Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ...

የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

ቀን:

በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ፣ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠየቀ፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የተመድ ጀኔቭ ልዑክ መሪ (አምባሳደር) ሎቴ ኩንዱሰን መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉባዔው ላይ፣ የተመድ የምርመራ ቡድን በኢትዮጵያ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ምርመራ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹የትግራይ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን ሰላማዊ የድርድር ሒደት መቀበሉን እንደ መልካም ማሳያ እንወስደዋለን፤›› ብለው ነበር፡፡

ለአምባሳደሯ ንግግር ምላሽ የጠየቁት በጄኔቭ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ፣ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የቆየ ግኙነት እንዳላት በመግለጽ፣ ‹‹ኅብረቱ ፅንፍ የያዘ ግፊት ማድረግና የኢትዮጵያን መንግሥት ጥረት ያጣጥላል ብለን አንጠብቅም፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 ቋሚ መልዕክተኛው አክለውም፣ የአውሮፓ ኅብረት ሕወሓትን ‹‹የትግራይ መንግሥት›› ብሎ መጥራቱ የሚያስቆጣና አገላለጹ ከኋላው ምን ዓይነት ዓላማ ያዘለ እንደሆነ ለማወቅ ግልጽ እንዳልሆነ በመጠቆም፣ ‹‹ኅብረቱ አፋጣኝ የሆነ ማብራሪያ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፤›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ከሳምንታት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ አካላት የፌዴራል መንግሥትን ‹‹ከፀበኛ ቡድን›› ጋር እኩል አድርጎ መጥራት ተቀባይነት የሌለውና ከእውነታው የራቀ ዕሳቤ ነው በማለት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲያከብር የጠየቁት ቋሚ መልዕክተኛው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከምርመራ ኮሚሽኑ ጋር አብሮ ለመሥራት አዲስ አበባ ድረስ ጠርቶ ለማነጋገር ያደረገውን ጥረት አውስተዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ተዋካይዋ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርት ውስጥ ያሉት ሁለቱ ወገኖች ከግጭት ወጥተው፣ በቀጥታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉና የመጨረሻ መፍትሔ እንዲያመጡ እንደግፋልን ብለዋል፡፡

ጦርነቱ እንዲቆምና የሰብዓዊ ዕርዳታው እንዲረጋገጥ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱና ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶች የተጀመረውን የሰላም ጥረት በሚያግዝ መንገድ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራም ጠይቀዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም በተደረገው ጦርነት ተፈጽሟል በተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰየመው የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ተፈጽሟል የተባለውን የመብት ጥሰት በቦታው ተገኝቶ ምርመራ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ መስጠት ባለመቻሉ በቦታው ተገኝቶ ምርመራ ማካሄድ አለመቻሉን፣ የመርማሪ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ለጉባዔው አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመው በሚኒስትሮች ግብረ ኃይል በኩል የቀረበለትን ጉዳይ በቦታው ተገኝቶ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ስብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል መርማሪ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ አንዲመጣ ፈቃድ የሰጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ያወጣው ሪፖርት ስም ማጥፋት የበዛባት፣ በስልክና በኢንተርኔት ብቻ የተከናወነና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ መቅረቡን ዘነበ (አምባሳደር)  ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን መሰል አገሮች ላይ የሚደረጉ የተዛቡ ሪፖርቶች የካውንስሉን ዝና የሚያበላሹ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ከሚጠበቀው በታች እንደሚሆኑ ገልጸው፣ ይህም ሪፖርት መሠረታዊ መርሆችን ባልተከተለ ምርመራ የቀረበ ነው ብለውታል፡፡

መርማሪ ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ውጪ ተንቀሳቅሶ ምርመራ ማድረግ ባይችልም፣ ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ሪፖርቶች የድርጅቱን መሥፈርት የተከተሉና ጠለቅ ያለ ምርመራ የተካሄደባቸው መሆኑን የኮሚሽኑ የባለሙያ ቡድን ሰብሳቢ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ዓለም አቀፍ የምርመራ ቡድኑ ከማናቸውም አካላት ጋር ምንም ዓይነት አጀንዳ እንደሌለውና ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መሥራቱን አብራርተዋል፡፡

እሳቸው ይህንን ይበሉ እንጂ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የምርመራውን ሪፖርት ድምዳሜ የሰሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ሰብሳቢዋንና ቡድናቸውን ነፃና ገለልተኛ ካለመሆናቸውም በላይ ኃላፊነት የጎደላቸው በማለት ወቅሰዋቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...