Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት ሁለት ቢሊዮን ብር ብድር ተፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቻይና ኤግዚም ባንክ ብድር መልቀቅ በማቆሙ ሳቢያ ሥራው ለአንድ ዓመት ቆሞ ለነበረው የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ፕሮጀክት፣ የፌዴራል መንግሥት ሁለት ቢሊዮን ብር ብድር መፍቀዱ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሞገስ ጥበቡ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱና የቃሊቲ – ቂሊንጦ መንገድ ፕሮጀክቶች ላለፉት አራት ዓመታት አበዳሪው የቻይና ኤግዚም ባንክ ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይከፍል በመቆየቱ ለአንድ ዓመት ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በብድር እንዲለቀቅ ለከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ በመስጠቱ ግንባታው መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

‹‹የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ የበጀት ጫና የሚያመጣ ቢሆንም፣  የኢምፖርት ኤክስፖርት ኮሪደር እንደ መሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ስለወሰኑ ለማመሥገን እወዳለሁ፤›› ሲሉ ሞገስ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰኔ 2014 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ ስለእነዚህ መንገዶች ጉዳይ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹ቃል የገባው አካል በራሱ ምክንያት ብድር ሊያፋጥን አልቻለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንገዱ ተጀምሮ በመቆሙ ሳቢያ የአካባቢ ነዋሪ መማረሩን ገልጸው፣ ‹‹በሚቀጥለው ዓመት ኤግዚም ባንክ ባይፈቅድም በራሳችን በጀት እንጀምራለን፤›› ብለው ነበር፡፡

ሁለቱ መንገዶች ከ50 በመቶ በላይ የሆነ ሥራቸው ቢከናወንም፣ በኮንስትራክሽ ግብዓቶች ዋጋ መጨመርና ፕሮጀክቱ በመጓተቱ ከተቋራጩ የሚነሳ የዋጋ ክለሳ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚጠይቀውን ገንዘብ ከፍ እንደሚያደርገው፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል፡፡

የፕሮጀክቱ የቀኝ መንገድ ክፍል አንድ ደረጃ አስፋልት ንጣፍ ተጠናቆ መከፈቱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የግራውን የመንገድ ክፍል የመጀመሪያ የአስፋልት ንጣፍ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ማድረግ የባለሥልጣኑ የበጀት ዓመቱ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት የግራ መንገድ ክፍል እንዳይሠራ ከአራት ዓመት በላይ እንቅፋት ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ አሥር ኪሎ ሜትር ርዝመት የነበረው የውኃ መስመር ባለፈው የካቲት ወር መነሳቱ፣ እንዲሁም የገንዘቡ ችግር በመፈታቱ የፕሮጀክት አፈጻጸሙ ከዚህ በኋላ እንዲፋጠን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ሞገስ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

ከመንግሥት ጋር የሚደረገው ድርድር ሲጠናቀቅ የቻይናው ኤግዚም ባንክ ብሩን ይለቃል የሚል እምነት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ጥያቄና ቅሬታ የሚነሳበትን የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በተያዘው የበጀት ዓመት ግንባታውን ለማፋጠን ርብርብ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

በ2015 የበጀት ዓመት ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን 8.95 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበለት ሲሆን፣ በጀቱም በአጠቃላይ 866 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡ መሥሪያ ቤቱ የከተማ አስተዳደሩ በሚበጅትለት፣ ብድርና ዕርዳታ አቅራቢዎች በሚያቀርቡት፣ እንዲሁም ከመንገድ ፈንድ ከሚገኝ በጀት የፕሮጀክት ግንባታና ጥገና እንደሚያደርግ ይታወቃል፡፡

በጀቱን መሠረት በማድረግ በትኩረት የሚሠራው ሥራ መንገዶችን ማጠናቀቅ መሆኑን የተናገሩት ሞገስ (ኢንጂነር)፣ ግንባታ ላይ የሚገኙ 25 ያህል መንገዶችን በተያዘው ዓመት ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የመጋጠሚያ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ስለሚያጋጥም በግንባታ ላይ የሚገኙት የኢምፔሪያል፣ የቦሌ ሚካኤልና የለቡ ተሻጋሪ መንገዶች (ማሳለጫዎች) በተያዘው ዓመት ከሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ውስጥ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የኮተቤ-ካራ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ከሚጠናቀቁ መንገዶች ተጠቃሹ መሆኑን ያስታወቁት ሞገስ (ኢንጂነር)፣ ከዚህ ጎን ለጎን ሦስት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ለመገንባት በቅርቡ ውል ከተገባላቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የአየር ጤና – ወለቴ የአምስት ኪሎ ሜትር መንገድ፣ ከአፍሪካ ጎዳና – ኤድናሞል አደባባይ – 22 ማዞሪያ – እንግሊዝ ኤምባሲ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ይጀመራል ብለዋል፡፡

የኤድናሞል – 22 ማዞሪያ – እንግሊዝ ኤምባሲ የአስፋልት መንገድ የብልህ ትራንስፖርት ሥርዓት (ኢንተለጀንት ትራንስፖርት ሲስተም) ያካተተ በመሆኑ፣ ሲጠናቀቅ መሠረተ ልማቶቹ መረጃን ወደ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል በመላክ ለከተማዋ ትራፊክ ፍሰቱ ትልቅ ዕገዛ እንደሚያደርግ ታምኖበታል፡፡

የመንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት፣ አዲስ አበባ ከ254 ቢሊዮን ብር በላይ ወቅታዊ ግምት ያላቸው የመንገድ መሠረተ ልማቶች አላት፡፡ ይህንን ትልቅ የሆነ መሠረተ ልማት መንከባከብ፣ ማደስና መጠገን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የመንገድ ጥገና ሥራን ባለሥልጣኑ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሠራ፣ 611 ኪሎ ሜትር የተለያየ ዓይነት የአስፓልት፣ የኮብል፣ የጠጠር መንገድ ጥገና ሥራዎች ይከናወናል ሲሉ አክለዋል፡፡

መንገዶች የታለመላቸውን አገልግሎት መስጠት እንዳይችሉ ትልቅ ፈተና የሆነው የመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸመው ስርቆት መሆኑ ተመላክቶ፣ ከዚህ በሻገር የዝናብ ውኃ ብቻ እንዲስተናግዱ የተተው መስመሮችን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ማድረግ እንዲሁም ከመንገድ ሥር የተቀበሩ መተላለፊያ መስመር መግቢያ ክዳን (ማንሆል) መሰረቅ ተደጋጋሚ የመንገድ ጉዳት ማድረሱን ሞገስ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች