Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የግሉ ዘርፍና የሕፃናት ማቆያዎች ዕጦት

  የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ሴቶች ለትምህርት ያልደረሱ ልጆቻቸውን የሚያውሉበት ማቆያ በየተቋማቱ እንዲስፋፋ መደረጉ ሊደገፍ የሚገባ በጎ ጅማሮ መሆኑ ይወሳል፡፡ በመሠረቱ ሴቶች በቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ባሻገር ሰፊ ሚና አላቸው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ ትውልድ እንዲቀጥል የማድረጉ ሥራ በተለይ ለሴቶች የተሰጠ የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድና በድኅረ ወሊድ ወቅት የተለየ እንክብካቤ ሊደረግላቸውና ጤናቸውም የሚጠበቅበት ሁኔታዎች ሊመቻችላቸው እንደሚገባ በየጊዜው ማሳሰቢያ ይሰጣል፡፡ ከነዚህም ሁኔታዎች መካከል አንደኛው የሕፃናት ማቆያዎችን ማመቻቸት ይገኝበታል፡፡ በዚህና ተያያዥ በሆኑ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የሴቶች መምሪያ ኃላፊን ወ/ሮ ራሔል አየለን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- በግሉ ዘርፍ በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው ተቀጣሪ የሆኑ እናቶች ምን ያህል በሕፃናት ማቆያ እጦት ይቸገራሉ? እናቶችን ከዚህ ችግር ለማላቀቅ ምን ዓይነት ጥረት እየተደረገ ነው?

  ወ/ሮ ራሔል፡- በግሉ ዘርፍ በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው በተወሰነ መልኩ ለትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት ማቆያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኛ እንደ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ በሚሻሻልበት ጊዜ የሕፃናት ማቆያዎች ለሴት ሠራተኞች በጣም አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ በኅብረት ስምምነት ውስጥ እንዲካተት አድርገናል፡፡ ይህም ማለት በኅብረት ስምምነት ውስጥ ከሚካተቱት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የሕፃናት ማቆያዎችን ማስፋፋት የሚመለከት ነው፡፡ ማቆያዎች ሴት ሠራተኞች ሥራቸውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲያከናውኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የኢንዱስትሪውም ምርታማነት ያድጋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ሴቶች ወደ ኢንዱስትሪው እየገቡ ነው፡፡ በሚወልዱበት ጊዜ ሕፃኖቻቸውን በእንክብካቤ የሚይዝላቸው ከማጣት የተነሳ ከሥራቸው ተስተጓጉለው ቤት የሚውሉበት፣ አንዳንዴም ሥራቸውን ጨርሰው የሚለቁበት አጋጣሚ ሲከሰት ይስተዋላል፡፡ ኢሠማኮም አምራች ኢንዱስትሪዎች ችግሩን ተረድተው ማቆያዎችን የማስፋፋት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫና የጉትጎታ (አድቮኬሲ) ሥራዎችን ቀጣይነትና ተከታታይ ባለው መንገድ እያከናወነ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- እያደረጋችሁት ያለው ግንዛቤ የማስጨበጡና የጉትጎታ ሥራ ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ የሆነበት ወይም በተወሰኑ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ማቆያዎች እንዲቋቋሙ ያደረጋችሁትን እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

  ወ/ሮ ራሔል፡- ቀደም ብዬ የገለጽኩትን አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ እንደ ኢሠማኮ ዋነኛ ሥራችን ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር ላይ ያተኮረ መሆኑ ሊታወቅልን ይገባል፡፡  ከዚህም ሌላ የሴት ሠራተኞችን በተመለከተ ከወሊድ ጋር የተያያዘ የወሊድ ፈቃድ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግበት ከማድረግ ባሻገር የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ ተሞክሯል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢሠማኮ ከጣሊያን ትሬድ ዩኒየን ጋር በመተባበር በኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ለትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት ማቆያ አሠርተን አስረክበናል፡፡ የማቆያው መቋቋም ከተጠቀሰው ዩኒየን ጋር በመተባበር ልንተገብራቸው ከያዝናቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛው ነው፡፡ በዚህ ማቆያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ 50 ጨቅላ ሕፃናት እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፡፡ ማቆያው በሠለጠነ የሰው ኃይልና በቁሳቁስ በሚገባ የተደራጀ ነው፡፡ ማቆያውን በዚህ ፋብሪካ ውስጥ ለማቋቋም የተቻለበት ምክንያት በአገሪቱ ከሚገኙ ፋብሪካዎች ሁሉ ብዙ የሴት ሠራተኞችን በመያዝ ግንባር ቀደም በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለሕፃናቱ ወላጆች ብቻ ከቤታቸው ወደ ፋብሪካው፣ ከሥራ በኋላ ደግሞ ከፋብሪካው ወደ ቤታቸው የሚያመላልስ ሚኒባስ ወይም የተለየ ሰርቪስ ተመድቦላቸዋል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- በሌሎች ኢንዱስትሪዎች ውስጥም ይህን መሰሉን የሕፃናት ማቆያ የማቋቋም ዕቅድና በዘርፉ የሚሠሩ እናቶች ሸክም እንዲቀል በማድረግ ረገድ የሠራችሁት ሥራ አለ?

  ወ/ሮ ራሔል፡- በዚህ ዙሪያ ፍላጎት ያላቸውን ተቋማት በማወያየት በኅበረት ስምምነቱ መሠረት የሕፃናት ማቆያዎችን ለማስፋፋት የሚያስችል ዕቅድ ተሠርቷል፡፡ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ይህንን በሚመለከት በቂ መረጃ ምናልባት ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ማግኘት ይቻል ይሆናል፡፡

  ሪፖርተር፡- በግሉ ዘርፍ የሕፃናት ማቆያዎች እንዲስፋፋ የሚያስችሉ ከፖሊሲና ከሕግ ማዕቀፎች ጀምሮ የተከናወኑ ሥራዎች አሉ፡፡ ይህንን እንዴት ይገመግሙታል?

  ወ/ሮ ራሔል፡- በመሠረቱ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸው በጣም ጥሩ ነው፡፡  ማቆያዎችን በማስፋፋት ረገድም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያረበክታሉ ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን ወደ መሬት ወርደው ተግባራዊ ሲሆኑ አይታዩም፡፡ ለተግባራዊነታቸውም ሰፋ ያለ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራና የኢንዱስትሪው ወይም የድርጅቶች ፈቃደኝነትንና ትብብርን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢሠማኮ በዚህ ዙሪያ የያዘውን ወይም እያካሄደ ያለውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ለትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት ማቆያዎችን በየተቋማት የማስፋፋት ነገር ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ትልቁ ነገር የበጀትና የሠለጠነ የሰው ኃይል ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ጉዳይ በምን መልክ ነው መስተካከል የሚችለው? በማስፋፋቱ ሥራ ላይ እንደ ችግር ሆኖ የሚታየው ምንድነው?

  ወ/ሮ ራሔል፡- ለትምህርት ያልደረሱ ሕፃናት ማቆያዎች ሲቋቋሙ ከዚሁ ጋር አብረው ተያይዘው የሚነሱ ወይም የሚመጡ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከሚነሱትም ችግሮች መካከል አንደኛው የሞግዚቶች ጉዳይ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በጀቱ ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ ማቆያ ብቻ ቢያነስ ሁለት ሞግዚቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህም በሕፃናት አያያዝና እንክብካቤ የሠለጠኑና ከማንኛውም የበሽታ ዓይነት ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ከቀሰሙት ሥልጠና አኳያ ሲታይ ወርኃዊ ደመወዛቸውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዚህም ሌላ የኤሌክትሪክና የውኃ ወጪዎች ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ እንደ እኔ እምነት ግን የሚያስፈልጉትን ወጪዎች ሁሉ ተቋማቱ መሸፈን አለባቸው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተቋማቱ ተጠቃሚ በመሆናቸውና አንድም ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ እንደ ችግር ሆኖ የሚታየው ምንድነው? ለተባለው የተቋማት ፈቃደኛ አለመሆን ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ማቆያዎችን የማቋቋም ሥራ እንደ ወጪ ብቻ አድርገው ስለሚያዩት ነው፡፡

   

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰሜኑ ጦርነት የተበላሹ ብድሮች ከባንኮች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ አይነሱም ተባለ

  ልማት ባንክ አሥር ቢሊዮን ብር ታማሚ ብድር እንዲነሳለት ጠይቋል የኢትዮጵያ...

  የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥያቄ ቀረበ

  በመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ከአቶ ደመቀ መኮንን...

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...

  የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

  ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የቤት ፍላጎትንና አቅርቦትን ለማጣጣም የተነሳው ተቋም

  በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ሲፈተኑ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙ ኖሯቸው መኖሪያ ቤት ለመሥራት...

  የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት የመቀየር ጉዞ

  ብርሃን ለሕፃናት የማኅበረሰብ ተሃድሶ መርህን መሠረት በማድረግ፣ በዋናነትም አካል ጉዳተኛና ሌሎች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ለማገዝ ከ25 ዓመታት በፊት በጥቂት በጎ ፈቃደኞች የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡...

  ‹‹ኅብረተሰቡ አስፈሪ ብሎ የፈረጃቸውን ልጆች በመደገፍ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ እያሳየን ነው›› የቢቢአር ኤፍ የውባንቺ ፕሮጀክት ኃላፊ ፀደይ ተፈራ    

  የብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን  (ቢቢአር ኤፍ) በሕጋዊ መንገድ ከመመዝገቡ ከአራት ዓመታት በፊት አገልግሎት የሚሰጡት በበጎ ፈቃደኝነት ነበር፡፡ ለውባንቺ ፕሮጀክት መከፈት ምክንያት የሆነውም እነሱ በበጎ...