Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያ ግብርና ለምን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ አቃተው?

የኢትዮጵያ ግብርና ለምን አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ አቃተው?

ቀን:

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት

በዚህ ርዕስ ለማለት የፈለኩትን ሐሳብ ከመግለጼ በፊት አንድ የውጭ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ ጓደኛዬ ያጫወተኝን ጠቅሼ ልጀምር፡፡ ይህ ጓደኛዬ የሚሠራው የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ሲሆን፣ ይህንን መረጃ ማግኘት የቻለው የእናቱ እናት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታው፣ ከእናቱ ጋር ገጠር ሄዶ ነው፡፡ ይህንን  መረጃ ከለቅሶ ከተመለሰ በኋላ ለሚሠራበት ድርጅት እንደ መረጃ እንዳቀረበው፣ በዚህ በቀረበው መረጃ ምክንያት በሚሠራበት የውጭ ድርጅት ከፍተኛ አድናቆት እንዳተረፈ ነግሮኛል፡፡

ታሪኩ ይህንን ይመስላል፡፡ ይህ ሰው የእናቱ እናት መሞታቸው ከተሰማ በኋላ እናቱ ወደ ገጠር ለመሄድ ዝግጅት ሲያደርጉ፣ ‹‹ወደ ገጠርማ ብቻሽን አትሄጂም፣ እኔ አብሬሽ እሄዳሁ፤›› ብሎ ከእናቱ ጋር ጉዞ ይጀምራል፡፡ የሟች ቤት ከዋናው መንገድ ገባ ያለና ረዘም ላለ ሰዓታት በእግር ያስኬድ ስለነበር፣ መንገዱን በከፍተኛ ድካም ከተጓዙ በኋላ የተባለው ለቅሶ ቤት ይደርሳሉ፡፡ ለቅሶ ቤት ደርሰው በአገሩ ባህል መሠረት መደረግ ያለበት ሁሉ ከተደረገ በኋላ፣ ይህ ሰው ከጥቂት ቀናት በኋላ እስኪ አካባቢውን ዞር ዞር ብዬ ልመልከተው ይልና በእግሩ ሠፈር ውስጥ ካለ አንድ ጎረምሳ ጋር ሆኖ አካባቢውን መቃኘት ሲጀምር አንድ ነገር ይመለከታል፡፡

ወቅቱ እህል ተሰብስቦ ያለቀበት ስለነበር፣ የእርሻው መሬት ሳይታረስ ባዶ ሆኖ ይመለከታል፡፡ ከተመለከታቸው የእርሻ መሬቶች መካከል አንደኛው ከሌሎቹ የእርሻ መሬቶች በተለየ ሁኔታ በመሀሉ አንድ አነስተኛ የምንጭ ውኃ ትፈሳለች፡፡

በዚህ ጊዜ ይህ ጓደኛዬ ግራ በመጋባት፣ ‹‹ለምንድነው የምንጩን ውኃ በመጠቀም የመሬቱ ባለቤት በበጋ ወቅት የተለያዩ ምርቶችን የማያመርተው?›› የሚል ጥያቄ ራሱን ይጠይቃል፡፡ በመቀጠል የመሬቱ ባለቤት መኖሪያ ቤት ያመራና የቤቱን አባወራ ካገኛቸው በኋላ ለራሱ የጠየቀውን ጥያቄ ያቀርብላቸዋል፡፡

የመሬቱ ባለቤት ጥያቄው እንደቀረበላቸው ትንሽ አሰብ አድርገው፣ ‹‹አየህ ልጄ እንተ እንዳልከው ይህንን የምንጭ ውኃ ተጠቅሜ በበጋ የተለያዩ ምርቶች ባመርት፣ የወረዳው ኃላፊዎች በመስኖ የምታለማ ከሆነ ይህ ሁሉ መሬት ለአንተ ይበዛብሃል ብለው መሬቱን ቆርሰው ይወስዱብኛል፡፡ በመሆኑም ክረምት ሲመጣ ብቻ ጠብቄ ነው የማርሰው፤›› ብለው ይመልሱለታል፡፡

ይህንን መልስ እንዳገኘ ጉዳዩ በእጅጉ ስላሳሰበው በጉዳዩ ላይ ሰፊ ዘገባ ሠርቶ ለመሥሪያ ቤቱ ሪፖርት እንዳደረገ፣ ጉዳዩም የአንድ ወቅት የመሥሪያ ቤቱ መነጋገሪያ እንደነበር አጫውቶኛል፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት ስታራምደው የነበረው የመሬት ፖሊሲ በዚህ ደረጃ ዜጎች በይዞታቸው ሥር ያለን መሬት አቅማቸው በፈቀደ መጠን አልምተው፣ ለራሳቸውም ለአገራቸውም ተጨማሪ ምርት ማስገኘት እንዳይችሉ የመሬት ባለቤትነት አለመኖሩ፣ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ በጉልህ ማስረዳት ከሚችሉ ታሪኮች አንዱ ነው፡፡

ዜጎች በይዞታቸው ሥር የሚገኝን መሬት የራሳቸው እንደሆነ ሙሉ በሙሉ መተማመን ከቻሉ፣ እጃቸው ላይ የገባን ማንኛውንም ገንዘብ መልሰው መሬቱ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የበለጠ ለም እንዲሆን፣ የመስኖ መሠረተ ልማት እንዲኖረውና አፈሩ እንዳይሸረሸር በማድረግ የበለፀገ የእርሻ መሬት እንዲኖር ተግተው መሥራት የሚሉችበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት መሬት መሸጥ ለባለሥልጣናት ብቻ የተሰጠ መብት አድርገው፣ የኢትዮጵያ ገበሬ የመንግሥትና የካድሬዎች ጭሰኛ ሆኖ ላለፉት 50 ዓመታት እንዲኖር አድርገውታል፡፡  

እያንዳንዱ ገበሬ ማሳ ላይ የተፈጠረ እሴት ድምር ውጤት አገራዊ አመርቂ የግብርና ሥራ ውጤት እንደሚያመጣ፣ መሪዎቻችን መቶ ጊዜ ቢነገራቸውም አይገባቸውም፡፡

ከመላው አፍሪካ ገበሬ የመሬት ባለቤት ያልሆነባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ባለው መሬት ላይ አዛዦቹ የወረዳ ካድሬዎች እንጂ መሬቱን የሚያርሰው ገበሬ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 80 በመቶ ሕዝብ የሚኖረው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ በከተሞች የሚኖረው የሕዝብ ብዛት 20 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ገጠር የሚኖሩት 80 በመቶ ገበሬዎች፣ 20 በመቶ የሆነውን የከተማ ሕዝብ መቀለብ አልቻሉም፡፡ በአሜሪካ 94 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው በከተሞች ነው፡፡ ስድስት በመቶ ብቻ ነው ገጠር የሚኖረው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ስድስት በመቶ ገበሬዎች በከተማ የሚኖረውን 94 በመቶ ሕዝብ አብልተው፣ አጥግበውና ለዕርዳታ የሚሆን የምግብ ምርት ጭምር ያመርታሉ፡፡

በአሜሪካና በኢትዮጵያ ይህንን ያህል ልዩነት የተፈጠረው አሜሪካኖች ልዩ ፍጡር ስለሆኑ ሳይሆን፣ በአሜሪካና በኢትዮጵያ ያለው የግብርና ፖሊሲ በእጅጉ የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ፖሊሲን በመለወጥ ብቻ ረሃብን ታሪክ ማድረግ ይቻላል፡፡ ገበሬ የመሬቱ ሙሉ የባለቤትነት መብት እስከ መሸጥ መለወጥ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ 

‹‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አገር መገንጠል መብት ነው›› ይልና ገበሬው የደከመበትን፣ እሴት የጨመረበትን መሬት መሸጥ መለወጥ ይከለክላል፡፡ መሬት መሸጥ መለወጥ ዋነኛ ጥቅሙ መሬቱን የሚያለማው አዲስ ሐሳብ ይዞ የመጣ ሰው እጅ ይገባል ማለት ነው፡፡

እዚህ አዲስ አበባ መሬት መሸጥ መለወጥ በመቻሉ የጭቃ ቤት እየፈረሰ ከተማው ፎቅ በፎቅ የሆነው፣ የመሸጥና የመለወጥ ሥርዓት ስላለ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለሀብት የ20 ገበሬዎችን መሬት ቢገዛ መሬቱን በቀጥታ ወደ ሳይንሳዊ (ዘመናዊ) እርሻ ስለሚለውጠው፣ በመጀመርያ ከፍተኛ ምርታማነት ይኖራል፡፡ በመቀጠል በርካታ የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ፡፡

መሬቱን የሸጡ ገበሬዎች ገንዘቡን ቢያባክኑት እንኳን መሬቱን የሸጡለት ባለሀብት የሥራ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ የእርሻ መሬት ወደ ሳይንሳዊ እርሻ የለወጡ ባለሀብቶች የምርት ማቀነባበሪያ ስለሚገነቡ፣ ያም ተጨማሪ የሥራ ዕድል በተለይ ለሴቶች ይፈጥራሉ፡፡ አንድ አገር ረሃብን፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማሸነፍ የግድ ሳይንሳዊ ሥልጣኔ መተግር አለበት፡፡ ከተሞች ሲስፋፉ፣ ኢንዱስትሪ ሲስፋፋ ለኢንዱስትሪ ሠራተኞች በርካሽ ተሸምቶ የሚበላ ምግብ መኖር አለበት፡፡

በየትም ዓለም በባህላዊ እርሻ በመጠቀም የተገነባ ሥልጣኔ የለም፡፡ ግብርና እንዲዘምን ደግሞ የእርሻ መሬት ሊያዘምነው የሚችል ሰው እጅ መግባት አለበት፡፡ በተጨማሪ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አሁን የሌለ፣ ነገር ግን መሬት መሸጥ መለወጥ ሲጀመር የሚፈጠር ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምክንያት ይፈጠራል፡፡ ከገንዘብ ዝውውር ጋር በተጓዳኝ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችና የታክስ ገንዘብ ለወረዳዎች መገኘት ይጀምራል፡፡

የገጠር መሬት መሸጥ መለወጥና ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፡፡

ከምንም በላይ አገራዊ ፋይዳ የሚፈጠረው ገበሬው ከዕለታት አንድ ቀን መሬቴን መሸጥ ከፈለኩ መሸጥ እችላለሁ ብሎ እርግጠኛ ከሆነ፣ መሬቱ ላይ የሚጨምረው እሴት፣ በእያንዳንዱ ገበሬ ማሳ ላይ የሚፈጠረው እሴት ድምር ውጤት እጅግ ከፍተኛ አገራዊ ብልፅግና እንዲፈጠር ያስችላል፡፡

አንድ አገር ሠለጠነችና ድህነትን ቀነሰች የሚባለው በየጊዜው በሁሉም የሥራ ዘርፎች በሚፈጠር እሴት እንጂ፣ ገጠሩን ረስቶ ከተማ ብቻ ፎቅ በመቆለል ሥልጣኔ ማምጣት አይቻልም፡፡ ድህነትን መቀነስ አይቻልም፡፡ 80 በመቶ የሆነውን የአገሪቱን ኅብረተሰብ ሕይወት ሊለውጥ የሚችል ፖሊሲ የግድ መኖር አለበት፡፡

የገጠሩ ሕዝብ ሕይወት አብዮት ተጀመረ ከተባለበት ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት ጀምሮ ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣም፡፡ በገጠር ኢትዮጵያ ሲሚንቶ የሚገዛም የሚሸጥም ገበሬ የለም፡፡ ሲሚንቶ በመጠቀም ሕይወቱን ለመለወጥ አቅም የፈጠረ ገበሬ የለም፡፡

ሲሚንቶ የገጠሩን ገበሬ ሕይወት ለመለወጥ ዋነኛ ግብዓት ነው፡፡ ሲሚንቶን በመጠቀም ትንንሽ ግድቦች በመሥራት ውኃን ማጠራቀም ይቻላል፡፡ የእህል ጎተራ፣ የእህል መውቂያ፣ የከብቶች በረት፣ ንፁህ መፀዳጃ ቤትና ሌሎችም እጅግ በርካታ ተግባራት በማከናወን የገበሬውን ሕይወት በሲሚንቶ ምርት ሙሉ በሙሉ መለወጥ ይቻላል፡፡

ገበሬው በስፋት ሲሚንቶ ተጠቀመ ማለት የራሱ በሆነው መሬት ላይ፣ በማንኛውም ጊዜ ሊሸጠው ሊለውጠው በሚችለው መሬት ላይ ቋሚ እሴት ጨመረ ማለት ነው፡፡ ሰዎች ደግሞ በተፈጥሮ ሀብት ማፍራት እንወዳለን፡፡ ብዙ ሀብት ባፈራን ቁጥር ተጠቃሚነታችን ይጨምራል፡፡ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖረን ቦታ ከፍ ይላል፡፡ በሌላ አነጋገር የራሳችንን ሰብዕና ሀብት በማፍራት ለመገንባት የምናደርገው ጥረት ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠርን፣ ለአገራችን የግብር ገንዘብ እያመነጨን፣ ለትውልድ የሚሆን ደግም ቋሚ ሀብት እናፈራለን፡፡ የባለቤትነት ስሜት ማለት ይህ ነው፡፡ ዓለምን የለወጣት የባለቤትነት ስሜትን ለመፍጠር የሚጥሩ ትጉህ ሰዎች ትጋት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ብልፅግና በኢትዮጵያ ውስጥ አመጣለሁ ካሉን፣ ይኼው አሁን አራት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ግብርናው ሳይዘምን በተዓምር ብልፅግና አይመጣም፡፡ ግብርናው እንዲዘም ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሎ የገጠር መሬት ባለቤትነት እስከ መሸጥ መረጋገጥ አለበት፡፡ በተጨማሪ ዶ/ር ዓብይ ወደ ብልፅግና እንዴት እንደሚወስዱን ፍኖተ ካርታውን አላሳዩንም፡፡ ‹‹መደመር›› የሚለውን መጻሐፋቸውን አንብቤዋለሁ፡፡ የብልፅግና ፍኖተ ካርታ ምን ሊሆን እንደሚችል መጽሐፉ ውስጥ ማግኘት አልቻኩም፡፡ ብልፅግና የግድ ፍኖተ ካርታ ይፈልጋል፡፡ ፍኖተ ካርተው ከተዘጋጀ በኋላ ዜጎች አምነውበት ከመንግሥት ጋር ሲሠሩ ብቻ ነው ውጤት መመዝገብ የሚችለው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት እንኳን ብለፅግና ሊመጣ ቀርቶ፣ ገና ፍኖተ ካርታ ምን እንደሆነ ካላወቅን እንዴት አድርጎ ነው ብልፅግና የሚመጣው?

ከዚህ ቀደም ለንባብ በበቃው አንድ ጸሑፌ ላይ እሳቸው በቤተክርስቲያናቸው ከብዙ ሰዎች ፊት ለፊት ቆመው ሰፊ ንግግር ካደረጉ በኋላ ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ፣ ሁሉም ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡ አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ማይክራፎን ይዘው የተናገሩትን ነገር በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ ለንግግር ብቻ ተብሎ የሚቀርብ ነገር መኖር የለበትም ብዬ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የተናገሯቸውን በርካታ ንግግሮች ብንመረምር፣ ተናግረውት ያልፈጸሙት ነገር ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ይህንን ሁኔታ የሚገልጽ አንድ ማስረጃ ላቅርብ፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. የስዊዘርላንድ ከተማ ወደሆነችው ዳቮስ አቅንተው ነበር፡፡ ይህ ቦታ በየዓመቱ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የሚካሄድበት መድረክ ነው፡፡ ‹‹Reviewed Ethiopian Vision Strategic Repositioning›› በሚል ርዕስ ኢትዮጵያ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የሕዝብ ንብረቶችን በከፊልና በሙሉ ወደ ግል እንደምታዞርና መሠረታዊ የሆነ የፖሊሲ ለውጥ እንደምታደረግ፣ የዓለም ወሳኝ ሰዎች በተገኙበት መድረክ ላይ ከገለጹ በኋላ ይኸው እስካሁን ምንም የተደረገ ነገር የለም፡፡

ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ተቀባይነት ያለው የገበያ መር ሥርዓት እንድትገባ የሚያስችለውን ሕገ መንግሥት የማሻሻል ሥራ አልተጀመረም፡፡ አንድ መሪ ከምንም በላይ ዜጎች የሚከተሉት የተናገረውን ቃል ወደ ተግባር በመለወጥ ብቃቱ ነው፡፡

በርዕሱ እንደተጠቀሰው ግብርና የኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንደመሆኑ መጠን፣ በከፍተኛ ደረጃ የተፋጠነ የፖሊሲ ማሻሻያ ያስፈልገዋል፡፡ አገራችን ሰማኒያ ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ የሚታረስ መሬት እያላት፣ በተበላሸ ፖለሲ ምክንያት አሥራ አምስት ሚሊዮን ሔክታር ብቻ እያረስን መራብ የለብንም፡፡ በተጨማሪም ግብርና የውጭ ምንዛሪ ልናገኝ የምንችበት ትልቁ ዕምቅ ሀብታችን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታዳሽ ኤሌክትሪክ የማምረት ዕምቅ አቅም ያላት አገር እንደ መሆኗ፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በባትሪ የሚሠሩ እጅግ በርካታ መሣሪያዎች ስላሉ ዘመናዊ የእርሻ ሥራ የማካሄድ ዕድሉ በእጃችን ላይ ነው ያለው፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ማረሻ፣ ማጨጃና ውኃ መሣቢያ የመሳሰሉ መሣሪያዎች ቻርጅ በተደረገ ባትሪ የሚሠሩ በመሆኑ የገበሬውን ሕይወት በማቅለል የግብርና ምርታነትን በእጅጉ ማሳደግ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ አገሮች በተለየ መልኩ ሁሉም ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት፣ የተስማማ አየር፣ በቂ የውኃ ሀብት፣ በአጠቃላይ ሁሉም ያሏት አገር ነች፡፡ የሚጎድላት ብቃት ያለው መሪ ብቻ ነው፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) በዓለም ላይ ካሉ መሪዎች ሁሉ እጅግ የተሻለ ዕድል ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ እኚህ ሰው ሥልጣን የያዙበት ዘመን ተዓምር መሥራት የሚያስችላቸው ዘመን ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ያለ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገን አገር፣ ዘመን አመጣሹን ቴክኖሎጂ በማጣመር ተዓምር መሥራት የሚቻልበት ዘመን ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ደሃ አገሮች ዘመን አመጣሹን ቴክኖሎጂ መጠቀም ይችላሉ፡፡ በቂ የተፈጥሮ ሀብት የላቸውም፡፡ የበለፀጉት አገሮች ደግሞ ዘመን አመጣሹን ቴክኖሎጂ መጠቀም ቢችሉም፣ ቴክኖሎጂ ከመምጣቱ በፊት እነሱ አገራቸውን አልምተውታል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ግን የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ቴክኖሎጂ፣ ርካሽ የወጣቶች ጉልበት፣ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል የውጭ ብድርና ሌሎችንም ግብዓቶች በመጠቀም በአጭር ጊዜ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመለወጥ ታሪክ መሥራት ይችሉ ነበር፡፡ አገር ለመለወጥ ትልቁ ማነቆ የሆነውን ሕገ መንግሥት እንኳን ከአራት ዓመታት በላይ ተሸክመው በመዞር ረዥም ጊዜ አቃጥለዋል፡፡ አሁንም ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የተጀመረ ምንም ዓይነት ሥራ የለም፡፡

የብዙ አገር መሪዎች አገራቸውን ለመለወጥ ቁርጠኝነቱ ቢኖርም፣ የኢነርጂ እጥረትና በቂ የምግብ ሰብል አለማምረት የመሳሰሉት ማነቆ ስላለባቸው ያሰቡትን ሥራ ለማከናወን ይቸገራሉ፡፡ እኛ ግን ቁርጠኝነቱ ካለ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚጎድለን ነገር የለም፡፡

ከምንም በላይ ዓብይ (ዶ/ር) ውጤት ለማምጣት ውጤት ማምጣት የሚያስችል ብቃት ያላቸው ሰዎች በካቢኔያቸው ማሠለፍ አለመቻላቸው፣ ከምንም በላይ ውጤት እንዲርቃቸው ዋናው ምክንያት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ዓለማችን ወደፊት ከሚገጥማት እጅግ ፈታኝ ችግር አንዱ በቂ የምግብ ሰብል ማምረት አለመቻል ነው፡፡ ብዙ የእርሻ መሬቶች በጨዋማ ውኃ እየተበከሉ ናቸው፡፡ ብዙ የእርሻ መሬቶች ለረዥም ጊዜ በኬሚካል ማዳበሪያ የተመረዙ በመሆናቸው በየዓመቱ ምርታነታቸው እየቀነሰ ነው፡፡ የዓለም የሕዝብ ብዛት ደግሞ እየጨመረ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አገራችን የምግብ ሰብል በበቂ ሁኔታ ለማረት ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የምትችልበት ዕድል በመኖሩ፣ መንግሥት ሥር ነቀል የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ያለንን የእርሻ መሬት ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ በማዋል ወጣቱ ትውልድ የእርሻ መሬት ባለቤት በማድረግ እጠቅማለሁ በሚል ስሜት ተግቶ እንዲሠራ በማድረግ ተዓምር መሥራት ይቻላል፡፡

የመንግሥት ሥልጣን የተሰጣቸው ባለሥልጣናት ዋነኛ መገለጫቸው ሥልጣንን እንደ ርስት በመቁጠር ሕዝብን በመርሳት የራሳቸውን አጀንዳ ብቻ ያራምዳሉ እንጂ፣ የሕዝብ አደራ አለብን ብለው እንቅልፍ አጥተው ለውጥ ለማምጣት የመሥራት ብቃት የላቸውም፡፡ ሥልጣንና እሳት በጣም ይመሳሰላሉ፡፡ እሳት እየነደደ ብዙ ለሰው ልጆች የሚጠቅም ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ እሳት ይዞ መዘናጋት ደግሞ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ወይም እሳት ይዞ ማንቀላፋት ራስን እንደ ማጥፋት ነው፡፡ ሥልጣን የያዘ ሰው ሥልጣኑን እንደ እሳት ቆጥሮ በጥንቃቄ ሠርቼ፣ ሕዝብን ተጠቃሚ አድርጌ፣ ታሪክ ልሥራ ማለት አለበት፡፡ እንጂ ሥልጣን ይዞ የግል አጀንዳውን ብቻ የሚያራምድ ከሆነ በእጁ ላይ ለሥልጣን ልክ እንደ እሳት አቃጥሎ ይገድለዋል፡፡

ብዙ ሰዎች ውሻ የሚባል የቤት እንስሳት ይወዳሉ፡፡ ለውሻቸው ግን የሚሰጡት ኃላፊነት የተገደቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የሚወደውን ውሻ ቤቴን ጠብቅልኝ ሊለው ይችላል እንጂ፣ ለቅርጫ የተዘጋጀውን ሥጋ ጠብቀኝ አይባልም፡፡ ከውሻው ባህርይ አኳያ ውሻው ሥጋውን መብላቱ አይቀርም፡፡

የአገራችንም ባለሥልጣናት የመንግሥት ሥልጣን የያዙት ሕዝብን እንዲያገለግሉ፣ በግብር መልክ የተሰበሰብ ገንዘብ በአግባቡ ሕዝብን ሊጠቅም በሚችል መልኩ ሥራ ላይ እንዲያውት እንጂ ለግል ጥቅማቸው እንዲያውሉት አይደለም፡፡

እኛ አገር ግን ሥልታን የተሰጣቸው ሰዎች ልክ ሥጋ ጠብቅልኝ እንደተባለው እንስሳ፣ አደራቸውን ትተው የሕዝብ ሀብት ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት ነው፡፡

ሰሞኑን ጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋ ማርያም በቴሌቪዥን ያሳየን ዘገባ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ የሚገልጽ ነገር ነው፡፡ ዓባይ ፀሐዬ የተባለ የቀድሞ ባለሥልጣን የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊ በነበረበት ጊዜ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ተዘርፎ በአዲስ አበባ የተገነቡ ሕንፃዎችን በቴሌቪዥን አሳይቶናል፡፡ አዲስ አበባ ይህንን ያህል ሀብት ከተገኘ ውጭ አገር ደግሞ ምን ያህል ሀብት ይኖራል? አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የዓብይ መንግሥት ይህንን ንብረት በጊዜ ወደ ገንዘብ ለውጦ ለምን አሁን አገራችን ያለባትን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ላለፉት አራት ዓመታት ለምን አልጣረም?

ደርግ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናትን ንብረት ለመውረስ ዓመት እንኳን አልፈጀበትም፡፡ የተዘረፉ የሕዝብ ሀብቶች በአጭር የፍርድ ሒደት ተወርሰው አገሪቱ ላለባት አጣዳፊ ችግር መፍትሔ መሆን ሲገባ የሕወሓት ባለሥልጣናት አሁንም ከአዲስ አባባ በሚላክላቸው ገንዘብ መልሰው እኛን እየወጉን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት ምን ያህል ወንጀለኞችን እየታገሰ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሥቃይና መከራ እንደተራዘመ በጉልህ ይታያል፡፡

ከእስር የተለቀቀው ስብሃት ነጋ አሁን በሚደረገው ሦስተኛ ዙር ጦርነት ላለመሳተፉ ማነው ማረጋጫ የሚሰጠው? በአገራችን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ መቼ ነው በሙሉ አቅማችንን ወደ ልማት የምንዞረው?

የገጠሩ ሕዝብ ሰቆቃ መቼ ነው የሚበቃው? በምግብ፣ በመድኃኒት፣ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በመሠረተ ልማት ዕጦት የሚቸገረው የገጠሩ ሕዝብ አሁን ደግሞ የጦርነት ከበሮ እየተደለቀበት እስከ መቼ ነው በዚህ ሁኔታ የሚቀጥለው፡፡ ኧረ በሕግ አምላክ?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...