Wednesday, April 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር ህልውና ሲባል ለአዲሱ ትውልድ ዕድል ይሰጥ!

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጨርሶ ተስፋ መቁረጥ ባይገባም፣ ተስፋ እንዲኖር ግን አንዳንድ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ለአገር ህልውና ሲባልም የግድ ነው፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች በመከላከል ብዙውን የዕድሜያቸውን ክፍል አሳልፈው በክብር ሲያልፉ፣ በተነፃፃሪ የተሻለ ዘመን ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ሲናቆሩ አገራቸውን ለድህነት መዳረጋቸው ብዙዎችን የሚያስቆጭ ነው፡፡ የዘመነ መሣፍንት ማብቂያ ከተበሰረበት ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ በሰሜን ኢትዮጵያና በተለያዩ አካባቢዎች  ውጊያዎችና ግጭቶች ሙሉ በሙሉ በሚቻል ሁኔታ የተደረጉት በኢትዮጵያውያን መካከል ነው፡፡ በምሥራቅ ከሶማሊያ ጋር ከተደረገውና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች በኋላ በባድመ ሰበብ ከተደረጉ ጦርነቶች በስተቀር፣ ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ያለችው በገዛ ልጆቿ ምክንያት ነው፡፡ ይህችን የመሰለች በተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለች አገር የከፋ ድህነት ውስጥ ተዘፍቃ፣ ሌላው ቀርቶ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስት ዙር ጦርነቶች እየተካሄዱባት መሆኑ ዕብደት እንጂ ምን ሊባል ይችላል? አገር የሚረከበው አዲሱ ትውልድም ሆነ፣ እየተከናወነ ያለውን አውዳሚ ድርጊት የሚታዘቡ ታዳጊዎች የሚፈጠርባቸው አሳዛኝ ስሜት ሲታሰብ ያስደነግጣል፡፡

ኢትዮጵያ ምንም ሳታጣ የነጣች ደሃ የሆነችው በምን ምክንያት እንደሆነ በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የየዘመኑ ፖለቲከኞች ችግሮቻቸውን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ቢችሉ ኖሮ፣ አገርን ከማንኛውም ዓይነት ወረራ የመጠበቅ አኩሪ ታሪካዊ እሴት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተዓምር መፍጠር እንደሚችሉ ማንም አይስተውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠርቶ የሚያሠራው ቢያገኝ እንኳን ለአፍሪካ ለዓለም የሚተርፉ ምርቶችን ማምረት ይችል ነበረ፡፡ በቀን ሦስቴ መመገብ የሰማይ ያህል ሊርቀው ቀርቶ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ኤክስፖርተር መሆን አያቅተውም፡፡ ልዩነቶቻቸውን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ባቃታቸው ፖለቲከኞች ምክንያት ግን፣ እንኳንስ የተመጣጠነ ምግብ ሊመገብ ቀርቶ በቀን አንዴ በልቶ ለማደር የኤቨረስት ተራራን የመውጣት ያህል እየከበደው ነው፡፡ በአፍሪካ በእንስሳት ሀብት አንደኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ሕዝቧ ሥጋ፣ ቅቤ፣ ዶሮ፣ እንቁላልና መሰል ተዋፅኦዎች ሁሌም ብርቁ ናቸው፡፡ የአፍሪካ የውኃ ቋት በምትባለው ኢትዮጵያ ንፁህ የመጠጥ ውኃም ሆነ ዓሳ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ከ80 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ሊታረስ የሚችል ለም መሬት ያላት ኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝቧ ምግብ ይናፍቀዋል፡፡

ከሰሃራ በታች ከሚገኙ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ጋር ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ስትነፃፀር አሁንም ወለል ላይ ናት የምትገኘው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው በተለያዩ መስኮች በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚወጡ ዓመታዊ ሪፖርቶችን ማገላበጥ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጥንታዊ ሥልጣኔ ስማቸው ከሚነሳ ጥቂት የዓለም አገሮች መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡ የአክሱም ሐውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎችም በርካታ ቅርሶች በዋቢነት ይጠቀሳሉ፡፡ በአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ታላቁ የዓድዋ ድል፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካውያን ብቻ ሳትሆን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ፈርጥ እንዳደረጋት ዓለም የመሰከረው ሀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ፋና ወጊ ከመሆኗም በላይ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መሥራችነትም ትታወቃለች፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ታላላቅ ክንውኖች ባለቤት የሆነች አገር ከኮሪያ ልሳነ ምድር ጀምሮ በዓለም ሰላም አስከባሪነት ዝና የተጎናፀፈችም ናት፡፡ መጪው ትውልድ እነዚህን የታሪክ ድርሳናት እየጎለጎለ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ምን ዓይነት ምላሽ ነው የሚሰጠው የሚለው ካላሳሰበ ሌላ የሚያሳስብ ነገር አይኖርም፡፡

በተለይ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በየተራ የተቀያየሩ ትውልዶች አሁን ቆም ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ አዲሱ ትውልድ በተለያዩ መንገዶች ጥያቄዎችን ማቅረብ ሲጀምር፣ እንደተለመደው በግትርነት ምላሽ ለመስጠት አይታሰብም፡፡ ለሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ስንል ልዩነቶቻችንን በምክክር ለማጥበብ አቅቶን ነው የምንፋጀው ተብሎ ድርቅ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ትናንት አንድ ርዕዮተ ዓለም እየተከተሉ በጠባብ የመስመር ልዩነት ምክንያት እንደተፋጁት ፖለቲከኞች፣ ዛሬም ልዩነታቸው ምን እንደሆነ በውል ሳይታወቅ እርስ በርስ የሚሳደዱና የሚጋደሉ ጠበኞች በርክተዋል፡፡ የትናንቱ የስህተት መንገድ በተለያዩ ተዋንያን ሲደጋገም፣ ችግሩ ያለው አሁንም ከፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ መውጣት የማይፈልጉ የትናንት ሰዎች ዘንድ ነው ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አንድን ነገር በተመሳሳይ መንገድ እያከናወኑ ውጤት መጠበቅ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በተለመደ ስህተት ውስጥ እያለፉ የማይመጣ ነገር መጠበቅም ሞኝነት ነው፡፡ ስለዚህ በፖለቲካው ጎራ ውስጥ ያሉ የቀድሞ ሰዎችና ስብስቦች ለአዲሱ ትውልድ ቦታውን ይልቀቁ፡፡ እነሱ ለዓመታት ያዳበሩት ቂም፣ በቀል፣ ጥላቻና ክፋት ኢትዮጵያን መቀመቅ ውስጥ ቀረቀራት እንጂ ምንም አልረባትም፡፡ ለአገራችሁ የምታስቡ ከሆነ የቀድሞዎቹ ገለል በሉ፡፡

‹‹አዲሱ ትውልድ የአገር ተረካቢ ነው›› ሲባል እንዲሁ ለአባባል ያህል የሚነገር መሆን የለበትም፡፡ ትውልዱ ከበፊቱ ትውልድ መልካም የሚባሉትን ነቅሶ በማውጣት፣ አይረቤዎቹን ደግሞ የማስወገድ ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በርትቶ ትምህርቱን መከታተል፣ የዘመኑን የቴክኖሎጂ ትሩፋቶች መታጠቅ፣ ዓለም የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ማጤን፣ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ መስጠት፣ ከአድልኦና ከሌብነት ራሱን ማራቅ፣ በሞራልና በሥነ ምግባር መታነፅና ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ የማስተናገድ ጨዋነትን መላበስ ከብዙ በጥቂቱ ሊረዳቸው የሚገቡ ተግባራት ናቸው፡፡ በተጨማሪም ለአገር ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ግንባር ቀደም ዘብ መሆን፣ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች ጥብቅና መቆም፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን አርዓያ መሆንና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሥልጣንና ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ አገር ስትከበርና የሕዝብ ድምፅ ሲደመጥ፣ ለግጭትም ሆነ ለአውዳሚ ጦርነት የሚዳርጉ ሰበቦች በሙሉ ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ በሕዝብ ስም መቆመርና ማጭበርበር አይቻልም፡፡ አዲሱ ትውልድ እርስ በርሱ እየተከባበረ ሲፎካከር ዴሞክራሲ የማንም መቀለጃ አይሆንም፡፡ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ቅቡልነት ያለው ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል አስተማማኝ ምኅዳር መፍጠር የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዶ በሰላም መኖር የሚቻለው እርስ በርስ በመከባበርና ዕውቅና በመሰጣጠት እንጂ፣ አዲሱ የበፊቱን እየወቀሰና እያዋረደ የራሱን ሥርዓት ለማፅናት በሚያደርገው አጉል ዕብሪት አይደለም፡፡ አዲሱ ትውልድ ከዚህ አሳዛኝ ታሪክ በመማር የራሱን አሻራ ለማሳረፍ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በበጎም ሆነ በክፉ የሚታወሱ ታሪኮች አሉ፡፡ እነሱ ለአዲሱ ትውልድ የመነታረኪያ አጀንዳ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በሥልጣኔ ወደፊት የገፉ አገሮች ከበፊቱ መልካሙን በመውሰድ፣ አስከፊውን ደግሞ በመተው ነው ግስጋሴያቸውን ያሳመሩት፡፡ የራስን ግዳጅ ሳይወጡ የበፊቱ ላይ አተካራ መፍጠር የደካማ ፖለቲከኞች ተግባር መሆኑን በመገንዘብ፣ አዲሱ ትውልድ የራሱን ደማቅ ታሪክ የሚያጽፈው የአገር ግንባታ ላይ ያተኩር፡፡ ይህችን የመሰለች በተፈጥሮ ፀጋ የታደለችና ብርቱ ሕዝብ ያላት አገር ከተሠራባት፣ ከራሷ ተርፈው ለዓለም የሚዳረሱ በረከቶች አሏት፡፡ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን በሙሉ አዲሱ ትውልድ አገር እንዲረከብ ከቤተሰብ ጀምሮ አግዙ፡፡ ለአገር ህልውና ሲባል ለአዲሱ ትውልድ ዕድል ይሰጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...