ያ ጠቢብ ያሉት ሰው…. እጅግ ‹‹የተማረ››፣
እጁን ባፉ ጫነ… ጆሮው ደነቆረ፣
‹‹ማር ነው›› ሲባል ከርሞ… ከኮሶ መረረ፣
ሕሊናውን ሽጦ…. ለሆዱ አደረ፣
በማይጠቅም ሥሌት መልካሙን ቀየረ፡፡
በክፋት ቋጠሮ – ጠፍቶ መላቅጡ፣
በቂም በጥላቻ – ወጥቶ ውጥንቅጡ፣
ያስተማሩት ድሆች…
የኳሉ የዳሩት – መደገፊያ ሲያጡ፣
በቀንና ሌሊት – በችግር ሲቀጡ፣
በብሔር በጎሳ እንዲህ ሲናወጡ፣
እርሱ ግድየለሽ ነው እያወቀ በውስጡ፡፡
ግና…!!
ለእግዜር የተገዙ … ሕሊናን ያልሸጡ፣
ከእርግማን የሸሹ … ከአዚም ያመለጡ፣
የጥበብን ውኃ … ለትውልድ ያጠጡ፣
በጥልቅ አሳቢነት መልካምን ያመጡ፣
ጠቢባን፣ ምሁራንም አሉ ለእኛ የተሰጡ፡፡
በጸሎት በምልጃ ለሕዝባቸው ተግተው፣
ፍቅርን ተጎናጽፈው ሰላምን አንግበው፣
አሉ በየዋሻው የበግ ሌጦ ለብሰው፣
በገዳም በደብሩ … በከተማ፣ ጎጡ፣
ብዙ ጀግኖች አሉ ለሀገር የተሰጡ፣
ብዙ ቅኖች አሉ ለሕዝብ የተሰጡ፡፡
‹‹ወዳጅ ሆይ፥ ነፍስህ እንደሚከናወን ፥ በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ፡፡ ወንድሞች መጥተው አንተን በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና፤ ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም፡፡›› (3ኛ የዮሐንስ መልዕክት ቁጥር 2-4)
- በአባ ያዕቆብ ሊቀጳጳስ- ምሥራቃዊ ወመስአዊ ዘኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን