Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለማድረግ መድፈርና ሌሎች የተስፋ ምንጮች

በንጉሥ ወዳጅነው

እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬ አገራችን መልሳ በጦርነትና በፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ ብትገባም፣ ትናንት በነበረችበት ቁመና ላይ አልነበረችም፡፡ በአንፃራዊ ዕድገትም ሆነ በልማት በተደማመረ ውጤት ከቀደሙት ዘመናት አንፃር ወደፊት ተራምዳለች፡፡ በዓለም አቀፉ ተፅዕኖም ሆነ በራሷ ልጆች ጥረት የተለወጠችባቸው ገጽታዎችም አሉ፡፡ አንገታችንን ቀና አድርገን የምንራመድባት፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ዙሪያ የማናፍርባት አገር ለመሆን ጠንክሮ መሥራትና ተደማምጦ መገኘት ከተቻለ ያለንበት ሁኔታም ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን አይችልም፡፡

ምክንያቱም ቢያንስ ከነበርንበት ፍፁማዊ ድህነት (Absolute Poverty) መውጣት ጀምረን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የአሁኑ ድህነታችንም ቢሆን አንፃራዊ (Relative Poverty) የሚባል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቢያንስ የፍትሐዊነቱ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ አድጓል፡፡ የእናቶችና የሕፃናት ሞት ቀንሷል፡፡ የዜጎች ዕድሜ ከነበርንበት ከፍ ብሏል፡፡ ዛሬ ከምንጊዜውም ይበልጥ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ችለዋል፡፡ መንገድ፣ ጤና ተቋም፣ ከፍተኛ ትምህርት… ተስፋፍቷል፡፡ እየተንገዳገድንም ቢሆን ቢያንስ እዚህ ላይ ደርሰናል፡፡

ይህ እውነት ቢሆንም ‹‹ችግሮች የሉብንም›› ማለት አይደለም፡፡ ብዙ መስተጓጎሎች አሉ፡፡ ሰዎች ተደማምጠውና ተረዳድተው የሚኖሩባት አገር ገና አልተፈጠረችም፡፡ ልትፈጠር ስትልም ወደኋላ መመለስ ሆኗል ጉዞው፡፡ የዴሞክራሲያዊነትና  የፍትሐዊነት እሳቤያችን አሁንም ግንጥል ነው፡፡ እኔ እኔ ማለት ተበራክቶ ይታያል… በከተሞች ከፍተኛ የኑሮ ውድነት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ ትራንስፖርት ጥበቃ ሠልፍ በዝቶ እየታየ ነው፡፡ የመብራትና የውኃ መቆራረጥ ችግር አለ፡፡ የተሠራው መንገድ እየተቦረቦረ ውኃ ሲቋጥር፣ በጥራት ማነስ የተሠራው መንገድ ሲፈርስ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በገጠርም ድህነትና ተረጅነት ገና እንደበረታ ነው፡፡

ሙስና፣ ብልሹ አሠራርና የመልካም አስተዳደር ችግራችን መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ የትምህርት ጥራት ላይ ያለን ቅሬታ ገና በወጉ አልተወገደም፡፡ የፖለቲካ ኢሊቱ በሕዝብ ስም እየነገደ አገር የሚያፈርስ ጦስ ሲያመጣ በጋራ አልታገልነውም፡፡ አሁንም ለችግሮች መፍቻ ጦርነትና ግጭትን (ኃይልን) የምናስቀድመው ወገኖች ትንሽ አይደለንም፡፡… የመጣንባቸውን መንገዶች ፈትሾ በመግባባት ወደ መጪው ጊዜ የሚወስዱን መንገዶችን ከመጥረግ ይልቅ በታሪክ መወዛገብና በቁርሾ መነታረክን ነው የምናስቀድመው፡፡

ሀብት፣ የሰው ኃይልና ጊዜን የሚበላው ጦርነት ውስጥ ዳግም ገባን እንጂ፣ አሁን ከደረስንበትና ወደፊት ልንደርስበት ከምንፈልገው ዕድገት አንፃር ሲታዩ ግን አሁንም  ችግሮቻችን ተስፋ አስቆራጭ አልነበሩም፡፡ የዕድገት ሒደትና የለውጥ መሻት በራሱ ጊዜ ይዞት የሚመጣው ችግር አለ፡፡ አሁን ያለው ዕድገትም ይሁን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ለውጥ ፍላጎት ብሔራዊ ቅርፅ ያለው ነው፡፡ ዕድል መስጠቱ ባይደብና ግለቱ ተጠናክሮ ቢቀጥል፣ በርካታ ባለምጡቁ አዕምሮ ዜጎችንና ታሪክ የሚቀይሩ ስብዕናዎች ብቅ ብቅ ማለታቸውም አይቀርም ነበር፡፡

ለሁሉም በዛሬው ጽሑፋችን ለማንሳት የወደድነው እንደ አገር ከገባንበት ቅርቃር እየወጣን፣ በግለሰብም ደረጃ ሆነ እንደ ሕዝብ ልናተኩርባቸው ስለሚገቡ መልካም ተሞክሮዎችና የሥነ ልቦና ውቅሮች ጥቂቱን ለመጥቀስ ነው፡፡ በተለይም የሰው ልጆች ወደ ሀብትና ወደ ደስተኝነት ያመሩ ዘንድ ስለሚመከሩት አምስት ቁልፍ ጉዳዮች ሰፋ አድርገን እንመለከታለን፡፡ እንደ አገርም ቢሆን ትናንትን ፈትሸን ነገን ለማማተር ይረዱናልና ታነቡት ዘንድ ወደናል፡፡

መድረስ የምትፈልግበት ቦታ ለመድረስ ማየት የምትፈልገውን ነገር ሆኖ ለማየት መስማት የምትፈልገውን ሁሉ ለመስማት ትችል ዘንድ ለዚህ ከሚያበቃህ መንገድ አንዱ ፍርኃትን በአግባቡ ማስተናገድ (Handling Frustration) መቻል ነው ይላሉ የሥነ ልቦና ምሁራን፡፡ እንግዲህ እኛም ከሁሉ ቀድመን ከችግራችን ለመውጣት፣ አገርን ለማስቀጠል፣ ማሻሻያዎች ለመጀመር፣ ዕርቅ ለመፈጸም ወይም ሌላ… ሥራ ለመሥራት ከፍርኃት የመውጣት አገራዊ ግዴታ እንዳለብን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

አንድ ነገር ለማድረግ ስትነሳ የመጀመርያ ዕርምጃህ አለመፍራት መሆን አለበት፡፡ ሳያስፈራና ሳያስጨንቅ የሚገኝ ሀብትና ደስታ የለም፡፡ ሳይፈራና ሳይጨነቅ አሁን ለደረሰበት ስኬት የደረሰ ሰው የለም፡፡ ፍርኃት አለ፡፡ ጭንቀት አለ፡፡ ቁም ነገሩ ፍርኃትን በአግባቡ የመያዝን ዘዴ ማወቅ ነው፡፡ የሚለው ዕሳቤ በአፅንኦት የሚነግረንም ፍርኃትና ይሉኝታ ምን ያህል ሰንክለው እንደሚያስሩን ነው፡፡

መቼም አንድ ድርጅት ቢሆንም የአገር ያህል አቅም የፈጠረን ኩባንያ በምሳሌነት መጥቀስ ስህተት አይመስለኝም፡፡ (Federal Express) ስለሚባል ድርጅት ሳንሰማ አንቀርም፡፡ ከዓለም ታላላቅ የፖስታ (የመልዕክት) አመላላሽ ኩባንያዎች አንዱ ነው፡፡ ይህን ድርጅት የመሠረተው ሰው ፍሬድ ስሚዝ ይባላል፡፡ ድርጅቱን ለመመሥረት ያለውን ትንሽ ገንዘብ በሙሉ ሥራ ላይ ሲያውል በጣም ፈርቶ ነበር፡፡ ቢከስር ሌላ ገንዘብ አልነበረውም፡፡ በመጀመርያው ዓመት 150 ፖስታዎችን (እሽጎችን) ለማድረስ አቅዶ ነበር፡፡ ማድረስ የቻለው ግን አሥራ ስድስት ፖስታዎችን ብቻ ነበር፡፡ ለዚያውም አምስቱ ፖስታዎች ለአንዱ የድርጅት ተቀጣሪ የተላኩ ነበሩ፡፡

ነገሮች ተባባሱበት የሠራተኛ ደመወዝ ለመክፈል እንኳ ተሳነው፡፡ በፍርኃትና በጭንቀት ተዋጠ፡፡ በእየ ቀኑ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን የመንቀሳቀሻ ገንዘብ ፍለጋ ሲያስብ ውሎ ሲያስብ ያድር ነበር፡፡ ፍሬድ ስሚዝ ፍርኃቱንና ጭንቀቱን በአግባቡ ይዞ በመንቀሳቀሱ ግን ዛሬ (Federal Express) ባለ ቢሊዮን ዶላር፣ ባለ ብዙ ሺሕ ሠራተኞችና ባለምጡቅ ቴክኖሎጂ የፖስታ ድርጅት ወይም ኩባንያ ለመሆን ችሏል፡፡ ለፍርኃት እጅ መስጠት ሳይሆን፣ መፍትሔው ፍርኃትን በአግባቡ ይዞ መንቀሳቀስ ነው፡፡

ሁለተኛው የሀብትና የደስታ ቁልፍ ተደጋጋሚ ተቃውሞ ማስተናገድን ማወቅ ነው፡፡ ላሰብከው ፕሮጀክት የብዙ ሰዎችን ድጋፍ ስትጠይቅ ‹‹እምቢ›› (No) ይሉሃል፡፡ ይህ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በዚህ አትደናገጥ፡፡ ይኼኛው እምቢ ሲልህ ወደሌላኛው ዘንድ ሂድ፡፡ እሱም እምቢ ካለህ ወደሌላኛው ሰው ዘንድ ቀጥል፡፡ ብዙ እምቢዎችን ለመሸከም የሚችል ትከሻ ይኑርህ፡፡ (በነገራችን ላይ በእኛም አገር ባለፉት አራት ዓመታት ሊታይ የሞከረውን ለውጥ የገጠመው ፈተና ይኸው ይመስለኛል፡፡)

አሁንም በጀመርነው የግል ኩባንያዎችና የግል ስብዕናዎች ለመቀጠል ግን እዚህ ላይ (Rambo) የሚባል ስም ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡ ሲልቨስተር ስታሎን የተባለ የሲኒማ ተዋናይ ነው፡፡ ራምቦ በመላው ዓለም ታዋቂ ሊሆን ችሎ የነበረው መዓት ጊዜ እምቢ (No) የሚል ምላሽ ካገኘ በኋላ እንደነበር ነው ጥናቶች የሚያስረዱት፡፡ መንገዱ ሁሉ ጨርቅ በጨርቅ ሆኖለት አይደለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው፡፡ ለፊልም ሥራ ቅጠሩኝ ሲል ‹‹እምቢ›› ሲሉት ያላንኳኳው በር የለም፡፡

ከሺሕ ጊዜ በላይ ‹‹እምቢ›› የሚል ምላሽ እየሰጡት ከአንዱ ወደ አንዱ እየሄደ ሲጠይቅ ከርሞ ከዕለታት አንድ ቀን በአንዱ ‹‹እሺ›› ተብሎ ተቀጠረ፡፡ (Rocky) የተባለውን ፊልም ሠርቶ ችሎታውን አሳየ፡፡ ከዚያ በኋላ ሲልቨስተር ስታሎንን የሚያቆመው ኃይል በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ጠፋ፡፡ በዝና ላይ ዝና በሀብት ላይ ሀብት እየጨመረ በመላው ዓለም ታዋቂ ሊሆን የቻለው ብዙ እምቢዎችን መሸከም በመቻሉ ነው፡፡ (ይህ አንድ ማሳያ ሆኖ ነው እጂ ሌሎች ሺሕ አብነቶችንም ብንጠቅስ ተቃውሞና ክልከላን ማሸነፍን ያህል ጉብዝና እንደሌለ እንገነዘባለን፡፡)

አንተስ ስንት ጊዜ ‹‹እምቢ›› ሲሉህ መሸከም ትችላለህ? በእርግጥ እምቢ ወይም አይሆንም ወይም አንፈልግም (No) እንደሚለው መልስ ራሥ የሚያዞር ቃል የለም፡፡ ይህን ለመሸከም የሚችል ትከሻ ግን ያስፈልግሃል፡፡ ሰው ያውም ብርቱ ሰው ለመሆን፡፡ ሦስተኛው የሀብትና የደስታ ቁልፍ የገንዘብ ጫና (Financial Pressure) የመቋቋም ዘዴን ማወቅ ነው፡፡ ገንዘብ በሰዎች ላይ ብዙ ዓይነት ጫናዎችን ይፈጥራል፡፡ ገንዘብ አይጠገብም… ገንዘብ ስስታም ያደርጋል… ገንዘብ ቅናትን፣ ማታለልን፣ ሲቃዡ ማደርን ሥጋትን፣ ጥርጣሬን፣ ብቸኝነትን፣ ሽሽትን… ወዘተ. ይፈጥራል፡፡ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ የገንዘብ ጫናን ለመቋቋም ገንዘብ እንዴት እንደሚገኝና አያያዙ እንዴት እንደሆነ ገንዘብን ሠርቶ ማግኘትና መቆጠብን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ገንዘብ ማጣትም ቢሆን የሚፈጥረው የራሱ የሆነ ጫና አለው፡፡ ብዙም ይኑርህ ጥቂት የገንዘብ ተፅዕኖንና የአያያዝ ዘዴን ካላወቅህበት ያጠፋሃል፡፡ የገንዘብ ተፅዕኖን በመቆጣጠር ዘዴዎችና በዚህ ረገድ ስለተሳካላቸው ሞዴል ሰዎች ጆኦርጅ ክላስን የተባሉ ምሁር ‹‹The Richest man In Babylon›› በተባለ መጽሐፋቸው የጻፉትን ማንበብ የነብስ ምግብ ነው፡፡

መጽሐፉ ከምታገኘው ገንዘብ ሁሉ ላይ አሥር ፐርሰንት ያህሉን ለተቸገሩ ሰዎች መስጠት ከገንዘብ ተፅዕኖ የሚያላቅቅ ድንቅ ዘዴ መሆኑን ያስተምራል፡፡ አናደርገውም እንጂ መስጠትን የመሰለ ፀጋን የማግኛ ዘዴ የለም ነው የሚለው፡፡ (በእውነቱ እንደ አገር ከገባንበት ቀውስ አንፃር፣ መስጠትና መርዳት ብሎም መተጋገዝን ማጠናከር ግድ ይለናል፡፡)

መስጠት እህል እንደመዝራት ነው፡፡ መስጠት ያስገኝልሃል እንጂ አያሳጣህም ስጥ ይሰጥህማል… እንዲል መጽሐፉ በየዕለቱ ካለህ ገንዘብ ላይ ጥቂቱን ስጥ አለመስጠት ሞት ነው፡፡ የምትሰጠው ሲጠይቁህ ብቻ ሳይሆን የቸገረውን ሰው ፈልገህ መስጠት አንተ ከምትሰጣቸው ሰዎች የተሻልክ መሆንህን ለራስህ ይነግርሃል፡፡ ሁልጊዜ ለመስጠት ትጋ፡፡ ልትረዳው የፈለከው ሰው ርዳታህን በማግኘቱ የሚሰማውን ደስታና ለአምላኩ የሚያቀርበውን ምሥጋና ከማየትና ከመስጠት የበለጠ ደስታ የትም አታገኝምና፡፡

በመሠረቱ የምትሰጠው ብዙ ሲኖርህ ብቻ አይደለም፡፡ ካለችህ ጥቂት ገንዘብም ውስጥ ቢሆን የተወሰነውን መስጠት የሚፈጥርልህን ደስታ ከየትም ልታገኘው አትችልም፡፡ የተቸገሩትን ዕርዳ እጅህን ዘርጋ እጅህ ሁል ጊዜ የታጠፈና የተቆለፈ ከሆነ፣ ሽባ እንጂ ጤነኛ እጅ አይሆንልህም፡፡ የማይሰጥ እጅ ምንም አይጠቅምህም፡፡ ሀብትና ደስታን የምትሻ ከሆነ የተቸገሩትን ለመርዳት ደፋር ሁን፡፡ ከምታገኘው ገንዘብ አሥር ከመቶውን ስጥ፡፡ ሌላ አሥር ከመቶውን ደግሞ ለዕዳዎችህ መሸፈኛ አውለው፡፡ ሌላኛው አሥር ከመቶ ለተቀማጭህ አውለው ወይም ለኢንቨስትመንት አድርገው፡፡ ለአንተ 70 ከመቶው በሆነው ገቢ ብቻ ብትኖር ይበቃሃል፡፡

አራተኛው የሀብትና የደስታ ቁልፍ ለምቾት ትኩረት አለመስጠት ነው፡፡ ብዙ ታታሪ የነበሩ ሰዎች ወይም አትሌቶች ጥቂት ውጤቶችን ከጨበጡ በኋላ ይቆማሉ፡፡ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ገና ብዙ ሊሠሩና ሊያገኙ ሲችሉ ለዓለማዊ ምቾት ቅድሚያን በመስጠታቸው ከዓላማቸው ይሰናከላሉ፡፡ ራሳቸውን በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ያነፃፅራሉ፡፡ በተለይ እኛን ለመሰለ አብዛኛው ደሃ ማኅበረሰብ ደግሞ ቸል ማለት፣ መሳነፍና መቆም አክሳሪና እጅግ አድካሚ ነው፡፡

በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ይህን ያህል አለኝ… ከእነ እከሌ እሻላለሁ፡፡ በማለት ይኩራራሉ፡፡ አንተ ግን አትፍራ አትኩራ፡፡ የአንተ ማነፃፀሪያ ራስህ ካስቀመጥከው ግብ ጋር እንጂ ከሌሎች ሰዎች ጋር አይደለም፡፡ ከአንተ ያነሱ ብዙ ሰዎች ያሉትን ያህል ከአንተ የበለጡ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን አትርሳ፡፡ የቡና ላይ ወሬን (Coffeepot Seminars) አስወግድ የሚለውን ምክር መዘንጋት አይገባም፡፡

ከአዲሱ ትውልድ አንፃርም ከማይሆኑ ሰዎች ጋር በጫት፣ በሻይና ቡና ሰበብ እየተገናኙ እያንዳንዳቸው ስላደረጉት ዓላማዊ ነገር፣ ስለወሲባዊ ሕይወታቸውና እገሌ ከእገሊት ጋር ስለመተኛቱ ወዘተ. የመሳሰሉት ቁምነገር የሌላቸው ወሬዎች ላይ መጠመድ ኪሳራው የበዛ ነው፡፡ እነዚህ ሳንካዎች ሰውን ከዓላማው ለማፈናቀል ከፍተኛ ሚና ስላላቸው፣ ከእነዚህ አጋጣሚዎች መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ከንቱ ነገር የሚያወሩ ሰዎች አያስፈልጉም፡፡ ከእነሱ ገጥሞ የእነሱን የማይረባ ዓለማዊ ድርጊት መስማት የራስህን ጥሩ ልምድ ለማካበትና ለማካፈል ዕድል አይሰጥህም፡፡

የመጨረሻውና አምስተኛው የሀብትና የደስታ ቁልፍ ሰዎች ካደረጉልህ የበለጠ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ከምትቀበለው የበለጠ መስጠትንም መልመድ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለሰው ስለሚሰጡት ነገር ሳይሆን ከሌላ ሰው ላይ ስለሚያገኙት ነገር ይጨነቃሉ፡፡ ለማግኘት ወይም ለመቀበል ብቻ እያንዳንዱን አጋጠሚ መጠቀም ይፈልጋሉ፡፡

መቀበል በራሱ ችግር ላይሆን ይችላል፡፡ መቀበል እንደውቅያኖስ ነው፡፡ ወደ እርሻ ቦታ ሄደህ አፈሩን እንዲህ ዓይነት እህል ወይም ምርት ስጠኝ ብትለው ምን የሚልህ ይመስልሃል? ‹‹ይቅርታ ጌታዬ ለዚህ ሠፈር አዲስ ነህ መሰለኝ፡፡… የጨዋታውን ሕግ አላወቅከውም… ትንሽ እንኳን ዘር ሳትሰጠኝ ምርት አምጣ ማለትህ ልክ አይደለም›› የሚልህ አይመስልህም፡፡

መጀመርያ ቆፍር… አለስልሰው… ዝራበት… አረሙን ንቀልለት… ተንከባከበው ከዚያ በኋላ ‹‹ስጠኝ›› ብትለው ካሰብከው በላይ ምርት ሊያስታቅፍህ ይችላል ‹‹ስጠኝ›› ከማለትህ በፊት ‹‹እንካ›› ማለትን ዕወቅ፡፡ አድርግልኝ ከማለትህ በፊት ላድርግልህ ማለትን አስቀድም፡፡ የኬኔዲ አባባል ትዝ ይበልህ፡፡ አገሬ ምን አደረገችልኝ ከማለትህ በፊት እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት በል፡፡ ለአገሩ… ለሕዝቡ… ለሌላው ችግረኛ ወንድሙ የማያደርግ ሰው የቱንም ያህል ገንዘብ ቢኖረው ደስተኛ ሊሆን አይችልም፡፡

ደስታ በምግብና በመጠጥ ማማረጥ በአልባሳትና በቁሳቁስ ማጌጥ ወዘተ. አይደለም፡፡ ዋናው ደስታ መንፈሳዊ ደስታ ነው፡፡ ከሚሰጡት ነገር ላይ ምን እንደሚያገኙ በቅድሚያ የሚያሰሉ… ወይም አንዳች ነገር በምላሹ በመጠበቅ የሚሰጡ አስሊዎች (Calculative Citizens) ውስጣዊ ደስታ የላቸውም፡፡ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ብቻ በማሰብ የሚሰጡ ብፁአን ናቸው፡፡ ለዚያውም ቢሆን የምትሰጠው እኮ የራስህ የሆነ ነገር የለህም፡፡ የምትሰጠው እግዜር ከሰጠህ ላይ ነው፡፡ አንተ አስተላላፊ ነህ እንጂ ሰጪው እግዚአብሔር ነው፡፡

በአጠቃላይ ይህቺ ታሪካዊና ቀደምት አገራችን እንዲህ ያሉ መልካም እሴቶችንና የሥነ ልቡና ውቅሮችን የያዙ ብዙ ግለሰቦችና ዜጎች ነው የሚያስፈልጋት፡፡ መሪዎቻችንና ፖለቲከኞቻችንም ቢሆኑ ከእንዲህ ያለው ስብስብ መሀል ሊገኙ እንዲችሉ ነው የምንመኘው፡፡ ለዚህም ፈጣሪ ይርዳን ብሎ መመኘት ይሻላል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles