Sunday, May 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ስለመጻሕፍትና ኅትመት ብላችሁ ተዘከሩን!

በደረጀ ገብሬ (ረ/ፕሮፌሰር)

‹‹አንባቢዎች መሪዎች ይሆናሉ›› የሚል ድንቅ መፈክር ትምህርት ነክ ውይይቶች በሚካሄድባቸው መድረኮችና በየትምህርት ቤቶች ግድግዳዎች ላይ ተለጥፎ ማንበብ የተለመደ ነው፡፡ ስለመጻሕፍት ጉዳይ የሚነጋገሩ ወገኖች ስለማንበብ ትሩፋትና ተግዳሮት ሳያነሱ አያልፉም፡፡ ስለ አዕምሮ ልማትና ዕድገት ጉዳያቸው የሆኑ አካላት ስለመጻሕፍ አስፈላጊነት፣ ኅትመትና ሥርጭት ሳያወሱ አይተውትም፡፡ ከልቡናቸው አፍልቀው፣ ከአዕምሮአቸው አመንጭተውና አስልተው ሐሳባቸውን ለወገናቸውና ለትውልድ ለማካፈል የሚያስቡ ቸር ደራስያን ዋነኛ መነጋገሪያ ርዕሳቸው መጻሕፍትና ኅትመት መሆናቸው እውነት ነው፡፡

አዎ! መጻሕፍትና ኅትመት!

መጻሕፍትን ስናስብ ኅትመት፣ ኅትመት ሲታሰብ ወረቀትና ቀለም የሚታለፍ አይደለም፡፡ ከማንኛውም ዕቃ ውድነት በላይ እየሆነ መሄዱ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ፣ ነገን አጨላሚ መሆኑ ሲታሰብ ሰቅጣጭ ነው፡፡ በሌሎቹ ሸቀጣሸቀጦች ላይ እንደሚታየው የዋጋ ንረት ሁሉ የውጭ ምንዛሪ ሰበብ ሆኖ፣ ተንኮልና ስግብግብነትም ተደምረውበት ዛሬ ያለ የወረቀት ዋጋ ነገ ሢሶ ወይ እኩል በኩል ተጨምሮበት ይገኛል፡፡ ስለዚህም የተዘጋጀ መጽሐፍ ረቂቅ ያለው የኅትመት ብርሃን ለማግኘት ዙሪያው ገደል ሆኖበታል፡፡ በማሳተምም ሆነ በማሠራጨት ላይ የሚሳተፉ ወገኖች የዕለት ተዕለት እሮሮ ሆኖ ይታያል፡፡

በአጠቃላይ በወረቀት ተያያዥ የኅትመት ቁሳቁሶች ላይ ጉዳዬ የሚል ወሳኝ ባለሥልጣን የጠፋ ይመስላል፡፡ ስለዘይት፣ ስኳርና ጨርቃ ጨርቅ፣ ስለልዩ ልዩ የፋብሪካ መለዋወጫዎች፣ ስለመድኃኒት፣ ስለመኪና ውድነት የሚነገረውን ያህል ለትውልድ ግንባታ መሠረት የሆኑ የመማሪያም ሆኑ አጋዥ መጻሕፍት ታትመው እንዲቀርቡ ዋና ጉዳይ በሆነው ወረቀትና ተጓዳኝ ቁሳቁሶች ዕጦትና ውድነት ላይ ሲነገር ሰምቼ አላውቅም፡፡

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ አንድ ጥሩ ዜና ሰምቼ ነበር- ለመኪና ፈላጊዎች ተስፋ የሚሰጥ፡፡ ዜናውም፣ በዕለቱ እንዳዳመጥሁት፣ (በኤሌክትሪክ ስለሚንቀሳቀስ መኪና ነው) የመኪናው ሙሉ ዕቃ ሳይገጣጠም ወደ አገር ውስጥ ከገባና እዚሁ ከተገጣጠመ ከቀረጥ ነፃ፣ በከፊል ተገጣጥሞ ከመጣ አምስት በመቶ፣ ሙሉ በሙሉ ተገጣጥሞ ከመጣ ደግሞ 15 በመቶ ቀረጥ ይከፈልበታል የሚል ነው፡፡

እዚህ ላይ ይህን የኤሌክትሪክ መኪና ለማስመጣት ፍላጎቱ ያላቸውንና በዕድሉ የሚጠቀሙትን በንፁህ ልቦና ይሁንላችሁ እላለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ከውጪ ለሚመጡ ዕቃዎች ቀረጥ የመጣልም ሆነ የማንሳት ወይም የማስተካከል ሥልጣን ያለው ኢትዮጵያዊ ድርጅት ለመኪና አስገቢዎች የሰጠውን ይህን ዕድል ለወረቀትና ለመሳሰሉት የኅትመት ቁሳቁሶች አስመጪዎችስ ቢሰጥልን የዛሬዎቹን ብቻ ሳይሆን ተከታታይ ትውልዶችን ጭምር ከአዕምሮ ዝግመትም ሆነ ምክነት እንዳዳነ እቆጥረዋለሁ፡፡ ይህን በማድረጉም በየገጠሩ፣ በየከተማው፣ በሁሉም የኑሮ አካባቢ ለሚኖሩ ወገኖች የአዕምሮ ልማት የሚያግዝ መሠረታዊ አስቤዛ በየትምህርት ቤቱ እንዲደርስ አደረገ፣ ትውልድንም ታደገ፣ ‹‹አንባቢ መሪዎችንም›› አፈራ ማለት እንድንችል መልካም ፈቃዱ እንዲሆን ተማፅኖ አቀርባለሁ፡፡

የወረቀትና ሌሎች የኅትመት ቁሳቁሶች ጉዳይ ከመጻሕፍ ኅትመት ጋር ብቻ አይደለም የሚያያዘው- ከደብተር፣ ከእርሳስና እስክሪብቶም ጋር ቁርኝቱ ጥብቅ ነው ከሦስት ዓመት በፊት 12 ብር ይገዛ የነበረ ባለ50 ቅጠል ደብተር ዛሬ 80 ብር ሆኖ ማየት ወላጅ ሆኖ ችግሩን ለሚጋፈጥ ደሃ አሰቃቂ ነው፡፡ ባንድ በኩል ከትምህርት ቤት የሚቀር ሕፃን እንዳይኖር እንላለን፣ ሕፃኑ ወደ ትምህርት ቤት ሲገባ ደግሞ የሚያነበውና የሚጽፍበት ነገር ችግር ሆነ፡፡ ስለዚህም እባካችሁ የቀረጥን ጉዳይ የምትወስኑ ባለሥልጣኖቻችን እንደ መኪናው ሁሉ ለትምህርትና ለዕውቀት፣ ለአዕምሮ ልማትና ለሰብዕና ግንባታ አፋጣኝ መፍትሔ ፈልጉ! ፈጣሪ ቀና ቀናውን ያስመልክታችሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡    

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles