Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውዳሴ ከንቱ!

ሰላም! ሰላም! ለመሆኑ እንዴት ሰነበታችሁልኝ? ሥራስ እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ሥራውማ እንግዲህ ከውጭ ምንዛሪ ጋር አብሮ ተሰደደ አትሉኝም። የዛሬን አያድርገውና ከዶላር ይልቅ ዩሮ ትከሻው ደንደን ያለ ነበር። ‹‹አሁንስ? ዛሬስ ምን ሆነ?›› ብላችሁ ብትጠይቁ መልሱ ‹‹ቦታ ተለዋውጡ…›› ተብሎ አይቆምም። አይ ለውጥ፣ ስንቱን ሽሮ ስንቱን ሾመው? አንዴ እባካችሁን ተባብረን እንሳቅ እንዳልል ምንም የሚያስቅ ነገር የለም፡፡ ‹‹ምናለበት ተባብረን መሥራት ቢያቅተን ተባብረን ብንስቅ?›› ይላሉ የአራዳ ልጆች ድሮ፡፡ ‘ሆድ ይፍጀው’ አለ የአገሬ ሰው። የአገሬ ሰው ያላለው፣ ‘አለ የአገሬ ሰው’ የሚለውን ብቻ ነው፡፡ ብቻ ስለዚሁ ስለቦታ መለዋወጥና አሠላለፍ ሳስብ ከፖለቲከኞቻችን ይልቅ ጭንቅ እያለኝ የመጣው የእኛ አጉል በማያገባን ጉዳይ ማገዶ መፍጀታችን ነው። ፖለቲከኞቻችንማ ቦታ ተለዋወጡ ወይም ተጠጋጉ ቢባል ለእኛ ምን ይሠራልናል ብላችሁ ነው? በበኩሌ ጥቅሙ እስካሁን አልታየኝም። ‹‹እነሱም ቢሆኑ ከመጠጋጋቱ ይልቅ መገፋፋቱ ላይ የበረቱ ይመስላሉ…›› ያለኝ ማን ነበር? ማን ምን የማይለኝ አለ መሰላችሁ። ይኼ መጠጋጋት ግን ከታክሲና ከፖለቲካ ወጣ ሲል አይደብርም? በኋላማ የደላላ ጭንቅላት ስለያዝኩ ይሆን ይኼ የመጠጋጋትና የመገፋፋት ፎርሙላ ያልጣመኝ አልኩና ራሴን ጠየቅኩት። መልስ ግን የለም!

እከሌ እንዳለው የሚባልበት ዘመን ስለሆነ አስተሳሰቤን ለማስመርመር ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ዘንድ ሄድኩ። በሌላ አባባል ማኅተም ለማስደረግ ማለት ይቻላል። ጣል ማድረግ ከተፈቀደልኝ ምንም ነገር አብሰልስላችሁ ዲግሪ አልያም ዲፕሎም ከሌላችሁ ልክ ነህ የሚላችሁ የተማረ ሰው ግድ ይላችኋል። ምንም እንኳን የአየር በአየር ምሁራን ቢበዙም። የባሻዬን ልጅ እንዳገኘሁት ጥያቄውን ሳቀርብለት፣ ‹‹አንበርብር ምናለበት ባታስጨንቀኝ? ሲጀመር ቃሉ ራሱ እንደሚነግርህ ቦታ መለዋወጥ ማለት ግንዱ ሳይገነደስ ቅርንጫፎቹ ብቻ ሲደርቁ በአዲስ ይቀየራሉ እንደ ማለት ነው። አንድ ዛፍ ብቻ ያለበትን ምድረ በዳ ጫካ ብለህ ጥራው ነው ነገሩ። እኛ ግን ሲለዋወጡ ብቻ ሳይሆን ቦታ ቦታቸውንም ሲይዙ ሰላም ቢሆኑ ነው ደስ ሊለን የሚገባው…›› ሲለኝ ቅኔው ከብዶኝ ፊቴን ክስክስ አድርጌ አየሁት። ‘በገዛ ቋንቋችን ባይተዋር አደረጉን’ ያሉት ነገር አሁን መጣና አረፈው፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!

ነገርና ቋንቋ ተደበላልቆብኝ ሳለሁ የእጅ ስልኬ ድንገት ጮኸች። ድንገት ልበል እንጂ እኔም በጉጉት የስልኬን ጩኸት እየጠበቅኩ ነበር። ‹‹እኔስ አንዳንዴ የዘመኑን ሥራ ጉዳይ ሳስብ ከእንጀራ ገመዳችን ይልቅ የሚያሳስበኝ፣ የዘንድሮ ሰው ዓመል መክፋቱ ነው፡፡ ከመፋቀሩ ፀበኛነቱ፣ ከመተጋገዝ የጎሪጥ መተያየቱ እየባሰበት በመጣ ዘመን ለሥራ መገናኘቱ ምን ይሠራል ያሰኛል…›› የምትለው ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ናት። ይህን ትበል እንጂ ስልኬ ተደውሎ ተጠርቼ መሥራት እንዳልቻልኩ ስታይ፣ ‹‹አሁን ገና በዓይኔ መጣ…›› ትላለች ማንን እንደሆነ ሳትለይ፡፡ ደግነቱ የሚሰማት የለም እንጂ። ‹‹የዘንድሮ ወሬኛ እንኳን ምስኪኗን የእኔዋን ውዷን ማንጠግቦሽን ድፍኑን የኢትዮጵያን ሕዝብ መቼ ይሰማል?›› ስል የሰማኝ አንድ ደላላ ወዳጄ፣ ‹‹ልስማስ ቢል ምላሱ እየቀደመ እንዴት ይሰማል?›› ብሎ ምድረ ወሬኛን ያማልኛል። የወሬኞችን ነገር እዚህ ላይ ብንተወው ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም ብለነው ብለነው ስለማንጨርስ እየቆጠብን ብንጫወተው እንደ ገብስ ቆሎ ለጨዋታችን ለዛ ስለሚሰጥልን ነው። ‹‹ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር፣ እንደ አዲስ አድርገው ያወሩልን ጀመር›› ተብሎ የለ? ኑሯችንንማ እንኳን ለዛ ሊሰጥ የነበረውንም አጥፍቶ አለዝዞታል። ከንቱ ጊዜ!

አንዱ መንገደኛ ያለውን ነግሬያችኋለሁ? ሰሞኑን የአንዳንዶቻችን ሲም ካርድ የአየር ሰዓት ከሞላ ሰነበተ ተብሎ ከመሬት ተነስቶ እንደ ፋሲካ ዶሮ ክልትው ሲል አይደል የሰነበተው? አዎ! እሱም የዚህ ገፈት ቀማሽ ነው መሰለኝ። እንዲያውም በኋላ ሰዎች አረጋግተውት ሲናገር እንደሰማሁት ከሆነ ፍቅረኛውን ‘አይ ላቭ ዩ’ ሊላት ሲል ነው ሲም ካርዱ ከኔትወርክ ዓለም የተሰናበተው። መቼም ጉድ ሳይሰማ ምን መስከረም ብቻ? ጉድ ሳንሰማ ነገስ መቼ ይነጋል? ፍቅረኛውም ‘አይ ላቭ ዩ’ ሲላት ካልሰማች ለሁለት ሳምንት የማኩረፍ የማይቀለበስ አቋም እንዳላት በሐዘን ነገረን። ‹‹እሺ ይኼ ምን ይባላል?›› ይላል እየቆየ። አንዱ ይህንን ሲሰማ የቆየ እንደ እኔው አልፎ ሂያጅ፣ ‹‹አይዞህ አንዳንዴ እኮ መፆም ጥሩ ነው። ሁሌም ሥጋ ጥሩ አይደለም…›› ቢለው እዚያ የተሰበሰብነው እንደ ዕብድ አየነው፡፡ ‹‹ዘንድሮ ከሁሉም ጋር ያላበደ ብቻውን ለሰባት ዓመት ያብዳል…›› ይባል ነበር ድሮ፡፡ ድሮ ቀረ ማለትም ሊከብድ ነው እንዴ!

እና እንዳልኳችሁ ስልኬ ሲጠራ ፊቴ በፈገግታ አብርቶ ለማንሳት ሳልቸኩል ረጋ ብዬ ሳስተውለው ቆየሁ። እንቁልልጭ ለማለት ጭምር እየቃጣኝ። በኋላ ግን በራሴ ላይ እንደ ሊደርስ የሚችለውን እውክታ ሳስብ ቶሎ አነሳሁት። አንድ በጥሩ ይዞታ ላይ ያለ ቅጥቅጥ እንዳሻሽጥ ነበር የተነገረኝ። ስከንፍ ባለቤቱን በአካል ሄጄ ተዋወቅኩና ገዥ ማፈላለጌን ቀጠልኩ። በዚህ መሀል አንድ የሙያ አጋሬ አገኘኝ። ‹‹እህ? ዛሬ ምን ይሆን የተገኘው?›› ብሎ በሰው መሀል ድምፁን ከፍ አድርጎ ጠየቀኝ። የምሯሯጥበትን ሥራ ማለቱ ነው። ‹‹ቅጥቅጥ…›› ብዬ ሳልጨርስ ክትክት ብሎ ሳቀብኝና፣ ‹‹አይ አንበርብር! ያላለልህ እኮ ነህ። ጓደኞችህ ተመችቷቸው ‘መርሰዲስ’ና ‘ቪኤይት’ ይነዳሉ አንተ እስካሁን እንደ ቆራሌው አሮጌን ከአሮጌ ታገናኛለህ…›› ብሎ አይሳለቅብኝ መሰላችሁ? ደግሞ በአካባቢያችን የነበሩ ሁሉ መስማታቸው እኮ ነው የባሰው። ንድድ ብሎኝ እኔም እንዲህ አልኩት፡፡ ‹‹ወንድሜ ይኼንንም ሲልልህ ነው። እነማን በየት ሄደው ምን ሠርተው የት እንደ ደረሱ የማናውቅ መሰለህ? ንቀን ብንተወው እኛው ተንቀን አረፍነው አይደል…›› ስል አንዳንድ አዛውንት ደላሎች ሰምተውኝ፣ ‹‹ኧረ ንገረው ይህንን አነካኪ…›› እያሉ ያጋግሉኝ ጀመር። የጋጋሪ ቆስቋሹንና በምላሱ የሚያድረውን እንዲህ ነግረነው ቢሰማን ጥሩ ነበር። አሁንማ የባሰው በቁም ከሚዘርፈንና ከሚቀጥፈን ይልቅ ‘ኮሜንታተሩ’ ሆኗል እኮ፡፡ ያውም እንደ ቁራ እየጮኸ!

ጨዋታን ጨዋታ እያስታጠቀውም አይደል? ታዲያ የሚያስታጥቀው ጠመንጃ ስላልሆነ አይዟችሁ አትደንግጡ። ለነገሩ ብትደነግጡም አልፈርድባችሁም። ‘እንዴት?’ አትሉኝም ታዲያ? የከተማ ታጣቂው በዝቷላ፡፡ እንደ ነገርኳችሁ ቅጥቅጡን ለማሻሻጥ ወዲያ ወዲህ ስል ምሁሩን የባሻዬ ልጅ እግር ጥሎት አገኘሁት። ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› እየተባባልን ሳለን ከበስተጀርባችን አምባጓሮ ተፈጥሮ ገላጋዩና ታዛቢው ይግተለተላል። የመገላገላቸውን ቁርጥ ያወቁት ፀበኞች ማዶ ለማዶ ቆመው ‘እገልሃለሁ… እገልሃለሁ…’ ይባባላሉ። እኛም እንደ ቀልድ እየሰማናቸው ለአፍ ልማድ ለፀብ ሞገስ እንዲያ የሚባባሉ ስለመሰለን ነገሩን አላካበድነውም (አቦ አታካብዱ በሚባልበት ዘመን ሁሉ እየከበደን ተቸገርን እንጂ)፡፡ ኋላማ አንዱ እንደ ጀምስ ቦንድ መሳይ በብርሃን ፍጥነት ሽጉጡን አወጣና ‘ዶንት ሙቭ’ ቢል ሰማይ ምድሩ ድብልቅልቅ፣ አዳሜ ሁሉን ነገር ትቶ ሩጫ በሩጫ። ‹‹ወይ ዘመን፣ አንድ እንኳ ዘራፍ የሚል ይጥፋ?›› ስል የሰማኝ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ከራሱ ዘራፍ ከሚለው ቃል ውጪ ዘራፍ ባይ ደመ መራራ በእነ አባዬ ጊዜ ቀርቷል…›› ብሎ መለሰልኝ። ጉድ ነው አትሉም፡፡ በነገራችን ላይ ጥያቄ ባቀርብ፣ ‹‹ለስንቱ ብለን እንችለዋለን? ብል መልሱ፣ ‹‹ብናውቀው ምን አስደበቀን?›› ነው አይደል? በኋላ ነገሩን ፖሊሶች መጥተው እንደ ምንም ሲያረጋጉት የባሻዬ ልጅ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹እኔምለው አንበርብር እነዚህ ሰዎች ጦር ሜዳ ከርመው ነው እንዴ የተመለሱት? ታጣቂው በዛብኝ እኮ…›› ሲለኝ፣ እኔም ነገርን በነገር አውቅበት የለ? ‹‹ወንድሜ ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ቢሆንም እዚህ አገር መልስ የሌለው ጥያቄ መጠየቅ ብታቆምስ?›› አልኩታ። እንዲህ ነው እንጂ አትሉኝም? ለማንኛውም እግረ መንገዴን አንድ ሁለት ነገር ጣል ላድርግላችሁና ቅጥቅጡን ልሽጠው። አንደኛ ከአልፎ ሂያጅ መንገደኛ ጋር አፍላፊ ማብዛት ቀንሱ። ሁለተኛ አንደኛ ብዬ የተናገርኩትን ደጋግማችሁን አንብቡ። ‘እስኪ ፈገግ’ ይል ነበር ፎቶ አንሺ ቢኖር ኖሮ!

ከፀቡ ግርግር ወዲያው ወደ ራሴ ግርግር ተመለስኩና ገዥ ማሰሴን ቀጠልኩ። ብዙም አልባከንኩ ደግነቱ አንድ ቀና ሰው (መሳይ ልበል ይቅርታ ‘ሰውን ማመን ቀብሮ ነው ያውም የ21ኛ ክፍለ ዘመንን’ ሲባል አልሰማችሁም? ማንበብ ትታችኋላ) አግኝቼ በጥሩ ኮሚሽን ልፋቴን ደመደምኩ። ደላላና ደራሲ ዕረፍት የላቸውም ሆነና (ለራስ ሲቆርሱ) ደግሞ ሌላ ሥራ ማባረሬን ተያያዝኩት። በተያያዘ ወሬ እዚሁ ላይ ሁሌ የሚከነክነኝን ነገር እንዳነሳ ይፈቀድልኝ። ከተፈቀደልኝ ደላላ የሚኖረው ሻጭና ገዥ፣ አከራይና ተከራይ፣ ወዘተ ሲኖሩ ነው። ደራሲም ሊኖር የሚችለው ጥሩ አንባቢና ሂስ የሚያውቅ ኅብረተሰብ ውስጥ ነው ብዬ አምናለሁ። በአገራችን አያያዝ ከልቤ ከማዝንላቸው ለፍቶ አዳሪዎች (ያውም ከማንም በላይ) መሀል ደራሲዎች ዋነኞቹ ናቸው። የዘመናችን የአቋራጭ ዕውቀት ፍለጋ ፍልስፍና ከባህል ዕድገት ይልቅ የሕንፃና የመንገድ ግንባታ ዕድገት ላይ ብቻ ማተኮሩ በእጅጉ እየጎዳን ነው እላለሁ። በዚህች የደላላ ዕውቀቴ ማለት ነው፡፡ እናም ይገርማችኋል ከንፈር ከመምጠጥ የበኩሌን ለመወጣት በማለት መጽሐፍ መደርደሪያ ገዛሁ፡፡ ምንም እንኳ የአንድ መጽሐፍ ዋጋ አቅሜን ቢፈታተነውም ስንዴውን ከገለባው እየለየሁ ማንበብ ጀምሬያለሁ። ደግሞስ እኛን ለመሰለ ወሬኛ ከንባብ የተሻለ ምን አጋዥ መሣሪያ አለ ትላላችሁ? ቢያንስ እያወቅን ማውራትም ያባት ነው እኮ። እኔ ልሙት ‘ከበጣም መጥፎ መጥፎ ይሻላል’ እንዳሉት አበው ማለት ነው፡፡ አንዳንዴም ቢሆን እናስታውሳቸው እንጂ! 

ከመሰነባበቴ በፊት ስለምሄድበት ሥፍራ ላጫውታችሁማ። ከተማችንን ወፍጮ ቤት እያስመሰለ ያስቸገረውን አቧራ ለማራገፍ ወደቤቴ ጎራ ስል ማንጠግቦሽ ተክዛ አገኘኋት። ምን እንደሆነች ስጠይቃት አንድ የቅርባችንን ሰው ስም ጠርታ፣ ‹‹ታመመ እኮ…›› አለችኝ። እኔ ደግሞ ‹‹አረፈ›› የምትለኝ መስሎኝ ደንግጬ አጠገቤ የነበረ ወንበር ላይ አረፍ አልኩ። ‹‹ምን?›› አልኳት ደግሜ። ‹‹ታመመ…›› አለችኝ እሷም ደግማ። ‹‹እና ተነሺ ሄደን እንጠይቀው…›› ስላት፣ ‹‹የለም አንጠይቀውም…›› አለችኝ። ‹‹ለምን?›› ከማለቴ፣ ‹‹ሕመሙ የሚያስጠይቅ አይደለም…›› ብላኝ እንባዋ ዱብ ዱብ ይል ጀመር። እንዲያ ስትለኝ በእነ ማንጠግቦሽ ቋንቋ ‘ቫይረሱ’ መስሎኝ ሌላ ነገር ስቀባጥር ቆየሁ። ኋላ አቋረጠችኝና፣ ‹‹ኧረግ? ኧረ እሱ አይደለም ካንሰር ነው ነው የሚሉት። ለዚህ ብዬ ነው አንጠይቀውም ያልኩህ። መገላገሉ አይቀርም ያኔ መሸኘት ነው…›› ብላኝ አሁንም ዕንባዋ ዱብ ዱብ ማለት ጀመረ። ስለሰማሁት ነገር አዛውንቱን ባሻዬን አግኝቼ ብነግራቸው፣ ‹‹ይገርማል፣ ይኼ ካንሰር ብሎ ብሎ እኛ ዘንድ መጣ? ለነገሩ መገኛው የት ሆነና…›› ሲሉኝ፣ ‹‹ማለት?›› አልኳቸው ተጨማሪ ማብራሪያ ፈልጌ። እሳቸው ግን የዕድር ስብሰባ ስለነበረባቸው ቸኩለው፣ ‹‹አንበርብር፣ በግለሰቦች ሲመጣ እንበረግጋለን እንጂ አገራችን በስንት ዓይነት ካንሰር እንደተያዘች አጣኸው? ከፖለቲካችን እስከ ኢኮኖሚያችን ከማኅበራዊ ሕይወታችን እስከ የግል ጓዳችን ስንት ዓይነት ‘ካንሰር’ እንዳለ አጣኸው? ይኼው የውጭ ምንዛሪውንም ያዘው መሰለኝ….›› ሲሉኝ መዓት እንደ ወረደበት ዝም ብዬ እሰማ ነበር። እና አሁን የምሄደው ማንጠግቦሽ ካልሞተ አንጠይቀውም ወዳለችኝ ሰውዬ ቤት ነው። ‘ወይ ካንሰር?’ ስንቱን ፈጀው? አገርንም ጭምር!

ሕመምተኛውን ጠይቀን በሐዘን ድባብ ውስጥ እንዳለሁ ስልኬ ጮኸ፡፡ ‹‹ሃሎ?›› ከማለቴ፣ ‹‹አንበርብር ቅጥቅጥ ገዥ ነኝ፡፡ በቶሎ ሻጭ ፈልገህ አገናኘኝ…›› አለኝ አንድ ድምፅ፡፡ ቀጠሮ ተሰጣጥተን ስልኬን ዘጋሁት፡፡ በታማሚው ሰው ሁኔታ የደበዘዘው ፊቴ ሲፈካ ማንጠግቦች ታዝባኝ፣ ‹‹ገንዘብ ከአምላክ እኩል የሚታይበት ዘመን…›› እያለች ስትገላምጠኝ ደነገጥኩ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አንዴ፣ ‹‹ሥልጣንን ለገንዘብ ማካበቻ፣ ሕዝባዊ አደራን ለግል ጥቅም ማግበስበሻ ያደረጉ ህሊና ቢሶች የበዙበት ዘመን ውስጥ ነው ያለነው…›› እያለ ሲብከነከን የነበረው ትዝ አለኝ፡፡ ምንም እንኳ ለፍቶ አዳሪ ምስኪን ብሆንም ለገንዘብ የማልሰግድ ሐሞተ ኮስታራ መሆኔን አውቀዋለሁ፡፡ ጉራ አበዛህ አትበሉኝና ለገንዘብ የሚሰግዱ ምስኪኖች ያሳዝኑኛል፡፡ የማንጠግቦች መከፋት የታየው ፊቴ ፈካ በማለቱ ቢሆንም፣ እኔ ወንድማችሁ አንበርብር ምንተስኖት ለገንዘብ አልሰግድም፡፡ ሁሌም የምሟገተው ከህሊናዬ ጋር በመሆኑ በራሴ እተማመናለሁ፡፡ ለገንዘብ ሲሉ ህሊናቸውን ከሚሸጡ ከንቱዎች ይልቅ ኩሩዎች ይመቹኛል፡፡ ከከንቱዎች ይልቅ ኩሩዎች የልጆቻችን አርዓያዎች ናቸው፡፡ ኩሩዎች ሲወደሱ በውዳሴ ከንቱ የሚመፃደቁ ይወገዙ! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት