የአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደር ዞን 6.4 ሚሊዮን ኩንታል የሚገመት ሰሊጥና አኩሪ አተር ለመሰብሰብ፣ አንድ ሚሊዮን የቀን ሠራተኞችን ለመቅጠር ጥሪ አቀረበ፡፡
ዞኑ ዓርብ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ጥሪ ከመላው ኢትዮጵያ ፍላጎት ላላቸው የቀን ሠራተኞች፣ ሙሉ ወጪያቸውን ከሙሉ ሕክምናና የቀን አበል ጋር በመክፈል እቀጥራለሁ ብሏል፡፡
በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ፣ መተማና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች፣ እንዲሁም ምድረ ገነትና መተማ ዮሐንስ በተባሉ ከተሞች አካባቢ 438,000 ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ ምርት ለመሰብሰብ መሆኑን፣ የዞኑ የግብርና መምርያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ወርቁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ምክትል ኃላፊው ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ፍላጎት ያላቸው ዜጎች፣ ከሚኖሩበት አካባቢ መታወቂያ በመያዝ በሥራው ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
ወደ 6.4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚገመት የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ የተዘራው ሰብል ትራክተሮችንና የፀረ ዓረም ኬሚካል በመጠቀም የተከናወነ ቢሆንም ምርቱን ለመሰብሰብ ወደ ዞኑ የሚያመሩ የቀን ሠራተኞች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ፣ ከመላው አገሪቱ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች እንዲያመለክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የግጦሽ መሬት ላይ ሳይቀር በከፍተኛ መጠን ዘር መዘራቱን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ምርቱን ለመሰብሰብ ግን ከወትሮው በተለየ በፀጥታ ሥጋት ወደ አካባቢው ይመጡ የነበሩ የቀን ሠራተኞች መቀነሳቸውን ተናግረዋል፡፡
የምርት ስብሰባው ሒደት በአማካይ ከጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን ሊቆይ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ በሥራው ለሚሰማሩት ዜጎች ሙሉ ወጪያቸው ማለትም የካምፕ፣ የምግብና የሕክምና አገልግሎት፣ እንዲሁም ከ250 እስከ 300 ብር የቀን አበል እንደሚከፈል አስረድተዋል፡፡
በኢንቨስተሮችና በገበሬዎች በኩታ ገጠም የተዘራውን ሰብል ለመሰብሰብ የሰብል ማጨጃ ማሽን (ኮምባይነር) ባለመኖሩ፣ አሁን የሰው ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡
ዞኑ በ2013 ዓ.ም. ከታረሰው 131 ሺሕ ሔክታር መሬት 930 ሺሕ ኩንታል ምርት ማግኘቱን፣ ከብሔራዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡