Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ይኼን ሰሞን የገጠሙኝ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ለገጠመኜ መነሻ ሁነውኛል፡፡ የመጀመሪያውን እንዲህ ልንገራችሁ፡፡ ለረጅም ዓመታት የሥራ ባልደረባዬ የሆነ አንድ ወዳጄ ሁለት ልጆቹን ወልዶ ካሳደገበት ቤት ልቀቅ መባሉን ነገረኝ፡፡ ቤት አከራዮቹ ቤቱን እንዲለቅላቸው ምክንያት ብለው የነገሩት፣ ልጃቸው ከዓረብ አገር ከወለደችው ልጅ ጋር እንደምትመጣ አስተዛዝነው ነው፡፡ ይህም ሰብዓዊነትን የሚፈታተን ማሳሰቢያ የደረሰው ባለፈው ወር ነው፡፡ የሰዎቹ ትክክለኛ ምክንያት ግን በዶላር የውጭ ምንዛሪ ማሻቀብ ምክንያት የተሻለ ዋጋ ስላገኙ ቤታቸውን ለመሸጥ በማሰባቸው ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት የኖረበት ቤት የኪራይ ዋጋው ከሌሎች ቤቶች ጋር ሲነፃፀር በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ማለትም ምናልባት በግማሽ ያህል ያንሳል፡፡ በዚህ ኑሮ ውድነት ድንገተኛ የልቀቅልኝ ጥያቄ የቀረበለት ጓደኛዬ ያስጨነቀው ተረጋግቶ ይኖርበት ከነበረው አካባቢ መልቀቁ ብቻ ሳይሆን፣ በየቀኑ በሚተኮሰው የቤት ኪራይ ዋጋ ምክንያት የሚደርስበት ቀውስ ስላሳሰበው ነው፡፡ ለቀለብ፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች፣ ለልጆች ትምህርት ቤት፣ ለሕክምና አልብቃቃ ያለ ደመወዝ በዋጋ ንረት ያበደውን የቤት ኪራይ እንዴት ይቋቋማል?

የእኔም ሆነ የብዙ የማውቃቸው ወዳጆቼ ጭንቀት የመኖሪያ ቤት ችግር ነው፡፡ በአንድ ወቅት በ500 ብር ይከራይ የነበረ የኮንዶሚኒየም ስቱዲዮ ዛሬ እንደ ቦታው ከስምንት ሺሕ ብር በላይ ይጠየቅበታል፡፡ እሱም ቢሆን በደላሎች አሻጥር እንዲህ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ባለአንድ መኝታ ቤትማ ከ12,000 ብር በላይ ይጠራል፡፡ እሱንም ለማግኘት ፈተና ነው፡፡ የግለሰብ ግቢ ውስጥ ሰርቪስ ቤት ለመከራየት ሲፈለግ በትንሹ ከተባለ ከሰባት ሺሕ ብር በታች አይገኝም፡፡ በዚህ ላይ ውኃ፣ ኤሌክትሪክና መፀዳጃ ቤት ለማግኘት የተለያዩ ያልተጻፉ ሕጎች እየወጡ የሰውን ልጅ በገዛ አገሩ መከራ ያሳያሉ፡፡

በአንድ ወቅት ቤታቸውን ያከራዩኝ ሰው በምሽት የቤቴን በራፍ ያንኳኩና ያስከፍቱኛል፡፡ ገፍተር አድርገውኝ ገብተው ጠባቡን ሳሎንና መኝታ ቤቴን በዓይናቸው ከላይ እስከ ታች ከፈተሹ በኋላ፣ ‹‹የኤሌክትሪክ ምድጃና ካውያ እንደምትጠቀም ለማረጋገጥ ነው…›› ብለውኝ በፍጥነት ወጡ፡፡ በአጋጣሚ ፈተና ደርሶብኝ ስለነበር ሶፋዬ ላይ ከዘረጋኋቸው መጻሕፍትና ላፕቶፕ በስተቀር ምንም ማግኘት አልቻሉም፡፡ እሳቸው በድንገት ሳያስፈቅዱ ገብተው ቤቴን መፈተሻቸው ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው የሆነብኝ፡፡ በነጋታው በማለዳ ተነስቼ ቤታቸው ዘው ብዬ ከገባሁ በኋላ ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ቢፈጽሙ በሕግ እንደምጠይቃቸው ስነግራቸው፣ ‹‹በገዛ ቤቴ? በል ኮተትህን ይዘህ በአስቸኳይ ልቀቅ…›› ብለውኝ ተለያየን፡፡ የቤት ኪራይ ከዋጋ ንረቱ በተጨማሪ ሰብዓዊ መብትም ይጣስበታል፡፡ ጎጆአቸውን ቀልሰው የሚኖሩ ጠግበው ባይበሉ እንኳ ምንኛ የታደሉ ናቸው?

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ እንዲህ ነው፡፡ የምሠራበት መሥርያ ቤት አለቃችን ሰላማዊ ሰው ቢሆኑም፣ የጋጠወጥ ልጆቻቸው ባህሪ ግን በጣም ያናድደኛል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆኑት ሦስት ልጆቻቸውን ከሚገባው በላይ አሞላቀው ስለሚያሳድጓቸው ብልግናቸው በጣም ያሳዝናል፡፡ ያገኙትን ይሳደባሉ፣ ይተርባሉ፣ ያንቋሽሻሉ፡፡ በዚያ ላይ ቢሮ ሲገቡ ያገኙት ጠረጴዛ ላይ ወጥተው ይጨፍራሉ፡፡ ሠራተኞች ሥራ ላይ እያሉ በመጎንተልና ልፊያ በመፍጠር ያበሳጫሉ፡፡ እነዚህ ልጆች ቢሮ በመጡ ቁጥር በነፍስ ወከፍ እስከ አሥር ሺሕ ብር ይሰጣቸውና ወደ ፈለጉበት ቦታ ሄደው እንዲዝናኑ ይደረጋሉ፡፡

መቼም እኛ ሐበሾች ስንባል በይሉኝታ የታጠርን ነንና አንድም ቀን እነዚህን ልጆች ተናግረን አናውቅም፡፡ ወይም ከአባታቸው ጋር አንነጋገርም፡፡ አንድ ቀን ቢቸግረኝ በጸሐፊዋ በኩል ቀጠሮ ይዤ አለቃችን ዘንድ ገብቼ ስለልጆቻቸው ጉዳይ አነሳሁባቸው፡፡ በትክክል ተገስጸው አለማደጋቸውን፣ ይህንን ባህሪ ይዘው ቢሮ መምጣት እንደሌለባቸው፣ በየጊዜው ሲመጡ ይህን ያህል ገንዘብ እያፈሱ ለልጆች መስጠት ትክክል አለመሆኑንና ሌሎች ነገሮችንም ነገርኳቸው፡፡ አለቃችን ያልኩት ሁሉ ትክክል መሆኑን ከነገሩኝ በኋላ ለልጆቹ መበላሸት ሚስታቸውን ምክንያት አደረጉ፡፡

‹‹አየህ…›› አሉኝ፡፡ ‹‹…አየህ እኔ ልጆቹ በጥሩ ሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ እፈልጋለሁ፡፡ ለጥሩ ትምህርት ቤት ከፍተኛ በጀት መድቤ አስተምራለሁ፡፡ ሚስቴ  ደግሞ የሚበሉት፣ የሚጠጡትና የሚዝናኑበት ሳያንሳቸው ከአባቷ ከወረሰችው ቤት በወር የምታገኘውን 60 ሺሕ ብር የቤት ኪራይ ለሦስቱ ታከፋፍላለች፡፡ እነሱ እኔን እንደ ጨቋኝ እያዩኝ ስለሚጠሉኝ በመጡ ቁጥር በነፍስ ወከፍ አሥር ሺሕ ብር እሰጣቸዋለሁ…›› ሲሉኝ አዘንኩ፡፡ እኛ ለአንገት ማስገቢያ ከደመወዛችን ከግማሽ በላይ እንከፍላለን የቅንጡዎቹ ልጆች ከቤት ኪራይና ከትርፍ በሚገኝ የደለበ አበል ይንፈላሰሳሉ፡፡ እነሱ ያላግባብ የሚያገኙትን ገንዘብ ገበያ ውስጥ እየበተኑ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ከመፍጠራቸውም በላይ፣ ምስኪኖች እየተሳቀቁ በሚከፍሉት ገንዘብ እየጨፈሩ ስቃይ ይፈጥሩብናል፡፡ ምስኪን ተቀጣሪዎች ወር ሙሉ ላባቸውን ጠብ እያደረጉ የሚያገኙት ገንዘብ እንደ እሳት የሚለበልበውን የኑሮ ውድነት አልቋቋምም ሲል፣ የሀብታሞቻችን ሞልቃቆች ለ‹ዴይ ፓርቲ›፣ ለጫት፣ ለሐሺሽ፣ ለመጠጥና ለሌላም ለሌላም የሚረጩት የኃጢያት ገንዘብ ያንገበግባል፡፡ ድንቄም ዕድገት፡፡ ‹‹እናቱ የሞተችበትና ወንዝ የወረደችበት እኩል ያለቅሳሉ›› የሚባለው እንዲህ ዓይነቱ ፍፁም ተቃራኒ አኗኗር ሲያጋጥም አይደል?

(መኩሪያ ታመነ፣ ከሃያ ሁለት ማዞሪያ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...