የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)፣ መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለማካሄድ ያሰበው ጠቅላላ ጉባዔ፣ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ያልተከተለ ስለሆነ ዕውቅና እንደማይሰጠው አስታወቀ፡፡
ቦርዱ እንዳስታወቀው፣ ነሐሴ 21 ቀን 2ዐ14 ዓ.ም. የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት በሚል በተፈረመ ደብዳቤ፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ፣ ያልተሟሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ማሟላቱንና መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ እንዲደረግ መወሰኑን አሳውቋል፡፡
በፓርቲው የቀረበለትን ሰነድ መመርመሩን ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ተሰብስቦ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ማፅደቁና ‹‹የጠቅላላ ጉባዔ ቀን ወስኗል›› በሚል በቀረበው ቃለ ጉባዔ 12 አባላት እንደተሰበሰቡ፣ ይህም የሆነው ሁለት ጊዜ ብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ ጠርቶ ምልዓተ ጉባዔ ባለመሟላቱ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል ብሏል፡፡
በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል ከተባሉት ቦርዱ ዕውቅና ከተሰጣቸው 45 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት መካከል የተገኙት ሰባት ብቻ መሆናቸውን መመልከቱን አክሏል፡፡
የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በወሰነው ቦታና ጊዜ፣ ሁለት ጊዜ ተጠርቶ እንደነበርና ‹‹ምልዓተ ጉባዔውም በስብሰባዎቹ ያልተሟላ ስለመሆኑ አያሳይም›› በማለት ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ፣ በዚህም ምክንያት ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤቱ አካሂዶታል የተባለው ስብሰባ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
ከዚህ በሻገር በ12 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ተደረገ የተባለው ስብሰባ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ተከትሎ የተካሄደ ባለመሆኑ፣ መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ የተላለፈውን ውሳኔ የማይቀበል መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ፊርማ የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ቀርቦ ከመፅደቁ በፊት፣ በፕሬዚዳንቱ መመረጥ እንዳለባቸው ቢደነገግም፣ ነገር ግን የፓርቲው ፕሬዚዳንት የመረጧቸው ሥራ አስፈጻሚዎች የፀደቁ ስለመሆኑ የሚያሳይ ማረጋገጫ ወይም ማስረጃ ያልቀረበ በመሆኑ፣ ብሔራዊ ምክር ቤቱ አሳልፎታል የተባለው ውሳኔ በቦርዱ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
የባልደራስ ብሔራዊ ምክር ቤት ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ተሰብስቦ አሳልፏቸዋል የተባሉትን ውሳኔዎች ያልተቀበላቸው መሆኑን ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ፣ ፓርቲው በቀጣይ እሑድ ለማድረግ ያቀደው ጠቅላላ ጉባዔም ዕውቅና የሌለው በመሆኑ ታዛቢ እንደማይልክ ጨምሮ አስታውቋል፡፡