መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን፣ የንብረት ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ ሥልጣንን በተመለከተ ውሳኔ ማስተላለፍ የሁለቱ ምክር ቤቶች ቀዳሚ አጀንዳ እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶች በሚቀጥለው ሳምንት ዓመታዊ የጋራ ጉባዔ እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዕለቱም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመክፈቻ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ የመክፈቻ ንግግር በኋላ የንብረት ታክስ የመሰብሰብ ሥልጣንን አስመልክቶ የውሳኔ ሐሳብ ለሁለቱ ምክር ቤቶች እንደሚቀርብ፣ ምክር ቤቶቹም በዕለቱ ወይም በማግሥቱ ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደሚችሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፊስካል ጉዳዮችና የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት ጥናት ዳይሬክተር አቶ ዋቅቶሌ ዳዲ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሁለቱ ምክር ቤቶች በሚያደርጉት የጋራ ጉባዔ ላይ የሚያቀርበውና የንብረት ታክስ በማን ይሰብሰብ የሚለውን የተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳቡን የሚያዘጋጀው ከገንዘብ ሚኒስቴር የቀረበለትን የጥናት ወረቀት መርምሮ፣ እንዲሁም በሳምንቱ አጋማሽ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተገኙ ምክረ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የውሳኔ ሐሳቡ ላይ ከአንድ በላይ አማራጮች ከነማብራሪያቸው እንደሚካተቱ የተናገሩት አቶ ዋቅቶሌ፣ ሁለቱ ምክር ቤቶች የየራሳቸውን የውሳኔ ሐሳብ የሚያዘጋጁ ቢሆንም፣ በጋራ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩን አብረን እያየነው እየመጣን ስለሆነ ብዙም የሐሳብ ልዩነት አይኖረንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ይሁንና ሁለቱ ምክር ቤቶች የሚያዘጋጇቸውን የውሳኔ ሐሳቦች በጋራ ጉባዔው ላይ ከማቅረባቸው በፊት፣ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎቻቸው ያፀድቃሉ፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚመለከተው ሲሆን፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ይዞታል፡፡
ሪፖርተር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ያለበትን ዝግጅት ለማወቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ በመሆን ውሳኔ ለማሳለፍ ዝግጅት እያደረጉ ያሉት የገንዘብ ሚኒስቴር የንብረት ታክስ ለመጣል ያለውን ሐሳብ ገልጾ፣ ይህንን ታክስ የመሰብሰብ ሥልጣን የማን እንደሆነ እንዲወሰን ለሁለቱ ምክር ቤቶች ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው፡፡ የንብረት ታክስ ጉዳይ የመሰብሰብ ሥልጣንን በተመለከተ ጥያቄ ያስነሳው ይህ ታክስ በሕገ መንግሥቱ ላይ ያልተጠቀሰና ሥልጣኑም ተደንግጎ ያልተቀመጠ የታክስ ዓይነት በመሆኑ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 96 እስከ 98 ባሉት ክፍሎቹ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል እንዲሁም የጋራ የሆኑ የግብር ሥልጣኖችን ዘርዝሯል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 98 ተዘርዝረው ያልተወሰኑ የታክስና ግብር ሥልጣኖችን በተመለከተ፣ ሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ምክር ጉባዔ አድርገው በሁለት ሦስተኛ ድምፅ እንደሚያፀድቁ አስቀምጧል፡፡
ሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻቸውን ካከናወኑ በኋላ የሚያሳልፉት ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ ሁለት ቀጣይ ዕርምጃዎች እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ ዋቅቶሌ፣ ይህንን ግብር የመሰብሰብ መብት የክልል መንግሥታት ነው ተብሎ የሚወሰን ከሆነ ክልሎች በሕገ መንግሥታቸውና ባላቸው አዋጅ የማውጣት ሥልጣን ላይ ተመርኩዘው በራሳቸው ሕግ አውጥተው መተግበር እንደሚጀምሩ አስረድተዋል፡፡
ውሳኔው ከዚህ ተቃራኒ ሆኖ ከንብረት ግብር የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጋራ ሥልጣን ነው ተብሎ ከተወሰነ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁለቱ መንግሥታት ከግብሩ የሚገኘውን ገቢ እንዴት እንደሚከፋፈሉ ለመወሰን ወደ ቀመር ዝግጅት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ ጎን ለጎን ዝርዝር ጉዳዮችን የሚይዝ አዋጅ ያዘጋጃል፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ምክር ቤቱ ቀመሩን የሚያዘጋጀው የክልልና የፌዴራል መንግሥት ምን ያህል ድርሻ ይኑራቸው ብሎ ቢሆንም፣ ከተሞችም ምን ያህል ያግኙ የሚለውን አብሮ በምክረ ሐሳብነት ያቀርባል፡፡ ከተሞች ከንብረት ግብር ማግኘት የሚገባቸው ገቢ በምክረ ሐሳብነት የሚቀርበው ሕግ መንግሥቱ ዕውቅና የሰጠው በክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚሰበሰቡ ታክሶችን ብቻ በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ለከተሞች ክፍፍል ለማዘጋጀት ሥልጣን ስለሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ምክረ ሐሳብ ከማቅረብ በስተቀር ከክልል ወርደን ይህ ወረዳ ይህ ከተማ ይህ ድርሻ ይኑረው ማለት ይከብዳል፡፡ ግን ዝም ብለን ወደ ክልል ብቻ ወርውረን በኋላ ግብሩ የከተሞችን የልማት ችግሮችን የማይፈታ ከሆነም አስቸጋሪ ይሆናል፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አብራርተዋል፡፡
የንብረት ግብር የሁለቱ መንግሥታት የጋራ ሥልጣን ነው ተብሎ ከተወሰነ የድርሻ ክፍፍሉ ተዘጋጅቶ ከመፅደቁ በፊት፣ ውይይቶች እንደሚደረጉና የጋራ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና የገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ ዓመት ገቢውን ለማስፋት በማሰብ ሊያደርግ ካሰባቸው የታክስ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ውስጥ አንድኛው የንብረት ታክስ እንደሆነ የ2015 ዓ.ም. በጀትን አስመልክቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የበጀት ዝርዝር ላይ አሥፍሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከንብረት ታክስ ከሚገኘው ገቢ ውስጥ 25 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት፣ 75 በመቶ ደግሞ ለክልሎች እንዲሆን የውሳኔ ሐሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን በዚሁ ሰነድ ላይ አመልክቷል፡፡
አቶ ዋቅቶሌ የገንዘብ ሚኒስቴርን የውሳኔ ሐሳብ አስመልክቶ፣ ‹‹በሐሳብ ደረጃ ነው ያቀረቡት እንጂ እነሱ የሚወስኑት ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱ የገቢ ድርሻ ክፍፍሉን ቀመር የሚያዘጋጀው በራሱ አሠራር እንደሆነና ቀመሩ ሲዘጋጅ በሚኒስቴሩ ከቀረበው ሐሳብ ሊጨምር፣ ሊቀንስ፣ ወይም ተግባራዊ ለሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡