Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግንባታቸው የተጓተተ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዋጋ ማሻሻያ ተደርጎ እንዲጠናቀቁ ማሳሰቢያ ተሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተላለፉላቸው የመመርያ ሰርኩላሮች መሠረት፣ የግንባታ ዋጋ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እንዲያጠናቅቁ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም በዋጋ ግሽበት ሳቢያ ከ700 በላይ ፕሮጀክቶች መቋጫ ሳያገኙ መቆየታቸው ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የዋጋ ማሻሻያ ማስፈጸሚያ ሰርኩላሮች ተግባራዊ እንዲደረጉ ለተቋማቱ ቢላኩም፣ ወጥ የሆነ አፈጻጸምና ከግልጽነት ጋር ተያይዞ ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ከሰሞኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የሕንፃ ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዳለው ተመስገን (ኢንጂነር)፣ በመርሐ ግብሩ ላይ የግዥ መመርያውን በተመለከተ ለፕሮጀክቶች መጠናቀቅ አስፈላጊ የተባሉ አራት ተመጋጋቢ የሰርኩላር ሰነዶችን ምንነት አስረድተዋል፡፡

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙት የግንባታ ፕሮጀክቶች የተፈረሙበት ጊዜና ፕሮጀክቶቹ የሚሠሩበት ማቴሪያል ዓይነት እንደ መለያየቱ መጠን፣ በተቋማቱ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በሚል የተቋቋሙ አካላት በተቀመጠው መመርያ መሠረት የሰርኩላሮቹ ይዘት ተግባር ላይ መዋላቸውን መምራት ይገባቸዋል ሲሉ አቶ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ግንባታቸው ለተጓተቱት ፕሮጀክቶች በተላለፉት ሰርኩላሮች መሠረት የዋጋ ማሻሻያው ሲሠራ ግብዓቶች በዋናነት ከማምረቻ ተቋማት የሚገኝን ዋጋ መነሻ አድርገው እንጂ፣ ገበያ ውስጥ ባለው ዋጋ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የዋጋ ማሻሻያው ተግባራዊ የሚደረግባቸው ፕሮጀክት ሕጉን በተከተለ ሁኔታ ለሁሉም እንደሚያገለግል የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ ከ18 ወራት በላይ እንደሚቆዩ፣ እንዲሁም የዋጋ ማሻሻያው በዋናነት የሚመለከተው ከየካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን እንዳለው (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡

በየካቲት 2013 ዓ.ም. ከወጣው ሰርኩላር በፊት የተፈረሙ የግንባታ ውሎች ወካይ በሚባሉ አራት ግብዓቶች ማለትም የሲሚንቶ፣ የአርማታ ብረት፣ የሴራሚክና የነዳጅ ዋጋን መሠረት በማድረግ የዋጋ ክለሳ የሚያደርጉ ሲሆን፣ ነገር ግን ከየካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. አንስቶ የተፈረሙ ውሎች ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሚቀርብ ዋጋን መሠረት በማድረግ ሕጉን ተከትለው መሥራት እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

ነባር የግንባታ ውሎች በተለያዩ ምክንያቶች ውላቸው ከ18 ወራት በላይ በማስቆጠሩ የዋጋ ማሻሻያ መሥራት እንደሚችሉ፣ ይህ ሲሠራም ወካይ ግብዓቶች በዋናነት ከማምረቻው ባለው ዋጋ እንጂ ገበያ ላይ ባለው ዋጋ መነሻነት አለመሆኑን ግንዛቤ ሊወሰድ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ለተቋማቱ በተላለፉት ሰርኩላሮች አስፈላጊው መዘርዝር በመገለጹ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ወደ ተግባር መግባት እንዳለባቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ሌሎች ምክንያቶችን በመደርደር የሚባክን ተጨማሪ ጊዜ ሕዝብ የሚጎዳ እንደሆነ የሕንፃ ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የወጡት አራት የመመርያ ሰርኩላሮች ወጥነት አላቸው እንጂ አንደኛው ሌላኛውን እየጣለ የሚሄድ አይደለም ብለዋል፡፡

በጀትን በተመለከተ ከገንዘብ ሚኒስቴር የሚለቀቅ በመሆኑ የዋጋ ማሻሻያም ሆነ ጭማሪ በተመለከተ የሚደረጉ ክፍያዎችን ለመፈጸም፣ ተቋማቱ ሚኒስቴሩን በቅድሚያ ማነጋገር ተፈላጊ ጉዳይ መሆኑን በመድረኩ ላይ ለተገኙት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጆች፣ ፕሮጀክት ላይ ለሚሳተፉ አማካሪዎች ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት ባለው ሁኔታ ከ18 ወራት በታች ለሆነ ውል የዋጋ ማሻሻያ ተብሎ መፈረም የሌለበት ሲሆን፣ ፕሮጀክቶች 12 ወራት ሳይሞላቸው ደግሞ የዋጋ ጭማሪ ክፍያ መፈጸም እንደማይገባ እንዳለ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቱ በኋላ ተቋማቱ የግንባታ ጽሕፈት ቤቶችን በማጠናከር በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አለባቸው ብለዋል፡፡

የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ የሚጠቅመው ፕሮጀክቱን ብቻ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ባለሥልጣኑ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር ባቀረበው የፋይናንስ ተፅዕኖ ጥናት ለከፍተኛ ለተቋማቱ ግንባታ ማጠናቀቂያ ብቻ 24 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች