የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ለሚሰጠው የፈቃድ፣ የብቃት ማረጋገጫና ሌሎች አገልግሎቶች የሚያስከፍለውን ክፍያ በመከለስና አዳዲስ ተመኖችን በማውጣት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሊያስከፍል ነው።
ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጠውን አገልግሎት ማለትም የፈቃድ፣ የብቃት ማረጋጋጫ እንዲሁም ክትትልና ቁጥጥርን ጨምሮ ለሚሰጠው አገልግሎት የሚያስከፈለውን አዲስ የዋጋ ተመን የያዘ ረቂቅ መመርያ በማዘጋጀት ከፋይናንስ ተቋማቱ ተወካዮት ጋር ሰሞኑን ውይይት እንዳደረገ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።
ተቆጣጣሪው ባንክ ያዘጋጀው ረቂቅ መመርያ፣ ከዚህ ቀደም ክፍያ የማይጠየቅባቸውን አገልግሎቶችን ጨምሮ አዲስ የአገልግሎት ክፍያዎችን የያዘ እንደሆነ በውይይቱ የተሳተፉ ምንጮች ገልጸዋል።
አሁን ባለው አሠራር መሠረት አንድ ባንክ፣ ኢንሹራንስ ወይም ደግሞ የማክሮ ፋይናንስ ተቋም ተመሥርቶ ወደ አገልግሎት ለመግባት የፈቃድ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ አይጠየቅም። በተዘጋጀው ረቂቅ የአገልግሎት ክፍያ መመርያ መሠረት ግን የትኛውም የፋይናንስ ተቋም ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ ብሔራዊ ባንክ ለሚያደርገው ምርመራና ለሚሰጠው ፈቃድ ክፍያ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ለሁሉም የፋይናንስ ዘርፎች የተለያየ የክፍያ መጠን ተሠልቶ በረቂቁ ውስጥ እንደተካተተ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የተዘጋጀው መመርያ እንደ ፋይናንስ ተቋማቱ ዘርፍ ዓይነት ተለይቶ የተሰናዳና በየዘርፉ ዓይነት ራሱን የቻለ የአገልግሎት ክፍያ ተመን የተካተተበት እንደሆነ የሚገልጹት ምንጮቹ፣ ለአብነትም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አዲስ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቁት የአገልግልት ክፍያ እስከ አንድ መቶ ሺሕ ብር እንደሚደርስ ጠቁመዋል።
ወደ ኢንዱስትሪው ለሚገባ የጠቅላላ ኢንሹራንስ አገልግሎት ለሚሰጥ አዲስ ኩባንያ 75 ሺሕ ብር፣ የሕይወት ኢንሹራንስ ለሚሰጥ አዲስ የኢንሹራንስ ኩባንያ ደግሞ 25 ሺሕ ብር የፈቃድ አገልግሎት ክፍያ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለቱንም አጣምረው ለሚሠሩ ደግሞ 100 ሺሕ ብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ለፈቃድ ከሚከፍለው ክፍያ ባሻገር፣ ብሔራዊ ባንክ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ለሚያካሂደው ምርመራም (ኢንቨስቲጌሽን) ክፍያ እንዲከፍሉ ረቂቅ መመርያው እንደሚያስገድድና ለዚህም የተለያዩ የክፍያ ተመኖች መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
መከፈል አለበት ብሎ ረቂቁ ያስቀመጠው የገንዘብ መጠን የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ጠቅላላ የመድን ሰጪ ኩባንያ ላይ ለሚደረግ ምርመራ 37,500 ብር፣ እንዲሁም ለሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፉ ምርመራ ደግሞ 12,500 ብር የአገልግሎት ክፍያ መክፈል እንዳለበት መተመኑን ይገልጻል። ሁለቱንም አገልግሎት ለሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ደግሞ 50 ሺሕ ብር የሚጠይቅ መሆኑም ታውቋል፡፡ ለሱፐር ቪዥንና ለሌሎች ባንኩ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶችም የክፍያ ተመን መቀመጡን የሚገልጹት ምንጮቹ፣ ለተመሳሳይ አገልግሎቶች ባንኮች እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው የክፍያ መጠን፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በሚመለከተው ረቂቅ መመርያ ውስጥ የብቃት ማረጋገጫ ወይም ኩባንያው ሥራውን በአግባቡ መሥራት አለመሥራቱን ለማረጋገጥ ለሚደረግ ምርመራ፣ ‹‹Examination Fee›› በሚል አንቀጽ ሥር የቀረበው የክፍያ መጠን ደግሞ፣ የኢንሹራስ ኩባንያዎቹን በሦስት በመክፈል የተዘጋጀ ነው። በዚህም መሠረት ብሔራዊ ባንክ ትልልቅ ብሎ በሚመድባቸው ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ለሚያደርገው የክትትል አገልግሎት 500 ሺሕ ብር፣ ለመካከለኛ ኩባንያዎች 350 ሺሕ ብር፣ ለአነስተኛ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ 250 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ተመን በረቂቅ መመርያው ውስጥ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ ረቂቁ በዚህ አንቀጽ ሥር ለሚደረግ ምርመራ የጊዜ ገደብ እንዳላስቀመጠም ጠቁመዋል።
ለፈቃድና ለሱፐር ቪዥን ክንውኖች መከፈል ያለባቸው ክፍያዎች ከሁሉም የሚበልጡ መሆኑን የሚጠቅሱት ምንጮቹ፣ ከዚህ በፊት ክፍያ የማይጠየቅባቸው አገልግሎቶች በረቂቁ እንደተካተቱ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ቀደም 100 ሺሕ ብር ይከፈልበት የነበረ አገልግሎት እስከ 700 ሺሕ ብር የደረሰ መሆኑን የጠቆሙት እኚሁ ምንጮች፣ እስከ አንድ ሚሊዮን ክፍያ የሚጠየቅበት አገልግሎትም በባንኮች ረቂቅ ውስጥ መካተቱን ገልጸዋል፡፡ መመርያው ቅርንጫፍ ለመክፈት ለሚሰጥ ፈቃድ፣ ለምርመራና ለሌሎች አገልግሎቶች ጭምር ክፍያ ያስቀመጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህ ረቂቅ ማክሮ ፋይናንሶችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን ጭምር የሚመለከት መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ በተለይ ለፈቃድ ይከፈል የነበረው አገልግሎት እስከ 2,000 በመቶ የጨመረ መሆኑን ነው፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለፈቃድ ተብሎ ይከፍሉ የነበረው ክፍያ ከአንድ ሺሕ ብር የማይበልጥ እንደነበር የሚጠቁሙት ምንጮቹ፣ አሁን ወደ 100 ሺሕ ብር መድረሱ ከፍተኛ ጭማሪ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
ለሱፐር ቪዥን ተብሎ የሚከፈለው ክፍያ አዲስ መሆኑን የሚጠቅሱት ምንጮቹ፣ ብሔራዊ ባንክ ለቁጥጥር ብሎ የፋይናንስ ተቋማትን ሲመረምር ለሚያካሂደው ለእያንዳንዱ ምርመራ ክፍያ ማስከፈል ሊጀምር እንደሆነ ያመለክታል፡፡ በዚህ ረቂቅ ላይ የፋይናንስ ተቋማት ያላቸውን ሐሳብ እንዲሰጡ ዕድል የተሰጣቸው ሲሆን፣ ረቂቁ ከተሰጠው ሐሳብ ጋር ተገናዝቦ ማሻሻያ የሚደረግበት ከሆነ፣ ይኼው ማሻሻያ ተደርጎ በቅርቡ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባንኩ ይህንን አዲስ ረቂቅ ያዘጋጀው ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠትና ሥራውን የበለጠ ለማጎልበት ይረዳል በሚል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡