Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአገራችን ውስጥ የተፈለፈሉትና የተዘረገፉት ችግሮች መነሻና መፍትሔው ምንድነው?

አገራችን ውስጥ የተፈለፈሉትና የተዘረገፉት ችግሮች መነሻና መፍትሔው ምንድነው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በሕዝብ ላይ የደረሰን ያለፈም ይሁን የቅርብ ጊዜ በደልና ጉዳት እየነካኩ መጨስና ማጫጫስ፣ እንዲያም ሲል የትናንትናን ጉዳት በዛሬዎቹ ላይ የማወራረድ ዝንባሌ ወደ ማፋጀት ከመምራት በስተቀር፣ ለሰላምና ለዕድገት አንዲት ጠብታ እንደማያወጣ እስኪበቃ ታይቷል፡፡ በደም የጨቀየ ታሪክ ዓለማችን የተገነባችበት ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ልዩ ችግር፣ በየትም ታይቶ የማይታወቅ ነገር የተፈጸመ አስመስሎ ማላዘን አጥፊ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ በሚዛናዊ አዕምሮ ለመገንዘብ የሞከረ ሰው በታሪካችን ውስጥ በደቡብ ሕዝቦች ላይ የደረሱ ቅጣቶች (ቃጠሎዎች፣ ዘረፋዎች፣ ጭፍጨፋዎች፣ በባርነት የመነዳት፣ የሰለባና የፉነና ድርጊቶች… ሁሉ) በ‹‹ባዕድ›› ሕዝብ ላይ ያነጣጠሩ፣ ለ‹‹ባዕድ›› ሕዝብ ታስበው የተፈጸሙ እንዳልነበሩ በሰሜኑም ሕዝብ ላይ፣ ያውም ለረዥም ጊዜ ሲፈጸሙ የኖሩ እንደነበሩ ያስተውላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1770 ጎንደር የደረሰው ጀምስ ብሩስ (የተባለው በኢትዮጵያ ታሪክ በሰፊው የሚጠቀሰው ጸሐፊ) እንደ መሰከረው የጦር ምርኮኛ ሆኖ መሰለብ፣ ዓይንን መጎልጎል፣ ጆሮንና አፍንጫን ወይም እጆችን፣ እግሮችን መቆረጥና የመሳሰሉት ቅጣቶች የማንኛውም ሰው ፍርኃት የማንኛውም ውጊያና ጦርነት ውጤት ነበሩ፡፡

ከምኒልክ ዘመቻዎች ጋር ተያይዞ በደቡብ የታየው የመሬት ንጥቂያም በሥረ መሠረቱ የጦርነት ውጤት፣ የቅጣትና የምርኮ አንድ መገለጫ ነበር፡፡ ምኒልክን የተዋጉት አርሲ፣ ሐረርና ወላይታ ከሌሎች ቅጣቶች ሌላ የመሬት መነጠቅ ሲደርስባቸው፣ በሰላም እጅ የሰጡት ግዛቶች ግን ከዝርፊያ ድነው ዓመታዊ ግብር እየከፈሉ እንደ ቀድሟቸው እንዲተዳደሩ ተትተው የነበሩት (ታሪክ እንደመዘገበው) በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአጠቃላይ የገባርነት ሥርዓት ከሰሜን ወደ ደቡብ የመሸጋገር ሒደት ውስጥ፣ በሰሜን ያልነበረ የጭሰኝነት ሥርዓት በደቡብ መምጣትም፣ በዘመቻዎች አሸናፊ የነበሩት የነፍጠኛ ኃይሎች በራሳቸው ሊሠሩበት ከሚችሉት እጅግ የበዛ የመሬት ምርኮ የመገኘት አዲስ ሁኔታ የጎተተው ነው፡፡ ይህ አዲስ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መለስ ካለ በኋላ ግን መቆሚያ ያልነበረው መሆኑ እውነት ነው፡፡ የደቡብ ሕዝቦች በልዩ ልዩ መልክ መሬታቸውን እየተነጠቁ አጠቃላይ ምርኮ መውደቅ እስኪመስል ድረስ ለጭሰኝነት ሰቆቃ ተዳርገዋል፡፡

ይህንን እውነት አጠንክሮ ለማሳየት የደቡብ ሕዝቦች ባርነት ገቡ፣ ሁለተኛ ዜጋ ሆኑ ማለት አያስከፋም፡፡ ከዚህ ርቆ ወጥቶ፣ በሰሜኑ ሕዝብና በደቡብ መሀል ነፃ (ምርጥ) ሕዝብና ምርኮኛ (ገባር) የመሆን ልዩነት ለመሥራት መሞከር ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ ሁሉንም ሕዝቦች አንቆ የነበረውን አጠቃላይ የሥርዓቱን የአስገባሪነት የጋራ ባህርይ ከማየት ያደናቅፋል፡፡ በደቡብ ተደራጅቶ የነበረው የከፋ ምዝበራና ጭቆና ይነስም ይብዛ፣ ነባርና አዲስ የተፈለቀቁ የደቡብ ገዥዎችን ያካተተ እንደነበር ከማየትም የሚከለክል ነው፡፡  

ኃይልና ጉልበት ያለው ደካማውን እያስገበረ የተገነባችውን ኢትዮጵያን በኢምፓየርነት መግለጽ አዲስ አይደለም፡፡ የውጭም የውስጥም ታሪክ ጸሐፊዎች ተጠቅመውበታል፣ ፖለቲከኞችም እንዲሁ፡፡ ለዚህ መነሻ የሆናቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ከበቀለ ጥንታዊ ሥልጣኔና መንግሥት የተነሳና ለረዥም ጊዜ የተካሄደ፣ ጦር እያዘመቱ ግዛት የማስፋፋት ሒደት፣ ከዚሁ ጋርም ሲበጠስ ሲቀጠል የኖረ የአስገባሪና የገባር ግዛቶች ግንኙነት ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ጥንታዊ ሮማውያንም ሆነ እንደ ካፒታሊስት ኢምፓየሮች የቅኝ ይዞታዎች የመገንባት ዓይነት ባህርይ የነበረው አይደለም፣ አልነበረም፡፡ ምናልባት በአክሱማውያኑ ጊዜ የተለየ ካልሆነ በስተቀር፣ የላቀ የሥልጣኔና የወታደራዊ ኃይል ማዕከል በማበጀት ራሱን በኃያል ገዥነት ከአካባቢው ወይም በሥሩ ካስገባቸው ተገዥዎች የፈለቀቀ አውራ ቤተ ግዛት ይጎድል ነበር፡፡

ከአክሱማውያኑ ወድቀት በኋላ የሰሜኑ ሕዝብና ገዥዎቻቸው ወደ ታች ያደረጉት መንፏቀቅ የተሻለ መሬት ከመፈለግ ጋር የተያያዘ አገር የማስፋት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ አብሮም የሥልጣን ማዕከል መንሸራተት ከጊዜ ጊዜ የቀጠለበት፣ ጭራሹንም ዘዋሪ እስከ መሆን የደረሰበት ሁኔታ ውስጥ ተገብቶ ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ ሕዝቤ፣ አገሬ የሚልና ባዕዳን፣ ገባሮቼ የሚል ድንበር ወይም ልዩነት ለማበጀት የማይመች ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ የሕዝቦች የሁለት አቅጣጫ እንቅስቃሴ (ከሰሜን ወደ ታች የአማራ፣ የጉራጌ፣ የአርጎባ፣ የአደሬ፣ ከታች ወደ ላይ የሶማሌና በተለይ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ መዛመት) የሰፊ ዓውደ ሕዝብ መፈጠር መገለጫ ነበር፡፡

በሌላ አንፃር፣ እየዘመቱ ደካማውን በሥር የማስገባቱ ትግል በአንድ ወገን ማለትም በሰሜኑ ገዥዎች ብቻ የተካሄደ አልነበረም፡፡ የቀሪዎቹ ትግልም በሰሜኑ ኃይሎች ሥር ባለማደር ወይም ነፃ በመውጣት ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በሰሜን በመካከለኛና በደቡብ ምሥራቅ በነበሩ ቤተ መንግሥታት መካከል አሸናፊነትና ተሸናፊነት የታየባቸው የበላይነት ትንቅንቆች ተደርገዋል፡፡

ዞሮ ዞሮ የበላይነቱ ከሰሜኖቹ መዳፍ ያልወጣ ቢሆንም፣ የሰሜነኛ ኢምፓየር አልተገነባም፡፡ በዘመነ መሳፍንት ጊዜ በሰሜን የነበረው የኃይሎች ትንቅንቅ በስተኋላም እነ ቴዎድሮስ፣ እነ ዮሐንስና እነ ምኒልክ የነበራቸው ግብግብ የኢምፔሪያል ኃይሎች የውስጥ ክፍል ወይም ሰሜነኛ ያልሆኑት ሕዝቦችን በመግዛት ሽሚያ ላይ የሚካሄድ ፀብ አልነበረም፡፡ ካስገበረ ኃይል የመውጣት ትግሉ በደቡብ ብቻ ሳይሆን በሰሜንም ነበር፡፡ የበለጠ ጉልበት እያበጀ የመጣውም ሌሎችን በሥልጣኑ ሥር ጠቅልሎ ለማስገባት ታግሏል፡፡ ጎንደርን፣ ጎጃምን፣ ትግሬን ወሎንና ሸዋን በአንድ ማዕከላዊ ሥልጣን ሥር ለማስገባት የተካሄደው ትግልና ከዚያ ተያይዞ ቀጥሎ የተከናወነው ደቡብ ኢትዮጵያን የማስገበር ጉዞ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ሳይሆኑ የአንድ ሒደት፣ አንድ የተጠቃለለ ሥልጣንና አገር የመፍጠር ምዕራፎች ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጠበቀ ማዕከላዊ ሥልጣን ሳይፈጠር ግብር አስገቢ ግዛቶች የሚታዩበት ልል የሥልጣን ግንኙነት (እየተፈታ እየተቋጠረ) ለረዥም ጊዜ ሊቆይ የቻለውም ‹‹ሐበሾች›› ከደቡብ ሕዝቦች ጋር ለመቀላቀል ስላልፈቀዱ ሳይሆን፣ በወጉ ለመጠቅለልና የበላይነቱን ለማፅናት የሚያስችል የጉልበት ብልጫ ያለው ኃይል ሊፈጠር ባለመቻሉ ነበር፡፡ ገዥነት ‹‹የሐበሻ›› ተገዥነት ለደቡብ የሚል ገደልም አልነበረም፡፡ የየጁ የኦሮሞ መሣፍንት የተፈጠሩበትንና ጎንደር ቤተ መንግሥት የገቡበትን ታሪክ አስታውሷል፡፡ ከዚያም በኋላም ቢሆን የመኳንንትነት መንገዱ ለሌላው ብሔር የተዘጋ አልነበረም፡፡ የቱንም ያህል ትምክህት ቢዳብር አማራን፣ ትግሬን፣ አገውን በሐበሻነትና በበላይነት ለይቶ የሰቀለ አመለካከት አልተፈጠረም፡፡ ከደቡብ ሀብት እየተጋዘ የ‹‹ሐበሻ›› ምድርን (ትግሬን፣ አገውን፣ አማራን) ያበለፀገበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የሰሜን ሕዝቦች እንደ ሌላው በድህነት ሲማቅቁ፣ ከሌላ በላቀ ደረጃም ከረሃብና ከስደት ጋር ሲኖሩ የቆዩ ናቸው፡፡ የምኒልክ አንኮበር – መንዝ አካባቢ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትምህርት ቤትና መንገድ እንኳ ብርቅ ሆኖ የቆየበት ኋላቀር ሥፍራ ነው፡፡ ‹‹ጎጃሜ›› በወለጋ፣ ‹‹አጋሜ›› በአስመራ የኩሊ መጠሪያ የነበረው፣ ወሎ የረሃብተኛ ተምሳሌት የነበረበት ታሪክ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ምኒልክና ኃይለ ሥላሴ ከሚተቹባቸው ነገሮች አንዱ ኦርቶዶክስ ክርስትና በአማራና በትግሬ ባህልና በአማርኛ ቋንቋ አማካይነት አንድ ሕዝብ ለማነፅ መሞከራቸው ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ስለ ‹‹ሐበሻ ኢምፓየር›› የሚያወሩትም አይክዱትም፡፡ በአንድ በኩል አንድ ሕዝብ የመፍጠር ሥልት እንደነበር እየከሰሱና እየተናገሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቡብ ሕዝቦች በሰሜነኞች ሥር በባርነት እየማቀቁ ይገኛሉ ብሎ ማለት ራስን መቃረን ነው፡፡ ደርግ ጭሰኝነትን ካፈረሰ በኋላ፣ በኢሕአዴግም ጊዜ የብሔሮችን በቋንቋ የመሥራትና የመተዳደር መብት ተግባራዊ ተደርገ ከተባለ በኋላ ጭምር፣ ስለኢምፓየርና ስለገባርነት ሰበብ የሆነው የቱ እንደሆነ ለመለየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ደግሞም የሰሜነኞች ‹‹ኢምፓየር›› የሚያሰኘው የበላይ ገዥዎቹ ትግሬ – አማራ መሆናቸውና ሆነው መቆየታቸው ከሆነ፣ የበላይነቱ በኦሮሞዎች ቢተካ የኦሮሞ ኢምፓየር ሊባል ነው ማለት ነው? በሕወሓት ጊዜም እንዲህ እንደ አሁኑ ‹‹አይሰማም›› እንጂ ይኼው ይባል ነበር፡፡ ኢምፓየራዊ አገዛዝ አለ ለማለት ያስደፈረው (ያኔ ለምሳሌ) ትግራይ ከሌላው የተለየ ተጠቃሚ ሆናለች መባሉ ከሆነ ይህም የባሰ ስህተት ነው፡፡ ትግራይ ብቻዋን ሰሜን አትሆንም፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ክልል›› የማድላት ፖለቲካዊ ውዝግብ ራሱ ከእነ ስያሜው በቅርብ ጊዜ የመጣ ክስተት ነውና ከኢሕአዴግ በፊት ለነበረው ዘመን ማስረጃና መከራከሪያ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ኢምፓየሩ በኢሕአዴግ ዘመን ወይም የእሱ የበላይነት ሲቀር ጀመረ ካልተባለ በስተቀር፡፡

በአጠቃላይ የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ የገነባት ጦርነትም ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ቅርፅና ይዘት ብዙ ውጥንቅጦሽ የወጠወጠውና ያዛመደው ነው፡፡ ከላይ ወደ ታች ብቻ ሳይሆን ከታችም ወደ ላይ የተደረጉ ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አዝጋሚም፣ ፈጣንም የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ጭምር ኢትዮጵያን ፈጥረዋል፡፡ ሕዝብ የተንቀሳቀሰውም በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ በጦርነት ብቻም አይደለም፡፡ በጦርነትም፣ በፍልሰትም፣ በንግድም፣ በባርያ ፍንገላም ከላይ እስከ ታች (ከታች ላይ ጭምር) ሕዝብ ተንቀሳቅሷል፡፡ የኦሞ ሕዝብ ሰሜን ድረስ ተበትኗል፡፡ አማራና ትግሬ ጋሞጎፋ ድረስ ዘልቋል፡፡ ከሁሉም ይበልጥ የሚገርመውና መታወቅም ያለበት የገዥዎች የረዥም ጊዜ የመስፋፋት ትግልም ሆነ የሌላ ሕዝብ እንቅስቃሴ ካመጣው/ካስከተለው ለውጥ በላይ፣ የኦሮሞ ሕዝብ በዙሪያ ገብ ሥርጭቱ የሕዝቦች መያያዣ አውታር መሆን የቻለ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከጦርነት የበለጠ ኦሮሞ የኢትዮጵያ መሀል አገዳና የመሀል የዳር ሕዝቦች ዋና ማላላሻ ቅመም ሆኖ ኢትዮጵያን አዛምዷል፣ አገማምዷል፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ ለምሳሌ ከሌሎች መካከል የኦሮሞና የአፋሩን፣ የኦሮሞና የሶማሌውን፣ የኦሮሞና የአማራውን፣ የኦሮሞና የጉራጌውን ወዘተ፣ ‹‹ትክክለኛ›› መለያያ መስመር ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ቋንቋውም ሆነ ሕዝቡ አንዱ የት ላይ አብቅቶ፣ ሌላው የት ላይ ይጀምራል? ማለትን ለመመለስ እንደ ተላልሶሹ ጥልቀትና ስፋት መጠኑ የሚለያይ የሰካራም ክር ዓይነት ገጽታ አለው (ሰካራም ክር የሚባለው ልዩ ልዩ ቀለም ያለው ክር ሲሆን፣ በየቀለሞቹ መገናኛ ላይ የተቀላቀለ ገጽታ ያለበት ነው)፡፡ ለዚህም ነው ቋንቋንና ባህልን ተከትሎ ያለቀለት ‹‹ድንበር›› ለመሥራትና መሬትን በባለቤትነት ለመተሳሰብ አዳጋችና አደገኛ የሚያደርገው፡፡

ለምን በአንድ አገር ውስጥ (አንድ አገር ማለት ማንም የአገሪቱ ዜጋ በመረጠው፣ በፈቀደው፣ የአገሪቱ የትኛውም ክፍልና አካባቢ የመዘዋወር ብቻ አይደለም፣ አገሬ ብሎ የመኖር መብትና ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ በተሰጠበት አገር ውስጥ) ስላለቀለት ‹‹ድንበር››፣ ቋንቋና ባህልን ተከትሎ ስለሚሠራ ያለቀለት ወሰንና ድንበር አነሳን? ለምንስ በዚሁ አንድ አገር ውስጥ ከመደበኛውና ከደንበኛው፣ እንዲሁም ከታወቀው የመሬት ይዞታ ሕግና ማዕቀፍ ውጪ ስለሌላ የመሬት ‹‹ባለቤትነት›› ጉዳይ አነሳን? መብራራትና መፍትሔ ማግኘት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ አገራችን ውስጥ ለብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ ካለ ፖሊሲና የፖለቲካ ተግባር የፈጠሩ የትግተለተሉ ችግሮች አሉብን፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የፌዴራል አካላት ወይም አባላት አከፋፈል ወይም አሸናሸን ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ በጠቅላላ ድንጋጌዎቹ ውስጥ በሁለተኛው አንቀጽ የኢትዮጵን የግዛት ወሰን በአጠቃላይና በደፈናው ሲወስን (ወይም ስለዚህ ሲናገር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ፣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የተወሰነው ነው›› ይላል፡፡ ይህ ድንጋጌ በአጠቃላይና በደፈናው የሚሰጠው አገልግሎት ካለ የኢትዮጵያን አገር፣ ኢትዮጵያ የምትባለዋን አገር ዳር ድንበር ቢጋር በአጠቃላይ ይናገራል እንጂ፣ የፌዴራሉን አባላት/አካላት ዳር ድንበር (ደረቅ አድርጎ) አይወስንም፡፡

ከሕገ መንግሥትና ከሕግ ይልቅ ግን ፖሊሲና ፖለቲካ የተከለው፣ ገና ስለችግሩም ይሁን ስለመፍትሔው የጋራ መግባቢያና መገናኛ ያላገኘንበት ችግር/ችግሮች አለ/አሉ፡፡ የፌዴራል አካላትን/አባላትን የለየንባቸው ወሰኖች በአንድ አገር ውስጥ ለመልካም አስተዳደርና ትድድር፣ ለነፃነትና ለፍትሐዊ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተሰመሩ፣ በዚህም መመዘኛ በሕዝብ ፍላጎት ሊቀየሩ/ሊሻሻሉ የሚችሉ እርጥብ መስመሮች ናቸው? ወይስ ከኢትዮጵያ አገነባብ ታሪክና ከኢትዮጵያ ‹‹ኢምፓየርነት›› የተቀዱ? የወደፊት ‹‹አገሮች››ን ድርሻ ከወዲሁ የወሰኑና የመረቁ ደረቅ መስመሮች? የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሰላም የነሳ መፍትሔ ፍለጋ ቀርቶ በጥሞና መነጋርን አስቸጋሪ ያደረገ ነገር ነው፡፡

በአጠቃላይ ግን ስንከተለው የኖርነው ፖሊሲና ፖለቲካ የፌዴራል አካላት አከፋፈልን፣ የየራስና የየብቻ የመሬት ቅርጫ ማረጋገጫ አድርጎ መርቋል፡፡ የእኔና የእኔ ያልሆነ ሕዝብ ብሎ መለያየትን አምጥቷል፡፡ ባለቤትና ባለቤት ያልሆነ፣ ነዋሪና ባይተዋር አድርጎ አፈነቃቅሏል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የእኔ የሚሉትን መሬት በመተሳሰብ ውስጥ የመጠማመድ ጣጣ አምጥቷል፡፡ ምድሬ ባሉት ሥፍራ ውስጥ አትነግድብኝ፣ አትድረስብኝ የሚል ተቃውሞና ውድመት አስከትሏል፡፡ አካባቢያዊ ሥልጣን (ክልሎች) የተወሰነ ማኅበረሰብ ርስት ሆኖ መመረቁ ባለርስቶችን ጨቋኝ፣ ባይተዋሮችን ተንጓላይ አድርጓል፡፡ እያንዳንዱ የፌዴራሉ አባል/ክልል ከአንድ ብሔረሰብ ብቻ የተሠራ ስላልሆነ ደግሞ ማነህ? ማነስ አይደለህም? ማለትን የመሰለ የማያኗሩር ግንኙነት ፈጥሯል፡፡

ክልሎች ውስጥ ከዚህ በፊት በነበሩትም አሁን ባሉትም ዥንጉርጉርነት አለ፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ያልሆኑ፣ አማራ ውስጥ አማራ ያልሆኑ፣ ወዘተ አሉ፡፡ የ… (እከሌ) ክልል፣ የ.… ክልል መንግሥት መባሉ፣ ፓርቲያዊ አደረጃጀቱም ብሔረሰባዊ መሆኑ (እና አለመቅረቱ) እኔና አንተ፣ የእኔ ያልሆነ መባባልን አምጥቷል፡፡

እና ባለቤትና መጤ፣ የሰው አገር ሰውና የአገር ሰው መባባልን እንዴት እናስወግዳለን? ከየብሔረሰባዊ ክልል ውስጥ የሌላ ብሔረሰብ አባላትን እየለቅምን ወደ አድራሻቸው እንልካለን? ከዚያ በኋላስ ከ‹‹ተፈጥሯዊ›› አድራሻቸው ወይም ከእምዬ ክልላቸው ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ እናግዳለን? ሕገ መንግሥቱን፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ፣ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ አገር ዜጋ ጭምር በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር፣ የመዘዋወር ብቻ ሳይሆን የመኖሪያ ቦታውን የመመሥረት፣ የመኖር መብትና ነፃነት ይጥሳል፡፡ ከታሪክ፣ ከሰዎች ተፈጥሯዊ ተዘዋዋሪነት፣ ከልማትና ከዕድገት የሚቃረኑ አስተዳደራዊ ‹‹ግቢዎች›› ናቸው፡፡  

እነዚህን እንዴት አድርገን ፈጠርናቸው? ለምን እንዲህ ዓይተን የመሬት መተሳሰብ፣ የእኔ ብቻ ማለት ውስጥ ገባን? አገራችን ውስጥ ባለፉት 30 ዓመታት የተፈለፈሉትና የተዘረገፉት ችግሮች መፍትሔ ይጠይቃሉ ሲባል እነዚህን ችግሮች እየመገቡ እየቀለቡ የሚያሳድጉና የሚያፋፉ፣ እንዲሁም ከዚያ በላይ ያገነተሩ ትርክቶችንም መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ትርክት የኢትዮጵያ አገነባብ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ እውነት ነው የጦርነት ታሪክ ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአሁን ቅርጿን ያገኘችው ግን በጦርነት ብቻ አይደለም፡፡ የሕዝቦች መላወስና ፍልሰትም ኢትዮጵያን ፈጥሯል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ‹‹ኢምፓየርነት›› ሲሰበክ የኖረው እውነት ሆኖ ሳይሆን፣ የመገንጠልን ‹‹መብት›› መጀመርያ ለማስተዋወቅ፣ ቀጥሎም ለመጠጋትና ከዚያም ድጋፍ ለማሰባሰብና ቀስ እያሉም ‹‹ሕጋዊ›› ለማድረግ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...