Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንተርኔት መቋረጥ ንግዳቸውን ቴክኖሎጂ ነክ ባደረጉ ድርጅቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ጀማሪና ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ ንግዳቸውን በቴክኖሎጂ ያደረጉ ድርጅቶች፣ በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት አሉታዊ ተፅዕኖ እየደረሰባቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ከአክሰስ ናው ጋር በመተባበር፣ ‹‹በኢትዮጵያ የበይነ መረብ መዘጋት በጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ንግድ ላይ ያለው ተፅዕኖ›› በሚል ርዕስ ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት መቋረጥ በጀማሪ የቴክኖሎጂ ንግዶች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት፣ በአውስትራሊያ ሜልቦርን በሞናሽ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ዮሐንስ እንየው  ናቸው፡፡

በቀረበው ጥናት፣ በኢትዮጵያ የበይነ መረብ የሚዘጋባቸውን የተለያዩ ወቅቶች በማስታወስ፣ ችግር ተከሰተ ሲባል በፍጥነት በይነ መረብን መዝጋት መፍትሔ አለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ምርጫ ሲካሄድ፣ የሳይበር ጥቃት ሲያጋጥም፣ ሐሰተኛ መረጃ ሲሠራጭ፣ አገር አቀፍ ፈተናዎች ሲኖሩ፣ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲካሄድ በተወሰኑ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉና በከፊል በይነ መረብ የተዘጋባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

‹‹በተጠቀሱት ምክንያቶች ኢንተርኔት መዝጋት ሕጋዊ አይደለም፡፡ የበይነ መረብን ማቋረጥ ሲያስፈልግ ከሚታወቅ የመንግሥት አካል ሕጋዊነት በመቀበል፣ ተቀባይነት ማግኘት፣ አስፈላጊነቱ ምን ያህል እንደሆነ ማጥናትና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ አሳስበዋል፡፡

የበይነ መረብ መቋረጥ በአስመጪና ላኪዎች እንዲሁም በትልልቅ የንግድ ሒደቶች ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት ደግሞ፣ ለረዥም ዓመታት የኢንቨስትመንት አማካሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል ናቸው፡፡

‹‹የበይነ መረብ መቋረጥ ምክንያት በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶችን (Perishable Items) ማለትም አበባ፣ ኢንጆሪና የመሳሰሉትን የሚልኩ ድርጅቶች ገቢ ማጣት፣ ኢታክስ ማካሄድ አለመቻል፣ በኦንላይን የውል ስምምነት ማካሄድ አለመቻል፣ እንዲሁም በርካታ በኦንላይን የሚከናወኑ ንግዶች ችግር ይገጥማቸዋል፤›› ሲሉ አቶ ያሬድ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በይነ መረብ መዝጋት አስገዳጅ ሆኖ ከተገኘ የተወሰነ የበይነ መረብ መጠቀሚያዎችን በመዝጋት እንደ ኢሜይል፣ ኢታክስና ለንግድ የሚያስፈልጉ አነስተኛ ተጠቃሚ ያላቸውን አገልግሎቶች ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አቶ ያሬድ አሳስበዋል፡፡

‹‹በዓለም ላይ ያሉ ሀብታም ግለሰቦች ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገቡት በቴክኖሎጂ በመሆኑ፣ በአገራችን የኢንተርኔት አጠቃቀምን በመጨመር ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ለምሳሌም የዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም ከሆኑት ግለሰቦች መካከል የቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ባለቤት ኤለን መስክ ይጠቀሳሉ፡፡ የኤለን መስክ አጠቃላይ የተጣራ ገቢ 247 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ የአንድ ሰው የሀብት መጠን የኢትዮጵያ ጥቅል ዓመታዊ ምርት (GDP) ሁለት እጥፍ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም. የነበረው 0.02 በመቶ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ቁጥር፣ አሁን 21 በመቶ ማለትም 24 ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ መሆኑ ይነገራል፡፡

አሁን ካለው 21 በመቶ የኢንተርኔት ተጠቃሚ አሥር በመቶ ቢያድግ ለአገሪቱ 1.5 GDP አበርክቶ እንዳለው፣ ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025›› በሚለው ፖሊሲ ኢትዮጵያን እንዴት በመጪው አምስት ዓመታት በቴክኖሎጂ ማሳደግ እንደሚቻል ማሳያዎች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በአሥር ዓመቱ ዕቅድ መሠረት 18.6 በመቶ የሆነውን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር፣ በአሥር ዓመት ውስጥ መቶ በመቶ የማሳደግ ትልም ተይዟል፡፡

‹‹ከላይ የተጠቀሱት የ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያ ፖሊሲና የአሥር ዓመት የዲጂታል ዕቅድ የኢንተርኔት መዘጋትን አይደግፉም፡፡ በተጨማሪም ኢንተርኔት በመዝጋት ትልልቅ ዕቅዶችን ማስቀመጥ ዕቅዱ እንዳይሳካ ያደርገዋል፤›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ያቀረቡት ጥናት እንደሚያሳየው ብሪኪንግ የተባለው ተቋም እ.ኤ.አ. በ2016 በሠራው ጥናት መሠረት፣ በኢትዮጵያ ለአንድ ወር ኢንተርኔት ቢዘጋ 8.5 ሚሊዮን ዶላር ከኢኮኖሚ ላይ ያሳጣል ሲል ግምቱን ያስቀምጣል፡፡

በተጨማሪም ግሎባል ኔትወርክ ኢኒሼቲቭ በተመሳሳይ ወቅት ባደረገው ጥናት፣ በኢትዮጵያ ኢንተርኔት ለአንድ ቀን ቢዘጋ 500 ሺሕ ዶላር ያሳጣታል የሚል ግምት አለው፡፡

ጥናቶቹ በሚሠሩበት ወቅት የአገሪቱን የዋጋ ግሽበትና የእያንዳንዱን ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ገቢና ወጪ ያላከተተ ነው ሲሉ አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 570 ያህል ስታርትአፕ (የዲጂታል ንግድ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች) ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በአምስት የተለያየ ዘርፍ ማለትም ፊንቴክ፣ ኢኮሜርስ፣ ትራንስፖርትና ዴሊቨሪ፣ ሴክተር ቴክኖሎጂና ኢኮ ሲስተም በሚል የተከፈሉ ናቸው፡፡

በፊንቴክ ዘርፍ የሚገኙ እንደ ቴሌ ብር፣ ኤም ብር፣ ክፍያ፣ ሲቢኢ ብርና ሌሎችም ናቸው፡፡ በኢኮሜርስ ዘርፍ እንደ አፍሮ ታይ፣ ጂጂ፣ ሸጋ፣ ኢትዮ ፖስት፣ ኢትዮ ጆብስና ሌሎች የበይነ መረብ ግብይት የሚደረግባቸው ናቸው፡፡

በትራንስፖርትና በዴሊቨሪ አገልግሎት እንደ ራይድ፣ ታክሲዬ ዴሊቨሪ አዲስና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ በሴክተር ቴክ እንደ ቤትኪንግ፣ ሆፕ ኢንተርቴይንመንት፣ ኦርቢት ኸልዝ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በኢኮ ሲስተም እንደ አይስ አዲስ፣ ብሉሙንና 1888 ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በርካታ የበይነ መረብ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች የበይነ መረብ መቋረጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥርባቸው በመሆኑ፣ እንዲሁም እየተንቀሳቀሱ የሚያገኙትን ገንዘብ ማጣት ስለማይገባ ድንገተኛ የበይነ መረብ መዘጋት መቆም እንደሚኖርበት በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

በሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደው አገር አቀፍ ፈተና ምክንያት የበይነ መረብ መቋረጥ ቢፈጠር ከላይ የተጠቀሱት ችግር እንደሚገጥሙ በውይይቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ዝግጁ መሆን እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች