Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሁለት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኃይል ምንጭ ግብዓት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፓዮኒር ሲሚንቶና ኩዩ ሲሚንቶ የተባሉ ሁለት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ለማምረት እንዲችሉ፣ ፔትሮሊየም ኮክ (Petroleum Coke) የተባለ በከሰል ድንጋይ ምትክ የሚውል የምርት ግብዓት ከቀረጥና ከታክስ ነፃ እንዲያስገቡ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ ቀረበ፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፈው የድጋፍ ደብዳቤ መሠረት፣ ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የግል ማኅበር (ኖክ) ለፋብሪካዎቹ ይህንን ምርት ለማስመጣት የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፉ የጠየቀ ሲሆን፣ የምርቱ መምጣት ፋብሪካዎቹን በሙሉ አቅም እንዲያመርቱ ጥሩ የኃይል ምንጭ በመሆን እንደሚያገለግል ገልጿል፡፡

ሰኞ መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የማዕድን ሚኒስቴር ለገንዘብ ሚኒስቴር የጻፈው የድጋፍ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ሁለቱ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት የማምረቻ ቴክኖሎጂ ቨርቲካል ኪልን (Vertical Kiln) ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂም የሚወስደው የኃይል ምንጭ ፔትሮሊየም ኮክ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ከሁለቱ ፋብሪካዎች በተለየ በአገሪቱ ያሉ አብዛኛዎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የከሰል ድንጋይን እንደ ኃይል ምንጭነት የሚጠቀሙ ናቸው፡፡

ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንና የማምረት ቴክኖሎጂያቸውን ወደ ሆሪዞንታል ኪልን (Horizontal Kiln) በመቀየር የከሰል ድንጋይ በመጠቀም ማምረት እንዳለባቸው፣ በማዕድን ሚኒስትሩ ታከሉ ኡማ (ኢንጂነር) ተፈርሞ ለገንዘብ ሚኒስቴር የተጻፈው ደብዳቤ ይገልጻል፡፡ ፋብሪካዎቹም በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚቀየሩ ደብዳቤው ገልጿል፡፡

በዚህ ዓይነት የግብዓት ምርት እጥረት ሁለቱ ፋብሪካዎች ምርት እንዳያቆሙና የያዙትን የምርት ዕቅድ እንዲያሳኩ ድጋፍ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡ ፓዮኒር ሲሚንቶ በበጀት ዓመቱ 610,000 ቶን ለማምረት ያቀደ ሲሆን፣ ኩዩ ሲሚንቶም ተመሳሳይ ይዞት ያለው የሲሚንቶ ምርት ለማምረት አቅዶ ነበር፡፡ ይህን ዕቅድ ለማሳካት ለእያንዳንዳቸው ፋብሪካዎች 50,000 ቶን ፔትሮሊየም ኮክ የሚበቃ በመሆኑ፣ የገንዘብ ሚኒስቴርም የዚህን ኃይል ምንጭ ምርት ለማስገባት ነው የቀረጥና ታክስ ነፃ ድጋፉን እንዲያደርግ የተጠየቀው፡፡

ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) በኢትዮጵያ የተለያዩ የነዳጅና ተመሳሳይ የኃይል አማራጮችን የሚሸጥ ኩባንያ ሲሆን፣ ለሁለቱ ፋብሪካዎችም ፔትሮሊየም ኮክ ምርትን እንዲያስመጣና ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ የማዕድን ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲያደርግለት፣ መስከረም 13 ቀን 2015 ዓ.ም. መጠየቁን የማዕድን ሚኒስቴር ደብዳቤ ይገልጻል፡፡

በአገሪቱ ያለው የከሰል ድንጋይ ሀብት ከፍተኛ እንደሆነ በማስታወቅ፣ እሱን እያጠቡ እንዲጠቀሙ የሲሚንቶ አምራቾች ግፊት የሚደረግባቸው ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ጥር ወር 2014 ዓ.ም. ከዚህ በፊት አምራቾቹ ከውጭ እያስመጡ ይጠቀሙበት የነበረውን አሠራር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲቀይሩ ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያም የከሰል ድንጋይ በመጠቀም የሚያመርቱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ በአገር ውስጥ ያለውን የከሰል ድንጋይ መጠቀም መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ አገሪቱ የያዘችውን የከሰል ድንጋይ ከውጭ ማስመጣት የማቆም ዕቅድን ለማሳካት፣ ስምንት ድርጅቶች የከሰል ድንጋይ ማጠቢያ ፋብሪካ ለማቋቋም ባለፈው ዓመት ጥር ወር 2014 ዓ.ም. ፈቃድ ወስደው እንደነበር አይዘነጋም፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች