Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማንዋል የተሰጡ መታወቂያዎችን ኦዲት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማንዋል የተሰጡ መታወቂያዎችን ኦዲት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየወረዳው የሚገኙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽሕፈት ቤቶች ከዲጂታል ምዝገባ ውጭ በማንዋል የሰጧቸውን መታወቂያዎች ኦዲት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኦዲት ሥራ በአሥራ አንዱም ክፍላተ ከከተሞች ባሉ የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ሕገወጥ የመታወቂያ ዕደላ የታየባቸው ክፍላ ከተሞችና ወረዳዎች ቅድሚያ እንደተሰጣቸው አስተዳደሩ ገልጿል፡፡ እስካሁን ባለው የኦዲት ሥራ የቤት ባለቤቶች ፈቃድ ሳይጠየቁና እነሱም ሳይፈቅዱ በቤት ቁጥራቸው መታወቂያዎች፣ ተመዝግበውና ታድለው መገኘታቸውን፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. መጀመርያ አንስቶ የመታወቂያ አገልግሎትን አቁሟል፡፡ አገልግሎቱ የቆመበት ዋነኛ ምክንያት በአገሪቱና በከተማዋ ካለው የፀጥታ ሥጋት ጋር በተያያዘ መሆኑን ያስረዱት አቶ ጥራቱ፣ የከተማዋን ‹‹ፀጥታ የማደፍረስ›› ዓላማ ባላቸው ግለሰቦች ሳቢያ ባለፈው ዓመት መታወቂያ የማግኘት ፍላጎት ከፍተኛ ሆኖ መታየቱን ተናግረዋል፡፡ ሕገወጥ የመታወቂያ ዕደላውን ሲያከናውኑ የተገኙ የአስተዳደሩ ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አስታውሰዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የከተማዋ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መዋቅር የነዋሪነት መታወቂያ አገልግሎት የሚሰጠው፣ የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓትን በመጠቀምና ተዘጋጅቶ የሚቀመጥ መታወቂያ ላይ መረጃ ተጽፎ በሚሰጥበት የማንዋል አሠራር ነው፡፡ የማንዋል ሥርዓቱ የተዘረጋው የዲጂታል ሥርዓት የሌለባቸው ወረዳዎች በመኖራቸው ሲሆን፣ ሲስተሙ ብዙውን ጊዜ መቆራረጥ ስለሚያጋጥመው ተገልጋዮች እንዳይጉላሉ በማሰብ መሆኑ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

አቶ ጥራቱ፣ ‹‹አሁን ባደረግነው ማጣራት ሆን ብለው ሥርዓቱ እንዲበላሽ የሚያደርጉ የወረዳ ባለሙያዎች እንዳሉ አረጋግጠናል፤›› ብለው፣ ባለሙያዎች ይህንን የሚያደርጉት በማንዋል የተሰጠ ሕገወጥ መታወቂያን በቀላሉ ማግኘት የማይቻል ስለሆነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህንንም ሲያስረዱ፣ ‹‹የዲጂታል ሥርዓቱ ኦዲት የሚደረግና ምን ዓይነት መታወቂያና ለማን እንደተሰጠ የሚያሳይ ነው፡፡ በማኑዋል ሲሆን ግን ፋይል ተከፍቶ መታወቂያው መቼ? ለማን? በየትኛው ቤት ቁጥር? እንደተሰጠ ማጣራት ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡ ይህም ብዙ ሒደቶች ያሉትና ጊዜ የሚፈጅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የማንዋል መታወቂያዎች በከተማዋ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ታትመው፣ በዓመቱ መጀመርያ ለክፍላተ ከተሞች ተሰጥቶ ወደ ወረዳዎች የሚተላለፍ ሲሆን፣ መታወቂያው ያለቀባቸው ወረዳዎች በድጋሚ ይወስዳሉ፡፡

‹‹መታወቂያ የመስጠት ሒደት እንዲቆም ካደረግን በኋላ በአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች የተሰጡ መታወቂያዎች ኦዲት እንዲደረጉ ነው ያደረግነው፣ በዚህም ብዙ ክፍተቶች አግኝተናል፤›› ብለዋል፡፡ ተመዝግበው የተላለፉት ማንዋል መታወቂያዎች ለማን እንደተሰጡ ያልታወቀበት ሁኔታ ማጋጠሙን፣ ባለሙያዎች ለሚያውቁትም ግለሰብም ሆነ በገንዘብ መታወቂያ ሲሰጡ እንደነበር መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

‹‹የኦዲት ሥራችንን ስናጠናቅቅ ለሕዝቡ ይፋ የምናደርግ ቢሆንም፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግለሰቦች ሳያውቁ በቤት ቁጥራቸው መታወቂያ እንደሚወጣ በናሙናነት አግኝተናል፤›› በማለት፣ ሥራው ሲጠናቀቅ ተጠያቂ የሚሆኑ ባለሙያዎችና አመራሮች እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለሕገወጥ መታወቂያ ዕደላ ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል ብሎ የሚያምነው በማንዋል የሚሰጥ የመታወቂያ አገልግሎትን ማቆም ነው፡፡ እስካሁን ባለው አሠራር የዲጂታል ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት ላይ ያልዋለበት አንዱ ምክንያት ሥርዓቱ መቆራረጥ የሚያጋጥመው በመሆኑ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለማየሁ እንደሚያስረዱት፣ የዲጂታል ሥርዓቱ የሚከናወነው ለከተማዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተዘረጋው ወረዳ ኔት (Woreda Net) የኢንተርኔት መስመር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ ተቋማት የዲጂታል አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱና የዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት የሚወሰደው የባዮሜትሪክ መረጃ ከፍ ያለ ኢንተርኔት ፍጥነት የሚፈልግ በመሆኑ፣ ሥርዓቱ በአግባቡ እንዳይሠራ ማድረጉን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲ በ2014 ዓ.ም. ብቻ እስከ ወረዳ ባሉት መዋቅሮቹ ሦስት ሚሊዮን ተገልጋዮችን ማስተናገዱን አቶ ዮናስ ገልጸዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል ለኤጀንሲው አገልግሎት ብቻ የሚውል የራሱ የኢንተርኔት መስመር (Virtual Private Network – VPN) በኢትዮ ቴሌኮም እየተዘረጋለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የዲጂታል መታወቂያ ሲሰጥበት የነበረው ሥርዓት በአዲስ ለመቀየር በዝግጅት ላይ ነው፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ አዲሱ ሥርዓት ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው መታወቂያ ለማደስም ሆነ ለማውጣት አስፈላጊውን ሰነድና ማስረጃ ልከው ቀጠሮ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ሥርዓቱ ነዋሪዎች የማንዋልም ሆነ የዲጂታል መታወቂያ ይዘው መንቀሳቀስ ሳይጠበቅባቸው፣ በሞባይላቸው ማንነታቸውን የሚገልጽ መረጃ እንዲይዙ የሚያደርግ የሞባይል መታወቂያንም (Mobile ID) እንደሚይዝ አስታውቀዋል፡፡

ይህንን ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የሰነድ ዝግጅት ተጠናቆ የግዥ ሒደት መጀመሩን አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ፣ ይህንን ሥርዓት የመዘርጋት ሥርዓት በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ክትትል የሚደረግበት መሆኑን ገልጸው፣ በስድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅዱ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ የቆመውን የመታወቂያ አገልግሎት በተመለከተ፣ ‹‹የፀጥታ ሥጋቱ በሚቀንስበት ወቅት ዕገዳዎች እያነሳን እንሄዳለን፤›› ያሉ ሲሆን በትምህርት፣ በጉዞ፣ ወይም ሌሎች ወሳኝ በሆኑ ምክንያቶች መታወቂያ ማደስና ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ግለሰቦች ማመልከቻ በማስገባት አገልግሎት የሚያገኙበት አሠራር መኖሩን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...