Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመስቀል ክብረ በዓልና ገጽታዎቹ

የመስቀል ክብረ በዓልና ገጽታዎቹ

ቀን:

በዓለም ዙርያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በተለይም የምሥራቅም ሆነ የምዕራብ ትውፊትን የሚከተሉ ኦርቶዶክሶችና ካቶሊኮች፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የተገኘበትን ቀን በየዓመቱ በካሌንደሮቻቸው መሠረት በተለያዩ ቀናት ያከብራሉ፡፡ የመስቀሉን በዓል የግሪጎርያን ዘመን አቆጣጠር በሚከተሉት አገሮች ምዕመናን ከሁለት ሳምንት በፊት መስከረም 4 ቀን 2015 ዓ.ም. (ሴብቴምበር 14 ቀን 2022) አክብረዋል፡፡

የጁሊያን ካሌንደር የሚከተሉት በምሥራቅና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያንና ካቶሊካውያን የመስቀሉን በዓል ‹‹ሴብቴምበር 14 ቀን›› ብለው የሚያከብሩት የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ኮፕቲክ ቤተክርስቲያናት በሚያከብሩበት መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ነው፡፡ ዕለቱ በግሪጎርያን ሴብቴምበር 27፣ በጁሊያን ሴብቴምበር 14 ይውላል፡፡ ግሪጎሪያን ካሌንደር የጁሊያኑን እስከ ከለሰበት 16ኛው መቶ ዘመን ድረስ ሁሉም በአንድነት የመስቀል በዓልን ያከብሩ ነበር፡፡

የዘንድሮው የመስቀል በዓል እንደወትሮው በመላው ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያኒቱ ባለችበት ቦታ በዓለም ዙሪያ ጭምር  ይከበራል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ በሚገኙበት ደመራው መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ይለኮሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመስቀል ክብረ በዓልና ገጽታዎቹ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የከዚህ ቀደም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር በመስቀል አደባባይ

ጥንተ ነገሩ

በኢትዮጵያ ሁለቱ የመስቀል በዓላት መስከረም 17 ቀን እና መጋቢት 10 ቀን የሚውሉ ናቸው፡፡ መስከረም 17 ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል በቆስጠንጢኖስ እናት በቅድስት ንግሥት ዕሌኒ  በጎልጎታ ተቆፍሮ የተገኘበት ነው፡፡ የመጋቢት 10 መስቀል ደግሞ በሰባተኛው መቶ ዘመን በ629 በሕርቃል ቅዱስ መስቀሉ በፋርሶች (የአሁኗ ኢራን) ከተደበቀበት ቦታ የተመለሰበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቤተክርስቲያን አንዳንድ ቀደምትና የአሁን ዘመን መምህራን ባተሟቸው ጽሑፎቻቸው ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት ሰባት ወራት እንደወሰደባት፣ ይሀም ቁፋሮው መስከረም 17 ቀን ተጀምሮ መጋቢት 10 ቀን መገኘቱን ያወሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያሳተመችውና አሁንም በማገልገል ላይ ያለው  ጥንታዊው ስንክሳር በመስከረም 17 ንባቡ የአራተኛው ምዕቷ ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ስፍራ ማግኘቷ፣ በመጋቢት 10 ንባቡ የሰባተኛው ምዕት ንጉሥ ሕርቃል መስቀሉን ተዘርፎ ከተወሰደበት የፋርስ ግዛት ማስመለሱን በገሀድ አስቀምጦታል፡፡

 የመስከረም 17 ቀን በዓል በኮፕቲክ ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ ነው፡፡ የመጋቢት 10 በዓሉ ግን ለአንድ ቀን ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሁለቱ ቀናት በተጨማሪ ግማደ መስቀሉ የገባበት መስከረም 10 ቀን አፄ መስቀል፣ ግማደ መስቀሉ ባለበት ግሸን ማርያም ንግሡ መስከረም 21 ቀን የመስቀሉ ክብር ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደሚተረከው፣ መስቀል ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ተዳፍኖ ቆይቷል፡፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327) የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ይህን ታሪክ ትሰማ ነበርና አስቆፍራ ለማውጣት ጉዞዋን ወደ ኢየሩሳሌም ቀጠለች፡፡ እዚያም ደርሳ ገብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍርም መስቀሉ ያለበትን አላገኘችውም፡፡ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅላት አላገኘችም፡፡ በመጨረሻ ኪሪያኮስ የሚባል የዕሌኒን መቸገር አይቶ እንደሚከተለው ይመክራታል፡፡ ‹‹አንችም በከንቱ አትድከሚ ሰውም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ ከምረሽ ዕጣን አፍስሽበት በእሳትም አያይዥው የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኝዋለሽ›› አላት፡፡ እሷም ያላትን ሁሉ አደረገች፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አሳየ ያን ምልክት ይዛ አውጥታዋለች፡፡

የመስቀል በዓል ከአራተኛው ምዕት ዓመት ጀምሮ  መስከረም 16 ቀን የቤተክርስቲያን መታነፅና የደመራ ሥርዓት እንዲሁም መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል፡፡

የመስቀል በዓል፣ በኢትዮጵያ ለሁለት ሺሕ ግድም ዓመታት ሲከበር ኖሯል፡፡ የበዓሉን ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ገጽታ የተመለከተው ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ የዓለም ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ አድርጎ መመዝገቡ ይታወቃል፡፡

 ክብረ በዓሉ በትግራይና በአማራና ‹‹መስቀል›› ሲባል፣ በተለያዩ ብሔረሰቦች እንደየአካባቢው ቋንቋ የተለያየ መጠርያ አለው፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ‹‹ጉባ›› ወይም ‹‹መስቀላ››፣ በሀድያ፣ በወላይታ፣ በዳውሮ፣ በጋሞ፣ በጎፋ ‹‹መስቀላ››፣ በከምባታ ‹‹መሳላ››፣ በየም ‹‹ሔቦ››፣ በጉራጌ ‹‹መስቀር››፣ በካፊቾና ሻኪቾ ‹‹መሽቀሮ›› ይባላል፡፡ 

ግማደ መስቀል በኢትዮጵያ

በቤተክርስቲያን ታሪክ ላይ እንደተጻፈው፣ የመስቀሉ አንድ ክንፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ዐምባ ይገኛል፡፡ ግማደ መስቀሉ በአፄ ዳዊት ዘመን ከእስክንድርያ (ግብፅ) ሲመጣ ከመጨረሻ ስፍራው መስቀልያ ቅርስ ባለው ግሸን አምባ ከመድረሱ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ተዘዋውሯል፡፡ በዚህ ዘመን በሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ከሚከበርባቸው የዓዲግራቱ ቀንደ ዳዕሮና የመቐለው እንዳ መስቀል (ጮምዓ) አምባዎች እንዲሁም በተጉለት መስቀለ ኢየሱስ ግማደ መስቀሉ ለወራት ተቀምጦባቸው እንደነበር ይወሳል፡፡

የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥቲቱ ቅድስት ዕሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል በአይሁዶች ከተቀበረበት ለማውጣት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ የደመራ ሥነ ሥርዓቱ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡  በትግራይ፣ በላስታና ላሊበላ፣ በአክሱም፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣ በዋግ ሕምራ፣ በከፊል ጎጃምና በአዊ፣ በሽናሻ (ንጋት 11 ሰዓት) ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ  አካባቢዎች መስከረም 16 ቀን ምሽት ነው፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ ነገዶች ከመስከረም 13 ጀምሮ ደመራውና ከበራው ይቀጥላል፡፡

የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል መለያው ደመራው ነው፡፡ ደመራ ንግሥት እሌኒ፣ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል  ከተቀበረበት ለማውጣት በኢየሩሳሌም ቀራንዮ በሚባል አካባቢ በጎልጎታ ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ለማሰብ የሚከበር ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ የደመራ ሥነ ሥርዓቱ በመጠኑም ቢሆን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ በአክሱም፣ በዓዲግራት፣ በላስታ፣ ላሊበላ፣  በዋግ ሕምራ፣ በከፊል ጎጃምና በአዊ ዞን ደመራው መስከረም 16 ቀን ቢደመርም ሥርዓተ ጸሎቱ የሚካሄደውና ደመራው የሚለኮሰው መስከረም 17 ቀን ንጋት ላይ ነው፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በሸዋና በከፊል ጎጃም፣ በሐዲያ፣ በጉራጌ፣ በሸከቾ፣  ካፊቾ፣ ኮንታ ደመራው የሚበራው በዋዜማው መስከረም 16 ቀን ምሽት ነው ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን አቆጣጠር የመስከረም 17 የመጀመርያው ክፍል ነው፡፡ የደመራው አደማመርና አበራር ሥነ ሥርዓት ግን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ 

እንደ ዘመን መለወጫ

የመስቀል በዓል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፣ በገጠርም በከተማም፣ በደብርም በገዳምም እንደ ኅብረተሰቡ ባህልና ልማድ በታላቅ አክብሮት  በየዓመቱ ይከበራል፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ብሔረሰቦች እንደ ካምባታ፣ ሀዲያ፣ ኢሮብ፣ ትግራይ፣ ካፊቾ፣ ወላይታ፣ ሸክቾ፣ ኮንታ ወዘተ ያሉት እንደ ዘመን/ወቅት መለወጫ ይቆጥሩታል፡፡ በተለይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በሸከቾ በመሽቀሬ ባሮ በዓል ላይ ደመራ ነዶ ሲያበቃ አስራ ሁለት ጉማጅ እንጨቶችን ከውስጡ በመልቀም ስልቻ ውስጥ ያስቀምጡና አንድ ወር ባለፈ ቁጥር አንድ ጉማጅ እየተጣለ ከአሥራ ሁለት ላይ ሁለት ጉማጆች ብቻ ሲቀሩ የዘመን መለወጫ በዓል እየደረሰ መሆኑንና ድግሱ ከወዲሁ መጀመር እንዳለበት ኅብረተሰቡን ያሳስቡታል፡፡

ወላይታዎች የአዲስ ዘመን ብሥራትን ‹‹ጊፋታ›› በማለት ይጠሩታል፡፡ ጊፋታ/ ግፋታ ማለት ትርጉሙ በኩር ወይም ታላቅ ማለት ሲሆን፣ ብሔረሰቡ አዲስ ዓመትን አንድ ብሎ የሚጀምርበት የአዲስ ዓመት መግቢያ ብቻም ሳይሆን የብርሃን ጊዜ ማብሰሪያ ነው፡፡

የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እትም ላይ እንደሰፈረው፣ ጊፋታ ማለት ባይራ (ታላቅ)፣ መጀመሪያ እንደ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል፡፡ ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን የመስቀል በዓል አከባበር ከተቀረው የዓለም ክፍል የተለየ፣ ወቅቱም ክረምቱ አልፎ የበጋ በመሆኑ በዓሉ ካለው ሃይማኖታዊ ፋይዳ ባሻገር በርካታ ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይጠቀሳል፡፡

በመስቀል በዓል ተለያይተው የኖሩ የቤተሰብ አባላትና ዘመዳሞች የሚገናኙበትና የሚጠያየቁበት፣ ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን የሚፈቱበትና የሚረዳዱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበትና ራሳቸውን ለጋብቻ የሚያዘጋጁበት፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ቤተሰቦች የሚጠያየቁበት፣ የተጣሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና በጥል የተለያዩ ባልና ሚስቶች ባጠቃላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታት እርቅ የሚወርድበትና ሰላም የሚሰፍንበት እንደሆነ የቅርስ ባለሥልጣን ድርሳን ያትታል፡፡ 

ምርቃት

ክብረ በዓሉን ከሚገልጹት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ ምርቃት ነው፡፡ ለዓይነት የስድስት ብሔረሰቦች አመራረቅ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘነውን እነሆ፡፡

በሀዲያደመራ የሚቀጣጠለው መስከረም 16 ሲሆን፣ መጀመሪያ በዕድሜ ትልቅ የሆኑ በየመንደሩ ያሉ አዛውንቶች ‹‹እንኳን በሰላም አደረሰን እንኳን በሰላም ብርሃን አየን ከጨለማም ወጣን›› እያሉ በመመረቅ ችቦ ይለኩሳሉ፡፡ ከዚያም ወጣቶች እየተጫወቱ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ ሲነጋጋ ከብቶች ደመራውን ይዞራሉ፡፡

በወላይታ፣ ጨዋታው ሲያበቃ ለመስቀል የታረደውን በሬ እየተመገቡ ይመራረቃሉ፡፡ ‹‹እስከ መጨረሻው እንኖራለን የዳሞታ ተራራ እንደኖረ፣ የኮይሻ ተራራ እንደኖረ እኛም እንኖራለን፡፡ አህያ ቀንድ እስኪያወጣ እንኖራለን፡፡ ኮንድቾ (በጣም አጭር እንጨት) ምሰሶ እስከሚሆን እንኖራለን፤›› እያሉ መጪውን ዘመን በተስፋ በመቀበል ይለያያሉ፡፡

በሸከቾ፣ በበዓሉ ቀን ጧፍ በማብራት በየጓዳው በየእህል ማስቀመጫው ይዞ በመግባት ‹‹መጥፎ ነገር ከቤት ውጣ፣ ሀብት ግባ›› እያሉ ከመረቁ በኋላ ጎረቤት ተጠራርቶና ተሰባስቦ ችቦ ይበራል፡፡ በነጋታው የእርድ ሥርዓት የሚከናወን ሲሆን ቤተሰብና ጎረቤት በመስቀል ይጠራራል ይገባበዛል፡፡

በየም፣ በዋዜማው ሌሊት ሊነጋ አቅራቢያ ‹‹የረሀብ ምንቸት ውጣ ጥጋብ ግባ›› በማለት ችቦ ከተለኮሰ በኋላ ወደ ደመራው ቦታ ሁሉም ያመራል፡፡ ደመራው በአዛውንቶች ተመርቆ ይለኮሳል፡፡

በካፍቾ፣የደመራ በዓሉም የሚከበረው በባህላዊ እምነት መሪው ግቢ ውስጥ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ሰው ችቦ በየቤቱ ለኩሶ በራሱ ቤት ዙሪያ በመዞር ድህነት ውጣ፣ ሀብት ግባ ብሎ መልካም ምኞቱን ከገለጸ በኋላ የተቀጣጠለውን ችቦ የባህላዊ እምነት መሪው ግቢ በተዘጋጀው ደመራ ላይ ወስዶ ይለኩሳል፡፡ በማግስቱ ሠንጋ ይታረድና የደመራው እሳት በነደደበት ቦታ ላይ እሳቱን ለማቀዝቀዝ ሲባል ደም ይፈስበታል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ደሙን በእጁ በመንካትና ከአመድ ጋር በመለወስ ግንባሩ ላይ ይቀባል፡፡

      በጎፋ፣‹‹ማስቃላ ዮ! ዮ!›› እያሉ የተለያዩ የበረከት ሐሳቦችን ይለዋወጣሉ– መስቀል እንኳን መጣህልን እንደማለት ነው፡፡ አስከትለውም እየደጋገሙ፣ እየተቀባበሉ፡-

‹‹ማስቃላ ዮ! ዮ! ዳናው ዳና

አልባ ዙማዳን ዳና

ክንቲ ሻላዳን ዳና

መሪናው ዳና

ሀረይ ካጨ ከሳናዳን

ገላኦ ገል ውራናስ ዳና›› ይላሉ፡፡

ትርጉሙም እነሆ፡- አልባ ዙማ በአካባቢው የሚገኘው ትልቅ ተራራ ሲሆን፣ እንደሱ እንኖራለን እንደ ማለት ነው፡፡ ክንቲ ሻላ ማለት በአካባቢው የሚገኘው ትልቁ አለት ሲሆን እንደሱ እንኖራለን፣ ለዘለዓለም እንኖራለን ማለት ነው፡፡ አህያ ቀንድ እስከሚያበቅል ድረስ እንኖራለን፡፡ ሁሉም ልጃገረዶች እስኪያገቡ ድረስ እንኖራለን፡፡ እንዲህ እያሉ እርስ በርስ ይሸካከማሉ ይተቃቀፋሉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...