Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹በሌጣ የወረቀት ዶላር›› (Fiat Dollar) መሣሪያነት በተከፈተ የኢኮኖሚ ጦርነት ቤትና ንብረት አትጡ

‹‹በሌጣ የወረቀት ዶላር›› (Fiat Dollar) መሣሪያነት በተከፈተ የኢኮኖሚ ጦርነት ቤትና ንብረት አትጡ

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

‹‹የሌጣ የወረቀት ዶላር›› (Fiat Dollar) አጀማማር

በቅርቡ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ስካፈል፣ እንዲሁም ሚዲያዎች ላይ ለቃለ መጠይቅ ቀርቤ ስመልስ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳይሆን የዶላር መብዛት ችግር ነው ስል በመገረም አዳምጠው፣ ከእነዚህ መድረኮች በኋላም ለጥያቄና ለውይይት የጋበዙኝ በርካቶች ናቸው፡፡  የሰሞኑ የጥቁር ገበያ በብርና በዶላር መሀል ያለ የምንዛሪ መጠን ወደ 90 ብር መድረሱና በንብረት ገበያው ደግሞ፣ ለምሳሌ አምስት ሚሊዮን ብር ሲባል የነበረ ቤት ወይም ሌላ ንብረት በማግሥቱ አሥር ሚሊዮን መባሉ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር ሴራ መገለጫ ነው የሚል ምላሽ ስሰጥም በጥሞና የሚያዳምጡኝ አሉ፡፡ ዛሬ በምዕራቡ ዓለም ኢምፔሪያሊስቶችና በመሣሪያዎቻቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳዎች፣ በተለይም በንግዱ ዘርፍ ውስጥ በተሰገሰጉ ተላላኪዎቻቸው አስፈጻሚነት አገርን ለማፍረስና መንግሥትን ለመገልበጥ ታስቦ በውጭ ምንዛሪና በዶላር ፖለቲካ ዙሪያ የሚደረግን ሴራ ያልተረዳው የአገሬ ሰው  በጥቁር ገበያ ጨዋታ፣ ዶላር በሚባል የወረቀት ሌጣ ገንዘብ (Fiat Money) ንብረቱንና ሀብቱን በጠራራ ፀሐይ በብልጣ ብልጦችና በሌቦች እየተዘረፈ ነው፡፡ ጥቂቶች የኢምፔሪያሊስት ኃይል መሣሪያዎች የወረቀት ገንዘብ አሸክመውት፣ ቤቱንና ንብረቱን በግዥ ስም ይወስዱበታል፣ ይዘርፉታል፡፡ በማግሥቱ የተሸከመው የወረቀት ገንዘብ እንኳን ቋሚ ንብረት ሊገዛ የዕለት ጉርሱንም ለሟሟላት አያስችለውም፡፡

እዚህ ላይ ስለትክክለኛ ገንዘብ (Real Currency/Money) ታሪካዊ ክስተትና ሒደት፣ ብሎም ስለዕርባና ቢስ በአብዛኛው የፖለቲካ እንጂ የኢኮኖሚ መሣሪያ ሳይሆን ስለሚታየው ሌጣ የወረቀት ገንዘብ (Fiat Currency/Money) በትንሹም ቢሆን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በታሪክ የተለያዩ አገሮች የገንዘብ (Currency) ኅትመት ሦስት ደረጃዎችን ቆጥሯል፡፡ መጀመሪያ አገሮች ከከበሩ ማዕድናት ለምሳሌ ከወርቅና ብር የተሠሩ ሳንቲሞችን ለንግድና ለተለያዩ ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ማስፈጸሚያ ይጠቀሙ ነበር፡፡  ሁለተኛው በወረቀት ላይ የተለያየ ዋጋ ተሰጥቶት (10፣ 100፣ ወዘተ ኖት) የታተመ፣ የያዘውን ዋጋ የሚመጥን የውድ ማዕድናት (ወርቅ፣ ብር፣ ወዘተ) ታስቦለት ተቀማጭ የተደረገለት ገንዘብ ነበር፡፡ ሦስተኛው ፊያት ገንዘብ (Fiat Money) ነው፡፡ ዛሬ በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ አገሮች ታትሞ እየተሠራበት ያለው የገንዘብ ዓይነት ይህ ዓይነቱ ነው፡፡

ፊያት ገንዘብ በውድ ማዕድናት ታሳቢ ተደርጎ፣ በእነዚህ ማዕድናት ክምችት የሚደገፍ እሴት ያለው ገንዘብ አይደለም፡፡ ማስተማማኛው ወረቀቱ ሕጋዊ ሰነድ ነው ተብሎ (Legal Tender) እንደ ገንዘብ የሚከውናቸውን ሥራዎች ሲሠራ ተጠያቂነትን ያሳተመው አገር ይወስዳል ተብሎ መገመቱ ነው፡፡ እዚህ ላይ ከሁለተኛው ዓይነት መቼና ለምን ወደ ሦስተኛው ዓይነት፣ ማለትም ወደ ፊያት ገንዘብ የዓለም የኢኮኖሚና ንግድ ሥርዓት ተሻገረ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ ዝርዝር ጉዳይ ያለው ሲሆን በአጭሩ ግን እንደሚከተለው መግለጽ ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው ዓይነት ገንዘብ እስከ 1940ዎቹ ድረስ ይሠራበት ነበር፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ይህ ገንዘብ በዕንቁ ማዕድናት ክምችትና ከአሠራር ቅልጥፍና ጋር በተያያዘ ችግር ምክንያት፣ በተለይ አሜሪካና አውሮፓ ከገቡበት የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ መዛባት ጋር ተያይዞ በተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ ሥራ አጥነትና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዝቅጠትና የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋገት ክስተት ሳቢያ እ.ኤ.አ. በ1944 አሜሪካ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ በብረተን ውድ ሥርዓት (Bretoon Wood System)  የሚመራ የሁለተኛው ዓይነት በዕንቁ ማዕድናት የሚደገፍ የወረቀት ገንዘብ ኅትመት ተጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ የአሜሪካና የካናዳ ዶላርና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ገንዘቦች ለሌሎች አገሮች የገንዘብ ጥንካሬ መመዘኛ ሆነው እንዲሠሩ ተደረገ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ገንዘብ መገበያየቱ እስከ 1960ዎቹ በደህና ሲከወን ቆይቶ፣ በ1960ዎቹ በአሜሪካ ውስጥ በተፈጠረ የኢኮኖሚ ችግር አገሮች በዶላር ላይ  የነበራቸው እምነትና ቅቡልነት እየተሸረሸረ መጣ፡፡ በማናቸውም ወቅት በወርቅ ወይም በሌሎች ዕንቁ ማዕድናት እንቀይራለን ብለው ዶላር ያከማቹ አገሮች፣ እነ ፈረንሣይና ቤልጂየም የመሳሰሉትን ጨምሮ አሜሪካኖችን ዶላራችሁን ወስዳችሁ ወርቅ ስጡን ሲሉ ዞር በሉ ተባሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 1971  በፕሬዚዳንት ኒክሰን አስተዳደር ዶላር ከወርቅ ጋር ያለው ተገማችነት እንዲቀር ተወሰነ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዶላር ከማናቸውም ውድ ማዕድናት ጋር ያልተሳሰረ ሌጣ የወረቀት ገንዘብ (Fiat Money) ሆነ፡፡ 

በዚህ ሒደት ውስጥ በዓለም አገሮች መሀል ያለን የተለያየ ገንዘብ ሚዛን ማስጠበቅ ይቻል ዘንድ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund IMF) አገሮች የንግድ ሚዛናቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችላቸውን የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ልዩ መብት (Special Drawing Right-SDR) ሥርዓት መሠረተ፡፡ ይህ ሥርዓት  በወረቀት የማይታተም ግን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ልውውጥ የሚሠራ ድብልቅ የወረቀት ገንዘብ (Fiat Composite Currency) ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ታቅፈው አገሮች በኢኮኖሚና በንግድ እንቅስቃሴ በሚፈጥሩት የሸቀጦችና አገልግሎቶች ሽያጭና ግዥ ትስስር የገንዘባቸውን የመለዋወጫ ምጣኔ (Foreign Exchange Rate) ወስነው መሥራት ቀጠሉ፡፡

ዛሬም አሜሪካኖች የራሳቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ በዓለም ውስጥ በገፍ አትመው ያሠራጩት ዶላር በተለያዩ አገሮች የኢኮኖሚ ቀውስ እየፈጠረ እንደሆነ፣ በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. በ25ኛው የሴንት ፒተስበርግ የኢኮኖሚ ፎረም የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በግልጽ ተናግረውታል፡፡ እንደ እሳቸው መረጃ አሜሪካኖች በዓለም ውስጥ የበተኑትን ዶላር በቅርቡ በ38 መቶኛ ጭማሪ አድርገውበታል፡፡ ይህም በዓለማችን ዙሪያ የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት ከሚገባው በላይ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ የዚህ ክስተትና የእነ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ ዶላርን የአለመጠቀም አካሄድ፣ ሌላኛውን ማለትም አራተኛውን ደረጃ የገንዘብ ዓይነት በቅርቡ እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

መላምታዊ መነሻዎች

የዚህ ጽሑፍ መላምታዊ (Hypothetical) መነሻዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ) ምዕራባውያን አገሮች የወረቀት ገንዘብ የሆነውን ዶላር (Fiat Dollar) ቤሎች አገሮች የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ለመግባት፣ የራሳቸውን ፍላጎት ለሟሟላት እንደ ማናቸውም የጦር መሣሪያ እየተጠቀሙበት መጡ፡፡

ለ) ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ ይህን መሣሪያ በመጠቀም ኢኮኖሚውን በአሻጥር በማመስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሐ) በሻንጣ ገብቶ በጆንያ ታጭቆ በኢኮኖሚያችን ውስጥ በተሠራጨ ዶላር ምክንያት የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ሥነ ልቦና እንዲሰለብ፣ በሴራው ዙሪያ ዕውቀት የሌላቸው ዜጎች በኮርፖራቶክራሲ ኃይሎችና በፖለቲካና በኢኮኖሚ ባንዳዎች ምክንያት ቤትና ንብረታቸውን  እየተዘረፉ ነው፡፡

መ) አገራችንን ለማፈራረስ፣ ያለውን መንግሥት በአሸባሪዎችና በተገንጣዮች በኩል ለመጣል በሚሠራው የኢኮኖሚ ቀውስ ደባ፣ በጥቁር ገበያው በኩል የብርና የዶላር ምንዛሪ ተዛብቶ እንዲገኝ ሆኗል የሚል ነው፡፡

ከእነዚህ መላምታዊ መነሻዎች ጋር አብሮ አንባቢያን እንዲረዱት የምሻውና ወረድ ብዬ የማብራራው ሌላው ግምታዊ ዕሳቤ (Supposition) ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ችግር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የብር መብዛት፣ ወይም ዶላር በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት በውጭ እንዲቀር ተደርጎ ሳይሆን ዶላር በገፍ አገር ውስጥ መኖሩና በስፋት ተሠራጭቶ እንደ ብር ለኮንትሮባንድ ሥራና በአገር ውስጥ ለቤትና ለንብረት የመሻሻጥ ተግባር ማገልገሉ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዶላር መብዛት

በኢኮኖሚክስ ትምህርት አስተምህሮ የአንድ አገር የውጭ ምንዛሪ ክምችት (በዶላር፣ በዩሮ፣ በዲናር፣ በሩብል፣ በየን፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል) የሚፈጠረው፣ አገሪቱ ያላትን ሀብት አልምታ ካመረተቻቸውና ለውጭ አገር ገበያዎች ከምትሸጣቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች (Export) የሚገኝ ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ በዕውኑ ዓለም የአገሮች ማዕከላዊ ባንኮች ሥሌት እነዚህንና በተጨማሪም የአገሪቱ ዜጎች በውጭ አገሮች ሆነው ከሚልኳቸው ገንዘቦች (Remittance) እና በውጭ ኢንቨስተሮች በኩል የሚገቡ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ብዝኃና ሁለትዮሽ ድርጅቶች በአገሮች ውስጥ ለሚሠሯቸው ሥራዎች በሕጋዊ መስመር የሚያስገቡትን የውጭ ምንዛሪ ያካትታል፡፡ በአብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ሲባል የተለያዩ አገሮች ገንዘብ የአገር ውስጥ ክምችት በአሜሪካ ዶላር ተሠልቶ የሚገለጽ ነው፡፡ 

የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን አንድ አገር ሸቀጦችና አገልግሎቶችን ከሌሎች አገሮች ለመግዛት (Import) ጥቅም ላይ ታውለዋለች፡፡ በዚህ ዓይነት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት ተሠልቶ የአቅርቦት ክምችቱ ከፍላጎቱ ያነሰ ከሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በቅርብ ዓመታት በአማካይ ነበር የሚባለው ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ወደ 21 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ በገቢ ንግድ ለሚመጡ ሸቀጦችና አገልግሎቶች የሚከፈለው መጠን ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት ያሳያል፡፡ ይህም በአገሪቱ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ ያስብላል፡፡ ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለ ቢመስልም በእኔ ግምት በአገሪቱ ውስጥ ከ21 ቢሊዮን ዶላር እጥፍ በላይ በአገሪቱ ውስጥ ዶላር አለ፡፡ ይህም በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ውስጥ በፈጠረው ትርምስ የዋጋ ግሽበትንና የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ፈጥሯል፣ እያባባሰውም ነው ባይ ነኝ፡፡ ይህ ምልከታዬ ቅቡልነት ካገኘ ደግሞ ኢትዮጵውያን ኢኮኖሚስቶችም ሆንን ሌሎች፣ ይህንን በኢኮኖሚክስ ትምህርት መማሪያ መጻሕፍት ውስጥ ተጽፎ የማይገኝ ክስተትን ማጥናትና ለፖሊሲ አውጪዎችና ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ይጠበቅብናል፡፡

በውጭ ምንዛሪ እጥረትና በዶላር አገር ውስጥ መብዛት ጥምረት የተፈጠረን ችግርና መፍትሔውን በተለመደው የማክሮ ኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳባዊ (Macro Economy Theory) ትንተና ማግኘት አይቻልም፡፡ በተለይም በተለመዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪዎች ማለትም በገንዘብ ኅትመት፣ በወለድ ምጣኔ፣ በቀረጥና ታሪፍ፣ በክልከላ፣ በመንግሥት ወጪ፣ ወዘተ ላይ በማተኮርና በመተረክ ችግሩ ሊፈታ እንደማይችል መጤን አለበት፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ያለን ኢኮኖሚ የማዕከላዊ ባንክ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ) በሚያወጣቸው የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች መግታት ይቻላል ብሎ መሞገትም የዋህነት ነው፡፡

ከወጪ ንግድ፣ ረሜታንስ (ሃዋላ)፣ ወዘተ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በብሔራዊ ባንክ ይታወቃል ተብሎ ሊገመት ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለን በየቤቱና በተለያዩ የንግድና የሥራ ተቋማት በሻንጣም ሆነ በጆንያ ተከማችቶ ያለ የአሜሪካ ዶላር ብሔራዊ ባንክ ያውቃል ብሎ የሚገምት ግን ሞኝ ወይም የዋህ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በእኔ ግምት በየዓመቱ በብሔራዊ ባንክ ከሚጠቀሰው የአማካይ 21 ቢሊዮን ዶላር እጥፍ በአገሪቱ ውስጥ የዶላር ክምችት አለ፡፡

ከብሔራዊ ባንክ ውጭ የሚፈጠር የዶላር ክምችት ሕገወጥ በሆኑ አሠራሮች የሚፈጠር ነው፡፡ ሕገወጥ በሆነ መንገድ በዓለም ብዝኃና ሁለትዮሽ ተቋማትና ሠራተኞቻቸው በኩል በሚገባ፣ በኮንትሮባንድና በጥቁር ገበያ እንቅስቃሴዎች አማካይነት የሚፈጠር ነው፡፡ አንዳንዶች ይህን ብሔራዊ ባንኩ ከሌሎች ተቋማት ጋር ለምሳሌ ከጉምሩክና ከደኅንነትና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ሆኖ መከታተል፣ መቆጣጠርና በኢኮኖሚው ውስጥ ቀውስ እንዳይፈጠር ማድረግ አለበት ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ተገማች ዕሳቤ ነው፡፡ ይህ ካልሆነስ?

ይህ ካልሆነ ሌላኛው ቀላል ተገማች ጉዳዩ ከማዕከላዊ ባንክ፣ ከደኅንነትና ከፀጥታ ኃይሎች ክትትልና ቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው የሚል ግምታዊ ድምዳሜ ላይ ሊያደርስ ይችላል፡፡  ሌላው ጥያቄ ሕገወጦቹ እነማን ናቸው? ነው፡፡ ዶላር የሚያትመው አገር ገንዘቤ ነው፣ ሕጋዊ ማረጋገጫ እሰጣለሁ ብሎ ነው የሚያሳትመው፡፡ በተለያዩ አገሮች ዶላሩ ለግብይት ተግባር ሲውል፣ ተገበያዮቹ ለዶላር ቅቡልነት ሰጥተዋል በሚል ዕሳቤም ነው፡፡ ይህ በመግቢያዬ እንዳሳወቅኩት እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ እውነታ ነበረው፡፡ ዛሬ ግን አይደለም፡፡ ዛሬ ዶላር ሌጣ የወረቀት ገንዘብ ይዘት ኖሮት ለኢኮኖሚና ለንግድ እንቅስቃሴ ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ ለፖለቲካ ሥራ የሚውል የኢኮኖሚ አሻጥር (Economic Sabotage) መተግበሪያ መሣሪያም ነው፡፡

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው በ1940ዎቹ የወረቀቱ ገንዘብ ከከበሩ ማዕድናት ጋር የሚለካ ዋጋ ነበረው፡፡ ዛሬ ግን ተራ ወረቀት በሚመስል ሥርጭቱ የአገሮችን ሉዓላዊነት መዳፈሪያና የመንግሥት መገልበጫ የኢኮኖሚ አሻጥር መሣሪያ ሆኗል፡፡ የሚያትመው አገርም ገንዘቡ ለኢኮኖሚና ለንግድ ሥራዎች ካለው አገልግሎት ባሻገር፣ ለፖለቲካ ሥራ ይውል ዘንድ እያተመ በዓለም ዙሪያ እንደሚያሠራጨው ከላይ የተመለከተውን በፕሬዚዳንት ፑቲን የተገለጸውን መረጃ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ከአታሚው አገር ውጪ ያሉ የማዕከላዊ ባንኮች፣ የደኅንነትና ፀጥታ ኃይሎች የኅትመቱንና የሥርጭት መስመሩን ሊቆጣጠሩት የማይችሉ ከሆነ፣ በታዳጊ አገሮች ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ፡፡

ኮርፖራቶክራሲና የዶላር ሥርጭት

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ከብሔራዊ ባንክ የክምችት መረጃ ውጪ ያለን  የአሜሪካ ዶላር ክምችትና ሥርጭት ለማወቅ፣ ስለኮርፖራቶክራሲ ሥርዓት ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ስለኮርፖራቶክራሲ ማለትም ያደጉ ምዕራባዊ አገሮች፣ የእነሱ መሣሪያ የሆኑት የዓለም ገንዘብ ተቋማትና ድንበር ዘለል ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሪ አማካይነት ስለሚሠሩት መሰሪ ሥራ ለማወቅ፣ በጆን ፕርኪነስ ከተጻፈው መጽሐፍ አጣቅሼ በ2013 ዓ.ም. ‹‹ኮርፖራቶክራሲ፡- አገራዊ፣ የሚተገበር (ፕራግማቲክ) ብልፅግና ተኮር ፖስፕኢ›› የሚል መጽሐፍ ስላሳተምኩ ስለጉዳዩ በጥልቀት ለመረዳት መጽሐፉን እንድታነቡ እጋብዛለሁ፡፡ በአጭሩ የኮርፖራቶክራሲው ሥርዓት ዓለማችንን በርቀት ቅኝ አገዛዝ  ሥልት  ታዳጊ አገሮችን ለመያዝና ለመበዝበዝ የሚሠሩ አካላት ስብስብ ነው፡፡ ሥርዓቱ በኢኮኖሚ አሻጥር መሣሪያዎች ሆነ በጦር መሣሪያ ታዳጊ አገሮችን ለማንበርከክ፣ መንግሥቶቻቸው ለእርነሱ ተገዥ ካልሆኑ ለማስወገድ የሚንቀሳቀስ የምዕራቡ ኢምፔሪያሊስቶችና እነሱ የአደራጇቸው ተቋማት የፈጠሩት ነው፡፡

በእኔ ምልከታ በኢትዮጵያ ውስጥ የኮርፖራቶክራሲው ሥርዓት አባላት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከጦር መሣሪያ በተጨማሪ ዶላርን ለመፈንቅለ መንግሥት፣ ለአሸባሪና ለተገንጣይ ቡድኖች አገር አፍራሽ እንቅስቃሴ፣ በርቀት ቅኝ ለመግዛት ወዘተ ሴራዎች ማስፈጸሚያነት ሕገወጥ በሆነ እንቅስቃሴ፣ በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች አማካይነት እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ማዕከላዊ ባንኩ የማይቆጣጠረው በርካታ የዶላር ክምችትና ሥርጭት በአገሪቱ ውስጥ እንዲኖር በማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕጋዊ በሆነው የወጪ ንግድና ተጓዳኝ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዘዴዎች የሚኖር የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲሸረሸርና እጥረት እንዲፈጠር የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠር እያደረጉ ነው፡፡ ለዚህም በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ አገራዊ  ድርጅቶች ውስጥ ዜጎችን በዶላር በማማለል፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ባንዳ በማድረግ በርቀት ቅኝ ለመግዛት ካልሆነም አገሪቱን ለማፈራረስ እየሠሩ ነው፡፡

በአጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ወዘተ ዋነኛ መንስዔው የብር ኅትመት መብዛት፣ የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር መጠንከር፣ የብር በነፃ ገበያ ከሌሎች አገሮች ገንዘቦች ጋር በሚወሰን ዋጋ፣ ማለትም የውጭ ምንዛሪ ተመን አለማግኘት ሳይሆን፣ ከላይ በተጠቀሰው ሴራ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ዶላር በግለሰቦች እጅ በመኖሩ ነው፡፡ ይህም መደበኛ የማክሮ፣ የገንዘብም ሆነ የፊሲካል ፖሊሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም፣ ወይም የምንዛሪ ገበያን ነፃ  በማድረግ የሚፈታ ችግር አይደለም፡፡

ዶላር ሕገወጥ በሆነ መንገድ አገር ውስጥ ገብቶ በብዛት ተሠራጭቶ እየተሽከረከረ፣ ከመደበኛው የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ውጪ በአገር ውስጥ እንስሳቱን፣ ቡናውን፣ ስንዴውን፣ ወርቁን ወዘተ በመግዛት በኮንትሮባንድ ንግድ ከአገር ውስጥ እንዲወጣ ከተደረገ፣ ከዚያም በተገኘ ዶላር የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ መለዋወጫዎች፣ የአልኮል መጠጦች፣ ወዘተ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በሁለትና በሦስት እጥፍ ከተሸጠ፣ ዛሬ ላይ ያለው ችግር እየተጠናከረ ሊሄድ ይችላል፡፡ በተለይ ዛሬ ባለንበት የጦርነት ጊዜ ይህ ሲሆን በአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ አሁን ካለበት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሚነግረን ወርኃዊ አማካይ በሰላሳ መቶዎቹ ከመሆን ባሻገር በመቶዎቹ ብሎም በሺዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም አልገረምበትም፡፡ በመሆኑም አገር አትፈርስም፡፡ በዓለማችን በአሥር ሺሕዎች ወርኃዊ የዋጋ ግሽበት ያስመዘገቡ አገሮች ሳይፈርሱ ዛሬም አሉና፡፡

ለምሳሌ በጀርመን እ.ኤ.አ. ከ1921-23 ባለው ጊዜ አማካይ ወርኃዊ የዋጋ ግሽበቱ 322 በመቶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በሁለት ዓመት ውስጥ ሲጀምር በአንድ ብር ይሸጥ የነበረ ሸቀጥ (ለምሳሌ ዳቦ) በሁለተኛው ዓመት ላይ ዋጋው በፊደል ለመጻፍ በሚያዳግት ደረጃ 7,320,000,000 ሆኖ ነበር፡፡ በሃንጋሪ ውስጥ እ.ኤ.አ. ከ1945-46 በአማካይ ወርኃዊ የዋጋ ግሽበት 19,800 በመቶ ሆኖ ነበር፡፡ ማለት ዛሬ በአንድ ብር የተገዛ ዳቦ ከወር በኋላ 19,800 ብር ሆኗል ማለት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በደቡብ አሜሪካና በአፍሪካ ውስጥ በመቶዎቹ ፕርሰንት የዋጋ ግሽበት ያስመዘገቡ አገሮች በርካቶች ናቸው፡፡ እንዲያው ጊዜ ሲያልፍ ያልፋል ተብሎ እንጂ፣ በቅርቡ በእኛው አገር በትግራይ ክልል አንድ ኩንታል ጤፍ ሃያ ሺሕ ብር ገባ ሲባል ግሽበት በመቶዎቹ ፕርሰንት ሊሰላ እንደሚችል ጠቋሚ ነው፡፡

የሰሞነኛው የዶላር ምንዛሪና ከበስተጀርባው ያሉ አካላት – የአቶ ጉማሬና የአቶ ተኩላ ሥራ

ከላይ ያለውን በሺዎች የሚቆጠርን የዋጋ ግሽበት ተወት አድርገን ከሰሞነኛው በአገራችን የብር የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ 53 ብር ሆኖ በጥቁር ገበያው ከ90 ብር በላይ መድረሱ፣ የቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ዋጋ በመቶ ፕርሰነት ጭማሪ እንደሄደ የሚወራው ላይ ትኩረት ሰጥቼ ወደ መደምደሚያ ሐሳቦቼ ላምራ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ከማቅረቤ በፊት ግን ከሕገወጥ ንግድና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በተዘጋጀ መድረክ የተነሱ ሐሳቦችንና የመረጃ ጥቆማዎችን አስመልክቶ በሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ከወጣው ኅትመት የሚከተለውን ልጥቀስ፡፡

“…ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 70 ቢሊዮን ዶላር በደረሰኝ ማጭበርበር እንደምታጣ ጥናቶች ያመለክታሉ… በአሁኑ ወቅት አንድ ዶላር በባንክ 52 ብር ሲመነዘር በጥቁር ገበያ ከ82 ብር በላይ ደርሷል፡፡ እንደ አገሩ ሁኔታም የምንዛሪ ዋጋው እንደሚለያይ የጠቆሙት የኢኮኖሚ ባለሙያው በቱርክ አንድ ዶላር 110 ብር ይመነዘራል መባሉን መስማታቸውን ጠቅሰዋል… ይህ ዓይነቱን ሁኔታ በመፍጠር ሕገወጥ ንግዶች እየተበራከቱ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ፣ በዚህ ውስጥም  ሙሰኛ ባለሥልጣኖች ተሳትፎ እንዳላቸው አመልክተዋል…” ይላል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ብርን በዶላር በጥቁር ገበያ መንዝሮ ከብት፣ ቡና፣ ወዘተ በኮንትሮባንድ ከመነገድ ባሻገር፣ ብርን በዶላር በተለያዩ አገሮች ውስጥ በመመንዘር ብቻ በአጭር ጊዜ ሚሊየነር መሆን እንደሚቻል ይጠቁማል፡፡ የምንዛሪው ማሻቀብ በፍራንኮ ቫሉታ ለመክበር የሚፈልጉ፣ በርካታ ብር ኖሯቸው ብሩን በቤትና ንብረት ላይ ለማዋል የሚሯሯጡ ዜጎች ብቻ የሚፈጥሩት ትርምስ አድርጎ ከመገመት ባሻገር፣ በኢኮኖሚ አሻጥር አገር ለማፍረስ የውጭ ኃይሎች የሴራ ትግበራ ምልክት አድርጎ መገንዘብን ይሻል፡፡ ይህን ጉዳይ በዕሳቤያዊ ምሳሌ የእነዚህ ኃይሎች ተላላኪዎች በሆኑ ሁለት ግለሰቦች እንቀስቃሴ የሚፈጠርን ሴራ እንደሚከተለው በወፍ በረር ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ለምሳሌ አቶ ጉማሬ የሚባል 20 ሚሊዮን ብር ይዞ አዲስ አበባ ባለ የዶላር ጥቁር ገበያ፣ በአንዴም ሆነ በመመላላስ ከአቶ ተኩላ ጋር በዶላር ተቀያየረ እንበል፡፡ ስምምነታቸው ደግሞ አንድ ዶላር በዘጠና (1፡90) መቀየር ነበር፡፡ በዚህም አቶ ጉማሬ ወደ 222,222 ዶላር ቀይሮ ያዘ፡፡

አቶ ጉማሬ ዶላሩን በተለያየ ገበያ ሸቀጥ በመግዛት ገቢ ሊያገኝበት ይችላል፡፡ አንደኛውም ብርን እንደ ሸቀጥ መግዛትና መሸጥ ነው፡፡ በሕገወጥ የቀየረውን ዶላር ቱርክ ይዞ በመሄድ ብቻ ወደ 4.5 ሚሊዮን ብር አትርፎ ሊመለስ ይችላል፡፡ ምክንያቱም በ90 ብር የገዛውን ብር በ110 ብር ይሸጠዋልና ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የተለያዩ አማራጮች አሉት፡፡ አንደኛው በከፊል ብር መግዛት፣ በከፊል ደግሞ ውድ ዕቃዎችን መግዛትና በሁለት ሦስት እጥፍ በአገር ውስጥ መሸጥ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ በዶላሩ የገቢ ዕቃዎች ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ በዚህ አሠራር በ20 ሚሊዮን ብር 20 እና ከዚያ በላይ ሚሊዮን ብር ገቢ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ማለትም በአጭር ጊዜ የ40 እና ከዚያ በላይ ሚሊዮን ብር ክምችት ያለው  ባለሀብት ሊሆን ይችላል፡፡

አቶ ጉማሬም ሆነ ቀድሞ ዶላሩን ሸጦ ብር የገዛው አቶ ተኩላ ደግሞ በቤትና ንብረት ገበያው ውስጥ ገብተው አምስት ሚሊዮን ሊሸጥ የነበረን ቤት ወይም ንብረት እስከ አሥር ሚሊዮን በመክፈል ስለሴራው ግንዛቤ የሌላቸውን ዜጎች ንብረት አልባ ያደርጋሉ፡፡ ቤትና ንብረት የሸጡት ሰዎች በሳምንቱ መለስተኛ ቤት ወይም ንብረት  ሊገዙ ገበያ ሲወጡ ዋጋው 15 ሚሊዮን ብርና ከዚያ በላይ ሆኖ ይጠብቃቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሕገወጦችና ሙሰኞች አገርንና ዜጎችን ይዘርፋሉ ያሰቃያሉ፣ ዜጎች በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲያጡ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አገር ለማፍረስ የሚደረገው ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆነው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በእርግጥ ጥቂቶች ቢሆኑም ኢትዮጵውያን ይህን መሰሪ የኮርፖራቶክራሲውንና አጋሮቹን ሴራ ይገነዘባሉ፣ ተግተውም አገር እንዳትፈርስ ይሠራሉ፡፡

ከላይ የተገለጸውን በሰፊው አብራርቶ ማሳየት ይቻል ነበር፡፡ ከቦታ ጥበት እዚህ ላይ ቆም አድርጌ ጉዳዩን ቀደም ብዬ ካቀረብኩት ትንታኔ ጋር ላያይዘውና የመደምደሚያ ምክረ ሐሳብ ልስጥ፡፡ 

መደምደሚያና ምክረ ሐሳብ

ከላይ በምሳሌ የአቀረብኩትንና ሌሎች መሰል ተግባራት እንዲከወኑ፣ በሪፖርተር ጋዜጣ እንደተመለከተው የሙሰኛ ባለሥልጣናት ተሳትፎ እንዲኖር ይሻል፡፡ በአየርም ሆነ በየብስ ብርም ሆነ ዶላርም እንዲሁም ሌሎች ሸቀጦችን በሻንጣም ሆነ በካርቶን በሕገወጥ አሠራር ከአገር እንዲወጡና እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ሙሰኛ ባለሥልጣናትና በሥራቸው ያሉ የተለያዩ አመራር  አካላት በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር እንዲጨማለቁ በማድረግ አገርንና ዜጎችን ለቀውስ እየዳረጉ ያሉ የኮርፖራቶክራሲው አባላት፣ በተለይ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ አሉበት ብዬ እገምታለሁ፡፡ የእነዚህን መሰሪ ተግባር በተለመዱት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሣሪያዎች ማለትም በገንዘብ ኅትመት፣ በወለድ ምጣኔ፣ በወጪና በገቢ ንግድ ቀረጥና ታሪፍ፣ በመንግሥት ወጪ ማኔጅመንት፣ በክልከላ፣ በኮታ፣ በራሽን፣ ወዘተ መሣሪያዎች በመጠቀም ለማስቆም በቀላሉ አይቻልም፡፡ በተለይ ከሙሰኛ ባለሥልጣናት ጋር አንዳንድ የደኅንነትና የፀጥታ ኃይል አባላት በሕገወጡ ተግባር የሚሰማሩ ከሆነ ችግሩ የተወሳሰበ በመሆን እየሰፋና እየጨመረ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ቢሆንም የሚከተሉትን በማድረግ ስፋቱን፣ የጭማሪ ፍጥነቱንና በአገርም ሆነ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ይቻላል፡፡

  1. በአሁኑ ጊዜ ዜጎች ቤትና ንብረትን ከመሸጥ ይታቀቡ፡፡ ከዚህ ውጪ በምንዛሪ ገበያው ኩነቶች የሥነ ልቦናዊ መርበትበት በሽታ ውስጥ ከገቡ፣ ሌቦች በሚያቀርቡላቸው የሚሊዮን ብር ጭማሪ ቤትና ንብረታቸውን አጥተው፣ በተቀበሉት ብር ነገ የሚፈልጉትን ለማድረግ ሳይችሉ ሲቀሩ ጤናቸውን አቃውሰው፣ ቤተሰባቸው ተናግቶ መና ሊቀሩ ይችላሉ፡፡
  2. ኅብረተሰቡ ከትክክለኛና ለሕዝብና አገር ታማኝ ከሆኑ የደኅንነትና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት፣ ይህንን ሴራና እኩይ ተግባር ማስቆም ይችላል፡፡ በእኔ ሙያዊ ምልከታ በአገራችን ውስጥ አሁን የሚታየው የጥቁር ገበያው የአሜሪካ ዶላር ምንዛሪ ተመን መጨመር፣ የዋጋ ግሽበቱ ማደግ፣ ሰው ሠራሽ የሸቀጦች እጥረት መፈጠር በኢኮኖሚ አሻጥረኞች በተለይም በውጭ ኃይሎችና በእነሱ የሚመሩ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ባንዳዎች፣ በውጭ አገሮች ተገዥና ተላላኪ የሆኑ ዳያስፖራዎች፣ በዲፕሎማትና በዓለም አቀፍ ብዝኃና የሁለትዮሽ ድርጅት ውስጥ በሚሠሩ ሠራተኞች፣ በኢንቨስተርነት ስም በሚንቀሳቀሱ ወስላቶች የሚደረግ አገርን የማፈራረስና መንግሥትን የመገልበጥ ሴራ ታቅዶ የሚተገበር እኩይ ተግባር ስለሆነ፣ እውነተኛ ኢትዮጵውያን ሳይርበተበቱ ከትክክለኛና ለሕዝብና ለአገር ታማኝ ከሆኑ የደኅንነትና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የዚህን ዕቅድ ትግበራ ማስቆም ይጠበቅብናል፡፡
  3. በሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዙሪያ የተገኘን መረጃ ለሚመለከተው አካል በፍጥነት ማሳወቅ ይገባል፡፡ በሙሰኞች፣ በፖለቲከኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ የእነሱ አስፈጻሚና አቀባባይ ባንዳዎችና ድርጅቶች በኩል ዶላርን በሻንጣ ብሎም በጆንያ አከማችተው በአገር ውስጥ ሆነው የኮንትሮባንድ ንግድን፣ የብርና የውጭ ምንዛሪ ሽያጭን፣ ተገቢ ያልሆነ የዜጎችን ቤትና ንብረት ባለቤትነት የሚያሳጡ ድርጊት የሚፈጽሙ ነጋዴዎችንና ደላሎችን፣ በአየር ሆነ በየብስ መፈተሻ ጣቢያዎች በቀላሉ ወደ ውጭ አገሮች ገንዘብና የኮንትሮባንድ ሸቀጦች እንዲወጡና እንዲገቡ የሚያደርጉ የመንግሥትና ሕዝባዊ ተቋማት፣ እንዲሁም የንግድ ባንኮች አመራሮችንና ባለሥልጣናትን በመለየት ኅብረተሰቡ ለሚመለከተው ተዓማኒነት ላለው የደኅንነትና የፀጥታ አካል መረጃን በፍጥነት መስጠት ይኖርበታል፡፡
  4. በመጨረሻም የሴራው ጅማሮ የከረመ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ላሳስብ የምሻው ዛሬ እየሆነ ያለው ሁሉ ሊሆን እየዳዳው እንደነበር ከስምንት ዓመት በፊት በጻፍኩት መጽሐፌ ውስጥ ጽፌ አሳውቄያለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ በ2012 ዓ.ም. በጻፍኩት ‹‹ኢኮኖሚው፣ ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚለው መጽሐፌ፣ የውጭ ኃይሎች በሚያደርጉት ሴራና ተንኮል ኢትዮጵያ እንደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ እንዳትሆን ተግተንና ነቅተን እንሥራ ብዬ በምዕራፍ አምስት ያቀረብኩትን ማስገንዘቢያ፣ በምዕራፍ 14 ደግሞ ኢትዮጵያን የውጭ ኃይሎች በቢሊዮን በሚቆጠር የወረቀት ገንዘብ ሴራ ለማፈራረስ በ11ኛው ሰዓት ላይ ናቸው ብዬ ያቀረብኩትን ማስገንዘቢያና ተያያዥ ሌሎች ጉዳዮችን መጻሕፍቱን በማንበብ ዝርዝር ጉዳዮችን ያውቁ ዘንድ አሳስባለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻ y[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...