Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኢሬቻ/ኢሬሳ - የምስጋና ክብረ በዓል

ኢሬቻ/ኢሬሳ – የምስጋና ክብረ በዓል

ቀን:

ክረምቱ አብቅቶ የመፀው ወቅት፣ በአፋን ኦሮሞ የቢራ (ራ ጠብቆ ይነበባል) ወቅት የሚገባበትን ተከትሎ በየዓመቱ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ትናንት ቅዳሜ  መስከረም  21 ቀን  2015 ዓ.ም.  በ‹‹ሆራ ፊንፊኔ›› የተከበረ ሲሆን፣ በማግሥቱ ዛሬ  እሑድ መስከረም 22 ቀን  በቢሾፍቱ ሆራ  አርሰዲ  እየተከበረ ነው፡፡

የኢሬቻ ክብረ በዓል ኢሬቻ ቢራ (መልካ) በሐይቆች ወይም በወንዞች ዳር የሚከበር ነው፡፡ አበው እንደሚተርኩት፣ የባህል ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ አደይ አበባ፣ ለምለም ሳርና ዘንባባ ተይዞ የሚከበር ሲሆን የመፀው ወቅት መለያው ነው፡፡ ይኼም ከከባዱ የክረምት ወራት በሰላም ያሻገራቸውን ዘመድ አዝማድ መገናኘት በመቻላቸው፣ ክረምት የዘሩት የእህል ቡቃያ በማየታቸው ፈጣሪያቸውን ‹‹ዋቃ››ን ያመሰግናሉ፡፡ ከዚያም መጪው የበጋ ወራት የሰላምና የጤና እንዲሆንላቸውና የበቀለው ቡቃያ ፍሬ እንዲያፈራ ይለምኑበታል፡፡

ኢሬቻ/ኢሬሳ - የምስጋና ክብረ በዓል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢሬቻ በሌላ አካባቢ ኢሬሳ በመባል ይታወቃል፡፡  የባህልና ትውፊት ባለሙያውና በተለይ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ላይ ያጠኑትና ለኅትመትም ያበቁት አፈንዲ ሙተቂ ስለ ስያሜው ሲገልጹ፣ ባደጉበት ሐረርጌ አካባቢ በሚነገረው ትውፊት በዓሉ ኢሬሳ እየተባለ ይጠራል ብለዋል፡፡

‹‹ከቱለማ በስተቀር ሁሉም ኦሮሞዎች በዓሉን ‹ኢሬሳ› እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ ቱለማ ግን ‹ኢሬቻ› ነው የሚለው፡፡ ይህ ልዩነት ግን ሌላ ምስጢር የለውም፡፡ በሌሎች ዘዬዎች በምንናገርበት ጊዜ በ‹ሳ› ድምፅ የምናሳርገውን ቃል በቱለማ ዘዬ ‹ቻ› እያሉ መናገር የተለመደ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹ለሜሳ›፣ ‹ከሌሳ›፣ ‹በሬሳ›፣ ‹ሙርቴሳ› የመሳሰሉት ቃላት በቱለማ ዘዬ ‹ለሜቻ›፣‹በሬቻ›፣‹ሙርቴቻ›፣‹ከሌቻ› በሚል ድምፀት ነው የሚነገሩት፡፡››

አፈንዲ ሙተቂ ‹‹ቦረና እና በሬንቱ›› የተሰኘው የኢትኖግራፊ መጽሐፋቸውም ሆነ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለጹት፣ የኦሮሞ ሽማግሌዎች ‹‹የኢሬሳ በዓል የሚከበረው ለዋቃ ምስጋና ለማቅረብ ነው፤›› ይላሉ፡፡ መነሻውንም ሲያስረዱ ‹‹ዋቃ ክረምቱን በሰላም ስላሳለፈልንና ከሰማይ ባዘነበው ውኃ መልካም ፍሬ ስለሰጠን ያለ ክፍያ በቸርነቱ ለሚንከባከበን አምላክ ምስጋና ማቅረብ የተገባ በመሆኑ ነው፤›› ይሉናል፡፡

‹‹ዋቃ›› ፍጥረተ ዓለምን ያስገኘውና ሒደቱንም የሚያስተናብረው አንድ አምላክ ማለት ነው፡፡ ኦሮሞ ችግር ሲገጥመው አቤቱታውን የሚያቀርበው ‹‹ለዋቃ›› ነው፡፡ በደስታ ጊዜም ተሰብስቦ ‹‹ዋቃ››ን ያመሰግናል፡፡ ኢሬሳ የዚህ ዓይነቱ የምስጋና ማቅረቢያ በዓል ነው ሲሉም ያብራሩታል፡፡

በአፈንዲ ሙተቂ ማብራሪያ ‹‹ኢሬሳ በክረምቱ የወንዞች ሙላት ምክንያት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተ ዘመዶችና ልዩ ልዩ ጎሳዎች የሚገናኙበት በዓል ነው፡፡ በመሆኑም በበዓሉ የተገኙት ሁሉ ይቅር ይባባሉ፡፡ ገንዘባቸውን ለሌሎች ያበደሩ ሰዎችም በሌሎች ላይ ያላቸውን ዕዳ ይሰርዙላቸዋል፡፡

‹‹በዓሉ የሚከበርበት ቀን የዓመቱ መጀመርያ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ዓመቱ የደስታና የብልፅግና ይሆን ዘንድ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ይጎርፋሉ፡፡ የሕዝቡ መንፈሳዊ መሪ የሆነው ‹‹ቃሉ›› ለሕዝቡና ለአገሩ ‹‹ኤባ›› (ምርቃት) ያደርጋል፡፡ ታዲያ ማንኛውም ሰው ወደ በዓሉ ሥፍራ ሲሄድ አለባበሱን ማሳመር ይጠበቅበታል፡፡ በእጁም የወይራ ቀንበጥ፣ እርጥብ ሳር አሊያም የአደይ አበባን ይይዛል፡፡

በጥንቱ ዘመን ከዚሁ የኢሬሳ በዓል ትይዩ ሌላ በዓል በክረምቱ መግቢያ ላይ ይከበር እንደነበር የባህልና ትውፊት ተመራማሪው አፈንዲ እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡- ‹‹ይህኛው በዓል የሚከበረው የክረምቱ ዝናብ ሊጀምር በሚያስገመግምበት የሰኔ ወር መግቢያ ላይ ነው፡፡ የበዓሉ ማክበሪያ ሥፍራዎች ደግሞ ተራሮችና ኮረብታዎች ናቸው፡፡

‹‹መጪው ክረምት መልካም የዝናብና የአዝመራ ወቅት እንዲሆንልን ለዋቃ ጸሎት ማድረስ›› በሚል መንፈስ ነው የሚከበረው፡፡

   ‹‹በዓሉ በምዕራብ ሐረርጌው የኢቱ ኦሮሞ ዘንድ ‹‹ደራራ›› እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ የቱለማ ኦሮሞ ደግሞ ‹‹ኢሬቻ ቱሉ›› (የተራራ ላይ ኢሬሳ) ይለዋል፡፡ በደራራ ጊዜ የሚፈለገው ትልቁ ነገር ‹‹ጸሎት›› (Kadhaa) ማብዛት ነው፡፡ መዝፈንና መጨፈር አይፈቀድም፡፡ በኢሬሳ ጊዜ የሚፈለገው ግን ‹‹ምስጋና›› (Galata) ማብዛትና ደስታን ማብሰር ነው፡፡

በካፑቺን ፍራንቸስካና የፍልስፍናና የነገረ መለኮት ተቋም የአፍሪካ ፍልስፍና ፕሮፌሰሩ ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር) ስለ ኢሬቻ  ፍልስፍናዊ፣  ሃይማኖታዊና  ባህላዊ  አንድምታ በጻፉት መጣጥፍ እንደገለጹት፣ በኦሮሞ ሕዝብ  ዘንድ  ለምለም  ሳር  የሰላምና  የብልፅግና  ምልክት  በመሆኑ፣ በኢሬቻ  በዓል  ላይ  የሚሳተፈው  እያንዳንዱ  ግለሰብ፣  ይህንን  ለምለም  ሳር  በሁለት  እጆቹ  በመያዝ  አምላኩን  ያመሰግናል። 

‹‹ከሁሉም  በላይ  ክረምቱን  ከበረዶ፣  ከከባድ  ነፋስ፣  ከጎርፍና  ከውርጭ  የታደጋቸውን  ታላቅና  ቅዱስ  አምላካቸውን  አንድ  ላይ  ሆነው ያመሰግናሉ።  መኸሩንና  አዝመራውን  ደግሞ  እንዲባርክላቸው  ወደ  ፈጣሪ  ይጸልያሉ።  ስለዚህ  የኢሬቻ  በዓል  ከጨለማ  ወደ  ብርሃን  ላሻገረ  አምላክ  የሚሰጥ  የክብር  ዋጋ  ነው።

‹‹ውኃ  የሕይወት  ምልክት  ነው።  ለዚህም  ነው  ውኃና  ልምላሜ  እንደ  ዋቃዮ  ስጦታ  የሚታዩት።  ያለ  ውኃ  ሕይወት  ቀጣይነት  የለውም።  ውኃ  ዋቃዮ  ለፈጠራቸው  ልጆቹ  የሰጠው  ፀጋ ነው፤››  ሲሉም ያክሉበታል፡፡

በኢሬቻ ከሚቀርቡት ምስጋናዎች አንዱ ‹‹ዓምና በሰላም በጤና 13ቱን ወር አስጨርሰኸናል፡፡ መጪውን ዓመት ደግሞ በሰላም እንድታደርሰን ይሁን፡፡ ይኸንን ለሰው ልጅ ለሁሉም ፍጥረት ብለህ የፈጠርከውን ንፁህ ውኃ በአንተ ኃይል አጣርተህ ያስቀመጥከውን በሐይቅህ ላይ ምስጋናህን እናቀርባለን፡፡ ውኃ ንፁህ ነውና፡፡››

የአፍሪካ ፍልስፍና መምህሩ ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር) እንደሚያብራሩት፣ ኢሬቻ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው። ለምሳሌ ፋሲካ፣ አረፋ፣ ጥምቀት፣ ገና…፣ ወዘተ ሃይማኖታዊ በዓሎች ናቸው እንጂ፣ በራሳቸው ሃይማኖት አይደሉም፡፡ የኦሮሞ አገር በቀል ሃይማኖት ዋቄፋና ተብሎ ይጠራል።

‹‹Waaqa›› ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲሆን፣ ‹‹Faana›› ማለት ደግሞ መከተል ማለት ነው። ትርጉሙም ፈጣሪን/እግዚአብሔርን መከተል ማለት ነው። ለኦሮሞ ሕዝብ ዋቃ የሁሉ ነገር አስገኝ፣ የማይጠፋ፣ የማይለወጥ፣ ቋሚና ዘለዓለማዊ ነው። የሁሉም ነገር ምንጭ ዋቃ ነው። ዋቃ ምሉዕ በኩለሄ፣ ሁሉን ቻይ፣ ዘላለማዊ፣ ፍፁምና ገደብ የሌለው ነው።

የአፍሪካ ፍልስፍና መምህሩ ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በኢሬቻ  ከሚቀርበው ጸሎት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

‹‹ሀዬ!  ሀዬ!  ሀዬ! (አሜን አሜን አሜን)

ሀዬ!  የእውነትና  የሰላም  አምላክ!

ሀዬ!  ጥቁሩና  ሆደ ሰፊው  ቻይ አምላክ!

በሰላም  ያሳደርከን  በሰላም  አውለን!

ከስህተትና  ከክፉ  ነገሮች  ጠብቀን!

ለምድራችን  ሰላም  ስጥ!

ለወንዞቻችን  ሰላም  ስጥ!

ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!

ለሰውም  ለእንስሳቱም  ሰላም  ስጥ!››

ሀዬ!  ሀዬ!  ሀዬ! (አሜን አሜን አሜን!›› ይላሉ፡፡

በOromo Wisdom In Black Civilization መጽሐፋቸው፣ ድሪቢ ደምሴ ቦኩ እንደገለጹት፣ ‹‹ኦሮሞ ወንዝ፣ ጫካና ተራራ ይወዳል፡፡ የተፈጠረበትና ፍቅር ያገኘበት ስለሆነ በየዓመቱ ለምለም ሳርና የአደይ አበባ ይዞ ለኢሬቻ ከወንዝ ውኃ ዳርቻ በመሄድ፣ ተራራ ላይ በመውጣት፣ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል። በጤና፣ በሰላም፣ ለሰውና ለከብት ዕርባታ እንዲሰጠውም ይጸልያል።››

በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ (ሐይቅ) ዳርቻ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ በተዘጋጀ ኩሬ (በሆራ ፊንፊኔ)፣  የሚከበረው ኢሬቻ በእንስቶች ‹‹መሬ ሆ…›› ዜማ የሚታጀብ ነው፡፡

ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ሥርዓቱን ጠብቆ እንደሚመጣ ለመግለጽ ከፊት ለፊት ልጃገረዶች ቀጥሎ ሴቶች ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› እያሉና ባህላዊ ጭፈራዎችን እያሰሙ ሲጓዙ፣ አባ ገዳዎች፣ አዛውንቶች እንዲሁም ወጣቶች (ፎሌዎችና ቄሮዎች) ይከተላሉ፡፡

‹‹ኢሬቻ ሰላም ነው፣ ሰላም ጥልቅ ትርጉም አለው፣ ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላም ሊኖረው ይገባል፤›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የክብረ በዓሉ ጭብጥ ነው፡፡

በዕለተ ቀኑ ክብረ በዓሉ ሲከበር ልጃገረዶች ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› እያሉ የሚዘምሩት፣ ይኼም ማለት ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ሥርዓትን ጠብቆ ዞሮ መምጣቱን ለመግለጽ እንደሆነ ጥናቶቹ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ በዓል በፈጣሪና ፍጥረት መሀል ያለው ሥርዓት ሳይቋረጥ ሒደቱን ጠብቆ በመካሄዱ የሚከበር የምስጋናና የምልጃ በዓል እንደሆነ ለማስረዳት ነው፡፡ ምልጃውና ምስጋናው ክረምትና በጋ፣ ቀን ሌሊት፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ልጅነትና እርጅና እንዲሁም ሕይወትና ሞት የማያቋርጡ ሒደቶች እንደሆኑ ለማሳየት ነው፡፡

የፍልስፍና መምህሩ ዮሴፍ ሙሉጌታ (ዶ/ር) በመጣጥፋቸው ከጠቀሱት ለእውነትና  ለሰላም  አምላክ  ከሚቀርበው ልመና አንዱን አንጓ እነሆ፡-

‹‹ከመጥፎ አየር ጠብቀን!

ንፁሕ ዝናብ አዘንብልን!

ያለአንተ ዝናብ የእናት ጡት ወተት አይሰጥምና!

ያለአንተ ዝናብ የላም ጡት ወተት አይሰጥምና!

ያለአንተ ዝናብ መልካው ውኃ አይሰጥምና!

ያለአንተ ዝናብ ምድሩ ቡቃያ አይሰጥምና!

ከእርግማን ሁሉ አርቀን!

እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!

ከረሃብ ሰውረን!

ከበሽታ ሰውረን!

ከጦርነት ሰውረን!

ልጄ እያሉ አልቅሶ ከመቅበር ሰውረን!

ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...