Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ደላሎች ዋጋ ከመተን አልፈው ወደ ገበያ የሚገባ የምርት መጠን መወሰን ከጀመሩ ምን ቀራቸው?

በቅርቡ የኢትዮጵያን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና አጠቃላይ የግብይት ሒደት የሚመለከት አንድ ጥናት በዘርፉ ባለሙያ ቀርቦ ነው፡፡ ጥናቱ ይበልጡኑ እንደ ፓፓዬ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶ ሙዝና የመሳሰሉ የፍራፍሬ ምርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ 

በዚህ ጥናት ኢትዮጵያ በፍራፍሬ ምርቶች ዋጋ በአግባቡ ልትጠቀም ያለመቻሏን አጉልቶ አሳይቷል፡፡ በአገሪቱ አትክልትና ፍራፍሬ የሚመረትባቸው ቦታዎች በርካታ ቢሆኑም፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ፍራፍሬ ምርት እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ከሚመረተው ምርት አንፃር ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ምርት አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከሚላከው የፍራፍሬ ምርት 90 በመቶ የሚሆነውን የምትቀበለው ጂቡቲ መሆንዋ በዘርፉ ያለውን ችግር ያመላክታል ብሏል፡፡ 

ጥናቱ በአኃዝ ካስቀመጣቸው ምርትን የሚመለከቱ መረጃዎች በአገሪቱ ካሉ ስድስት የፍራፍሬ ማምረቻ ኮሪደሮች እያንዳንዱ የፍራፍሬ ምርቶች በሚሊዮን ቶን የሚመረቱ ናቸው፡፡ ከፍተኛ የሚባል የግብይት ችግር ያለበት ይህ ዘርፍ ለአገሪቱ የወጭ ንግድ ያለው አስተዋጽኦ አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም በተበላሸ የግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚያልፍ ነው፡፡ 

የአትክልትም ሆነ የፍራፍሬ ምርቶች በአገር ውስጥ ገበያ ዋጋቸው ተሰቅሎ የቅንጦት ምግብ እስከመሆን የተደረሰበት ዋናው ምክንያት በቂ ምርት ባለመመረቱና ባለመቅረቡ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ምርቶች ዋጋቸው የሚወሰነው ተቋማዊና ሕጋዊ አሠራርን በተከተለ መንገድ ባለመሆኑ እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ 

ጥናቱ በአጭሩ እንዳስቀመጠው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲህ የቅንጦት ምርት ይመስል ዋጋው የተጋነነበት ዋናው ምክንያት ገበያው በደላላ የሚመራ በመሆኑ ነው፡፡ ጥናቱ በዘርፉ አሉ ያላቸውን ችግሮች በሰፊው ያብራራ ሲሆን በማጠቃለያው ላይ እንደ መፍትሔ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል አንዱ የገበያ ችግሩን መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ በዘርፉ ያሉ በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው ከዋጋ አንፃር ያለውን ችግር ለመቅረፍ ግን ከዚህ ገበያ ውስጥ ደላሎችን ማስወጣት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡ 

የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በአብዛኛው ወደ ገበያ የሚቀርበው ደላሎች በዘረጉት ሰንሰለት ሲሆን፣ ወደ ገበያ የሚገባውን የአትክልትና ፍራፍሬ የምርት መጠንና ዋጋ የሚወስኑት እነዚሁ ደላሎች በመሆናቸው የተረጋጋ ገበያ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ 

በእጅ ያለ ምርት ወደ ገበያ እንዳይገባ ጭምር አርቴፊሻል እጥረት በመፍጠር ገበያውን በራሳቸው መንገድ በማስኬድ የሚፈጽሙት ሸፍጥ የዋጋ ንረቱን ከማባሱም በላይ ለኑሮ ውድነት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ 

ከሰሞኑም የፍራፍሬ ምርቶች ከእጥፍ በላይ ዋጋቸው ተሰቅሎ ለመታየቱ አንዱ ምክንያት ይህ የደላሎች ገበያውን ያለከልካይ ይዘው መዘወራቸው ነው፡፡ ይህ ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግብይት ሥርዓት ብልሹነት ብዙ ዋጋ እያስከፈለን መሆኑ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በየትኛውም የምርት ግብይት ውስጥ ገበያን መሠረት አድርጎ ዋጋ የሚተመን ቢሆንም አንዳንድ ምርቶች በደላሎች የሙጥኝ ተይዘዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ የንግድ ዘርፎችና ገበያዎች ውስጥ ዋጋ የሚወጣው በደላሎች መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል።

ነገሩን ጠለቅ ብለን ከተመለከትነው በተለይ የአገር ውስጥ የእርሻ ምርቶች ላይ የደላሎች እጅ እጅግ የረዘመ ነው፡፡ እነዚህ ደላሎች ዋጋን መተን ብቻ ሳይሆን ወደ ገበያ መግባት ያለበትን የምርት መጠን የመወሰን ሥልጣን ሁሉ በመያዛቸው ለወቅታዊው የኑሮ ውድነት ትልቁን ድርሻ እየወሰዱ ነው፡፡ ይህ ሥልጣን በሕግ የተሰጣቸው ሳይሆን፣ ባፈረጠሙት ጡንቻ ያለ ከልካይ እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱ ነው፡፡ ይህንን የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የደላሎች አሉታዊ ሚና የሚገለጽባቸው በርካታ ማሳያዎች ያሉ ሲሆን በከተማ አካባቢ እንደ ቤት መኪና፣ ሕንፃና መሰል ንብረቶች ሽያጭ ላይ እየፈጸሙ ያሉትን ድፍረት በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ደላሎች የቤት ኪራይ ዋጋን በማናር እየፈጠሩ ያሉትን ምሬት ማስቆም ባለመቻሉ ቀን እየቆጠሩ አከራዮችን እየጎተጎቱ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ የሚፈጥሩት ውጥረት የቤት ኪራይ ዋጋ ከብዙዎች አቅም በላይ እንዲሆን አድርጓል፡፡ 

ደላሎች በገበያ ውስጥ ያላቸው ረዥም እጅ በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ዛሬ የተሽከርካሪዎች ዋጋ ሰማይ መሰቀል የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረው ወይም ወደ አገር የሚገቡ ተሽከርካሪዎች መጠን መቀነስ አይደለም፡፡ በእርግጥ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ነገር ግን መሠረታዊ ምክንያቱ የደላሎች የተደራጀና የተናበበ ሸፍጥ ነው፡፡

መንግሥት ይህንን በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላል። እንዴት አድርጎ ከተባለም፣ ገበያ ላይ ያለውን የቤት አውቶሞቢሎች አማካይ ዋጋ በመያዝ አውቶሞቢል ለገዙ ግለሰቦች የተቆረጠላቸው ደረሰኝ ላይ ያለውን ዋጋ ወይም የባለቤትነት ስም በሚዞርበት ወቅት ከሚቀርበው የሽያጭ ውል ሰነድ ላይ የተጠቀሰውን ዋጋ ከትራንስፖርት ቢሮ አውጥቶ በማነፃፀር ሊደርስበት ይችላል። ይህንን በማድረግ ሕዝብ እንዴት እየተበዘበዘና መንግሥትም ምን ያህል የታክስ ገቢ እያጣ እንደሆነ ማረጋገጥ ይችላል።

በደላሎችና በነጋዴዎች ያልተገባ ግንኙነት የተነሳ ሕዝብ እየተበዘበዘ ነው መንግሥትም በራሱ ላይ ቀውስ እየቆለለ ነው። አንድ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለቤት ያወጣውን ወጪ አሥልቶ በዚህን ያህል ልሽጠው ቢል ደላሎች አይሰሙትም፡፡ ይህማ ይህንን ያህል ያወጣል ብለው ሻጩ ካሰበው ዋጋ በላይ ዋጋ ተምነው ዋጋውን የሚሰጡት እነሱ በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊ የሆነ ዋጋ በገበያ ውስጥ እንዳይሠራ እያደረጉ ነው፡፡ 

በጣም የሚገርመው ደላሎች ከቆረጡት ዋጋ ውጪ ለመሸጥ የማይቻልባቸው አጋጣሚዎች የበዙ ናቸው፡፡ ከደላሎች ውጪ ለመሸጥ መሞከርም ከባድ የሆነበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ በሚሊዮኖች እያሻሻጡ ከሚያገኙት ኮሚሽን ቤሳቤስቲን ለታክስ የማያውሉ መሆኑም የሚያሳድሩትን ጉዳት ያገዝፈዋል፡፡ ስለዚህ በሥሌት መሸጥና መግዛት እዚህ አገር እየጠፋ ፈላጭ ቆራጮቹ ደላሎች ሆነው እስከ መቼ እንደሚቀጥል ግራ ያጋባል፡፡ በደላሎች በሚፈጸሙ ሸፍጦች የሚፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች በሁሉም ቦታ እየተዘመተ በመሆኑ ይህንን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም መንግሥት መፍጠር አለበት፡፡ ካልቻለ ግን ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ እንዲህ ቀላል አይሆንም፡፡ በሁሉም ዘርፎች ደላሎችን ከገበያ እናስወጣለን የሚለው የመንግሥት ዛቻ እንዲሁ ከቀጠለ ገበያው የሕገወጦች መናኸሪያ ይሆናል፡፡ የተረጋጋ ገበያ እንዳይፈጠርም ምክንያት ሆኖ የሚቀጥል በመሆኑ መንግሥት ሥር እየሰደደ ያለውን በደላሎች የሚመራ ገበያ በአስቸኳይ መላ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት