በጋሹ ሃብቴ (ዶ/ር)
በኢትዮጵያ በምግብ ራሳችንን መቻል እጅግ በጣም የተወሳሰበ ፈታኝና አዳጋች ግብ ነው። ይህም በዋነኝነት የሆነው ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያ በርካታ ምርታማነትን የሚፈታተኑ ችግሮች ገጥመዋት ስለነበሩ ነው። ከገጠሙዋት በርካታ ችግሮች መካከል የሶሻሊዝም ሥርዓት፣ የተዛቡና ሙሉ ያልሆኑ የመሬት ባለቤትነትና የአጠቃቀም ፖሊሲዎች፣ ጦርነት፣ ዘረኝነትና የተዛባ ሚዛናዊ ያልሆነ አስተዳደርን በዋነኝነት ይጨምራል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ከፈሩ ካስለቀቁ በጣም የቆየ በመሆኑ ወደ ቦታውና ተገቢ አቅጣጫ መልሶ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሙያተኞች እንደሚናገሩት ቀላል ሥራ ሊሆን በፍፁም አይችልም። ስለሆነም በምግብ ራሳችንን ለመቻል የግብርናን ውስብስብነት መረዳት እጅግ በጣም አስፈላጊ ይሆናል።
ለጉዳዩ እጅግ አስቸጋሪነት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋነኝነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል የሚከተሉትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል።
- በአሁኑ ሰዓት ከምናመርተው ምርት አኳያ ሲታይ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ ያላት አገር (በዓለም 12ኛ) በመሆኗና የሕዝቧም ቁጥር በፍጥነት እያደገ ያለ በመሆኑ፣
- 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በግብርና ዘርፍ ያለ ቢሆንም ለራሱም ሆነ ለገበያ የሚያመርበት መንገድ ኋላቀር በመሆኑ የሚመረተው ምርት ለራሱ የማይበቃና የማይተርፈው በመሆኑ፣
- በኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና ምርት የሚመረተው በዝናብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በቂ ዝናብ በማይኖርበት ወቅት የአገራችን ምርት በቀላሉ ስለሚዛባና ስለሚቀንስ፣
- ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶች እጥረትና ችግር በመኖሩና አብዛኞቹ ከውጭ አገር የሚገዙ በመሆናቸው፣
- ለእነዚሁ ግብዓቶች (ማዳበሪያ፣ የእርሻ መሣሪያዎች፣ ኬሚካሎች፣ ወዘተ) መግዣ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ምንጭና አማራጭ ችግር ያለብን በመሆኑ፣
- በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዘመናዊ ቴክሎጂ የመጠቀም ልምዳችን እጅግ ያልዳበረና ያላደገ በመሆኑ፣
- በተለያየ ጊዜ በነበሩበት የመሬት ባለቤትነትና ባለመብትነት ጋር ተያይዞ የገበሬው ይዞታ ከቤተሰብ ወደ ቤተሰብ በመተላለፉና በመከፋፈሉ የእርሻ መሬት ይዞታ በጣም እያነሰ የመጣ በመሆኑ፣
- ይኼው እያነሰ የመጣ ይዞታ ለዘመናዊ እርሻና ለሜካናይዜሽን አለመመቸቱ፣
- ከጥበት በመነሳት በተደጋጋሚ የታረሰ መሬት እጅግ በጣም አድርጎ ምርታማነቱ የሚቀንስ በመሆኑ፣
- ከይዞታ ማነስና ከምርት መቀነስ የተነሳ በርካታ በደን የተሸፈኑ ቦታዎች እየተመነጠሩ በመሆናቸው ለአየር መዛባት ምክንያት በመሆኑ፣
- ለእርሻ የማይሆኑ ተዳፋት ቦታዎች ካለምንም ቅድመ ዝግጅቶች ታርሰው የአፈር መታጠብ ረዘም ላለ ጊዜ ስለገጠመንና ለዚሁ ችግር ማስተካከያና ማረሚያ ምንም ዓይነት በተግባር የሚታይ ፖሊሲ ባለመኖሩ፣
- ባለፉት 75 ዓመታት የአገራችን የደን ሽፋን ከ45 በመቶ ወደ ሦስት በመቶ የቀነሰ በመሆኑ ተራሮች ተራቁተው በቂ ውኃ ስለማያቁሩና በክረምት እንጂ በበጋ በቂ የወንዝ ውኃ ስለማይለቁ ከወንዞች የሚገኝ ትነትና እርጥበት በማነሱ፣
- በተመነጠረው ደን ምክንያት ምንጮችና የትናንሽ ወንዞች ውኃ እየቀነሰና እየደረቁ በመምጣታቸው፣
- ሐይቆች በደለል እየተሞሉ በመሆናቸው ምርታማነታቸውና በአየር ጠባይ ላይ ተፅዕኖ በማድረጋቸው፣
- ባለሀበቶች ያለቸውን ሀብትና ዕውቀት ይዘው እንደማንኛውም ክፍለ ኢኮኖሚ በግብርናው ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚጋብዝና የተመቻቸ ፌዴራላዊም ሆነ ክልላዊ ፖሊሲ አመቺ አለመሆንና አለመኖሩ፣ ካለም አለመተግበሩ፣
- የሴቶችን ምርታማነት ለማሳደግ ለየት ያለ የግብርና ትምህርትና አገልግሎት አለመኖሩና መቀነሱ በሴቶች ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ፣
- ወጣቶች ወደ ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ገብተው በማምረት ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ የተዘጋጀና በሥራ ላይ የዋለ የማበረታቻ ፖሊሲና አገልግሎት በሰፊው አለመኖሩ፣
- ለአዳዲስና ትንንሽ ወደ ግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ለመግባት ለሚፈልጉ ማናቸውም ግለሰቦች አበረታች፣ አመቺና አነሳሽ የሆነ ፖሊሲ አለመኖሩ ወይም ቢኖርም ለመጠቀም በጣም አዳጋች በመሆኑ፣
- በዝናብ ወቅት የሚመረተውን ተረፈ ምርት ለበጋው ጊዜ ለማቆየት አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ የመጋዘንና የማቆያ አገልግሎቶች ባለመኖራቸው የምርት አቅርቦት የተዛባ መሆኑ፣
የኢትዮጵያ ግብርና ልማት ከዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ደኅንነት ጋር በጣም የተቆራኘ በመሆኑ በሌሎች አገሮች ያሉ ችግሮች የኢትዮጵያን የግብርና ግብዓትና ገበያ ስለሚያውኩ በዚያው ልክ የግብርናችንን ምርት የሚታወክ በመሆኑ ነው።
ከላይ የጠቀስኳቸውና ሌሎች በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የማነሳው በእነዚህና በሌሎች ላይ ከፍተኛ ርብርብ ካልተደረገ፣ በቀላሉ በምግብ ራሳችንን የመቻላችንን አዳጋችነት ለማሳየት ነው። እነዚህና ሌሎች ችግሮች ምርታማነታችንን የሚፈታተኑ መሆናቸውን በደንብ ከተገነዘብን በከፊልም ቢሆን መደረግ ስላለበት መጠቆምና መወያየት እንችላለን። ይህንንም ለማድረግ የሚመለከተው ሁሉ ፈቃደኛ መሆንና የበኩሉን ማድረግ አለበት።
በዚህ መሠረት እንደ መፍትሔ ጥቆማ በማድረግ ሦስት ዋነኛ ናቸው ተብለው ሊጠቀሱ የሚገባቸውን ጉዳዮች በጥቂቱም ቢሆን ሳነሳ፣ የመንግሥትና ያገባናል የሚሉ ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማስታወስ ነው።
- የግብርናና ከግብርና ጋር የተያያዙ በርካታ ፖሊሲዎች መሻሻል፣ መለወጥና አዲስ መውጣት ያለባቸው መኖራቸው ታውቆ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ ለማሳሰብ ነው።
በምግብ ራስን ለመቻል ሦስት የግብርና ምርት ምሶሶዎች፡- የምርታማነት ምሰሶ የሆኑት የግብርና ትምህርት የግብርና ምርምርና የግብርና ሥርጭት ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዞ ማየትና ያሉበትን ደረጃና ጥምረት፣ ከራሳችንና ከሌሎች አገሮች ተመክሮ አኳያ መመርመርና በተቻለ መጠን ክፍተት ባለበት ሁሉ ማስተካከያ ለማድረግ ጥረት ቢደረግ።
- ወሳኝና አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርት ማሻሻያ ግብዓቶች፡- ወሳኝና እጅግ አስፈላጊ ስለሆኑ ለግብርና ሥራ ምርታማነትና መሻሻል ስለሚያስፈልጉ፣ ግብዓቶችና የአመራረት ሁኔታዎችን በከፊልም ቢሆን መመልከትና ማንሳት ይሆናል።
የግብርና ፖሊሲ
የግብርና ፖሊሲ እጅግ ሰፊ በመሆኑ ምን መደረግ አለበት በሚል ከሙያው የተሰባሰቡ ባለሙያዎች ሊነድፉት የሚገባ ሲሆን፣ በዚህ ርዕስ ሥር ዋና ዋናዎቹንና ጥቂቶቹን ለማንሳት እፈልጋልሁ። የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ መሬትን የገበሬ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ መሬትን የመንከባከብ ግዴታ አብሮ አልተሰጠም። በመሆኑም የመጠቀም መብት እንጂ የመንከባከብ ግዴታ አልተሰጠውም። በመሆኑም የመጠቀም እንጂ የመንከባከብ ግዴታ የሌለበት ገበሬ፣ ከይዞታ ማነስና ከምርታማነት ማነስ በመነሳት መታረስ የሌለባቸውን ቦታዎች ያለ አፈር ጥበቃና አንዳች እርከን በማረስ ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር እንዲፈጠር ስላደረገ፣ መታረስ ለሌለባቸው ይዞታዎች ወይም ከታረሰም መሠራት ስላለበት የእርከን ፖሊሲ መውጣት አለበት። ይህ ካልሆነ የመሀሉና የደቡብ አገራችን ክፍሎችም የሰሜኑን ለመቀላቀል በጥፋት ላይ መሆናችውን ግንዛቤ መወሰድ አለበት፡፡
ግብርናን የማዘመን ፖሊሲ ትኩረት የሚሻና ምርት ለማሳደግ መውጣት ያለበት ፖሊሲ ነው። ይህንንም የማዘመን ፖሊሲ ተግባር ላይ ለማዋል የእርሻ መሣሪያዎች፣ የመሬት አጠቃቅም፣ ከዝናብ ሌላ የተለያዩ መስኖ ሥራዎች፣ አስፈላጊ የግብርና ኬሚካሎች መጠቀም፣ የተመረተ ማንኛውም ምርት እንዳይባክን ማድረግና ሌሎች ሥራዎችን በተግባር ላይ ማዋል ማለት ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ እንደ ማንኛውም ክፍለ ኢኮኖሚ የግለሰቦች ተሳትፎ የሚያሳድግ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ግለሰቦች ያላቸው ዕውቀትና ገንዘብ ይዘው የሚሳተፉበት ግብርና አሁን ከተያያዝነው ትንንሽና ምርታማ ያልሆኑ አሠራር ተላቀን፣ ሰፋፊ እርሻዎች የአገራችን እርሻ አካል ለማድረግ የሚረዳ ፖሊሲ ነው፡፡ በመሆኑም አበረታች ድጋፍና አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ ለግለሰብ ባለሀብቶች ጥሪ የሚያደርግ ፖሊሲ መኖርና መተግበር አለበት፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ የደን ልማት፣ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ፖሊሲ ተሻሽሎ እየገረጣ የሄደውን የአገራችንን የእርሻ መሬት ለማሻሻል የሚረዳ ፖሊሲ መውጣት አለበት። በአገራችን የደን መመንጠርና የአፈር መሸርሸር በአየር ሁኔታና ምርት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተገንዝበን፣ እጅግ ከፍተኛ ዘመቻ ሊደረግበት የሚገባ ዘርፍ በመሆኑ በፕላንና በበጀት የተደገፈ ተግባራዊነቱም ክትትል የሚደረግበት ፖሊሲ መኖር አለበት። የእንስሳት ሀብት ልማት ፖሊሲ ያለውን አሻሽሎ መጨመር፣ ያለውን ደግሞ በማከል ተፈጥሮ የሰጠንን ፀጋ በአግባቡ አጣጥሞ ለመጠቀም የሚረዳ ፖሊሲ ነው። በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ደግሞ አሥረኛ የሆነችው አገራችን ከዚህ ፀጋ በአግባቡ ስላልተጠቀመች የዘር ማሻሻል፣ የመኖ ማሻሻል፣ የከብት ሕክምና ማሻሻል፣ ዘመናዊ ዕርባታ፣ የገበያና የተለያዩ ሥራዎችን በዘርፉ ለማሻሻል የሚያስችል ፖሊሲ መቅረፅና በተግባር ላይ ማዋል ነው።
ከእነዚህ ዋና ዋና ካልኳቸው አምስት የፖሊሲ አርዕስቶች (የመሬት አጠቃቀም፣ ግብርናን የማዘመን፣ የግለሰቦች ባለሀብት ተሳትፎን ማሳደግ፣ የደን ምንጣሮ፣ የአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ የእንስሳት ልማት ፖሊሲዎች) በተጨማሪ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርት መጨመር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ፖሊሲዎች እንዳሉ በመጠቆም ጥቂቶቹን ለማንሳት እሞክራለሁ። ይህም ሊያጠቃልል የሚገባው ለግለሰብ የሚደረግ ድጋፍ ፖሊሲ፣ በጋራ መሠራት ስላለባቸው የግብርና ሥራዎች ፖሊሲ (መስኖ፣ ዘመናዊ መጋዘን፣ ዘመናዊ መጓጓዣ፣ ወዘተ) የሴቶችንና የወጣቶችን ምርታማነት በማሳደግ ፖሊሲ (ብድር፣ ገበያ፣ የወተት ጊደሮች፣ የዶሮ ጫጩቶች፣ የአትክልት ዘርና ችግኝ፣ የእርሻ መሣሪያ አገልግሎቶችና ሌሎችንም የሚጨምር) ይሆናል። ስለዚህ ፖሊሲን በተመለከተ ከላይ ያነሳኋቸውንና ሌሎች በርካታ በየዘርፉ ሊነሱና ሊተገበሩ የሚገባቸው ፖሊሲዎች መኖራቸውን በመጠቆም፣ ለዚህ ፖሊሲ ቀረፃ በርካታ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት አካል ተፈጥሮ ያለውን ፖሊሲ በመዳሰስና በመመዘን ሊሻሻልና አዲስ መኖር የሚገባው ፖሊሲ እንዲቀረፅና ተግባራዊነቱም ክትትል እንዲደረግበት ለመጠቆም እፈልጋለሁ።
በምግብ ራስን ለመቻል ሦስት የግብርና ምርት ምሰሶዎች
በግብርና ትምህርት አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከሕዝባችን ቁጥር ፍላጎት ጋር አጣጥሞ ለዘርፉ ሙያተኛ የማፍራት፣ ኃላፊነትንና ጥረትን ይጨምራል። ቻይናና ህንድ ሕዝባቸውን ለመመገብ ከተጠቀሙባቸው በርካታ ግብዓቶች አንዱ፣ በዘርፉ የሠለጠነና እጅግ ብዙ የተማረ ዜጋ ማፍራታቸውና በተግባር ሥራ ላይ በማዋላቸው ነው። ስለዚህ ባህላዊ ከሆነ አመራረት ሒደት ተላቀን ወደ ዘመናዊ እርሻ በመሸጋገርና በምግብ ራሳችንን መቻል ስላለብን የግብርናው ትምህርት ማሻሻል ይኖርብናል። በርካታ በዘርፉ የተማሩ ዜጎች ያስፈልጉናል። መማሩ ብቻ ደግሞ በቂ ስለማይሆን የተማሩትና ከተማሩ በኋላ የሚከፈሉበትን ሙያ በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው፣ የሚያረጋግጥ የአመራር ኃላፊነት ተነድፎ የካዱና የኢፒድ ልምድ በሥራ ላይ መዋል አለበት።
የእርሻ ምርምር በምግብ ራሳችንን ለመቻል እጅግ ወሳኝ ነው። ሆኖም ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍና ትኩረት የሚገባውን ያህል እንዳልሆነ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ ከጥቂት ዓመታት በፊት በእርሻ ምርምር ከሚሠሩ ተመራማሪዎች ዘጠኝ በመቶ ብቻ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ መሥሪያ ቤቱ የምሁራን ድርቀት የደረሰበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በበጀትም ከታየ በኢትዮጵያ በግብርና ከሚመረተው ጠቅላላ ምርት ገቢ 0.20 በመቶ የሚሆን ብቻ ለምርምር በጀት እንደሚውል በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ። ጎረቤት አገር ኬንያ ከ2.5 በመቶ በላይ ከእርሻ የሚገኝ ገቢ ለእርሻ ምርምር የሚውል ሲሆን፣ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የእርሻ ምርምር በጀት ከእኛ ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍ ያለ ነው። የላቲን አሜሪካ አገሮች ለምርምር ሥራ በሰጡት ከፍተኛ ትኩረትና የበጀት ድጎማ የግብርና ምርታቸውን እንዳሳደጉ በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል ብራዚል ለምርምር ባደረገችው ትኩረት ከፍተኛ የግብርና ምርት እንዳስገኘች ይነገርላታል። ስለሆነም ከበጀት በተጨማሪ የምርምር አመራር እጅግ የጠለቀ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሻሻልና የሌሎችንም ልምድ የሚያካትት መሆን እንዳለበት ታምኖ በዚህ ረገድ መሠራት ያለበት ይመስለኛል።
በትምህርትና በምርምር የታጀበ የግብርና ሙያ የሥርጭት አግልግሎት
ኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ያለው የእርሻ አገልግሎት ሥራ የሚሠሩ ሠራተኞች አሏት (GFRAS፡ Global Forumfor Rural Advisory Services)፡፡ በዚህም ሪፖርት እንደተጠቀሰው 108,576 የእርሻ አገልግሎት ሠራኞችና 45,812 የእርሻ ወኪሎች ሲሆኑ፣ 62,764 ደግሞ የዕድገት ወኪሎች (DA) በመባል ይታወቃሉ። የእርሻ ወኪሎችንም ቁጥር እንኳን ብንወስድ ኢትዮጵያ ከቻይና (910,000 የእርሻ ወኪሎች) ከህንድ (90,000 የእርሻ ውኪሎች) ካላቸው አገሮች በመቀጠል በሦስተኝነት ደረጃ ነው ያለችው። ይህንን ለምናውቅ የኢትዮጵያ ወረዳዎችና ዞኖች ጭላሎ እርሻ ልማት ያሳየውን ዓይነት ውጤት ለማሳየት በቂ የሰው ኃይል እንዳላቸው እንረዳለን። ነገር ግን ምን ሆነ? ለምን አልሆነም? የሚለውን መመርመርና መነሻ ማድረግ ይኖርብናል ብዬ እገምታለሁ።
በእኔ ግንዛቤ መከላከያና ፖሊስን ሳይጨምር ሌሎችም መሥሪያ ቤቶች ሊኖሩ የሚችሉ ቢሆንም፣ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር (ከአንደኛ እስከ 12ኛ ያሉ አስተማሪዎች) የከፈለውን ያህል የሚያሠራ መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ ያለ አይመስለኝም። በየቀኑ፣ በየሳምንቱ፣ በየወሩ ትምርት ቤት ካልተዘጋ በዳይሬክተሩ ዕርዳታ መምህራኑ ቢያንስ 30 ሰዓት በሳምንት ማስተማራቸውን እርግጠኛ እየሆነ ነው ወሩ ደርሶ ደመወዝ የሚከፈላቸው።
በዚህ ዓይነት የግብርና አግልግሎት ሰጪዎችን ማሠራት አይቻልም፡፡ ግን ገና ከጅምሩ በሚወጣው የግብርና ፖሊሲ ዕቅድ ነድፎ ለተነደፈው ዕቅድ አስፈላጊው በጀት ተመድቦ፣ የወጣው ዕቅድ ሥራ ላይ መዋሉን ክትትልና ግምገማ በተከታታይ ቢደረግ በቁጥር በቂ የሆነ የግብርናውን ዘርፍ አሁን ካለበት በበለጠ ለማንቀሳቀስ የሚችል የሰው ኃይል በግብርና ልማት ሥራ ላይ እንደተሰማራ ይታወቃል። የጭላሎ እርሻ ልማት ይህንን ነው ያደረገው፡፡ በአምስት ዓመት የአንድ አውራጃ ልማት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ሲለወጥ፣ የቀጠራቸው ሠራተኞች በሙሉ ለሚከፈላችው ክፍያ እንዲሠሩ ያደርግ ነበር። ስለዚህ የኢትዮጵያ በምግብ ራስን መቻል አሁን ያለው በግብርና ሚኒስቴርና በየወረዳው ባሉ አጠቃላይ ሠራተኞች እጅ ላይ ነው። አሁንም በድጋሚ ፖሊሲ ወጥቶ፣ ፕላን ተሠርቶለት፣ በጀት ተመድቦለት፣ ግምገማና ተጠያቂነት ያለው ሥራ በዘርፉ ከተሠራ ከፍተኛ የምርት ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
የግብርና ልማት አስተዳደርና አመራርን በተመለከተ በበላይና በበታች ሠራተኞች መሀል በቂ መናበብ ቢዳብር፣ በእንቅስቃሴው የተጠቃሚዎች በተለይም የገበሬዎች ተወካይ ተሳትፎ ቢኖር፣ ስለሚሠራው ሥራ አስፈላጊው ግምገማ፣ ተጠያቂነትና የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባልተወጡ ላይ ኃላፊነት ስለመኖሩ ቢረጋገጥ የሠራተኛውን ምርታማነት መጨመርና ማሳደግ ይቻላል። በትጋት ለሠራው የሚገባውን አድርጎ ያልሠራውን ደግሞ የሥራውን እንዲያገኝ የሚያደርግ ደንብ ተግባር ላይ መዋል አለበት።
ኢፒድ የካዱን ያህልም ባይሆንም ሱፐር ቫይዘር አሰማርቶ የሥራ ክትትል ሲያደርግ በየዓመቱ መጨረሻ ከጥቅምና ዕድገት ጋር የተያያዘ ግምገማ ያደርግ ነበር። ይህን በማድረግም ሠራተኛውን ማበረታታትና ምርታማነቱን በወቀቱ ማሳደግ ችሎ ነበር። አሁንም ቢሆን የግብርና አገልግሎት መመዘን ቀላል ባይሆንም ከላይ እንደጠቀስኩት በየአካባቢው ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች ተዘርዝረው፣ አስፈላጊው በጀት ወጥቶላቸው እያንዳንዱ ሠራተኛ ኃላፊነት ቢወሰድ፣ ኃላፊነቱን ከምን እንዳደረሰው የሚከታተል አካል ቢኖር ጥሩ ውጤት ማየት ይቻላል። ከእነዚህ በተጨማሪ ወሳኝ የሆኑ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ምርታማነት የሚያስፈልጉ ሥራዎችን በከፊልም ቢሆን ለማንሳት እሞክራለሁ።
መስኖን መጠቀምን ማስፋፋት
የመስኖ ሥራን በማስፋፋት ልምድና አገልግሎቱን ማሳደግ አለብን። ወንዞችን በመጥለፍም ሆነ አቅጣጫ በማስቀየር፣ የወንዝ ውኃ በመከተር፣ የጉድጓድ ውኃን የመጠቀም ልምድን በማሳደግ፣ ውኃ በዝናብ ጊዜ የማቆር ልምድን በማሳደግ፣ የውኃ ሞተሮችን በመጠቀምና ሌሎችንም ዘዴዎች በመጠቀም በግል፣ በመንደርና ከዚያም በላይ ሰዎች በሠፈሩባቸው አካባቢዎች ውኃ የመጠቀምንና ምርት የማምረትን ይጨምራል።
የእርሻ ሜካናይዜሽን
ይህ ደግሞ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችንና በርከት ያሉ የምርምር ውጤቶችን የመጠቀም ልምድን ማሳደግንና መደገፍን ይጨምራል። በጋራ ባለቤትነት በጥቅም ላይ መዋል የሚችሉ የእርሻ መሣሪያዎች፣ ማጨጃዎች፣ የውኃ ፓምፖች፣ ዘመናዊ መጋዘኖች፣ ዘመናዊ ማጓጓዣዎች፣ የእርሻ ሰብል በከፊል ፕሮሰስ ማድረጊያዎችንና ሌሎችንም በርካታ ዘመናዊ አመራረቶችንና አሠራሮችን ይጨምራል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለየ ምርት ምርታማነት ለሚታወቁ አካባቢዎች ተገቢ የሆኑ የእርሻ መሣሪያዎችን መስፋፋትንና የመጠቀም ጥረትን ይጨምራል። ከእነዚህም በተጨማሪ እነዚህንና ሌሎች ዘመናዊ የእርሻ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚፈልጉትን ግለሰቦች መጋበዝ፣ መርዳትና ማበረታታትን ይጨምራል።
የእርሻ ግብዓቶችን ማቅረብ
የእርሻ ግብዓቶችን ለገበሬው የማቅረብ ሥራ ደግሞ የእርሻ መሣሪያዎችን፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን፣ የእርሻ ኬሚካሎችን፣ የተለያዩ ችግኞችን፣ የቡና ችግኝን፣ የወተት ጊጀሮችን፣ የእንቁላልና የሥጋ ዶሮዎችን፣ የከብት መኖ ዘርና የከብት ሕክምና አገልግሎትንና ሌሎች በርካታ ምርታማነትን በመጨመር የገበሬውን ምርትና ገቢ አሳድጎ የሥራ ዕድል ለመክፈት መቻልን ይጨምራል። በምግብ ራሳችንን ለመቻል የእነዚህንና የሌሎችን አገልግሎቶች ከሕዝብ ቁጥር ጋር አብሮ ማደግን ሁልጊዜ እርግጠኛ መሆንን ይጨምራል። ከመንግሥት ድጋፍ በተጨማሪ የግለሰቦችን ተሳትፎ የመጨመርንና የማሳደግ ጥረትንም ይጨምራል።
የቤተሰብ አገልግሎት
ይህ አገልግሎት በተለይ በግብርና ዘርፍ ያሉ ሴቶችን በተለያዩ መንገዶች ለመርዳት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ትምህርቱም ስለመሰጠቱ እጠራጠራለሁ። ይህ የአገልግሎት ዘርፍ በተለይ የገጠር እናቶችን በአትክልት ምርት፣ በትናንሽ እንስሳት ዕርባታ፣ በቂና ስለተመጣጠነ ምግብ፣ የቤተሰብ ጤና አገልግሎትን፣ የተመረተ ምርትን ለገበያ ማዋልንና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን ይሰጥ የነበረ በመሆኑ እስካሁንም መኖር የነበረበት አገልግሎት ነው። በመሆኑም በሙያተኞች የበሚመራ የአገልግሎቱ መኖር ለበርካታ የገጠር ሴቶች የሚሰጠው አሰተዋጽኦ እጅግ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ፣ አገልግሎቱ መኖር ስለሚገባው ሊታሰብበት ይገባል።
የእርሻ ብድርና ድጋፍ
ይህ ዘርፍ ደግሞ በአጠቃላይ ለምርት መሻሻል የሚያስፈልጉ ግበዓቶችንና የገንዘብ ድጎማንም ይጨምራል። ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ያለበትን ገበሬ በመርዳት በምርት መጨመር ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ነው።
የገበያ አገልግሎት
ይህ እጅግ ወሳኝ የሆነ ለግብርና ምርት ማደግ የሚያስፈልግ አገልግሎት ነው። ምርትን ከማምረት እስከ በላተኛው ድረስ ያለውን እጅግ ረዥምና የተወሳሰበ ውጣ ውረድን የሚያካትት ተግባር ነው። በዋነኝነት ምርት ከገበሬው መግዛትን፣ ተገቢ የመጋዘን አገልግሎትን፣ ተገቢ ማጓጓዣዎችን፣ በከፊልና ሙሉ በሙሉ ፕሮሰስ ማድረግን፣ ደረጃ ማውጣትን፣ ዋጋ መተመንን፣ ተገቢ ገበያን መፈለግን፣ ሕገወጥ የሆኑ የግብርና ምርት ዝውውርና ሽያጮችን መቆጣጠርን፣ በእነዚህ መንገዶች ሲያልፍ ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆን የሚጠፋውን ምርት የመቀነስ ሥራንና ሌሎች አገልግሎቶችን ያጠቃልላል። ስለሆነም በርካታ የገበያ ማሻሻል ሥራዎች መሠራት አለባቸው።
የደን የአፈርና የውኃ ልማትና ጥበቃ ሥራ ማስፋፋትና ማጠናከር
ይህ የሥራ ኃላፊነት በምግብ ራሳችንን ለመቻል ወሳኝና እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ታውቆ፣ በአገራችን በማንኛቸውም ቦታዎች ከፍተኛ ትኩረትና ክትትል እየተደረገ መሠራት አለበት። እጅግ የተለየ ጥረት በዚህ ዘርፍ ካልተደረገ፣ ከሕዝባችን ማደግና ከምርታማነት ማነስ ጋር ተደምሮ ፈታኝ ሁኔታዎች አገራችንን በምግብ ሊገጥማት ይችላል።
የእንስሳት ዕርባታ
በምግብ ራስን ለመቻል ተገቢውን ትኩረት ያልተሰጠው የእንስሳት ዕርባታ ዘርፍ ነው። በመሆኑም ከዘርፉ ሊገኙ የሚቻሉ ምርቶች ሁሉ መሆን የሚገባቸውን ያህል አልሆኑም። ኢትዮጵያ በከብት ቁጥር በአፍሪካ አንደኛ ስትሆን በዓለም ደግሞ አሥረኛ ነች። ይህም ዕምቅ ሀብት መሆኑ ቢታወቅም በዚህ ረገድ በሥጋ፣ በወተት፣ በእንቁላልና በሌሎችም ምርት አመርቂ ሥራ እንዳልተሠራ ይታወቃል። ስለዚህ በምግብ ራስን ለመቻል በዘርፉ በቂ ምርት አልተመረበትም። በአጠቃላይ በዘርፉ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም፣ ዋና ዋናዎቹ የተሻሻለና የዘመናዊ ከብት ዕርባታ አገልግሎት አለመኖሩና አለመስፋፋቱ፣ የከብት መኖ አለመሻሻልና ማነስ፣ የከብት ሕክምና ማነስና አለመኖር፣ በቂና አስተማማኝ የገበያ አገልግሎት አለመኖርና አለመስፋፋት፣ አገር በቀል የሆኑ ምርታማ ዘርያዎችን መርጦ የማሻሻልና የማባዛት አገልግሎትና ልማድ እጅግ ያዘገመ መሆኑ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልማድ በዘርፉ ያልተስፋፋ መሆኑ፣ የመሬት ጥበት የመኖ ችግር፣ በቂና የንፁህ ውኃ እጥረትና ሌሎችንም የሚጨምር ይሆናል።
በአጠቃላይ
የግብርና ፖሊሲ በሙያተኞች ተሳትፎ በየዘርፉ ያለው እንቅሰቃሴና ችግር ተፈትሾ የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የረዥም ጊዜ ፖሊሲ ማውጣት፣ ያለውን መርምሮ ማሻሻልና መቅረት ያለበትንም ፖሊሲ የመሰረዝ ሥራ መከናወን አለበት። ለግብርና መሻሻል ምሰሶ የሆኑትን የትምህርት፣ የምርምርና የሥርጭት በየፊናቸው ያሉበትን ደረጃ መርምሮ የማሻሻል፣ የማጣጣምና በአዲስና በተጠናከረ መንገድ አብሮ የመሥራትን ባህል ማሳደግ ሥራ መከናወን አለበት። ይህ ሲባል የራሳችንና የሌሎችን ልምድ በማካተት መሻሻል ያለበትን ማሻሻል ይሆናል።
እጅግ በጣም ለምርት ወሳኝ የሆኑ የመስኖ፣ የሜካናይዜሽን፣ ሌሎች ግብዓቶችን የማቅረብ፣ የቤተሰብ አገልግሎት፣ የገበያ አገልግሎት፣ የእንስሳት ሀብት ልማት፣ የደንና አፈርና ውኃ ልማት ሥራ በተጠናከረ መልኩ የማከናወን ሥራ ይጨመር። ስለግብርና ልማት ዕውቀታቸውን በሥራቸው ያስመሰከሩ ምሁራንን ያሰባሰበ የአማካሪዎች ቡድን ለፌዴራል መንግሥትና ለግብርና ሚኒስቴር ማቋቋም ያስፈልጋል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፈው ከጅማ እርሻ ኮሌጅ ዲፕሎማ፣ ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ፣ ከኦክሎሃማ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪ በእርሻ ኢኮኖሚክስ ሲኖራቸው በግብርና ሚኒስቴር በእርሻ ወኪልነት፣ በጅማ እርሻ ኮሌጅ በመምህርነት፣ በክፍል ኃላፊነት፣ በተማሪዎች ደኅንነትና በኮሌጅ ዲንነት ከማገልገላቸውም በላይ በአሜሪካ አርከንሳስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት የሠሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡