን አሠራር የሚቀይር ነው፡፡ በአዲሱ መመርያ መሠረት በክልሉ የሚገኙ ደላሎች 30 በመቶ የገቢ ግብርና አሥር በመቶ ተርን ኦቨር ታክስ የሚከፍሉት፣ የተሳተፉበት የንብረት ዝውወር ወይም የኪራይ ውል እንደፀደቀ ነው፡፡

መመርያው የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭና ኪራይ ወይም የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ነው ተብሏል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም ደጀኔ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ይኼንን መመርያ ያወጣው፣ ብዛት ያላቸው ሰዎች ያለ ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ የድለላ ዘርፉን እየተቀላቀሉ መሆኑን፣ ይህም ገብይት ሥርዓቱ ‹‹ጤናማ እንዳይሆን›› በማድረጉ ነው፡፡

‹‹ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው ከሚንቀሳቀሱት ይልቅ ገበያው ውስጥ ያሉት ፈቃድ የሌላቸው ደላሎች ናቸው፤›› ያሉት አቶ ፍቅረማርያም፣ ቢሮው በዚህ መመርያው ገቢ ከመሰብሰብ ይልቅ የግብይት ሥርዓቱን ጤናማ ለማድረግ ዓላማ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፣ በብዛት እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ፈቃድ የሌላቸው ደላሎች ለማግኘት ሲባል ቢሮው ሥርዓቱን ገዥና ሻጭ ላይ ማጥበቅን ምርጫ አድርጓል፡፡ ‹‹ገዥና ሻጭ መሀል ስንቆም ነው ደላላውን ማግኘት የምንችለው፤›› ሲሉም ይኼንኑ አስረድተዋል፡፡

መመርያው በድለላ የተሰማሩ ሰዎች ላይ የጣለው ግዴታ ሕጋዊ ዕውቅና መያዝ፣ ገቢን ማሳወቅና ግብር መክፈል የሚሉ ናቸው፡፡ ሻጭና ገዥ በአንፃሩ ያሻሻጣቸውን ወይም ውሉ እንዲፈጸም የረዳቸውን ደላላ ማንነት የማሳወቅ፣ የድለላ ክፍያውን በባንክ ፈጽመው ለቢሮው የማቅረብ፣ እንዲሁም ውል ለመፈጸም ሲመጡ የደላላውን ሕጋዊ ፈቃድ አያይዞ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው፡፡

ገዥና ሻጭ የተገናኙት ሕጋዊ ፈቃድ በሌለው ደላላ ከሆነና ለዚህ አገልግሎት ክፍያ ከፈጸሙ፣ 30 በመቶ የገቢ ግብርና አሥር በመቶ ተርን ኦቨር ታክስ የመክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በአንፃሩ የአገልግሎት ክፍያውን መክፈል የሚጠበቅባቸው ያገናኛቸው ደላላ የንግድ ፈቃድና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የምስክር ወረቀት ሲያቀርብ ብቻ እንደሆነ በመመርያው ሠፍሯል፡፡

ያለ ደላላ ተገናኝተው ግብይት የፈጸሙ ግለሰቦች የገቢ ግብር የመክፈል ግዴታ የለባቸውም፡፡ ነገር ግን በደላላ ይኼንን ሳያሳውቁ ከተገኙ ደላላው ይከፍል የነበረውን የገቢ ግብርና ተርን ኦቨር ታክስ በእጥፍ እንደሚከፍሉ መመርያው ደንግጓል፡፡ በየደረጃው ያሉ የገቢ ተቋማት ግብይቱ ያለ ደላላ እንደተፈጸመ ተገልጾ፣ የቀረበ ውል ላይ በኢንተለጀንስና ክትትል ባለሙያዎች የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡

ምክትል የቢሮ ኃላፊው አቶ ፍቅረማርያም በደላላ አልተፈጸሙም የሚባሉ ግብይቶችን በተመለከተ፣ ‹‹ከሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሚሰወር ግብይት አይኖርም፣ በደላላ አልተፈጸመም ተብሎ የተጭበረበረ ግብይት መታወቁ አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት እስከ 50 በመቶ የሚደርሰውን የክልሉን ወጪ ለመሸፈን ዕቅድ የያዘው የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በቅርቡ ባስተላለፋቸው ትዕዛዞች፣ ሕንፃ አከራይተው ገቢ ከሚያገኙ የሃይማኖት ተቋማትና በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሠራተኞች የገቢ ግብር በክልሉ የገቢዎች ቢሮዎች እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በነሐሴ 2014 ዓ.ም. በክልሉ ለሽያጭ ከሚቀርብና ለሽያጭ ከሚጓጓዝ ጫት ላይ በኪሎ 30 ብር ቀረጥ እንዲሰበሰብ የሚያዝ መመርያ ወጥቷል፡፡

የክልሉ መንግሥት በ2014 በጀት ዓመት 26.9 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም ይዞት ከነበረው ዕቅድ 89.8 በመቶ ነው፡፡ በቀጣዩ በጀት ዓመት ይህንን ገቢ በ11.39 ቢሊዮን ብር ጨምሮ 38.37 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ከመደበኛና ከከተማ አገልግሎት ሊሰበሰብ የታቀው አጠቃላይ ገቢ 42.84 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም የክልሉ መንግሥት ለ2015 በጀት ዓመት ያፀደቀውን 95.32 ቢሊዮን ብር 44 በመቶ ይሸፍናል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች