ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ የቆየው የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ ቁጥር 341/1995 በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑ፣ መሻሻል እንደሚኖርበት በመግለጽ ሲሞገትበት ከቆየ 20 ዓመታት ሊሞላው ነው፡፡
‹‹አዋጁ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን አጣምሮ እንዲሰናዳ መደረጉ፣ እንዲሁም አጠቃላይ አደረጃጀቱ እንከን ያለበት ነው›› በሚል እየጠነከረ የመጣው ሙግት ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ በተደራጀ መልኩ ጥያቄው እንዲቀርብ አስገድዷል፡፡
አዋጁ ያሉበትን ችግሮች በመጥቀስ በተለይ በኢትዮጵያና በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች በኩል የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት ጭምር ከመድረኮቹ የተነሱትን ሐሳቦች በመጥቀስ መንግሥት እንዲያውቃቸው ቢደረግም፣ እስካሁን አዋጁን ማስተካከል አልተቻለም፡፡ የረቂቅ ዝግጅቱም ዓመታትን ሊወስድ በመቻሉ ንግድ ምክር ቤቶች ችግር ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል፡፡
የንግድ ምክር ቤታችን እንደገና እንዲደራጅ በሚያስገድደው በዚህ አዋጅ የተደራጁ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ደካማ እንዲሆኑ አድርጓል የሚለው የንግድ ምክር ቤቶቹ አቋም ማሻሻያው በቶሎ እንዲተገበርም ይሻሉ፡፡ በዚህ አዋጅ ከፌዴራል ጀምሮ በክልል፣ በወረዳ፣ በዞንና በከተማ ደረጃ የሚዋቀሩ ንግድና ዘርፍ ማኅራት ምክር ቤቶች ተደራራቢ ኃላፊነቶችን የሚሰጥ አንዱን ከአንዱ የሚያጋጭ እንደነበርም ይገልጻል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል ይህ አዋጅ ከፅንሱ ጀምሮ ችግር ያለበት እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ቀመር ያለው ነው ይላሉ፡፡ በወቅቱ የነበረው የኢሕአዴግ መንግሥት ለራሱ በሚመች መልኩ ያዘጋጀውና ነጋዴን የሚከፋፍል እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ይህንን አዋጅ ለማሻሻል ወደ ስምንት ዓመታት ጥረት ሲደረግ እንደነበር የሚገልጹት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ፣ በመንግሥቱ የማሻሻያ ሥራው ረዥም ጊዜ ወስዷል፡፡ የማሻሻያው ዝግጅት ላይ ንግድ ምክር ቤታችን ጨምሮ በግል ዘርፉ ዙሪያ ያሉ አካላት ከመንግሥት የተውጣጣ ቡድን ተዋቅሮ ረቂቅ እንዲዘጋጅ ተደርጎ ለቀድሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቀርቦ ለመጨረሻ ውሳኔ እንዲረዳ የሌሎች አገሮችን ልምድ እንዲካተትበት ተደርጓል ይላሉ፡፡ አሁን ለመጨረሻው ረቂቅ በቂ ግብዓት ቀርቧል ብለው የሚያምኑት አቶ ውቤ፣ ከዚህ በኋላ መዘግየት እንደማይገባውም ያመለክታሉ፡፡
በሥራ ያለው አዋጅ ብዙ ማነቆዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ ውቤ፣ በፌዴራል፣ በክልልና በከተማ ደረጃ የተዋቀሩ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዋጁ ተመሳሳይ ኃላፊነቶችን የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለግጭት ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡ ሌሎች ለአሠራር እንቅፋት የሆኑ ድንጋጌዎች እንዳሉበት አስረድተዋል፡፡ ከብዙ ምክክርና ውጣ ውረድ በኋላ ይህንን አዋጅ የሚያሻሽል የሕግ ረቂቅ ተዘጋጅቶ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ረቂቁን እያሰናዳው ያለው ቡድን ለሚመለከተው አካል በማቅረብ የማሻሻያ አዋጅ በዚህ ዓመት ይፀድቃል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ የንግድ ኅብረተሰቡ አካላት ደግሞ በረቂቅ ደረጃ የተመለከቱት የሕግ ማዕቀፍም ቢሆን ብዙ የሚቀሩት ነገሮች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ረቂቅ ተብሎ ባለድርሻ አካላት የተመለከቱት ረቂቅ አዋጅ ከቀድሞ ብዙም የተለየ ነው ብለው አያምኑም፡፡ በእርግጥ ከአዋጁ ስያሜ ጀምሮ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ በይዘት ደረጃ ግን ‹‹አልሸሹም ዞር አሉ›› እንደሚባለው ነው የሚሉት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ በተለይ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ውስጥ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት ድጋሚ የንግድ ኅብረተሰቡ ሊመክርበት ይገባል ብለዋል፡፡ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች መሠረት በመሆናቸው አዋጁ ተገቢ ቦታ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡ ነባሩ አዋጅ የንግዱን ኅብረተሰብ አዳክሟል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ዮሐንስ፣ ጠንካራ የንግድ ምክር ቤቶች እንዳይኖሩ ምክንያት ሆኖ የቆየ በመሆኑ የሚሻሻለውም አዋጅ ይህንን ያገናዘበና የንግዱን ኅብረተሰብ ፍላጎት የሚያሟላ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በአጠቃላይ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ አወጣጥ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው፣ በደርግ ጊዜ የነበረው የቀድሞው የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅ ግን የተሻለ ምክንያታዊ አቀራረብ እንደነበረው ይጠቅሳሉ።
የቀድሞው አዋጅ አንድ ብሔራዊና በርካታ ከተማ ንግድ ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ የሚፈቅድና በጣም ጠቃሚ እንደነበር የሚገልጹት አቶ ዮሐንስ፣ በኢሕአዴግ ወቅት የመጣው አዋጅ ግን በጣም የወረደና ልክ እንደ ምርጫ ቦርድ የፌዴራልና የክልል አደረጃጀታችን ወስኖ የመጣ መሆኑን፣ ይህም ንግድ ምክር ቤቶቹ ከሚገባቸው የአደረጃጀት መንገድ የወጣ እንዳደረገው ያስረዳሉ፡፡
‹‹የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በፌዴራል መንግሥት ነው የሚወጣው ተብሎ ተደንግጓል፡፡ የምርጫ ቦርድንም እንደዚሁ፡፡ እነኚህን ሕግጋት በሕገ መንግሥቱ መወሰኑ አግባብ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ንግድ ምክር ቤቶች ዓይነት ማኅበር ማቋቋም በዚህ መልኩ መደራጀት አለብህ ተብሎ አስገዳጅ የአደረጃጀት ተቀርፆ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ተደራጁ መባሉ ንግድ ምክር ቤቶችን የፖለቲካ ድርጅት ያስመሰላቸዋል፤›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ ፣ በዚህም ምክንያት ሥራ ላይ ያለው አዋጅ ንግድ ምክር ቤቶችን የሚመጥናቸው እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡
ይህ አደረጃጀት የግሉ ማኅበረሰብ አንድ ድምፅ እንዳይኖረው የሚያደርግ ስለመሆኑ ጭምር የገለጹት አቶ ዮሐንስ፣ እንዲህ የሆነውም በወቅቱ በነበሩት የኢሕአዴግ የባለሥልጣናት እጅ ገብቶበት የተሠራ በመሆኑ፣ የአዋጁ ችግር ይዞት ከተነሳው ዘውግ የሚመዘዝ ነው ይላሉ፡፡ መሆን የነበረበት ግን በፌዴራል ደረጃ አንድ፣ በከተሞች ደግሞ አንድ ንግድ ምክር ቤት እንዲቋቋም ማድረግ ነው ብለዋል።
ይህንን የአቶ ዮሐንስ ሐሳብ የሚያጠናክሩት የሕግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ ይህ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ከፖለቲካ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ንግድ ምክር ቤቶች የፌዴራል ቅርፁን ተከትሎ መልሶ ተደራጀ፡፡ ነጋዴ ደግሞ ንግድ ከፌዴራል ሥርዓቱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ነጋዴ ሁሉ እንደ ነጋዴ ነው እንጂ ምክር ቤቱን ማቋቋም ያለበት በክልል መከፋፈል የለበትም የሚል አቋም የንግዱ ኅብረተሰብ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
የአዋጁ ሌላው ችግር ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ መንግሥት የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ያለውን ነጋዴ ማግለልና በማምረት ላይ ያለውን ደግሞ ወደፊት የማምጣት ፖሊሲ እንደነበረው የሚያመለክት በመሆኑ ነው፡፡
ይህም መከፋፈልን የፈጠረ እንደሆነ የንግድ ኅብረተሰቡ እያነሳ ከሚገኘው ጥያቄ መረዳት እንደማይቻል የጠቆሙት አቶ ፈቃዱ፣ ለምሳሌ አገልግሎት ላይ ያሉ ባንኮችና የመሳሰሉት ዘርፎችና ነጋዴዎችን ኪራይ ሰብሳቢ ነው፣ ለፖለቲካዬ አይታመንም በሚል የተቀረፀው አዋጅ አድርገው የሚወስዱትም አሉ ይላሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ፣ በአንፃሩ ጋራዥ፣ ጫማ አምራች፣ ወፍጮ ቤቶችና እንደ ዘርፍ የሚታዩ የቢዝነስ ሰብስቦችን የበለጠ ዕውቅና የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አዋጁ ውዝግብ ሲያስነሳ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ለምሳሌ በጣም አስፈላጊ የሚባለው የፋይናንስ ዘርፉ በተለይም እንደ የባንኮች ማኅበር በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ዕውቅና አይሰጣቸውም፡፡ እነዚህ ማኅበራት እንደ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ታይተው ምዝገባቸው በመንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሚመዘገብበት ኤጀንሲ እንዲከናወን መወሰኑም ችግሩን ያሳያል ይላሉ፡፡
ለወፍጮና ለመሳሰሉ ማኅበራት ግን በአዋጁ ዕውቅና በይበልጥ መስጠቱና መንግሥት በጣም ወደ ውስጥ ገብቶ ነጋዴን ከፋፍሎ ለአንዱ ዕውቅና ሰጥቶ አገልግሎት ዘርፉን ማግለሉ ትልቅ ጉድለት ነው ተብሏል፡፡ ሌላው አዋጁ በፌዴራል በክልል እያለ ከፋፍሎ ጣልቃ ገብቶብናል በሚሉ ነጋዴዎች ጥያቄ የሚነሳ መሆኑን የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ ስለዚህ የአብዛኛው ፍላጎት ልክ እንደ ቀድሞ የነጋዴዎች ማኅበር ኖሮ እንደ ነጋዴው አቅም በየከተማው ቅርንጫፍ እንዲኖረው ፍላጎት አላቸው፡፡ አዋጁ ሌላው ሊመልስ ይገባዋል ተብሎ የተጠቀሰው የንግድ ምክር ቤቶች አባላት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ይሁን አይሁን የሚለው ነው፡፡ በረቂቁ ላይ አባልነት በግዳጅ ይሁን በሚል ይካተት የሚለው ሐሳብ የብዙዎች ሲሆን፣ የመጨረሻው ውሳኔ አልለየም፡፡ አባልነትን በተመለከተ አቶ ውቤ በግዴታ ይሁንና በሒደት መስተካከል የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዓላማችን ንግድ ምክር ቤቶች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ አባልነት በግዴታ የሚተገበርባቸው ናቸው፡፡ ይህ ንግድ ምክር ቤቶች የራሳቸውን መተዳደሪያ ደንብ አውጥተው ከአባሎቻቸው ገቢ በማሰባሰብ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ በብዙዎች አገሮች ውጤት ያገኙበት እንደሆነም አቶ ውቤ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለው አዋጅ አባልነት በፈቃደኝት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጾ፣ አባል የሚሆኑትን ደግሞ ይዘረዝራል፡፡ ይህ አሠራር የተምታታ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ይሁን ብሎ መንግሥት ከወሰነ ለንግድ ምክር ቤቶች የገቢ ምንጭ ከመንግሥት መለቀቅ ይኖርበታል፡፡ በነባሩ አዋጅ ላይም ይደጉማሉ የሚል ቢሆንም ይህ አልተተገበረም፡፡ ዋናው ነገር ግን ይደጉመን ሳይሆን፣ የንግድ ምክር ቤቶች የራሳቸው ገቢ ይኑራቸው የሚል ነው፡፡ አባልነት በፈቃደኝነት ከሆነ ምክር ቤቶች በራሳቸው መንገድ መራመድ ይችላሉ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ መንግሥት ምክር ቤቶቹ ገቢ የሚያገኙበት አሠራር በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርበታል የሚል አተያይ አላቸው፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት የረዥም ጊዜ አባልና በቦርድ አባልነት አገልግለው የነበሩ አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ የንግድ ምክር ቤቱ ማቋቋሚያ አዋጅ ካለበት ክፍተት የበለጠ የንግዱን ኅብረተሰብ ጥንካሬ እየሸረሸረ ያለው በጎን ‹‹የኢሕአዴግ ደጋፊ ነጋዴዎች ማኅበር›› በሚልና በሌሎች ስያሜዎች ነጋዴዎች እንዲደራጁ መፍቀዱ ነው፡፡ ከሌለው ንግድ ኅብረተሰብ በመነጨ የተወሰኑ ነጋዴዎች እንዲህ ባሉ ማኅበር ተደራጅተው ከመንግሥት ጋር መሥራታቸው አሁን በየንግድ ምክር ቤቱ ላሉ ችግሮች እንደ ምክንያት መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ የተደራጀ ንግድ ምክር ቤት እያለ በጎን የሚቋቋሙ እንዲህ ያሉ ማኅበራት መከልከል ያለባቸው እንደሆነም ያምናሉ፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች አዋጅን ለማሻሻል የሚወጣው አዋጅም በደጋፊነት ስም የተደራጁና የሚደራጁ ማኅበራን ማስቀረት ይኖርበታል ብለው ይሞግታሉ፡፡
አቶ ፈቃዱ የተሻለ የሚሆነውና ነጋዴ እንዲጠነክር ከፈለገ እንዲህ ባለ አዋጅ መጫን ሳይሆን በራሱ እንዲመሠረት አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ በርካታ ምክክሮች የተደረገበት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ውቤ፣ በዚህ ረቂቅ ላይ መካተት ይገባቸዋል ያልናቸው ሐሳብ ሁሉ አቅርቦና ስለዚህ ይህ ማሻሻል የንግድ ምክር ቤቶቹን በሚጠቅም የንግድ ኅብረተሰቡን ሊያጎለብት በሚችል ደረጃ የመጨረሻው ማሻሻያ ይወጣል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡
አዝጋሚ ሒደት የነበረ ቢሆንም ከ2014 ዓ.ም. በተሻለ መነቃቃት እየተሠራበት ስለመሆኑ መረጃ እንዳላቸው የገለጹት አቶ ውቤ ደግሞ፣ የመጨረሻው ረቂቅ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ቀርቦ እንደተባለው በዚህ ዓመት የተሻሻለው አዋጅ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ነገር ግን ይህ የንግዱ ኅብረተሰብ የዓመታት ጥያቄ እንደተባለው የተሻሻለው አዋጅ ፀድቆ በዚህ ዓመት የማይወጣ ከሆነ ግን የንግድ ምክር ቤቱ እንደተዘነጋ ነው የምንቆጥረው ነው ብለዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ፀድቆ እንዲወጣም ምክር ቤታቸው አሁንም ጥረቱን የሚቀጥል እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ውቤ፣ በዚህ ዓመት አዋጁ ካልፀደቀ የንግድ ኅብረተሰቡ እንደተዘነጋ ነው የምንቆጥረው የምንለውም በዚህ አዋጅ ጠንካራ የንግድ ኅብረተሰብ መፍጠር ስለምንፈልግ ነው፡፡
‹‹ምክንያቱም የተደራጀ የግል ዘርፍ የኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲ ለሚባለው ነገርም ትልቅ ድጋፍ ስለሚያደርግ ነው፤›› የሚሉት አቶ ውቤ፣ የዚህ አዋጅ መውጣት በአገር ደረጃ ትልቅ ጥቅም የሚሰጥ ተቋም ለማደራጀት ስለሚያግዝ አዋጁ በቶሎ ወጥቶ እንዲተገበር ግፊታቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡ ሰሞኑን በተካሄደው አዲስ አበባ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተሻለ በልሁ እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ፣ ይህ ረቂቅ አዋጅ በዚህ ዓመት እንዲፀድቅ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የብዙዎች ሙግት ግን ይህ ረቂቅ ጊዜውን የዋጀ መሆን ስለሚገባው አሁንም ረቂቁ በደንብ መታየት አለበት፡፡ እንደ አቶ ፈቃዱ እምነትም የንግድ ኅብረተሰቡንና የንግድ ምክር ቤቶችን ሊያሳደግ የሚችልና ለዚህ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል፡፡
‹‹የንግድ ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ›› በሚል የተሰናዳው ረቂቅ ሕግ ወደ 35 አንቀጾችን የያዘ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤትና የክልል የንግድና የኢንዱትሪ ምክር ቤት ያለው ሲሆን፣ የክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አካላት የሚሆኑት ግለሰብ ነጋዴዎች፣ የሽርክና ማኅበራት፣ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የንግድ ማኅበራት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራትና የንግድ ሥራ ዘርፍ ማኅበራት በሚል ይጠቅሳቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አባላት ደግሞ የክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶችና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በመመርያ በሚወስነው መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋሙ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራትና የንግድ ዘርፍ ማኅበራት መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ እንዲህ ያለው አደረጃጀት አሁንም ጥያቄ ያስነሳል የሚሉ ወገኖች የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች በዚህ አደረጃጀት ውስጥ መጠቀሳቸው ያሳስበናል ይላሉ፡፡