Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊከአማራጭ ክብካቤ በሚወጡ ወጣቶች ላይ የሚያተኩረው አዲሱ ፕሮጀክት

  ከአማራጭ ክብካቤ በሚወጡ ወጣቶች ላይ የሚያተኩረው አዲሱ ፕሮጀክት

  ቀን:

  ከአማራጭ ክብካቤ በሚወጡ ወጣቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገና ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ፕሮጀክት መጀመሩን ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች አስታውቋል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 11ዱ ክፍላተ ከተማ ላይ የሚተገበረው ፕሮጀክት 95.6 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ሲሆን፣ ገንዘቡ ከዴንማርክ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዳኒዳ) የተገኘ መሆኑን ኤስኦኤስ ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

  አማራጭ የሕፃናት ክብካቤ በተለይ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት የሚያገኙበት ነው፡፡

  መስከረም 10 ቀን 2015  ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ‹‹አንድም ወጣት ወደ ኋላ እንዳይቀር›› የሚል መሪ ቃል ያለው ሲሆን፣ በክፍለ ከተማ በክፍለ ከተሞቹ በሚገኙ 1,400 ወጣቶች ላይ የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል፡፡

  የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማም ከተለያዩ አማራጭ እንክብካቤ የሚወጡ ወጣቶች ራሳቸውን የሚችሉና ምርታማ የማኅበረሰብ ክፍል እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑን የኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች  የፕሮግራም ዳይሬክተር ወ/ሮ አቻምየለሽ ተፈሪ ተናግረዋል።

  ለፕሮጀክቱ  የገንዘብ ድጋፍ ካደረገው ዳኒዳ በተጨማሪ በማማከር፣ በፕሮጀክት ቀረፃና ክትትል በማድረግ ኤስኦኤስ ዴንማርክ  እንደሚገኝበት ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

  ድርጅቱ በኢትዮጵያ የወጣቶችን ችግሮች በጥልቀት በመረዳት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

  ፕሮጀክቱ ከአማራጭ ክብካቤ የወጡትን ወጣቶች የሚያግዙ ደጋፊ ፖሊሲዎችና ሕጎች እንዲወጡና እንዲተገበሩ ለማስቻል፣ እንዲሁም ለወጣቶቹ ፍላጎቶች ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው ለማስቻል ያለመ ነው፡፡

  ከአማራጭ ክብካቤ የወጡ ወጣቶች መብቶቻቸውን የሚጠይቁ እንዲሁም በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

  የኤስኦኤስ ኢትዮጵያ የሕፃናት መንደሮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳህለ ማርያም አበበ በበኩላቸው፣ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከተመደበው 95.6 ሚሊዮን ብር ውስጥ፣ 84.6 ሚሊዮን ብር ቀጥታ ለፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን፣ ቀሪው ለተለያዩ አስተዳደራዊ ወጪዎች ይውላል ብለዋል፡፡

  ተቋሙ እንደገለጸው፣ የፕሮጀክቱ ትግበራ ዋነኛ ባለድርሻ አካላት የከተማዋ የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የወጣቶችና ስፖርት፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮዎች ናቸው።

  በተጨማሪም በኢትዮጵያ የኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፕሮጀክቱን ለመተግበር  ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ድርጅቶች (ሰላም የሕፃናት መንደሮች፣ ቢታንያ ግሎባል፣ ቢቢአር፣ ሰላምታ፣ ወዘተ) ጋር በመተባበር የሚሠራ ይሆናል።

  ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች እ.ኤ.አ. በ1949 የተመሠረተ ዓለም አቀፍ ምግባረ ሠናይ ድርጅት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በ1967 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ድርቅና ጦርነት ተከትሎ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን የሚያድጉበት መንደር በመቀለ ከተማ በማቋቋም ሥራውን መጀመሩ ተገልጿል። 

  በኢትዮጵያ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አምስት አሠርታት ያህል በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሐረር፣ በሶማሌ፣ በደቡብና ትግራይ ክልሎች፣ እንዲሁም  በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ ሕፃናትና ወጣቶችን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 

  በሁሉም ፕሮጀክቶች 17,300 ልጆች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ልጆች የሚንከባከቡ 8,700 እናቶች ደግሞ የሥራ ዕድል ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...