ወደ ውጭ የሚላኩ የሰብል ምርቶች በመጋዘን ውስጥ እየተከማቹ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገልጸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኢንቨስተሮች በራሳቸው ማሳ ከሚያመርቱትም ሆነ በኮንትራት እርሻ የሚያገኙትን ምርት በስድስት ወራት ውስጥ ለገበያ እንዲያቀርቡ ግዴታ ጣለ፡፡
ኢንቨስተሮች በኮንትራትም ሆነ በኢንቨስትመንት እርሻ ያለሙትን የሰብል ምርት በበጀት ዓመቱ በማስመዝገብ ለገበያ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው፣ ሚኒስቴሩ አዲስ ባወጣው በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የለማ ምርት የግብይት አፈጻጸም መመርያ ደንግጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ ምርታቸውን ያላስመዘገቡም ሆኑ አስመግበው ለገበያ ያላቀረቡ ኢንቨስተሮች፣ በቀጣዩ የምርት ዘመን ምርታቸውን ማስመዝገብም ሆነ ወደ ውጭ መላክ እንደማይችሉ ተመልክቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኢንቨስተሮቹ በራሳቸው ማሳ ካመረቱት ወይም በኮንትራት እርሻ ካስመረቱት ምርት ውጪ ለገበያ ማቅረብ፣ ማጓጓዝ ወይም ማከማቸት እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን መመርያ ያወጣው በውልና በኢንቨስትመንት እርሻ የተመረቱ ምርቶች ግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል፣ እንዲሁም በውድድር ላይ የተመሠረተ የግብይትን ሥርዓት ለማሳለጥ በመፈለጉ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ይህንን አሠራር በመዘርጋትም ከኤክስፖርት ምርቶች የውጭ ገበያ የሚገኘውም ገቢ የማሳደግ ዓላማ አለው፡፡
በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 72 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ከግብርና ምርቶች ውስጥ ደግሞ ቡና 1.4 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ቀዳሚ ነው፡፡ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ የዕቅዱን 69 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ሚኒስቴሩ ሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም. በአዳማ፣ በቡራዩ፣ በቃሊቲና በገላን ከተሞች ባደረገው ፍተሻ በ26 መጋዘኖች ውስጥ ከ235 ሺሕ ቶን በላይ ጥራጥሬና የቅባት እህል ተከማችቶ ማግኘቱን አስታውቆ ነበር፡፡ እነዚህ መጋዘኖች ለሦስት ወራት ታሽገው ከቆዩ በኋላ ሐምሌ ወር ላይ ተከፍቶላቸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ፣ ‹‹ምርቶቹ የተከማቹት የመሸጫ ዋጋ ከፍ ይላል በሚል ግምት ተጨማሪ ትርፍ ለማግኘት ነው፤›› የሚል ግምት ያለው ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ የሚኖራቸውን ድርሻ ያሻሽላል የሚል ግምት መኖሩም ምክንያት እንደነበር ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ ያወጣው አዲስ መመርያ፣ አስመራችም ሆነ አምራች የሆኑ ኢንቨስተሮች የሰብል ምርታቸውን መጠንና ዓይነት በአካባቢው በሚገኝ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት መረከቢያ ማዕከል በማቅረብ ማስመዘንና ትክክለኛ የምርቱን መጠን ማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡ የተመዘነውንም ምርት መጠን መረጃ በአሥራ አምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
ይህንን የሰብል ምርት በምርት ዘመኑ እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም ምርቱን በማዘጋጀት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሽያጭ መፈጸም እንዳለባቸው በመመርያው አስቀምጧል፡፡ ኢንቨስተሩ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሽያጭ መፈጸም ካልቻለ ወደ ሚኒስቴሩ ቀርቦ አሳማኝ ምክንያት በማቅረብና በማስመዝገብ፣ እስከ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲራዘምለት ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፡፡
ኢንቨስተሮቹ የምርታቸውን ዓይነትና ብዛት መረጃ በሚያቀርቡበት ጊዜ የመረጃውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም በመመርያው ላይ የተቀመጡ ሌሎች ድንጋጌዎችን ለማስፈጸም ሲባል፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የክልል ንግድ ቢሮዎች ልዩ ኮሚቴ እንደሚያቋቁሙ መመርያው ያመላክታል፡፡
የሰብል ምርቶቹ በትክከለኛ ዋጋ ምርት ስለመገዛቱ ወይም በዓለም አቀፍ የመሸጫ ዋጋ የሎጂስቲክስ ወጪን ታሳቢ በማድረግ፣ ለውጭ ገበያ ስለመሸጡ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነትም ሚኒስቴሩና ቢሮዎቹ ላይ ተጥሏል፡፡
ሚኒስቴሩ በ2015 በጀት ዓመት 221,916 ቶን የቅባት እህልና 274,785 ቶን የጥራጥሬ ምርቶችን ወደ ውጭ የመላክ ዕቅድ ያለው ሲሆን፣ ከዚህም 595.19 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ይዟል፡፡ ዘንድሮ ከጥራጥሬና ቅባት እህል ይገኛል ተብሎ የታሰበው ገቢ ባለፈው ዓመት ከተገኘው በ118.1 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ያለው ነው፡፡