Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአጎዋ መቋረጥ የተጎዱ ኩባንያዎች ለተጨማሪ ስድስት ወራት ምርታቸውን በአገር ውስጥ እንዲሸጡ ተፈቀደላቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአሜሪካ መንግሥት ከኮታና ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) በመቋረጡ ምክንያት የተጎዱ ኩባንያዎች፣ ምርታቸውን በአገር ውስጥ እንዲሸጡ ተፈቅዶላቸው የነበረውን የአራት ወራት ጊዜ በአግባቡ ባለመጠቀማቸው፣ ዕድሉ ለተጨማሪ ስድስት ወራት ተራዘመላቸው፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ኩባንያዎቹ ምርቶቻቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደላቸው በግንቦት 2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዕድሉም ለአራት ወራት የሚቆይ ነበር፡፡ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ውል ገብተው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሥራ የጀመሩት ኩባንያዎቹ፣ ምርታቸውን ሚኒስቴሩ ግንቦት ላይ ፈቃድ የሰጣቸው በአጎዋ ዕድል መቋረጥ ምክንያት፣ በሥራቸው ያሉ ሠራተኞች የሥራ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሲል ነው፡፡

ይሁንና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉት ኩባንዎቹ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት የተፈቀደላቸውን ዕድል ሳይጠቀሙበት ጊዜው መሄዱን፣ ሚኒስቴሩ ጳጉሜን 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጉምሩክ ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል፡፡ በተጨማሪም የአጎዋ ዕድል መሰረዝ አሁንም ‹‹በተወሰኑ›› ኢንዱስትሪዎች ላይ ‹‹ከፍተኛ የሥራ ጫና›› እየፈጠረ መሆኑም፣ ዕድሉ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም መደረጉ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እንደሚያስረዱት፣ በተለይ ጨርቃ ጨርቅ ላይ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች የሚጠቀሙት የቢዝነስ ሞዴል ምርታቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ አይጋብዝም፡፡

ብዙዎቹ ኩባንያዎች ጥሬ ዕቃ የሚቀርብላቸው ከገዥዎቻቸው እንደሆነ የሚያመርቱትም የገዥዎቻቸውን ፍላጎት ተከትለው መሆኑ አንደኛው ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ሳንዶካን እንደሚገልጹት፣ ኩባንያዎቹ ጥሬ ዕቃ ከገዥዎቻቸው የሚቀርብላቸው በመሆኑ፣ በአገር ውስጥ መሸጥ የሚችሉት ገዥዎቻቸው በተለያዩ ምክንያት ውድቅ ያደረጓቸውን ምርቶች ብቻ ነው፡፡ ምርት ውድቅ የሚደረግበት አንደኛው ምክንያት የጥራት መጓደል እንደሆነ አስረድተው፣ ‹‹ጥራቱ አነስተኛ ነው ማለት ሳይሆን፣ የተቀባዩን ኩባንያ ጥራት አላሟላም ማለት ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሪፖርተር ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ያገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ድረስ በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ላይ የተሠማሩ አምስት ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ አቅርበዋል፡፡ ኤቨረስት አፓረል፣ ሲልቨር ስፓርክ አፓረል፣ ኢፒክ አፓረል፣ አሽተን አፓረል ማኑፋክቸሪንግና ኢዛቤል ሶክስ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ገደማ የሚያወጣ ምርት በአገር ውስጥ ሸጠዋል፡፡

ሌሎች ሰባት ኩባንያዎች ደግሞ በአገር ውስጥ ለመሸጥ ፈቃድ ቢያገኙም ምርታቸውን አላቀረቡም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ለወደፊት ምርቱን የማቅረብ ዕቅድ ሲኖራቸው፣ ሦስቱ ምርታቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሁለቱ ደግሞ የሚያመርቱበትን ጥሬ ዕቃ የሚያቀርብላቸው ምርታቸውን የሚገዛቸው ድርጅት በመሆኑ፣ ምርታቸውን በአገር ውስጥ እንዲያቀርቡ አይፈቅድላቸውም፡፡ አርቪንድ (Arvind Lifestyle Apparel Manufacturing PLC) የተባለ የአልባሳት አምራች ኩባንያ በአንፃሩ ምርቱን በአገር ውስጥ ለማቅረብ ቢፈልግም፣ የተጣለበት ታክስ ከፍተኛ በመሆኑ ምርቱን በአገር ውስጥ መሸጥ እንዳልቻለ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኩባንያዎቹ ምርታቸውን በአገር ውስጥ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ ታክስ ስለሚከፍሉና ሽያጩ የሚከናወነውም በብር መሆኑ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡  አርቪንድ ኩባንያ ምርቱን ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት ቢኖረውም፣ ለምርት ግብዓትነት ያስገባቸውን ዕቃዎች ጉምሩክ የገመተው በገበያ ውስጥ ካለው ዋጋ ‹‹በጣም ከፍተኛ›› በመሆኑ፣ ያቀረበው ዋጋ ተቀባይነት ሊያገኝ ስላልቻለ ምርቱን አላቀረበም፡፡

በተጨማሪም አንዳንዶቹ ኩባንያዎቹ ምርታቸውን በብር የመሸጥ ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹት አቶ ሳንዶካን፣ ‹‹እጃቸው ላይ በቂ ብር ስላላቸው ያለውን ማስወጣት ነው የሚፈልጉት፤›› በማለት ምክንያቱን አስረድተዋል፡፡

ከእነዚህ ውጪ ግን የፀጥታ ኃይሎች አልባሳት በማምረት ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በመተካት ላይ የተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች መኖራቸውን አክለዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረበው ዕድል ለችግሩ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከአሜሪካ ውጩ ባሉ ሌሎች አገሮች ገበያ የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አውስተዋል፡፡ በአሜሪካ የሚገኙት ትልልቅ ገዥዎች ከኩባንያዎቹ ጋር የተገናኙት በኢትዮጵያ መንግሥት የማግባባት ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹በተመሳሳይ በሌሎች አኅጉራት ያሉ ትልልቅ ገዥዎችን ሎቢ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ባለው ሁኔታ ምክንያት ያላቸው እምነት የተሸረሸረ ገዥዎችን ለመመለስም፣ ‹‹የአንድ ለአንድ ውይይቶች›› እየተደረጉም መሆኑንም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት ከተሰረዘች በኋላ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ አምስት የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያዎች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ከአምስት ሺሕ በላይ ሠራተኞች ከሥራ እንደተሰናበቱ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) መረጃ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች