Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት ለሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ለመስጠት ቃል ገባ

መንግሥት ለሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ለመስጠት ቃል ገባ

ቀን:

የኢትዮጵያ መንግሥት ለጎረቤት አገር ሶማሊያ የመንግሥት ሠራተኞችና የፀጥታ አካላት የተለያዩ ዓይነት ሥልጠናዎች ለመስጠት ቃል መግባቱ ተገለጸ፡፡

በሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ የሆነውን ፕሬዚዳንታዊ ጉብኝት ከመስከረም 18 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ያደረጉት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በነበራቸው ቆይታ በርካታ ስምምነት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

የጉብኝቱን መጠናቀቅ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው፣ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ባደረጉት ውይይትና ስምምነት የሶማሊያ የመንግሥት ተቋማትን አቅም ለመሻሻል የሚረዱ ሥልጠናዎችንና ነፃ የትምህርት ዕድሎች በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እንዲቀርቡ የሚያስችሉ ስምምነቶች ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ አገሮች በንግድ፣ በኢኮኖሚ፣ በኮሙዩኒኬሽንና በመሠረተ ልማት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር መስማማታቸውን በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ሕዝብን ማዕከል በማድረግ ሉዓላዊነታቸውንና የግዛት አንድነታቸውን የጠበቀ ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ሽብርተኝነት፣ ጽንፈኝነትና የጋራ ጠላቶቻቸው ላይ አብረው ለመሥራት፣ የደኅንነት መረጃዎች ልውውጥ ለማድረግና በትብብር የሚሠሩባቸውን ጉዳዮች የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸው ተሰምቷል፡፡ በቅርቡ በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አልሸባብ የፈጸመውን ጥቃት ለመከላከል የተወሰደው ዕርምጃ በመሪዎቹ አድናቆት እንደተቸረው በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

የሁለቱ አገሮች መሪዎች ሶማሊያ የአልሸባብ የሽብር ቡድን የሚያደርሰውን የፀጥታ ሥጋት መመከት የሚያስችል በቂ አቅም ላይ እንድትሆን፣ ከ30 ዓመታት በላይ ተጥሎ የቆየውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ጥያቄውን እንዲያጤነውና ማዕቀቡን እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች በጋራ በሰላም ግንባታና በፀረ ሽብር ትግል ላይ የጀመሯቸውን ትብብሮች ሚና ሊቀንስ የሚችል የውጭ ኃይሎች ያልተፈለገ ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ በጋራ ለመሥራት፣ መደበኛ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ሊያስከብሩ የሚችሉ ቀጣናዊና ዘርፈ ብዙ ትብብሮች ላይ ለመሥራት መስማማታቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ለተከታታይ ዓመታት በድርቅ እየተጎዳ ያለውን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናና የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ለመታደግ አሁን እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጥፍ በማሳደግ እንደሚሠሩ መስማማታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ለጋሽ አካላት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠይቀዋል፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሁለት ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ዓርብ መስከርም 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ባለፈው ግንቦት ወር ሶማሊያ ውስጥ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን የለቀቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ (ፎርማጆ)፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ከኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጉብኝትን በተመለከተ ስለሚፈጥረው ፖለቲካዊ አንድምታ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፤ መሐመድ አብዱላሂ (ፎርማጆ) ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ሶማሊያ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሶስት የፈጠሩት ግንኙነት ሲታይ በጥሩ ሊገለጽ የሚችል እንደነበር፣ ነገር ግን በተቃራኒው አዲሱ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ወደ ግብጽ አምርተው ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር በተለይም ስለህዳሴ ግድብ ሰጡት የተባለውን ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ያስከፋ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በግብፅ ጉብኝታቸው ወቅት የህዳሴ ግድቡ ድርድር የግብፅና ሱዳንን ፍላጎት በሚጎዳ መንገድ መደረግ እንደሌለበት በሰፊው ተወርቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሰሞነኛው የፕሬዚዳንቱ የአዲስ አባባ ጉብኝት በሁለቱ አገሮች ዙሪያ ሲያንዣብብ የነበረውን ብዥታ፣ በሁለቱ አገሮች ላይ ይነሱ የነበሩ አስተያቶችንና ዕይታዎች በተለይም ፕሬዚዳንቱ የግብፅን ፍላጎት እንጂ የኢትዮጵያን ፍላጎት አያራምድም የሚለውን እሳቤ የማስተካከል ሁኔታ እንደሚፈጥር ሳሙኤል (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ሳሙኤል (ዶ/ር) እንደሚሉት በሁለት የአገር መሪዎች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ቁርጠኛ የሆኑ ጉዳዮች እንዳለ ማሳያ መሆኑን፣ በመካከላቸው ያሉ ችግሮችን ለመነጋገርና ለመፍታት የሚወሰድ ዕርምጃ ተደርጎ እንደሚወሰድ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የቀረበው የሥልጠናና ነፃ የትምህርት ዕድል ደግሞ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የተደረገ አንድ ትልቅ ዕርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ የተጣለውን የመሣሪያ ግዥ ማዕቀብ እንዲነሳ ከሁለቱ መሪዎች የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ አስተያታቸውን የሰጡት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ አልሸባብ አሁንም ቢሆን ከሶማሊያ አልፎ በዙሪያው ላሉ አገሮች አሥጊ እንደሆነ፣ ነገር ግን ደግሞ መሣሪያ መግዛት የአንድ አገር ሉዓላዊ መብት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በቀጣናው አስተማማኝ ሰላም በሌለበት ሁኔታ እንደዚህ ዓይነት የማዕቀብ ይነሳልኝ ማለት የሚያስቸግር ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን የመሰሉ አገሮች የድጋፍ መስጠት እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ ገብቶ ጥያቄው ተገቢ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ አሁንም ቢሆን መደረግ ያለበት ጠንካራ የሆነ የፀጥታና የወታደራዊ አቅም፣ እንዲሁም በቀላሉ በአሸባሪ እጅ መግባት የማይችል ኃይል ከማደራጀት ጋር አብሮ የሚሄድ ጉዳይ መሆኑን አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ ሁለቱ አገሮች ቁርጠኛ ከሆኑና ሰላምን የጋራ ጉዳይ ካደረጉ፣ በመተሳሰርና ፀጥታ በማስፈን ዘላቂ የሆነ ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት ይቻላል ሲሉ ሳሙኤል (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...