Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሌላው የማራቶን ታሪካዊ የክብረ ወሰን ቀን በበርሊን

ሌላው የማራቶን ታሪካዊ የክብረ ወሰን ቀን በበርሊን

ቀን:

በጀርመን ትልቋና ዋናዋ ከተማ በርሊን አዳዲስ የአትሌቲክስ ታሪኮች መጻፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዓመታዊ የማራቶን ውድድር አዲስ ክስተት የማያጣው የበርሊን ማራቶን ዘንድሮም ሌላ ታሪክ ማስመዝገብ የተቻለበትን አጋጣሚ አሳይቶ አልፏል፡፡ እሑድ መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የበርሊን ማራቶን በሁለቱም ፆታ አገር ጉድ ያስባለ ክብረ ወስን ተመዝግቧል፡፡

ወትሮም ክብረ ወሰን የማያጣው የበርሊን ጎዳና ዘንድሮ ደግሞ በሁለቱም ፆታ አዲስ ክብረ ወሰን መመዝገብ በመቻሉ አግራሞት ፈጥሯል፡፡ በሴቶች ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ 2፡15፡37 በሆነ ጊዜ የዓለም ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፋለች፡፡ ግና የመጀመሪያዎቹን አጋማሽ ኪሎ ሜትር ያጋመሰችበት ሰዓት የተመለከቱ ‹‹ትዕግሥት በበርሊን ጎዳና ላይ እየበረረች ነው፤›› ሲሉ ሙገሳ ያስቸራትን ብቃት አሳይታለች፡፡ አትሌቷ የ42 ኪሎ ሜትሩን ግማሽ 1፡08፡13 ማጋመስ ችላለች፡፡

የ28 ዓመቷ ትዕግሥት ባለፈው መጋቢት ወር በሳዑዲ ዓረቢያ ማራቶን ላይ ከገባችበት 2፡34፡00 ሰዓት 20 ደቂቃ በማሻሻል ጭምር አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ በዚህም ትዕግሥት የዓለም ሦስተኛው የማራቶን ፈጣን ሰዓት ማስመዝግብ ስትችል፣ ኬንያዊቷ ብርጊድ ኮስጊ (ቺካጎ ማራቶን 2019 2፡14፡04)፣ ፓውላ ራድክሊፍ (2፡15፡25 ለንደን ማራቶን 2003) በመቀጠል አዲስ ታሪክ ማጻፍ ችላለች፡፡ ትዕግሥት የውድድር ቦታውን ክብረ ወሰን ከማሻሻል ባሻገር፣ ብሔራዊ ክብረ ወሰን ጭምር አሻሽላለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ዝግጅቴ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ የምፈልገውን መከወን ችያለሁ፡፡ ልምምዴ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፤›› በማለት ከውድድሩ በኋላ ትዕግሥት አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

በሴቶች ማራቶን ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን ማራቶን (2፡17፡56)፣ ወርቅነሽ ደገፋ ዱባይ ማራቶን (2፡17፡41)፣ እንዲሁም የዓለም ዘርፍ የኋላ ዘንድሮ በጀርመን ሀምቡርግ ማራቶን (2፡17፡23) በመግባት ፈጣን የማራቶን ሰዓት ማስመዝገብ የቻሉ ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ናቸው፡፡

ትዕግሥት የእነዚህን አትሌቶች ሰዓት ከማሻሻል በዘለለ ‹‹ትዕግሥት አሰፋ እንደ አበበ ቢቂላ›› የሚል ሙገሳም ሊሰጣት ያስቻላት ሲሆን፣ ይህም አበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ ማራቶንን በጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም ሲያሸንፍ የገባበት ሰዓት 2፡15፡16 ሲሆን፣ መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ትዕግሥት የበርሊን ማራቶንን ስታሸንፍ የቦታውና የኢትዮጵያ ክብረ ወሰን ያሻሻለችበት ሰዓት የአበበን ያህል ነው አስብሏታል፡፡

በውድድሩ ኬንያዊቷ ሮስመሪ ዋንጂሩ 2፡18፡03 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ፣ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ትዕግሥት አብአያቸው 2፡18፡03 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ ወርቅነሽ ኢዴሳ 2፡18፡51 በሆነ ሰዓት አራተኛ እንዲሁም መሠረት ሲሳይ 2፡20፡58 አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ የቻሉ ኢትዮጵያውያት  ናቸው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለመጪው ፓሪስ ኦሊምፒክ ለሚኖራት መሰናዶ ተስፋ የሚሆኑ አትሌቶችን ያየችበት ውድድር ሆኗል፡፡

በወንዶች ኬንያዊው ኤሎድ ኪፕቾጌ የራሱን ሰዓት በማሻሻል ማሸነፍ ችሏል፡፡ ኪፕቾጌ ርቀቱን 2፡01፡39 በማጠናቀቅ እ.ኤ.አ. 2018 በርሊን ማራቶን 2፡01፡39 በማሻሻል የማራቶን ንግሥናውን አስቀጥሏል፡፡

የ37 ዓመቱ ኬንያዊ በ17 ማራቶኖች ላይ ተሳትፎ 15ኛውን ድሉን ተቀዳጅቷል፡፡ ለአራተኛ ጊዜ የበርሊን ማራቶን ማሸነፍ የቻለው ኪፕቾጌ (2015፡2017፡2018 እና 2022)፤ የመጀመሪያውን 21 ኪሎ ሜትር 59፡51 ያጋመሰው ሲሆን ቀሪውን ኪሎ ሜትር 61፡18 ሮጦታል፡፡

ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች አስተያየቱን የሰጠው ኪፕቾጌ፣ ‹‹የመጀመሪያውን ግማሽ 60፡50 እንዲሁም የሁለተኛውን 60፡40 በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ አለብኝ ብዬ ነበር፡፡ በእርግጥ እግሮቼም በጣም ፈጥነው ነበር፡፡ እስኪ 2፡00 ሰዓት ላይ ላጠናቅቅ ብዬም ሳስብ ነበር፡፡ ግን ምንም ሆነ ምንም አሁን ደስተኛ ነኝ፤›› በማለት ተናግሯል፡፡

ከዓመት ዓመት የማራቶን የውድድር ክብረ ወሰን እያሻሻለ የመጣው ኪፕቾጌ  የበርሊን ማራቶንን አራት ጊዜ ማሸነፍ ከቻለው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጋር ታሪክ መጋራት ችሏል፡፡ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በበርሊን ማራቶን በተሳተፈበት (2006፣ 2007፣ 2008 እና 2009 ዓ.ም.) በተከታታይ ማሸነፍ ችሏል፡፡

በእሑዱ ወድድር ላይ ታዱ አባተ 2፡06፡28 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ አንዱአምላክ በልሁ 2፡06፡40 አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

ቀድሞ የማይደፈሩት የአትሌቲክስ ክብረ ወሰኖች፣ ከቅርብ ጊዜ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተሻሻሉ መምጣት ከጀመሩ ሰንባብተዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተለያዩ መላምቶች ቢጠቀሱም በየዓመቱ እየተሻሻሉ የመጡት ዘመናዊ የመሮጫ ጫማዎች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...