Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርአስቸኳይ የፓስፖርት ዕድሳትና በተቋማት ላይ እየተደረገ ያለው አድልኦ በኢሚግሬሽን

አስቸኳይ የፓስፖርት ዕድሳትና በተቋማት ላይ እየተደረገ ያለው አድልኦ በኢሚግሬሽን

ቀን:

ሰሞኑን ለአስቸኳይ የሚድያ ሥራ ወደ ውጭ ትሄዳለህ ተብዬ ፓስፖርቴን ለማሳደስ በኢትዮጵያ ኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ተገኘሁ። ለአስቸኳይ ዕድሳት የመሥሪያ ቤት ደብዳቤ፣  የፓስፖርት ኮፒና 3,000 ብር (በሳምንት ከሆነ 2,100 ብር ነው) ‹‹ይዘህ ና›› በተባልኩት መሠረት ይዤ ሄድኩ።

ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ የአስቸኳይ ዕድሳት አገልግሎት ወደ ሚሰጥበት ቢሮ ቁጥር 101 ስደርስ ሠልፉ ከክፍሉ ተርፎ አንድ ትልቅ ድንኳን ውስጥ ከትሟል። ገሚሱ ቁጭ ብሎ ሲተክዝ፣ ገሚሱ ቆሞ ሲቆዝም ለቅሶ ቤት እንጂ ፓስፖርት ለማሳደስ የተሰበሰበ ሕዝብ አይመስልም።

በጣም የተንቀረፈፈ አሠራር በመኖሩ ሠልፋችን ፈቀቅ ሳይል 6:30 ሰዓት ሆኖ የተራ ቁጥር ተሰጥቶን ‹‹7:30 ሰዓት ተመለሱ›› ተብሎ ሁሉም ለምሣ ተበተነ።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከምሣ በኋላም ይበልጥ ሠልፋ ተጓተተ። አጠገቤ ያሉት ከሁለት ቀናት በላይ መመላለሳቸውንና ሁሉንም ዶክመንት ቢያሟሉም ‹‹አይቻልም›› መባላቸውንና ምንም ግልጽ አሠራር አለመኖሩን እያነሱ ያወጋሉ። ባለፈው ወር ወደ አሥር የሚጠጉ  መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸውንም ግራ ቀኙን ገልመጥ ብለው እያዩ ያወራሉ። በዚህ ምክንያት ሠራተኛ ቀንሶ ሥራ በዝቶባቸው ይሆን? የሚል ግምት አደረብኝ፡፡

ብቻ ለአስቸኳይ ሥራ፣ ለትምህርት፣ ለሕክምናና ሌሎች ምክንያቶች እዚያ የተገኘው ሰው ብዛት አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ከሚጎርፈው ሕዝብ ጋር ሲደመር  የአገሪቱ ነዋሪ ውሎ እዚያው ይመስላል፡፡

የአስቸኳይ የዕድሳት ክፍሉ ውስጥ ሁለት ሠራተኞች ብቻ አሉ። መንግሥት ወጪ ለመቆጠብ ብሎ በሁለት ሠራተኛ ይኼን ሁሉ ዜጋ በሠልፍ ከሚያንገላታ የተሻለ አገልግሎት ሰጥቶ ለምን ገቢ አይሰበሰብም እያልኩ አሰላስላለሁ። በመንግሥት አገልግሎት መጓተት የሚደርሰው የኢኮኖሚ ጉዳትና የግለሰቦች ሕይወት መቃወስስ? የሚለውም ሐሳብ ይሞተኝ ጀመር፡፡

ከሠልፉ መንቀርፈፍ በላይ ደግሞ የሠልፍ አስከባሪዎችና የቢሮ ሠራተኞቹ ተገልጋይን ትንሽ ትልቅ ሳይሉ በስድብ ከፍ ዝቅ ሲያደርጉ መስማት መመልከት ‹‹ምነው የውጭ ጉዞ ባልኖረኝ?›› ያሰኛል።

አንድ ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሩ እንዲህ ጥንብ እርኩሱ ከወጣ በባዕድ አገር ሄዶ ቢንገላታ ምን ይገርማል? በሰው አገር ችግር ላይ ሲወድቅስ የሚደርስለት ይኼ ተቋም ነውን?

የሚያስቀው ዜጎችን እያስመረሩ አገልግሎት የሚሰጡ እነዚሁ የመንግሥት ተቋማት፣ ነገ ዳያስፖራውን የውጭ ምንዛሪ በባንክ ላኩ ማለታቸው ነው። እንኳን በአገሩ ተመልሶ ኢንቨስት ሊያደርግ ምሬቱ አይወጣለትም። ታክስ እያነቀ ለመሰብሰብ፣  የንግድ ቤት ለማሸግ ወይም መብራት ለመቁረጥ አንዲት ቀን የማይታገሰው መንግሥት ዜጎችን ለቀላል አገልግሎት ለሳምንት ሲያመላልስ ቅር አይለውም። ቆይ መንግሥት ነው እኛ ነን ሕግ አክባሪ? ማንስ ነው የመቆጣት መብት ያለው? መንግሥት በግድ ግዛ የተባለ እንጂ ምረጡኝ ብሎ ማኒፌስቶ አርቅቆና እየዞረ በሞንታርቦ እየቀሰቀሰ ምረጡኝ ያለ አይመስልም። ወጣቱስ ቢሆን በሕገወጥ መንገድ የሚሰደደው ይኼ ሠልፍ ሰልችቶት ይሆን እያልኩኝ ንዴቴን ለመርሳት ከራሴ ጋር ስነጋገር፣ በመሀል ሠራተኞቹ እየተጠራሩ ጥግ ላይ ወዳለ አንድ ቢሮ ተመሙ። ለካ ዕለቱ ስኳር የሚከፋፈልበት ቀን ነው። ሁለት ሁለት ኪሎ በፌስታል ይዘው እየወጡ ‹‹ዱቄቱስ መቼ ነው የሚመጣው?›› እያሉ ይጠያየቃሉ። የግል መሥሪያ ቤትና የመንግሥት መሥሪያ ቤት ማርስና ቬኑስ ናቸው ብዬ ልፈላሰፍ ሞከርኩ። አንዳቸውም በሌላኛው ጫማ ውስጥ ቆመው ማሰብ አይችሉም። ምናልባት እስካንድኔቪያን አገሮች በሚባሉት የሶሻል ዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ካልሆነ በቀር።

ልክ አሥር ሰዓት ሊሆን ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩ ተራየ ደርሶ ገባሁ። ገና ደብዳቤውን ሳያነብ ርዕሱ ላይ የመጣሁበትን የግል ሚዲያ ተቋም ስም ሲያይ ደብዳቤውን ሰጠኝና እንድወጣ ወደ በሩ ጠቆመኝ፡፡ ‹‹ለመንግሥት ሚድያ ብቻ ነው በአስቸኳይ ማሳደስ የሚፈቀደው አለኝ፡፡ ታዲያ ለምን ደብዳቤ አምጡ ትላላችሁ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩኝ፡፡፡ ‹‹ለግል ሚድያ፣ ለኤንጂኦና የግል ድርጅቶች ፓስፖርት በአስቸኳይ አይታደስም። የመንግሥትን ሕግ መቀየር አልችልም፤›› በማለት ተጨማሪ ማናገር እንደማይፈልግ ሲነግረኝ ወጣሁ እንደበገንኩ። ቀኔን አቃጥዬ ከጉዞዬም ቀርቼ። የግል ጋዜጠኛ ከኤንጂኦ እኩል እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይቆጠራል?

የሚድያ ሥራ ዘወትር በእንቅስቃሴ የተሞላና ፋታ የማይሰጥ ሁሌም ከሰዓት ጋር ግብግብ መግጠም መሆኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ያውቁታል።

የግልም ሆነ የመንግሥት ሚድያ ተቋማት በብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ ተሰጥቷቸው ለአንድ አገር እየሠሩ ሳለ፣ በጎን ግን የግል ሚድያ ተቋማትን ከማግለልም አልፎ በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ጠልፎ የሚጥል አሠራር ማበጀት ካለፈው ገዥ መንግሥት ተወርሶ በዚህኛውም መንግሥት አገዛዝ የዘለቀ ያልተጻፈ ፖሊሲ ነው። ለማጣራት ስሞክር ሌሎች የሥራ ባልደረቦቼም ተመሳሳይ ገፈት ቀምሰዋል።

በዶክተር ዓብይ አገዛዝ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ የሕግ ማሻሻያዎች ቢደረጉም፣ ነፃ ፕሬስ አሁንም ከስቅላት አልዳነችም። አንዴ የኅትመት ወረቀት በመከልከልና ቀረጦችን በመቆለል፣ ሌላ ጊዜ በግልጽም፣ በሥውርና በተለያዩ ጫናዎች የግል ሚድያ ተቋማትን መጎሰም የዕለት ተዕለት ልምድ ሆኗል። እንዳይከፋው ጥራው… የምትለዋ መርህ ሁሌም የምትሠራ ይመስላል።

በጥቅሉ ‹‹የግል›› የተባለን ሚዲያ ሁሉ ፀረ አገራዊ አድርጎ መቁጠርስ ኮሙዩኒዝም ነው ወይስ አለማወቅ? ‹‹የግል›› የተባለ ሚዲያ በሙሉ ሲፈለግ ብቻ መረጃ ለመስጠት እንደሚጠራ የጉልበት ሠራተኛ፣ የገዥው ፓርቲ አባላትና የመንግሥት ሠራተኞች ግን ‹‹አንደኛ ደረጃ ዜጋ›› አድርጎ መመደብ፣ ለሁሉም የሚሆን አንድ አገር ለሚገነባ ሕዝብ ፊውዳልና ጭሰኛ እንደመፍጠር ነው።

በመሆኑም የሚመለከተው አካልና መንግሥት ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ነውና የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ፣ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ህልውና አግኝተውና ግብር እየከፈሉ ዜጎችን በማገልገል ላይ የሚገኙትን የሚዲያ ተቋማትን በሙሉ በእኩልነት እንዲያገለግልና የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ሊመለከቱትና ሊያሳስቡት ይገባል እላለሁ፡፡

  • ደረጀ ገለታ ገብረየሱስ
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...