Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ባንኮችን የማዋሃድ አስፈላጊነት ፍንትው ያደረገው ዓመታዊው የአፍሪካ ባንኮች የደረጃ ምዘና ሪፖርት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካ ባንኮችን በየዓመቱ በመመዘንና ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው አፍሪካ ቢዝነስ መጽሔት እ.ኤ.አ. የ2022 ዓመት ሪፖርቱንና ምርጥ ያላቸውን አንድ መቶ የአፍሪካ ባንኮች ዘርዝሮ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።

መጽሔቱ የአፍሪካ ባንኮችን መዝኖና ምርጥ ያላቸውን መቶ ባንኮች ደረጃ ሰጥቶ ይፋ ባደረገበት በዚህ ዓመታዊ ሪፖርት ውስጥ ውስጥ ሁለት የኢትዮጵያ ባንኮች ብቻ ተካተዋል።

በመጽሔቱ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከአንድ መቶ አፍሪካ ባንኮች ውስጥ ስማቸውን በሰንጠረዥ ውስጥ ያስመዘገቡት የኢትዮጵያ ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አዋሽ ባንክ ናቸው፡፡ በ2021 ሪፖርቱ ላይም ከመቶዎቹ ቀዳሚ ባንኮች ውስጥ እነዚሁ ሁለት የኢትዮጵያ ባንኮች ተካተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በ2022 የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 31ኛ አዋሽ ባንክ ደግሞ 91ኛ ደረጃ ላይ ማገኘታቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁለት ባንኮች የዘንድሮ የተቀመጡበት ደረጃ ባለፈው ዓመት አግኝተውት ከነበረው ደረጃ ዝቅ ያለ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል። የመጽሔቱ ዋነኛ መመዘኛ ተደርጎ የሚወሰደው የባንኮች የካፒታል መጠን ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባንኮች በዘንድሮው ሰንጠረዥ ከደረጃው ዝቅ ያሉትም ከዚሁ ካፒታል ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እነዚህ ሁለት ባንኮች የብር ካፒታል መጠናቸውን ዘንድሮ ያሳደጉ ቢሆንም፣ ይህ ካፒታል መጠን ከዶላር አንፃር ሲታይ ዝቅ ብሎ መገኘቱ ባለፈው ዓመት ይዘውት ከነበረው ደረጃ እንዲለቁ አድርጓቸዋል፡፡ 

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በመጽሔቱ ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ ባንኮች ደረጃ ዝቅ ማለት ባንኮችን ተወዳዳሪ ያለመሆናቸውን የሚያመላክት ነው ይላሉ፡፡

በኢንዱስትሪው ኢትዮጵያን የሚወክሉ ባንኮች መገኘታቸው መልካም ቢሆንም የባንኮቻችን አቅም ገና ስለመሆኑ ያሳያልም ይላሉ፡፡ ‹‹የአፍሪካ ቢዝነስ መጽሔት በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርት ባለፈው ዓመት (2021) ሁለት የኢትዮጵያ ባንኮች ነበሩ፡፡ ዘንድሮም (2022) እነዚሁ ባንኮች ከመቶዎቹ የአፍሪካ ባንኮች ውስጥ ነበሩ ያሉት አቶ ዘመዴነህ ደረጃቸው ግን ቀንሷል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ26ኛ ደረጃ ወደ 31ኛ፣ አዋሽ ባንክ ከ53ኛ ወደ 91ኛ ወርዷል፡፡

ባለፈው ዓመት ከነበረበት 26ኛ ደረጃ ወደ 31ኛ ደረጃ የተንሸራተተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጽሔቱ መረጃ መሠረት ያስመዘገበው ካፒታል 929 ሚሊዮን ዶላር ነው።

ከመቶዎቹ ምርጥ የአፍሪካ ባንኮች ውስጥ የሰንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጠው የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ ሲሆን፣ ባንኩ ያስመዘገበው የካፒታል መጠን 13.6 ቢሊዮን ዶላር ነው። በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የግብፅ ብሔራዊ ባንክ ሲሆን ያስመዘገበው የካፒታል መጠንም 7.27 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ መረጃው ያመለክታል። በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ባንክ የግብፁ ባንክ ኦፍ ምስር ሲሆን ያስመዘገበው የካፒታል መጠንም 7.23 ቢሊዮን ዶላር ነው። ከምሥራቅ አፍሪካ ባንኮች ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነው የኬንያው ኢኪዩቲ ባንክ ነው።

አቶ ዘመዴነህ የኢትዮጵያ ባንኮች አሁን ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ የሚቀጥለው ዓመት ከመቶዎቹ ምርጥ የአፍሪካ ባንኮች ዝርዝር ውስጥ ላይታዩም ይችላሉም ብለዋል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት እነዚህ ባንኮች ያስመዘገቡት ካፒታል ከዶላር አንፃር ሲታይ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹እነዚህ ባንኮችም ይሁኑ ሌሎች የግል ባንኮች ካፒታላቸውን በብር ደረጃ አሳድገዋል፣ ነገር ግን ይህ ካፒታላቸው ወደ ዶላ ሲመነዘር በጣም ትንሽ ነው፤›› የሚሉት አቶ ዘመዴነህ ከዚህም በፊት ቢሆን የኢትዮጵያ ባንኮች ካፒታላቸው አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ‹‹ባንኮቻችን በኢትዮጵያ ውስጥ  ያስመዘገቡት ካፒታልና ሀሴት እንደጨመረ ቢታወቅም ከዶላር ጋር ሲመዘን ግን ከሌሎች የአፍሪካ ባንኮች አንፃር አነስተኛ ደረጃ ላይ መሆናችንን ይጠቁማል›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሃራ በታች ከደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ቀጥሎ ሦስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ የሚባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዘመዴነህ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ግን በኢኮኖሚው ደረጃ ያደጉ አለመሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ ባንኮች አሁን በሚሄዱበት መንገድ ወይም አወቃቀር ተወዳዳሪ ሆነው መቀጠል እንደማይችሉ አቶ ዘመዴነህ ተናግረዋል። ‹‹እነዚህ ባንኮች አሁን ባሉበት ደረጃ በአፍሪካ ሦስተኛው ትልቅ ኢኮኖሚ የሚባለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያድግ የሚያደርግ አቅም የላቸውም፤›› ይላሉ፡፡ ይህ አቋማቸው ስለመሆኑ የሚያስረዱት አቶ ዘመዴነህ፣ ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቅሱት የኢትዮጵያ ባንኮች ከአገሪቱ ከኢኮኖሚውም ሆነ ከሌሎች አገሮች ባንኮች ጋር ሲነፃፀሩ ትንሽ መሆናቸውን ነው፡፡ በአንድ በኩል ተለቅ ያለና የ110 ጂዲፒ አለ፡፡ በሌላ በኩል ግን በአፍሪካ ደረጃ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ የሚባል ቢሆንም ሌሎች የአገር ውስጥ ባንኮች ግን በጣም ትንሽ የሚባሉ እንደሆነ በመጥቀስ ይህ መስተካከል እንዳለበት ይከራከራሉ። ይህ ሁኔታ ካልተስካከለ ከአፍሪካ 100 ባንኮች ዝርዝር መግባት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ 

ይህንን ነገር ለመቀየር ግን አሁን በመንግሥት ደረጃ የተያዘው አቅጣጫ መፍትሔ ያመጣል ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም መንግሥት በፖሊሲ ባንኮች ይዋሃዱ ወደሚል አቅጣጫ እየገባ መሆኑና የውጭ ባንኮች እዲገቡ መፍቀዱ ነው፡፡

አሁን ባለው የመንግሥት ፖሊሲ እነዚህ ባንኮች በአንድና በሁለት ዓመት ተዋህደው ሲጨርሱ ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት የንግድ ባንኮች ብቻ ይኖራል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡ ይህ ምልክታቸው ብዙ ጥናት በማድረግ የደረሱበት ድምዳሜ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ስለዚህ ባንኮቻችን ከአገር ውስጥ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ተዋህደው አምስት ባንኮች መፍጠር ስለመሆኑ የጠነከረ አቋም መያዛቸውን ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ስፔሻላይዝድ ባንኮች (ማለትም በእርሻ፣ በኢንዱስትሪ፣ ኮንስትራክሽን ያሉ ዘርፎችን አገልግሎት ለመስጠት የሚቋቋሙ) ግን ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ይህም የመንግሥት ፖሊሲ ሆኖ መምጣቱ አንድ ትልቅ ዕርምጃ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ከውህደቱ ባሻገር ደግሞ የውጭ ባንኮች ይግቡ የሚለውም የአገሪቱን ባንኮች በማጠናከሩ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸው፣ መዋሃዱ በራሱ የሚመጡት የውጭ ባንኮችን ለመሳብ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት በቅርቡ ባፀደቀው የባንክ ዘርፉን ለውጭ ውድድር የመክፈት ፖሊሲ፣ የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ ባንክ ላይ እስከ 40 በመቶ ድረስ እንዲይዙ የሚፈቅድ ነው።

መንግሥት ይህንን የፖሊሲ ውሰኔ ማሳለፉ በጣም ጥሩ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ዘመዴነህ፣ ነገር ግን መታሰብ ያለበት ነጥብ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ ኢንቨስት የሚያደርጉት ትልቅ ካፒታልና ገበያ ውስጥ የተሻለ ተደራሽነት ያላቸው ባንኮች ላይ እንጂ ትንንሾቹ ላይ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ትንንሾቹ ባንኮች ተዋህደው ጠንከር ያለ ባንክ ቢፈጥሩ የሚጠቀሙት እነሱ አንደሆነ ጠቀሙዋል። በአፍሪካ ደረጃ ከመቶዎቹ ባንኮች ሰንጠረዥ ውስጥ የሚገቡ የኢትዮጵያ ባንኮችን ለማብዛት መዋሃድ፣ ከዚያም ከውጭ ባንኮች ጋር በጆይንት ቬንቸር መሥራት የግድ የሚል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ውህደትና የውጭ ባንኮች መግባት አብረው የሚሄዱ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ ዘመዴነህ ይህንን ማድረግ የኢትዮጵያ ባንኮች በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ስቶክ ማርኬት ሲቋቋም ደግሞ እነዚህ በውህደት ትላልቅ የሆኑ ባንኮች አክሲዮናቸውን ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ያኔ የበለጠ ራሳቸውን የሚያሳድጉ ይሆናሉ፡፡ ካፒታላቸውም ይጨምራል፡፡

የባንኮች ተዋህዶ ጠንካራ ባንክ መፍጠር ብዙ ትርጉም ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዘመዴነህ አሁን ባላቸው አቅም የማበደር አቅማቸው እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ 

ለአንድ ተባሪ አንድ ቢሊዮን ብር ማበደር የማይችሉ ባንኮች ያሉን በመሆኑ ይህንን ለመለወጥም ቢሆን ተዋህደው ከፍ ያለ ካፒታል ሊይዙ ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ አንድ ቢሊዮን ብር  መበደር የሚፈልግ ተበዳሪ ሊበደር ይችላልና ሰብሰብ ብሎ ራስን ማጠንከር ወቅቱ የሚጠይቀው ከመሆኑም በላይ መንግሥትም በር መክፈቱ መልካም ነው ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ የአገሪቱ ሁሉም ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት ካፒታላቸውን በየዓመቱ በ27 በመቶ በማሳደግ መቻላቸው ነው፡፡ ነገር ግን ከውጭ ምንዛሪ አንፃር ዝቅ እያለ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት የአገሪቱ ሁሉም ባንኮች ያስመዘገቡት የካፒታል መጠን 98.92 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ በወቅቱ የምንዛሪ ዋጋ 2.38 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በ2022 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ አማካዩ 34.95 ብር በነበረበት ወቅት ባንኮች ያስመዘገቡት የካፒታል መጠን 114.59 ቢሊዮን ብር የደረሰ ቢሆንም ይህ የካፒታል መጠን ከዶላር አንፃር ሲታይ የባንኮቹ ካፒታል መጠን 4.13 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት ደግሞ የባንኮች ጠቅላላ ካፒታል ወደ 153 ቢሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ ከዶላር አንፃር ሲታይ ግን ከ2012 የሒሳብ ዓመት አንሶ 3.45 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት የባንኮች አጠቃላይ ካፒታል ወደ 200 ቢሊዮን ብር (199.03 ቢሊዮን ብር) የደረሰ ቢሆንም ከዶላር አንፃር ሲታይ 3.76 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በዘንድሮ የደረጃ ሰንጠረዥ ዝቅ ማለታቸው እንደተባለው የብር የመግዛት አቅም እያነሰ መሄድ አንዱ ምክንያት መሆኑን የገለጹልን አንድ የባንክ የሥራ ኃላፊ የምንዛሪ ዋጋ በጨመረ ቁጥር እንዲህ ዓይነቱ ችግር እየቀጠለ ይሄዳል፡፡ 

ይህ የሚያሳየው የአገራችን ባንኮች ተወዳዳሪ አቅም የሌላቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉ እኝሁ ኃላፊ ባንኮች በየጊዜው ካፒታላቸውን እየጨመሩ መሄድ እንዳለባቸው የሚያለክትም ነው ብለዋል፡፡

ይህ ሪፖርት የሚያሳየን አሁን የውጭ ባንኮች ይግቡ ቢባል ይዘውት የሚመጡት የውጭ ምንዛሪ በመሆኑ አንድ የውጭ ምንዛሪ ባንክ 500 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ካስመዘገበ ከሁሉም የግል ባንኮች የበለጠ ካፒታል ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

በ2022 ሪፖርቱ በአፍሪካ ውስጥ ጠንካራ ባንኮች በመሆን ከአንድ መቶ ባንኮች ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ያስመዘገቡት የደቡብ አፍሪካና የግብፅ ባንኮች ናቸው፡፡

የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ አዳዲስ ባንኮች መግባትም የኢትዮጵያ ባንኮች ደረጃን ዝቅ እንዲል ሌላው ምክንያት ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ባንኮች ሰንጠረዥ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ባንኮች ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ በዘንድሮው የመጽሔቱ ሪፖርት እነዚህ አንድ መቶ ምርጥ የአፍሪካ ባንኮች ውስጥ ከምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛውን ቁጥር ለማስመዝገብ የቻለችው ኬንያ ነች፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችን ለብቻው ነጥሎ ባደረገው ምዘና የኢትዮጵያ ባንኮች ካቀደው ዓመት በተሻለ ቁጥር የተካተቱበት ስለመሆኑ መረጃው ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉ ባንኮች ውስጥ ስማቸውን ማስመዝገብ የቻሉት ባንኮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዋሽ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ዳሸን ባንክና ልማት ባንክ ተካተዋል፡፡ 

ስለዚህ እነዚህ ባንኮች በብር በታሰበ የካፒታል መጠናቸው እየጨመረ ቢሄድም የብር የመግዛት አቅም ባነሰ ቁጥር የእነሱም አቅም አነስተኛ እየሆነ ይሄዳል ስለዚህ አቅማቸውን የበለጠ ለማጉላት ከሌሎች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የካፒታል አቅማቸውን እያሳደጉ መሄድ ግድ የሚል መሆኑን ነው፡፡

በዚህ ሪፖርት ምዘና ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡን ጉምቱው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ በበኩላቸው የአፍሪካ ባንኮች አብዛኛዎቹ በብዙ መልኩ ጥሩ ጊዜ ያሳለፉ መሆኑን ያሳያል፡፡

በአንድ ዓይነት  ከረንሲ ተለውጦ የቀረበው ሪፖርት የእኛ ባንኮች ሀሴት በኢትዮጵያ ብር ጨምረዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ከረንሲ ከሌሎች አገሮች ባንኮች ጋር ሲያወዳድሩን የእኛ የውጭ ምንዛሪያችን በጣም ስላሽቆለቆለ ወደ ኋላ መሄዳችን ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ሪፖርት የተጠቀሱ ባንኮች ዘንድሮ በዚህ ዓመት ወደ ታች ወርደዋል፡፡ ስለዚህ በአገር ውስጥ ጥሩ ዕድገት ቢያሳዩም ነገር ግን የውጭ ባንኮች ወደ አገር ይግቡ ሲባል የእኛን አቅም ሲያዩ ምን እንደሚመስል መገመት አያቅትም ብለዋል፡፡ ስለዚህ የባንኮችን ካፒታል ማሳደግ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚ የዳሰሰ ውሳኔ እንደሚያስፈልገን ያመለክታል ብለዋል፡፡

በዚህ ዙሪያ ተጨማሪ ሐሳቦችን የሰነዘሩት አቶ ዘመዴነህ ባለፉት 27 ዓመታት የተቋቋሙ ወጣት ባንኮች ያሉንና የባንክ ሥራ ጊዜ የሚፈልግ ነው የሚሉት አቶ ዘመዴነህ 27 ዓመት ከለላ ተሰጥቷቸዋል፡፡ አሁን በዚያ መንገድ መሄድ አይቻልም እስካሁን ውድድር የለባቸውም እየተወዳደሩ አይደለም፡፡ አሁን መንግሥት ያወጣውን ፖሊሲ እውነተኛው ውድድር እየመጣ ስለሆነ ለዚያ መዘጋጀት ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም ረገድ ዝግጁ ይሁኑ ሲባል ባለአክሲዮኖችንም ይመለከታል ይላሉ፡፡ 

ባለአክሲዮኖች እንደበፊቱ 20 እና 30 በመቶ የትርፍ ድርሻ ከመውሰድ ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያ በማዋል ባንኮቻቸው እንዲጠናሩ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

‹‹የእኔ ምክር አሁን ያለው 20 እና የ30 በመቶ የትርፍ ድርሻ ሊቀጥል አይችልም፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ የትርፍ ድርሻውን እየወሰዱ ያሉ ባንኮች ሊቀጥሉ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ባንክ እንዲኖራቸው ግፊት ማድረግ ያለባቸው ባለአክሲዮኖቹ ናቸው ብለዋል።

‹‹ዛሬ የሚወስዱን ብቻ የሚያዩ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ ይህን ካደረጉ ከሁለትና ሦስት ዓመት በኋላ አሥር በመቶ ዲቪደንድ ላይገኝ ይችላልና ባለው ስትራክቸር እነዚህ ትንንሽ ባንኮች የሚጠብቃቸውን ውድድር በማሰብ ዲቪደንዱን ካፒታል ላይ ማዋል ግድ ይላቸዋል፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች