Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ተቋማት አዲስ ሠራተኛ እንዳይቀጥሩ የሚደነግግ መመርያ አወጣ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ተቋማት አዲስ ሠራተኛ እንዳይቀጥሩ የሚደነግግ መመርያ አወጣ

ቀን:

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንግሥት ተቋማት ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ፈቃድ ሳያገኙ፣ አዲስ የሥራ መደብ ከፍተው፣ አዲስ ሠራተኞችን እንዳይቀጥሩ የሚደነግግ መመርያ አወጣ፡፡ ተቋማቱ በበጀት ዓመቱ መጀመርያ ላይ በዕቅድ አቅርበው ካልፀደቀላቸው በስተቀር፣ የኮንትራት ሠራተኞችን መቅጠር እንደማይችሉ በመመርያው ተገልጿል፡፡

በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሐሰን ተፈርሞ የወጣው የመንግሥት ተቋማት የወጪ ቅነሳና ቁጠባ መመርያ፣ የመንግሥት ተቋምት የሀብት አጠቃቀምና የወጪ አስተዳደር ላይ ክልከላን የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ለ2015 በጀት ዓመት የሚያገለግለው ይኼ መመርያ ተቋማት የአበል፣ የትራንስፖርት፣ የግዥና ተመሳሳይ ወጪዎችን ለመቀስነ ገደቦችን አስቀምጧል፡፡

የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግሥት ዲቢሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥት ይህንን መመርያ ያወጣው ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የሚሰበሰበው ገቢ እየቀነሰና ካለው ፍላጎት ጋር እየተጣጣመ ባለመሆኑ ነው፡፡

‹‹በተለይ በመተከልና በካማሺ ዞኖች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ገቢ እየተሰበሰበ አልነበረም፤›› ያሉት ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ከዚህም በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት ትኩረት ያደረገበት የመልሶ ግንባታ ተጨማሪ ወጪን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ፣ ‹‹በክልሉ ያለውን ውስን ሀብት ካለው የበዛ ፍላጎት ጋር አጣጥሞ ለመሄድ›› ይህንን መመርያው ማውጣት አስፈላጊ  ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ኃላፊዋ እንደሚያስረዱት፣ በመመርያው ውስጥ የተካተቱት አሠራርና ግዴታዎች በተለያየ መንገድ በሰርኩላር ተላልፈው የነበሩ ቢሆኑም፣ አፈጻጸም ላይ ጉድለት እንዳለባቸው በጥናት የተረጋገጡ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት በሰርኩላር የተላላፉት ትዕዛዞች የሕግነት ቅርፅ ይዘውና ተጠያቂነትን በሚያስከትል መንገድ እንዲፈጸሙ ሲባል መመርያው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በመመርያው ውስጥ ወጪን ለመቀነስ ተብለው ከተቀመጡት ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው፣ የሠራተኛ ቅጥርና ለሠራተኞች ለአበልና ለትራንስፖርት የተመደቡ ወጪዎች ናቸው፡፡ መመርያው እንደሚያስረዳው በተያዘው በጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቅጥር መፈጸም የሚችሉት፣ የተለቀቀ የሥራ መደብን ለመተካት ወይም ቀድመው ዕቅድ ውስጥ ባስገቡት መሠረት በጀት ለተያዘለት የሥራ መደብ ብቻ ነው፡፡

መመርያው፣ ‹‹በክልሉ መንግሥት ውሳኔ በአዲስ የተከፈተ አደረጃጀት ካልሆነ በስተቀር፣ አዲስ ክፍት መደብ መክፈትም ሆነ አዲስ ቅጥር መፈጸም አይቻልም፤›› የሚል ንዑስ አንቀጽ ይዟል፡፡ የኮንትራት ቅጥርንም በተመለከተ አስቀድሞ የተፈቀደና በጀት ያልተያዘለት ካልሆነ በስተቀር ቅጥር ማከናወን ተከልክሏል፡፡

በክልሉ የ2013 ዓ.ም. መረጃ መሠረት ከ32 ሺሕ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ትዕግሥት፣ ይህ የሰው ኃይል ብዛት ‹‹ከፍተኛ›› እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ትዕግሥት ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ባለው ‹‹የአሠራር ልምድ›› መሠረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በራሳቸው አዳዲስ መዋቅሮችን ዘርግተውና ክፍት የሥራ መደብ አዘጋጅተው የተጨማሪ ሠራተኞች ቅጥር ይፈጽሙ ነበር፡፡

‹‹ይህንን የሰው ኃይል እንዴት ውጤታማ አድርገን እንጠቀማለን የሚለው ላይ ነው ትኩረታችን፤›› ሲሉም በመመርያው ላይ ክልከላው የተቀመጠው፣ በመሥሪያ ቤቶች የሚተገበረውን የአዲስ ሠራተኛ ቅጥር በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መመርያው ለሠራተኞች የሚሰጡ አዳዲስ የጥቅማ ጥቅም ዓይነቶችን በተመለከተም፣ መሥሪያ ቤቶቹ በራሳቸው ማፅደቅና በሰርኩላር ማስተላለፍ እንደማይችሉ አስቀምጧል፡፡ ጥቅማ ጥቅሞች በቅድሚያ በክልሉ ካቢኔ መፅደቅ እንዳለባቸውም ደንግጓል፡፡

የትራንስፖርት አጠቃቀምን በተመለከተም የመሥሪያ ቤቶች ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች ለመስክ ሥራ በሚወጡበት ጊዜ የሚሄዱበት አካባቢ የትራንስፖርት ተደራሽነት ያለው ከሆነ፣ በሕዝብ ትራንስፖርት እንዲጓጓዙና መኪና እንዳይመድቡ ታዟል፡፡ የመኪና ሥምሪት ማድረግ የሚቻለው የሕዝብ ትራንስፖርት በሌለባቸው አከባቢዎች እንዲሆን፣ ሲመደብም ሠራተኞቹ በተናጠል ሳይሆን በቅንጅት መጠቀም እንደሚኖርባቸው በመመርያው ላይ ሠፍሯል፡፡

ከዚህም ባሻገር የክልሉ ካቢኔ አባል ከሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በስተቀር፣ በተያዘው በጀት ዓመት የላፕቶፕ፣ የሞባይልና የኢንተርኔት ራውተር መግዛት እንደማይቻል ተደንግጓል፡፡

መመርያው በግዥ ላይ ያስቀመጣቸው ትዕዛዞች ከክልሉ በጀት ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚወስደውን ወጪ ለመቀነስ ያሰበ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በተጀመረው የ2015 በጀት ዓመት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የያዘው በጀት 6.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የክልሉ መንግሥት ከሚያገኘው የሚሸፈነው 2.56 ቢሊዮን ወይም 38.2 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የፌደራል መንግሥት ዘንድሮ ለክልሉ የበጀተው 3.6 ቢሊዮን ብር የድጎማ በጀት፣ የክልሉን አጠቃላይ በጀት 53.7 በመቶ ይሸፍናል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከሚቀጥለው ወር አንስቶ ተፈጻሚ የሚሆን የአምስት ዓመት የመልሶ ግንባታ ዕቅድ ማፅደቁን፣ ለዚህም 38.5 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...