Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የእኛ ዓላማ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ማምጣት ነው›› ዮናስ አዳዬ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተርና ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲሆኑ፣ በኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል አስተባባሪም ናቸው፡፡ ዮናስ አዳዬ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ስለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የቅርብ ጊዜ ሥራ እንቅስቃሴና በኅዳር አጋማሽ ይጀመራል ተብሎ ለሚጠበቀው አገራዊ ምክክር የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ ኮሚሽኑ በቅርቡ ይጀምረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን የሙከራ ውይይትና የአወያዮች መረጣ ሒደት እንዴት እንደሚካሄድ ያብራሩበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ  ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ማዘጋጀታችሁን ይፋ ማድረጋችሁ ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ወደ ክልሎችም በመውረድ በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ላይ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ግብዓት ስትሰበስቡ ቆይታችኋል፡፡ በዋናነት ምን ይሻሻል የሚል ጥያቄ ቀረበላችሁ? ምን ዓይነት ግብዓት አገኛችሁ?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ወደ ክልሎች የሄድንበት ዋና ዓላማ አንደኛው ለመተዋወቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የክልሎችን ዝግጁነት ለማየት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ለሎጂስቲክስ ሥራዎች በክልሎችና በእኛ መካከል እንደ ድልድይ የሚያገለግሉ አገናኝ መኮንኖችን (ፎካል ፖይንቶችን) ለመፍጠር ነው፡፡ ከተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውልናል፡፡ ተጠያቂነታችን ለሕዝቡ ስለሆነ አቀራረባችንም ከታች ወደ ላይ በመሆኑ፣ እስከ ታች ሕዝቡ ጋ ለመድረስ በመዋቅር ውስጥ ያሉ አካላትን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ የየክልሎቹ አደረጃጀትና ዝግጁነት (የሥነ ልቦናዊም ሆነ የመሠረተ ልማት ዝግጁነት)  ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ያለመ ነበር ጉዞው፡፡ በዚህ ጉዞ ያገኘነው ነገር ከጠበቅነው በላይ ነበር፡፡ አንደኛውና ዋናው ሰዎች ምን ያህል ሰላም እንደተጠሙ ዓይተናል፡፡ በደረስንበት ሁሉ ጦርነት ሰልችቶናል፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሮቻችንን ተነጋግረን እንፍታ የሚል አስተያየት ነው ያገኘነው፡፡ በወረዳ ደረጃ፣ በዞን ደረጃ፣ ወይም በክልል ደረጃ የሚፈቱ ችግሮችን ለይተን አምጥተን በእነዚህ እርከኖች የማይፈቱ በአገር አቀፍ ደረጃ መፈታት የሚገባቸውን ለፎረም ማቅረብ ነው የእኛ ሥራ፡፡ መጨረሻ ላይ የሚወስነው ሕዝቡ ነው፡፡ የሕዝቡ የመጨረሻ ውሳኔ የተለያየ ዓይነት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ ይቀየርልኝ ሊል ይችላል፣ የፖለቲካ አደረጃጀቱ ይለወጥ ሊል ይችላል፣ ከመንግሥት ጋር ያለውን ማኅበራዊ ውል የተመለከተም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ሕዝቡ ራሱ የሚናገረውን  ሰብስበን እናቀርባለን፡፡ ካቀረብንም በኋላ ምላሽ ማግኘቱን እንከታተላለን፡፡ በአጠቃላይ ጉዟችን የተሳካ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ሁሉንም አካባቢዎች አዳርሰን ትግራይ ክልል እንሄዳለን ብለን ብናስብም፣ ነገር ግን በሁለተኛው ቀን ነበር ጦርነቱ እንደገና የተጀመረው፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥ ትግራይ ክልል ለመሄድ ዝግጅቱ ነበራችሁ? ግንኙነትስ ጀምራችሁ ነበር?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- አዎን ተዘጋጅተን ነበር፡፡ ትግራይ አንዱ ክፍለ አገራችን ነው፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ምን አደረሰን የሚለውን ማየት አለብን፡፡ ሁሉንም ማነጋገር አለብን፡፡ ኅብረተሰባችን ውስጥ እኮ ራሱን የቻለ ዕውቀት አለ፡፡ ወደ ምሥራቅም፣ ወደ ምዕራብም አይደለም መመልከት ያለብን ወደ ራሳችን ነው፡፡ ወደ ውስጣችን ማየት አለብን፡፡ እኛው እኮ ነን መነጋገር ያለብን፡፡ ችግሩ ብቻ ሳይሆን መፍትሔውም እኛው ውስጥ እኮ ነው ያለው፡፡ ለሚዲያ አሁን ይፋ መደረግ የሌለበት ቢሆንም ግንኙነቶች ተደርገው ነበር፡፡ ኢመደበኛ በሆኑ መንገዶች ለመገናኘት ተሞክሯል፡፡ ለሕዝብ ግልጽ ሆኖ መውጣት ባለበት ጊዜ ጥረታችን ምን እንደነበር ይፋ ይሆናል፡፡ ከሰውነታችን አንዱ አካላችን ቢታመም ሰውነታችን ጤናማ እንደማይሆነው ሁሉ፣ አንዱ ክፍለ አገራችን ስለታመመ ሁላችንም እንደተጎዳን ነው የሚቆጠረው፡፡ ደግሞም እዚያ ያለው ሕዝብ ወገናችን ነው፡፡ ችግሩ እንዴት ዓይነት አጀማመር እንደነበረው ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ መንግሥትም ወዶ የገባበት ነገር አይደለም፡፡ አሁን ግን ከዚያ ወጥተን እንዴት ወደ ሰላም እንግባ የሚለው ጉዳይ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፡፡ አፋርና ትግራይ፣ አማራና ትግራይ፣ የተቀሩ ክልሎችና ትግራይ በመካከላቸው የሚነሱ ጥልቅ የሆኑ ልዩነቶችን እንዴት አድርገን አጥበን ከኅብረተሰቡ በሚገኝ ዕውቀትና ብልኃት እንዴት ሰላማዊት ኢትዮጵያን እንፍጠር የሚለው ነው የእኛ ዓላማ፡፡ ዋናው ጠላታችን ድህነት ሆኖ ሳለ ወጣቶቻችን እርስ በርስ በመተላለቅ ለምን ይለቁ? የእኛ ዓላማ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ማምጣት ነው፡፡ ዓላማችን ሰላምን ባህል ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ውይይቱን ለመጀመር ምን ምን ዝግጅቶችን እያደረጋችሁ ነው?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- አምስት ምሰሶዎች ናቸው ያሉን፡፡ አንደኛው ቅድመ ዝግጅት፣ ሁለተኛው ዝግጅት፣ ሦስተኛው ሒደት፣ አራተኛው ትግበራ ሲሆን፣ አምስተኛው ክትትልና ግምገማ ነው፡፡ አሁን የምንገኘው ሁለተኛው የሥራ ምዕራፍ ላይ ሲሆን ቅድመ ዝግጅቶችንና የተሠሩ ሥራዎችን መከታተልና ከሕዝብ ጋር መተዋወቅ እያደረግን እንገኛለን፡፡ አካሄዳችን እንደ ናሙና የተመረጡ አካባቢዎችን ዝግጅት መዳሰስ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የተወሰኑ ወረዳዎችን፣ አዳማን ጨምሮ በምሥራቅ ኦሮሚያ፣ ድሬዳዋና ጅግጅጋን ዓይተናል፡፡ በሌሎች ክልሎችና አካባቢዎችም ምልከታ አድርገናል፡፡ ቀጣዩ ሥራችን ደግሞ አወያይ ባለበት፣ ቃለ ጉባዔ ያዥ ባለበት፣ ሁሉም ዶክመንት ባለበትና ሁሉም በተወከሉበት በሁሉም ቦታዎች በጥልቀት ገብቶ ውይይት ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ አስቀድሞ ግን አነስ ያሉ ውይይቶችን ማድረግ እንደ ዕቅድ ይዘናል፡፡ በተመረጡ አካባቢዎች የሙከራ ውይይቶች እናካሂዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ የናሙና ውይይቶች ከዋናው ውይይት ቀድመው ነው የሚደረጉት?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- አዎን ይቀድማሉ፡፡ ዋናውን ውይይት ለማካሄድ የአካሄድ ስህተት ካለ፣ አስተያትና ግብዓት ለማግኘት ይረዳሉ፡፡ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከሁሉም ግብዓት እናገኛለን፡፡ እስካሁን እኔ በግሌ ከሁሉም ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ ከመንግሥት እያገኘን ያለነው እጅግ የሚያበረታታ በጎ ምላሽ ነው እላለሁ፡፡ ሚዲያዎችን ጨምሮ በሁሉም ረገድ ያሉ ሰዎች ቀናና ገንቢ ሐሳብ ይሰጡናል፡፡ አገራዊ ምክክር ራሱ ለእኛ አዲሳችንና ከዚህ ቀደም ያልሞከርነው ነው፡፡ እኔ በሰላም ላይ አጥንቻለሁ፡፡ ግጭት አፈታት ላይ እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ተመራምሬያለሁ፡፡ ነገር ግን ማስተማር፣ መመራመርና ማወቅ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ወደ ተግባር ስትሄድ ሁሌም ክፍተቶችን ታገኛለህ፡፡ ያወቅከውን ነገር በተግባር መተርጎምና ማላመድ የምትችለው ስትሞክረው፣ በሌሎች ስታስተች፣ አስተያየትና ግብዓት ወስደህ አሻሽለህ ስትሠራው ነው፡፡  የአገር ጥቅምም ቢሆን በዚህ መንገድ ነው እየተሟላ የሚሄደው፡፡

ሪፖርተር፡- በእስካሁኑ እንቅስቃሴያችሁ የገጠማችሁ ችግር አለ? በጎ ምላሽ እያገኛችሁ ቢሆንም የሚቀሩና ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ ቢያብራሩልን?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- በእኔ ዕይታ በዋናነት ሁለት ነገሮች ናቸው ጎልተው የሚታዩኝ፡፡ የመጀመርያው እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች ናቸው፡፡ የአንድ ሰው መሞትም ቢሆን ያስከተለው በየቦታው ግጭት ማጋጠሙ ለእኛ እንቅፋት ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ መርህ ሁሉንም አካታች የሆነ ውይይት ማድረግ ነው፡፡ ማንም ያልቀረበትና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቢያንስ ድምፁን ማሰማት ባይችል እንኳ፣ በሚወክለው አካል የሚሰማበትን ዕድል ማመቻቸት ነው፡፡ ወደ እነዚህ ዓላማዎች እንዳንደርስ የሚያደርጉ እንቅፋቶች ደግሞ በዋናነት ግጭቶች ናቸው፡፡ ኦሮሚያ አካባቢ ታያለህ፣ ትግራይ ታያለህ፣ በየአካባቢው ያሉ ግጭቶች ተስፋ ባያስቆርጡንም እንኳ ለሥራችን ዋና ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ተግዳሮት ደግሞ አሉታዊ አስተያየቶች ናቸው፡፡ በግጭቶች መበራከትም ይሁን በሌላ ምክንያት በአንዳንድ ልሂቃን ይሰጡ የነበሩ አሉታዊና አንዳንዴም ያልተጣሩ አስተያየቶች እንቅፋት ናቸው፡፡ አሁን አሁን ቀነሰ እንጂ እንዲህ ያለው አስተያየት ሥራ ስንጀምር የበዛ ነበር፡፡ ሰላም በሌለበት አገር በጦርነት እንጂ በሰላማዊ መንገድ ሰላም ሊመጣ አይችልም ብሎ የመደምደም ስህተት ነበር፡፡ ውይይት የሚባል ነገር አይቻልም፣ ያሸነፈ ነው መምራት ያለበት የሚል ዝንባሌ ይታይ ነበር፡፡ ይህን መሰል አስተያየት መስማት ሥነ ልቦናዊ ዝግጅትና ብስለት ለሌለው ሰው ትንሽ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የምክክር ሐሳቡን መጀመሩ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሙከራው በራሱ ትልቅ ነው፡፡

በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ዕቅድ ሲጀመር አሉታዊ አስተያየቶች በርክተው ነበር፡፡ በቱኒዚያም ሆነ በኮሎምቢያ በመጀመሪያ አፍራሽ አስተያቶች የነበሩ ቢሆንም፣ ዛሬ ይኸውና ለዓለም ምሳሌ የሆነ ምክክር ማድረግ ችለዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ አይሆንም/አይካሄድም ሲባል በጥሩ ሁኔታ ተከናወነ፡፡ በኬንያም እ.ኤ.አ. በ2008 ምርጫ ማግሥት በተሳካ መንገድ ተካሂዷል፡፡ በኬንያ ከዚያ በኋላ ሰላም ነው የሆኑት፣ እየተሻሻሉ ነው የመጡት፡፡ ይህ ሁሉ ለእኛ ተስፋን የሚሰጠን ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የሕዝባችን ለዚህ ዓላማ በቆራጥነት መዘጋጀት ትልቅ ጥንካሬ ነው፡፡ በየቦታው ስንሄድ የሚያገኙን ሁሉ ምን እናግዝ ይሉናል፡፡ ይህ ነገር መሬት እንዲይዝ፣ ይህ ነገር ውጤት እንዲያመጣ፣ በአገሪቱ ሰላም እንዲመጣና ልጆቻችንም እኛም ወደ ልማት እንድናተኩር ምን እናድርግ ብለው የሚጠይቁን ብዙ ናቸው፡፡ ችግሮች የሉም አልልም፡፡ ነገር ግን ብርሃን ጨለማን ምን ጊዜም ያሸንፋል፡፡ አብዛኛው ብርሃን በመሆኑ የጨለመው አስተሳሰብ በሙሉ በብርሃን እየተሞላ እንደሚሄድ እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በተጨባጭ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ  በአገሪቱ አስቻይ ሁኔታ አለ?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- በሚገባ፡፡ ዋናው እኮ የህሊና ዝግጅት ነው፡፡ ሰው እኮ ጦርነት ሰለቸኝ እያለ ነው፡፡ ግጭት አልፈልግም እያለ ነው፡፡ ጅግጅጋ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብና ሲዳማ በሄድንበት ጊዜ የመጀመርያው ሕዝቡ የሚያነሳው ነገር ሰላም ነው፡፡ እንዲያው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተበላሸ በመሆኑ እንጂ፣ ሕዝብ ከተዘጋጀና ለአንተ ደጀን ከሆነህ ከሕዝብ በጎ ፍላጎት በላይ ለብሔራዊ ምክክሩ አስቻይ ሁኔታ የለም፡፡ በሄድንበት ሁሉ ሕዝቡ ዝግጁ መሆኑን አሳይቶናል፡፡ ምን ላግዛችሁ የሚለው ብዙ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ከዚህ በላይ ጉዳይ የለምና አመቻች (ፎካል ፐርሰን) ልሁናችሁ እያለ ዕገዛ ለማድረግ ፍላጎቱን የሚያሳይ ሰው ሁሉ ታገኛለህ፡፡ ተቃዋሚዎች ጭምር ይህን ጉዳይ በብዙ መንገድ እየደገፉት ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተውና እንዲህ ብታደርጉ በሚል የራሳቸውን ሐሳብ ቀርፀው ጭምር የሚሰጡን አሉ፡፡ ምሁራን በተለይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ስለብሔራዊ ምክክር ምንነት ካነበቡትም ሆነ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ አጣቅሰው በኢሜይልም በአካልም እያቀበሉን ነው፡፡ ያለንበትን ሁኔታ የሚቀይር ከሆነ ብለው ዶክመንት አዘጋጅተውና ግብዓት ይዘው የሚመጡ በርካታ ሰዎችን ሲታይ አስቻይ ሁኔታ እንዳለ ስለሚታሰብ ተስፋን ያለመልማል፡፡  ከመንግሥትም ወገን ቢሆን ያለው ቁርጠኝነት አስቻይ ሁኔታ መኖሩን ያሳያል፡፡ ኮሚሽኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር መመራት የለበትም ሲባል እሺ ብሎ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት  እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ስትራቴጂካዊ ዕቅዳችንን ጨምሮ ይፅደቅልን ያልነውንም አፅድቋል፡፡ አሁን ስትራቴጂካዊ ዕቅዳችን በሥራ ላይ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ዝግጁ ነው፡፡ ሌላው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ትልቅ ቅቡልነት ሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ሲቃወሙ የነበሩ ሰዎች ጭምር መጥተው ሒደቱ ተስፋ አለው ብለው እየደገፉት ይገኛሉ፡፡ ከእኛ ጋር በጋራ እየሠሩ ያሉ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡-  እንደ ወለጋ ዓይነት የፀጥታ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች የመድረስ ዕቅድ አላችሁ?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ወለጋ በግሌ ያስተማርኩበት፣ የኖርኩበት፣ አሁንም ድረስ ብዙ ዘመዶቼ ያሉበት አካባቢ ነው፡፡ ወለጋ መሄዳችን ምንም ጥያቄ የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ወለጋን ጨምሮ የማንደርስበት የኢትዮጵያ ክፍል አይኖርም፡፡ ለመሄድ ፍላጎቱም፣ ዝግጅቱም ብቻ ሳይሆን ግንኙነትም አለ፡፡  የሚያሳስብ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ የሚመሩ አወያዮችን መረጣው በምን ሒደት ላይ ይገኛል?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- አወያይ የሚለው ቃል ምናልባት በእንግሊዝኛው ‹‹ኮንቪነርስ›› (Conveners) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ውይይቱን የሚመሩት ሰዎች ናቸው፡፡ አወያዮች/ኮንቪነሮቹ በእኛ ሳይሆን በራሱ በሕዝቡ ነው የሚመደቡት፡፡ አወያዮቹ ቢያንስ ኅብረተሰቡን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ የአንድ ፖለቲካ ኃይል ወይም የመንግሥት ደጋፊ የግድ መሆን የለባቸውም፡፡ በተቻለ መጠን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው፣ ሁሉንም ወገን ማስተናገድ የሚችሉ፣ አገረ መንግሥቱንም ሆነ ብሔረ መንግሥቱን መቃወምም ሆነ መደገፍ የሚችሉ፣ የራሳቸው ነፃ አስተሳሰብ ያላቸው፣ መንግሥትን እንዲህ አድርግ/አታድርግ ለማለት ሥልጣን ያላቸው፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ በአካባቢው ተቀባይነት ያላቸውና ሕዝቡ ራሱ መርጦ ለእኛ ይሁኑልኝ ብሎ የሚሰጣቸው ናቸው አወያይ የሚሆኑት፡፡ አወያይ የሚሆኑት ሰዎች ስለተናገሩ ብቻ አይደለም፡፡ የቀበሌ ወይም የመንግሥት መዋቅርን ተከትሎ ብቻም አይደለም የሚሰየሙት፡፡ ከተቃዋሚዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከሁሉም ወገን ጋር በሚያግባባ አካታችና ተዓማኒ በሆነ መንገድ ነው የሚሰየሙት፡፡ የአወያዮች መረጣ ይካሄዳል፡፡ መረጣው የሚካሄደው ግን በሕዝቡ በራሱ ነው፡፡ በየውይይት መድረኩ አወያዮች አሉ፣ አመቻቾች አሉ፣ እንዲሁም ቃለ ጉባዔ ያዦች አሉ፡፡ ይህ እንዴት እንደሚካሄድ ወደፊት አንድ በአንድ ግልጽ ይሆናል፣ ስለዚህ አሁን ባልናገር ደስ ይለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ ምክክሩ በመንግሥትና በጦር ተፋላሚ ቡድኖች መካከል ሊጀመር ይችላል ተብሎ የሚጠበቅ የሰላም ድርድርን የሚተካ ነው? ድርድሩና ምክክሩ ጎን ለጎን መሄድ ይችላሉ? የድርድሩ መካሄድ የእናንተን ሥራ አይጋርደውም?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ድርድር መካሄዱ ለእኛ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ድርድር መካሄዱ የእኛን ሥራ የሚጋርድ አይደለም፡፡ በአገራችን ያለው የምክክር (Dialogue) አተረጓጎም መስመር ካለመያዙ የተነሳ ነው እንጂ፣ ድርድር (Negotiation) የዲያሎግ አንዱ ንዑስ ክፍል ነው፡፡ በድርድር ሁለት ተፋላሚዎች ፊት ለፊት የሚገናኙበት የሰላም ሒደት ነው፡፡ ሽምግልና (Mediation) የሚባል ሌላ የምክክር ሒደትም አለ፡፡ አፈርሳታ የሚባል ችግር መፍቻ አለ፡፡ አውጫጪኝ የሚባል ሒደትም አለ፡፡ አርቢትሬሽንና (Arbitration) ሌሎችም ብዙ የምክክር ክፍሎች አሉ፡፡ ጉዳዩ ሰፊ በመሆኑ ወደ እዚያ ብዙም አልገባም፡፡ ለእኛ ድርድሩ መካሄዱና መሳካቱ በጣም ነበር የሚጠቅመን፡፡ ምክንያቱም የምክክር አንዱ ክፍል እንደ መሆኑ ድርድሩ ቢሳካ ወደ እዚያ መሄዳችን በአንድም በሌላም መንገድ የማይቀር በመሆኑ ሥራ ያቀልልን ነበር፡፡ እኛ በዋናነት የምንሠራው ዘላቂ ሰላም መፍጠር ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለመቶዎችና ለሺሕ ዓመታት በተጓዘችበት ዘመን በሙሉ ወደፊት መጓዝ ሲገባት፣ የተጀመረው ነገር የእምቧይ ካብ እየሆነ ሁልጊዜ ወደኋላ የምትመለሰው ለምንድነው ለሚለው ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ከላይ ወደ ታች በሚመጣ የፖሊሲና የመንግሥት ለውጥ ሳይሆን፣ ሕዝቡ ራሱ ከታች ወደ ላይ በሚሰጠው አገር በቀል ዕውቀት ላይ አገሪቱ እንድትገነባ ማድረግ ነው፡፡ ሌሎች እንደ ኒውዚላንድ ያሉ አገሮች አድርገው ተሳክቶላቸዋል፡፡ የስካንዲኒቪያን አገሮችን ጨምሮ እነ ኮሎምቢያ አድርገዋል፡፡ ሕዝቡ ከራሱ የሚያመጣው መፍትሔ ዘላቂ በመሆኑ ወደኋላ እንዳንመለስ መሠረት ይጥላል፡፡ ብሔራዊ ምክክር ከድርድር በተለየ መንገድ ለአገር ዘላቂ መፍትሔ በመፈለግ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ድርድሩ ግን በዚህ ውስጥ አንዱ ንዑስ የችግር መፍቻ መንገድ ነው፡፡ ድርድሩ ቢሳካ ኖሮ በጣም ደስ ባለን፣ ለእኛም በጣም ይጠቅመናል፡፡ ድርድሩ ግን የእኛን ሒደት በፍፁም አይተካውም፡፡ ይህን ደግሞ ሁለቱም ለድርድሩ የተዘጋጁ ኃይሎች በደንብ ያውቁታል፡፡ ወደ ትግራይ ክልል እንሄዳለን የሚሉ ዘገባዎች ከወጡ በኋላ እጅግ በጣም በጎ ምላሾች አግኝተን ነበር፡፡ ድርድሩ ቢካሄድ በጣም ጠቃሚያችን ነው፣ ነገር ግን ባይካሄድም የእኛ ሥራ ይቀጥላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰላም በሌለበት አገራዊ ምክክሩን ማድረግ አይቻልም ለሚለው ሥጋት ምን ምላሽ አላችሁ?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ተገቢ ሥጋት ቢሆንም ነገር ግን ማካሄድ ይቻላል እላለሁ፡፡ በዓለማችን ብሔራዊ ምክክር ያደረጉ 150 አገሮችን ተሞክሮ እያየሁ ነበር፡፡ ቺቺኒያ፣ ሩሲያ፣ ጆርጂያ፣ ምሥራቅ አውሮፓና ሌሎችም አካባቢዎች የነበሩ ማሳያዎችን እየለቀምኩ ነበር፡፡ በዚያ በኩል ጦርነት እየተካሄደ በዚህ በኩል ድርድር ያደረጉበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ምክክር የተሸጋገሩበትን ሁኔታም ታገኛለህ፡፡ ጦርነትና ግጭት እያለ ድርድር ማካሄድ ይቻላል፣ ተችሏልም፡፡ የሌላ አገሮች ልምድ ይህን ያረጋግጣል፡፡ እኛ ዘንድ ድርድሩ እንዲካሄድና እንዲሳካ ምኞታችን፣ ፍላጎታችንና ፀሎታችን ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ነው ምንፈልገው፡፡ ለልጆቻችን የምናወርሳት ሰላማዊት ኢትዮጵያን ነው የምንፈልገው፡፡ ስለዚህ ግጭቱም ሆነ ድርድሩ ቢኖሩም ባይኖሩም አገራዊ ምክክር ማድረግ በጣም ጠቃሚያችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ መንግሥታትና የረድኤት ድርጅቶች በጎ ምላሽ እያሳዩ ነውን?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚባሉትን የውጭ መንግሥታትና የሲቪክ ማኅበራት አግኝተናቸው ነበር፡፡ ሁሉም በጎ ምላሽ ነው የሰጡን፡፡ ወደ ትግራይ ክልል ልንሄድ አስበን ነበር ስንል፣ በሦስተኛ ወገን ማለትም በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በኩል የሚደረጉ ግንኙነቶችን ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡ እነሱም ጉዟችንን ለመደገፍ ዝግጁ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ለሥራችን ገንቢ ሚና መጫወት የሚችሉ ብዙ የረድኤት ድርጅቶችና የዲፕሎማሲ ተቋማት አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር በየጊዜው እየሠራን ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ሳምንታት የተለያዩ የጋራ ሥራዎች እንዳሉን እንደምናሳውቅ መናገር እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የዳያስፖራውን ተሳትፎ በተመለከተስ ምን ትላላችሁ?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- ዳያስፖራውን በተመለከተ በቅርቡ ከዒድ እስከ ዒድ በተባለው ጥሪ ወደ አገር ቤት የመጡትን አግኝተናል፡፡ በዳያስፖራ አሶሴሽን አማካይነትም የተለያዩ ዳያስፖራዎችን አግኝተናል፡፡ በጣም በጎ ምላሽ ነው ያገኘነው፡፡ በውይይቱም ቢሆን ከዝግጅት ጀምሮ በሒደቱ ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የራሳቸውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ክላስተሮች ማለትም የሰሜን አሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የአውስትራሊያና በመሳሰሉ የዳያስፖራ ወኪሎች አማካይነት ውይይት አድርገናል፡፡ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉበትን ሒደት አመቻችተንና ዝግጅት ጨርሰን ወደ ሥራ ለመግባት እየሠራን ነን፡፡  

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ ከሒደቱ ምን ይጠበቅ?

ዮናስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፡- በየቦታው የምናደርጋቸውን የሙከራ ውይይቶች አጠቃለን እንደ ፈጣሪ ፈቃድ በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ የመጀመርያውን ዙር ምክክር በአገር አቀፍ ደረጃ ለማድረግ እየተዘጋጀን ስለሆነ እሱን መጠበቅ ይቻላል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የሚዲያውን ማኅበረሰብ ጠንካራና የነቃ ተሳትፎ ለመፍጠር እየጣርን ነው፡፡ ሚዲያው ገንቢ ሚና እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡ ሚዲያ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ አገር ስትታመም ሁላችንም ነንና የምንታመመው የእናንተም ገንቢ ሚና ወሳኝ ነው፡፡ የሚዲያውን ሚና በሁለት ነው የምናየው፡፡ መጠገንም ሆነ መስበርም ይችላል፡፡ ከሩዋንዳ የተማርነው እሱን ነው፡፡ ሚዲያው በከፍተኛ ትኩረት ሒደቱን እንዲከታተል እንፈልጋለን፡፡ በጎ አዘጋገብን በማዳበር ስንሳሳት ጭምር እንዲያርመን እንፈልጋለን፡፡ እያንዳንዱን ሒደት ለሕዝብ እንዲያደርስ እንፈልጋለን፡፡ ከሰሞኑ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ ስናቀርብ ከሁለት ሚዲያዎች የቀረበልን ጥያቄ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ኮሚሽነር ለፓርላማ ሪፖርት ሲያቀርቡ 24 ስላይዶችን አቅርበው 25ኛው ላይ የበጀት ጥያቄ በመነሳቱ ብቻ፣ የኮሚሽኑ አባላት ለሆዳቸው ይሠራሉ ተብሎ ተዘግቧል የሚል ጥያቄ አንስተውልናል፡፡ ይህ ዓይነቱ አዘጋገብ ቀርቶ ሁላችንም በኃላፊነት የምንዘግብበትና መረጃ ለሕዝብ የምናደርስበት ሒደት እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ አንድ አገር ናትና ያለችን ሁላችንም የሚጠበቅብን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፡፡ ተቃዋሚዎች ከሚጠበቀው በላይ ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ የሲቪክ ማኅበራትም እንደዚያው፡፡ መንግሥትም ሆነ የውጭ አጋሮች ሒደቱን በበጎ ተቀብለውታል፡፡ ከሚዲያም በእርግጥ ብዙ በጎ ሚና ቢኖርም ከዚህ በላይ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ በቅርቡ በምክክር አዘጋገብ ላይ ሥልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ የበለጠ አሳታፊ የሆኑ ሁኔታዎችን ለሚዲያዎች እናመቻቻለን፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...