Wednesday, April 17, 2024

የኢትዮጵያ የቀጣናዊ ትስስሮች ማዕከልነት ሚና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሶማሊያውን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድን ኦፊሴላዊ የትዊተር ገጽ ለሚከታተል፣ በሰውየው የአንድ ወር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እንደሚገረም ይጠበቃል፡፡ ሰውየው የሶማሊያ መሪ ከመባል ባለፈ በቀጣናዊም ሆነ በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች የራሳቸውን አሻራ የማሳረፍ ፍላጎት እንዳላቸው፣ ባለፈው አንድ ወር ካሠፈሯቸው የትዊተር ገጽ መልዕክቶች መከታተል ይቻላል፡፡

እ.ኤ.አ. መስከረም 13 ቀን 2022 በኬንያ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ላይ ታደሙ፡፡ ለበዓሉ ከተጋበዙ የቀጣናው አገሮች መሪዎች ጋር ሲገናኙም ታዩ፡፡ ከአራት ቀናት በኋላ አሜሪካ ተገኝተው ከፔንታጎን፣ ከዋይት ሐውስና ከውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት ጨምሮ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር ነበር የሰነበቱት፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 77ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመታደም ትኩረት የሳበ ንግግር ሲያደርጉ ነበር፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ ከሱዳንና ከሌሎች አገሮች፣ እንዲሁም እንደ ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ካሉ ተቋማት መሪዎች ጋር ታይተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ረቡዕ መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ መጥተው፣ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ቆይታ አድርገው ተመልሰዋል፡፡ ሰውየው በአጠቃላይ በመስከረም ወር ውጤታማ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ሲያከናውኑ ማሳለፋቸውን የበለጠ የሚያረጋግጠው ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አድርገውታል የተባለው የሁለትዮሽ ስምምነትና መግባባት ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ከመግባባት የደረሱባቸውን ጉዳዮች፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓቸዋል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ደግሞ፣ ‹‹ሁለቱ አገሮች ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት በሚያደርጉት የጋራ ጥረት ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ ሁለቱ መሪዎች ተስማምተዋል፡፡ ይህን ለማድረግም ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን፣ ሉዓላዊነታቸውንና የግዛት አንድነታቸውን ባከበረ መንገድ በመከባበርና በመግባባት ላይ ተመሥርተው የእርስ በርስ ውይይትና ትብብር ያደርጋሉ፤›› ተብሎ የሠፈረው ነጥብ ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡

የሁለቱ አገሮች መሪዎች በዚህ ሰሞነኛ ግንኙነታቸው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት ከፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ባለፈ፣ በንግድና በኢኮኖሚ የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፣ በዚህ ላይ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ተነግሯል፡፡ ይህ ሰላምና ፀጥታ ብቻ ሳይሆን ዳቦም ለቸገረው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ትርጉሙ ከፍ ያለ መሆኑን ነው በርካታ ተንታኞች እየተናገሩ የሚገኙት፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ተስፋዬ ይልማ (አምባሳደር)፣ ‹‹ሁለቱ አገሮች ዕጣ ፈንታቸው የተያያዘ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ላይ ማብራሪያ የሰጡት ተስፋዬ (አምባሳደር)፣ ‹‹በፊት ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ አሁን ደግሞ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በኢኮኖሚ እንዲጠናከር ከመግባባት ተደርሷል፡፡ ሁለቱ አገሮች ለጋራ ጥቅሞቻቸው ሲሉ መተጋገዝ አለባቸው፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት በንግድና ኢኮኖሚ የበለጠ ይጠናከር መባሉ ተገቢ መሆኑን በርካታ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ወደ 16 ሚሊዮን ሕዝብ ያላትና እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ 294 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሸቀጣ ሸቀጥ ከኢትዮጵያ በማስገባት ለአዲስ አበባ ጠንካራ የንግድ አጋር መሆኗን ካሳየችው ሶማሊያ ጋር፣ የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነትን ማጠናከር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ዕርምጃ መሆኑን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

ገና ተመርጠው ወደ ሥልጣን እንደመጡና ተቋርጦ የነበረውን የኬንያ ጫት ወደ ሶማሊያ ዳግም እንዲገባ በመፍቀድ እንደ ኬንያ ካሉ አገሮች ጋር የበለጠ ወዳጅነት የፈጠሩት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ፣ ከኢትዮጵያም ጋር የንግድ ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከርም ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ እንደገቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ሁለቱ አገሮች የጋራ ዕድሎቻቸውን የበለጠ ለመጠቀም መግባባታቸውን ተናግረውም ነበር፡፡

በግንቦት ወር የተመረጡትና በሰኔ ወር ሥልጣን የተረከቡት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ፣ ከሰሞኑ የጋራ ዕድል ያለን ብለው ያወደሷትን ኢትዮጵን ለመርገጥና ግንኙነት ለማጠናከር ይህን ሁሉ ጊዜ ለምን ዘገዩ? ለሚለው ጥያቄ መልስ አልተገኘም፡፡ ሰውየው ከቱርክ እስከ ካይሮ ባለፉት ወራት ሲሽከረከሩ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ምነው ዘገዩ የሚሉ ጠያቂዎች ግን፣ እሳቸው ወደ ኢትዮጵያ ያመጣቸው ጉዳይ ከንግድ ግንኙነት ማጠናከር በላይ ምክንያት ያለው መሆኑን ነው የሚገምቱት፡፡

መቀመጫውን ጅግጅጋ ያደረገ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የሚሠራ ዘጋቢ እንደሚናገረው ከሆነ፣ ፕሬዚዳንቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያ ጋርም ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት ማሳየታቸውን ይናገራል፡፡ በቅርቡ አልሸባብ በሁለቱ አገሮች አዋሳኝ ድንበሮች አካባቢ የፈጸመው ተደጋጋሚ ጥቃት እሳቸው ኢትዮጵያን በተመለከተ ያላቸውን አቋም እንዲለውጡ እንዳደረጋቸው ጋዜጠኛው ያስረዳል፡፡

‹‹ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፕሬዚዳንቱ ሲመጡ ከሶማሌ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሙስጠፋ ዑመር፣ ከአህመድ ሺዴና ከአደም ፋራህ ጋር በመሆን ያደረጉላቸው አቀባበል ለፕሬዚዳንቱ ልዩ መልዕክት ያለው ነው፤›› ሲል የሚናገረው ጋዜጠኛው፣ ፕሬዚዳንት ሐሰን ዞረው ዞረው ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ማዞራቸው የሚጠበቅ እንደነበር ያብራራል፡፡

የፕሬዚዳንቱን የኢትዮጵያ ቆይታ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሰደር)፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጉብኝት ብዙ ትርጓሜ ሲሰጠው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከመንግሥት ግንኙነት በላይ ነው፡፡ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በሁለት አገሮች የሚኖሩ አንድ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት እንዲፈጠር መስዋዕትነት ስትከፍል ቆይታለች፡፡ አሁን ደግሞ በንግድ የበለጠ ትስስር እንዲፈጠር መግባባት ላይ ተደርሷል፤›› ሲሉ ነበር መለስ (አምባሳደር) ስለዚሁ ጉብኝት ዋና ዓላማ ያብራሩት፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ‹‹አንድ ጣት ብቻውን ፊት አያጥብም፤›› በሚል ሶማሊያዊ ብሒል ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ፣ አገራቸው ለከበቧት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሁሉንም አጋርነትና ትብብር እንደምትፈልግ ተናግረው ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኢስታንቡል እስከ ናይሮቢ ያካለለ ጉብኝት ሲያደርጉ የከረሙት ፕሬዚዳንቱ፣ በስተመጨረሻ የአዲስ አበባን አጋርነት ፍለጋ መምጣታቸው ነው የተነገረው፡፡

ይህ የሶማሊያው መሪ ዕረፍት የለሽና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጥረት ስኬት ተደርጎ ቢታይም፣ በሌላ ጎኑ ግን ኢትዮጵያ በቀጣናው ጂኦ ፖለቲካ ላይ ያላትን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታም የሚናገር አጋጣሚ እንደሆነ ነው በርካቶች የሚናገሩት፡፡

ከሰሞኑ ከሶማሊያ መሪ በተጨማሪ ከ15 በላይ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማስከተል የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ታባን ጌንግ ጋይ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ጋር መገናኘታቸው የተነገረው ታባን ጌንግ፣ ቀጣናዊ ትስስሮሹን በኢኮኖሚ የበለጠ የሚያጠናክሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ስምምነቶችን ተፈራርመው መመለሳቸው ተነግሯል፡፡ ይህ የደቡብ ሱዳንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ስምምነት ደግሞ እንደ ጂቡቲ፣ ኬንያና ሱዳንን የመሳሰሉ አገሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ቀጣናዊ ቱሩፋት ያለው መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡   

ከሰሞኑ ከቀጣናው አገሮች ጋር ያደረገቻቸውን ግንኙነት ተከትሎ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትስስሮች ሁነኛ ማዕከል እየሆነች እንደመጣች የሚናገሩ በርክተዋል፡፡ ከጂቡቲ ተነስቶ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚዘረጋ የመንገድና የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሮጀክት ለመገንባት፣ ከቀጣናው አገሮች ጋር መግባባት ትልቅ ስኬት መሆኑን እንዲሁ ይናገራሉ፡፡ ከኬንያ ጋር የተወጠነው ‹‹የላሙ ላፕሴት›› ግዙፍ የሎጂስቲክስ ፕሮጀክት መተላለፊያ ኮሪደር መሆኗም ለዚህ ማጠናከሪያ ተደርጎ እየቀረበ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስሮሽ በሚፈጥሩ የጋራ በሆኑ የባቡር፣ የመንገድና የወደብ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለቀጣናው የኃይል አቅርቦት ዋና ምንጭ በመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑም ጎልቶ እየተነሳ ነው፡፡

ለቀጣናው አገሮች ዘላቂ የሆነ ታዳሽ ኃይል ከማቅረብም በተጨማሪ፣ የመጠጥ ውኃ በማቅረብ ጭምር ለቀጣናዊ ትስስሮሹ ጉልህ አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ እያደረገች መሆኑንም ብዙዎች በስኬት ያወሱታል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ቀጣናውን በማስተሳሰር ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት መፍጠር ከቻሉ፣ ሰላምም ሆነ ዳቦ ለቸገረው ክፍለ አኅጉር ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2019 የተጀመረውን የቀጣናው አገሮችን ‹‹Horn of Africa Initiative›› (የቀንድ አገሮች የኢኮኖሚ ትስስር) ፕሮጀክትን እንደ አንድ ማሳያ የሚያቀርቡት እነዚህ ወገኖች፣ የአካባቢው አገሮች ገና ያልተጠቀሙበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

በሆርን ኦፍ አፍሪካ ኢንሼቲቭ የኢኮኖሚ ትስስር ፕሮጀክት ሥር ሰፊ የመሠረተ ልማትና የንግድ አውታሮችን ለመገንባት ይፋ ያደረጉ ሰባት የቀንዱ አገሮች፣ ከለጋሾችና የልማት አጋሮች አበረታች ድጋፍ ማግኘታቸው ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኬንያ የታቀፉበት ይህ የሰባት አገሮች የኢኮኖሚ ትስስር ፕሮጀክት ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ሊደረግበት የታቀደ ግዙፍ ሥራ ነው፡፡

ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በውኃ፣ በመንገድ፣ በባቡር፣ በወደብና በንግድ መሠረተ ልማቶች ለቀጣናው አገሮች ዋና ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች ያካተተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአርብቶ አደር ልማት፣ በአንበጣ መከላከልና በጤና ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆን፣ ከቀጣናው አገሮች ጋር በአቅም ግንባታና በቴክኒክ የበለጠ እንድትተሳሰርም ይህ ፕሮጀክት በርካታ ሥራዎችን አካቶ መቅረቡ ይነገራል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ 532 ሚሊዮን ዶላር፣ የአውሮፓ ኅብረት 430 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም የዓለም ባንክ እስከ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ያደርጉበታል የተባለው ይህ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የቀጣናው አገሮች ከተጠቀሙበት በጋራ የማደጊያ ያልተነካ ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ማሳያ ተደርጎ የሚቀርብ ፕሮጀክት መሆኑ ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን መሰሉን ቀጣናዊ የጋራ ፕሮጀክትን ታሳቢ በማድረግ ብትሠራ በቀጣናዊ ትስስሮሽ ብዙ ልትጠቀም እንደምትችል የሚናገሩ በርቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ግዙፍ ቀጣናዊ ፕሮጀክቶችን አገሪቱ በማቀድ ችግር እንደሌለባቸው የሚጠቅሱ አንዳንድ ወገኖች፣ ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ በማድረግ በኩል አገሮች ሲፈተኑ መታየታቸውን ያወሳሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ የአዋጭነት ጥናቱ መገባደዱና በአሥር ዓመታት እንደሚተገበር ሲነገርለት የቆየው ከጂቡቲ በኢትዮጵያ እስከ ደቡብ ሱዳን የሚዘልቀው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታ እስካሁን አለመተግበሩን ለአብነት ያስረዳሉ፡፡

የአሜሪካው ብላክ ራይኖና የጃፓኑ ቶዮታ ያስጠኑት ይህ ቀጣናዊ ፕሮጀክት የቀጣናው አገሮችን ፕሮጀክቶች ዕውን የማድረግ ችግር ማሳያ ተደርጎም ይወሳል፡፡ ልክ እንዲሁ ቀጣናውን ያስተሳስራል ተብሎ የተወጠነውን የኬንያው ላሙ ላፕሴት የተባለ ግዙፍ የወደብና የሎጂስቲክስ ፕሮጀክት መዘግየትም፣ በቀጣናው አገሮች መካከል ለፕሮጀክቶች የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን አመላካች ተደርጎ ሲጠቀስ ይሰማል፡፡

ያም ቢሆን ግን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የሐሰን ሼክ መሐመድ ሰሞነኛ ጉብኝት ለቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ወይም ለሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ግንኙነት መጠናከር ባለው አስተዋጽኦ ብቻ መታየት የለበትም የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚሁ ግንኙነት ፋይዳ የዘገበው ዘ ኢስት አፍሪካን የዜና ምንጭ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናውም ሆነ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች በምታራምደው ፖለቲካ የሶማሊያን አቋም በትክክል ለመገንዘብ የፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባን መርገጥ ጠቃሚ መሆኑን አመልክቷል፡፡ የሶማሊያው መሪ ከግብፅ ጎን ተሠልፈው ኢትዮጵያን በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተነሳ ማውገዛቸው ሲነገር መቆየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ አሁን አዲስ አበባ መምጣታቸው ኢትዮጵያ የሶማሊያን አቋም እንደትገነዘብ የሚረዳ አጋጣሚ መሆኑን ገልጿል፡፡  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ባለሙያ ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር)፣  የሶማሊያ መሪ የኢትዮጵያ ጉብኝት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል የተደረገ ጉብኝት ተደርጎ ተብሎ ሊወሰድ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም አብይ (ዶ/ር)፣ ፎርማጆና ኢሳያስ ፈጥረውት የነበረውን ቀጣናውን የሚያረጋጋና የበለጠ የሚያስተሳስር ግንኙነት የእሳቸው መመረጥ የሚቀለብስ ሆኖ መታየቱን ያመለከቱት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ይህን ዕይታ ሊቀይር እንደሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጉብኝቱ ከሁሉ በላይ፣ ‹‹በሁለቱ አገሮች መካከል የግንኙነት መላላት ሁኔታ ተፈጥሯል ተብሎ የሚነገረውን ብዥታ፣ እንዲሁም ሰውየው እንደ ግብፅ ያሉ አገሮችን በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጥቅሞች በተፃራሪ የቆሙ ናቸው የሚለውን ጥርጣሬ የሚያጠራ ነው፤›› ሲሉ ነው የሰሞኑን ሁኔታ የገለጹት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -